Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘቢዳር ቢራን ለመጠቅለል የተነሳው ካስትል ግሩፕ ግዥውን መቋጨት አልቻለም

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለ40 በመቶ አክሲዮኖች 1.3 ቢሊዮን ብር አቅርቧል

በዘቢዳር ቢራ አክሲዮን ኩባንያ ውስጥ ዋነኛ ባለድርሻ የነበረውን የቤልጂየሙን የዩኒብራ ኩባንያን አክሲዮኖች ስለመግዛቱ ያስታወቀው ካስትል ግሩፕ፣ በኢትዮጵያውያን ባለድርሻነት የተያዙትን ቀሪዎቹን አክሲዮኖች ለመግዛት 1.3 ቢሊዮን ብር በማቅረብ ዘቢዳርን ለመጠቅለል እየተደራደረ ነው፡፡ አክሲዮኖቹን ለመግዛት ያቀረበው ዋጋ ግን ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ ራያ ቢራን ለመግዛት ከሰጠው ዋጋ እንደሚያንስ ተሰምቷል፡፡

ካስትል ግሩፕ፣ በዘቢደር ቢራ ውስጥ የ40 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ያላቸውን ባለአክሲዮኖች እያነጋገረ ቢሆንም፣ የዘቢዳርን አክሲዮኖች ለመግዛት ያቀረበው ዋጋ የተጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ እየተሰማ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም የአክሲዮን ሽያጩ እንዲዘገይ ማስገደዱን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡ 

የዘቢዳር ቢራ አክሲዮን ማኅበርን የ40 በመቶ ድርሻ የያዙት ዥማር በተባለው ኩባንያ በኩል የተወከሉት ኢትዮጵያውን ባለአክሲዮኖች፣ ካስትል ግሩፕም አክሲዮኖችን ለመግዛት በዥማር አክሲዮን ኩባንያ ውስጥ ዋነኛ ባለድርሻ የሆኑትን ባለአክሲዮኖች እያነጋገረ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ ዥማር አክሲዮን ኩባንያ፣ በዘቢደር ቢራ ውስጥ ያሉትን የአክሲዮን ድርሻዎች ለመሸጥ ካስቴል ኢትዮጵያ ባቀረበው ዋጋ ላይ ባለአክሲዮኖቹ የሐሳብ ልዩነት እንዳላቸው ይነገራል፡፡ በቀረበው ዋጋ መሠረት አክሲዮኖቻቸውን እንዲሸጡ እያግባቡም ቢሆን፣ በሁለቱ ወገኖች በኩል እስካሁን ከስምምነት ላይ አልተደረሰም፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ፣ በዥማር ኩባንያ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያላቸው ባለድርሻዎች አክሲዮኖቻቸውን እንዲሸጡ የቀረበላቸውን ጥያቄ እስካሁን እንዳልተቀበሉ ሲታወቅ፣ ካስትል ግሩፕ በበኩሉ የዘቢዳርን አክሲዮኖች ለመጠቅለል ግፊት እያደረገ ይገኛል፡፡ ካስትል ግሩፕ የዘቢዳርን የ40 በመቶ ድርሻ ለመግዛት አቅርቧል የተባለው ዋጋ፣ ቢጂአይ ኢትዮጵያ የራያ ቢራን አክሲዮኖችን ለመግዛት ከሰጠው ዋጋ ያነሰ በመሆኑ የዘቢደር ቢራ ባለአክሲዮኖችን በጋራም ሆነ በተናጠል አክሲዮኖቻቸውን ከመሸጥ እንዲያመነቱ ተፅዕኖ ማሳደሩ እየተነገረ ነው፡፡

የሽያጭ ስምምነቱ የወቅቱን የብር የምንዛሪ ለውጥ ታሳቢ ማድረግ እንደማይገባው በመግለጽ የግዥው ዋጋ ላይ ቅሬታ እንደተነሳም ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለአክሲዮኖች ገልጸዋል፡፡ ካስቴል ኢትዮጵያ የዥማርን አክሲዮኖች ለመግዛት ያቀረበው ዋጋ 1.3 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ይህም አንድ ሺሕ ብር ዋጋ ያለውን አክሲዮን በአራት ሺሕ ብር ለመግዛት የታሰበ እንደሆነ ይጠቁሟል፡፡ ይህ አክሲዮን ዝውውር በምን መልኩ ሊቋጭ ይችላል የሚለውን ጉዳይ በሚመለከት በመጪው ቅዳሜ፣ ሰኔ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. የባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ ተጠርቶ ውይይት እንደሚደረግ ታውቋል፡፡

በዥማር ሁለገብ አክሲዮን ማኅበር ውስጥ ከ300 በላይ ባለአክሲዮኖች ድርሻ አላቸው፡፡ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ካላቸው ውስጥ ንብ ባንክ፣ ሳንታማርያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ሐሮን ኮምፒውተር፣ ዴሉክስ ፈርኒቸርና፣ ፋንቱ ሱፐር ማርኬት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ከአሥር ሚሊዮን ብር ዋጋ ያላችው አክሲዮኖችን በባለድርሻነት ይዘዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች