በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አስተዳደር ላይ የጎላ ትችት በመሰንዘር፣ ሐሳባቸውንም በተባ ብዕራቸው በማስተጋባት ይታወቃሉ፡፡ ለዓመታትም በጋዜጦች ስለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ከሙያቸው አኳያ ሲጽፉ ኖረዋል፡፡ ቅዳሜ ግንቦት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. የዚሁ ትጋታቸው አካል የሆነውንና በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ የተመሠረተ ትንታኔ ያቀረቡበትን መጽሐፍ ይፋ አድርገዋል፡፡
አቶ ጌታቸው አስፋው ይባላሉ፡፡ ራሳቸውን የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ በመጽሐፋቸው የኋላ ሽፋን የቀረበው ገለጻ፣ በቀደመው ጊዜ የሰሜን ኢትዮጵያ ፕላን ቀጣና ጽሕፈት ቤት ውስጥ፣ በፕላንና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ኋላም በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ውስጥ ለዓመታት ማገልገላቸውን አስፍሯል፡፡ ላለፉት ሦስት ዓመታትም በዚሁ በሪፖርተር ጋዜጣና በውይይት መጽሔት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ጽሑፎችን ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወደየት?፣ የገበያ ኢኮኖሚ አመራርና የልማት ኢኮኖሚ አስተዳደር ግጭት›› በሚል ርዕስ አሳትመው ቅድሜ ያስመረቁት መጽሐፍ በስድስት ክፍሎችና በ15 ምዕራፎች የተቀነበበ ነው፡፡ በ387 ገጾች ውስጥ የታጨቀው የኢኮኖሚ ሙግት፣ በአብዛኛው ሕዝብ ዘንድ የሚብላሉ የኑሮ፣ የዋጋ ንረትና ግሽበት፣ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የቁጠባ፣ የመዋዕለ ንዋይ፣ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ሌሎችም በርካታ ሐሳቦች የተቃኙበት መጽሐፍ ነው፡፡
መጽሐፉ ይፋ በተደረገበት ዕለት፣ ከመጽሐፉ ክፍሎች በተወሰኑት ላይ በማተኮር ትንታኔ የሰጡ ባለሙያዎችም ስለመጽሐፉ ይዘት ለታዳሚው አብራርተዋል፡፡ አቶ አስፋው አዲሱ የተባሉ የማኅበረሰብ ጥናት ባለሙያ ከመጽሐፉ ውስጥ ስለዋጋ ንረት ወይም ግሽበት ጉዳይ ትንታኔ አቅርበዋል፡፡
በመጽሐፉ ምዕራፍ 12 ውስጥ ስለዋጋ ንረት የቀረበው ሐሳብ ስለዋጋ ንረት ምንነትና ዓይነቶቹ በመተንተን ብቻም ሳይሆን፣ ስለጥሬ ገንዘብ አሠራር፣ ሥርጭትና መሰል ጉዳዮች ሰፊ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡ አቅራቢው ከመጽሐፉ እንደጠቀሱት የዋጋ ንረት ማለት በአጭሩ ሲገለጽ ‹‹በእያንዳንዱ ሰው ኪስ ውስጥ ብዙ ጥሬ ገንዘብ ማስቀመጥ ነው፣ የጥሬ ገንዘቡ የመግዛት አቅም መቀነስ ማለት ነው፣ ብዙ ብሮች ጥቂት ሸቀጦችን ሲያሳድዱ ማለት ነው፤›› ብለው ጸሐፊው ለዋጋ ንረት የመጀመርያው መነሻ ምክንያት ይህ እንደሆነ ያሰፈሩትን ሐሳብ አብራርተዋል፡፡
ከሚመረተው ምርትና ሸቀጥ በላይ በገበያው ውስጥ ብልጫ ያለው የጥሬ ገንዘብ መሠራጨት ዋጋ ንረት ከማስከተል አልፎ፣ የኑሮ ውድነትን እንደሚያባብስ ጸሐፊው አቶ ጌታቸው በዝርዝር አስቀምጠዋል፡፡ ጥሬ ገንዘብን በመፍጠር ወይም በማሳተም ወደ ገበያ ውስጥ የሚያስገባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ሥርጭቱን የሚያጧጡፉት ንግድ ባንኮች በዋጋ ንረት ውስጥ ሚና እንዳላቸው ያብራራሉ፡፡ ከገዥው ባንክ የላቀ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት ላይ ሚና አላቸው በማለት የሚጠቅሷቸው ንግድ ባንኮች፣ የገንዘብ አስቀማጮች ወይም ቆጣቢዎችን ገንዘብ በማራባት የሚጫወቱት ሚና ለዋጋ ንረትም ለኑሮ ውድነትም አስተዋጽኦ ስለሚያደርግበት መንገድ አብራርተው ጽፈዋል፡፡
ስለመጽሐፉ ገለጻ ያቀረቡት አቶ አስፋው፣ በዋጋ ንረት ሳቢያ ስለሚከሰት የኑሮ ውድነት ባብራሩበት ወቅት አንድ ምሳሌ ጠቅሰው ነበር፡፡ ይኸውም በ1968 ዓ.ም. በተፈጠረ የምርት እጥረት ሳቢያ ከፍተኛ የስንዴ ምርት አቅርቦት ችግር መከሰቱን፣ በዚህ ሳቢያም ዳቦ ከሌሎች የእህል ዘሮች ጋር እየተቀላቀለ መጋገር ተጀምሮ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በመጽሐፉ ዙሪያ ሐሳብና ማብራሪያ እንዲያቀረቡ የተጋበዙት ሌላኛው ተጋባዥ ግለሰብ ወሮታው በዛብህ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ አቶ ወሮታው የሥራ ፈጠራ ላይ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚታወቁ ናቸው፡፡ በመጽሐፉ ስለሥራ አጥነት በተጻፈው ክፍል ላይ እንዲናገሩ ቢጋበዙም፣ ሥራ አጥነት ከሚባል ይልቅ ‹‹ህልም አልባነት፣ የፈጠራ አጥነት›› በሚል እንዲተካ ከመጠየቅ ባሻገር፣ በአገሪቱ ራዕይ አልባነት፣ እንዲሁም ፈጣሪነትና የፈጠራ ክህሎት እንደጠፋ በማብራራት ጊዜያቸውን አጠናቀዋል፡፡
ሌላኛው የኢኮኖሚ ባለሙያና የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ባልደረባ አቶ አሚን አብደላም በኢኮኖሚ መስክ የውጭ ግንኙነትና የንግድ ሚዛን ጉዳይ፣ በመጽሐፉ ከሰፈረው ጽሑፍ በመነሳት ሐሳባቸውን አካፍለዋል፡፡ አቶ አሚን ለመንደርደሪያነት ሲጠቅሱ ከአቶ ጌታቸው ጋር አብረው መሥራታቸውን በማስታወስ፣ በኢኮኖሚ ሙያ መስክ ከድሮም ጀምሮ በጽሑፍ ሐሳባቸውን በማካፈል፣ ሙያዊ ትችት በማቅረብ በኩል የረዥም ጊዜ ልምድ እንዳላቸው ተናግረውላቸዋል፡፡
አቶ አሚን በሙያቸው መነሻነት በኢትዮጵያ ለዋጋ ግሽበት ወይም የዋጋ ንረት በሚሰጡ ትንታኔዎች ውስጥ ቸል ሲባል ይታያል ያሉትን ሐሳብ በመጥቀስ ጭምር ዕይታቸውን አስፍረዋል፡፡ የዋጋ ንረት በዓመታት ውስጥ ያሳየውን ለውጥም ማየት ይገባል ያሉት አቶ አሚን፣ በአብዛኛው የየዓመቱ የዋጋ ለውጥ ላይ ከማተኮር ባሻገር ባለፉት አምስትና አሥር ዓመታት ውስጥ የዋጋ ንረት የደረሰበትን ደረጃም ማየት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር መጽሐፉ ሰፊ ትችት ከሚያቀርብባቸው ክፍሎች ውስጥ የአገሪቱ የወጪ ንግድና የሚዛን ጉድለቱን የሚያሳየውን ሐሳብ በመንተራስ ሲያስረዱም፣ የውጭ ምንዛሪ ተመን የተደረገው የወጪ ንግዱንና በዚህ ንግድ መስክ የተሠማራውን ለማበረታታት ታስቦ እንደሆነ ቢገለጽም፣ በተግባር እንደሚታየው ግን ነጋዴው ተጎጂ እየሆነ ስለመሆኑ አቶ አሚን ማጣቀሻ ያደረጉት በባንኮችና በጥቁር ገበያው መካከል ያለውን የምንዛሪ ልዩነት ነው፡፡ ባንኮች አንድ ዶላር በ27.80 ብር ይገበያሉ፡፡ በአንፃሩ በጥቁር ገበያው ለአንድ ዶላር እስከ 34 ብር ግብይት ይፈጸማል፡፡ ስንት ውጣ ውረድ ዓይቶ ምርቱን ወደ ውጭ ልኮ ዶላር የሚያመጣው ነጋዴ ግን ዓይኑ እያየ ያስገኘው ዶላር ከጥቁር ገበያው ባነሰ ዋጋ ለመሸጥ መገደዳቸው በራሱ የወጪ ንግዱ ላይ ተዋናይ ለመሆን ከማያበረታቱ አሠራሮች አንዱ መሆኑን አቶ አሚን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህ እንግዲህ በዚህ ዓመት የተደረገውን የ15 በመቶ የምንዛሪ ለውጥ አካቶ የሚሰማ ችግር ነው፡፡
ሌላኛው አቶ አሚን የፖሊሲ ትችት አማራጭ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን መከተል አለመቻልን የሚቃኝ ነው፡፡ በሌሎች አገሮች ‹‹ፖሊሲ ዳይኮቶሚ›› የሚባል ይህኛው ባይሠራ ያኛው፣ እየተባለ የሚኬድበት አማራጭ በኢትዮጵያ ብዙም ትኩረት እንደማይሰጠው አብራርተዋል፡፡ ለወጪ ንግድ የሚሰጠውን ትኩረት ያህል ለተተኪ ምርቶች ማለትም ከውጭ የሚገባውን ምርትና ሸቀጥ በአገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችሉ አምራቾችም ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ፣ ይህ ሲደረግ የአገሪቱ የንግድ ሚዛን ጉድለት ሊሻሻል እንደሚችል ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
አቶ ጌታቸው በመጽሐፋቸው ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ባቀረቡት የማጠቃለያ ሐሳብና ትንታኔ ወቅት ከቁጠባና ከዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ጥቂት ነጥቦችን አንስተዋል፡፡ በተለይም በቁጠባ ምክንያት አነስተኛ ገቢ ያለው ሕዝብ ላይ ያለውን ጫና ለማመላከት ሞክረዋል፡፡ በመጽሐፋቸውም ‹‹እንደ እኛ የሚቆጥብ ማን አለ?›› በሚለው የምዕራፍ ዘጠኝ ንዑስ ርዕስ ውስጥ ካካተቷቸው ሐሳቦች በመነሳት የተናገሩት ሐሳብ ታዳሚውን ፈገግ አሰኝቷል፡፡ ‹‹ባንኮች ድሃው እንዲቆጥብ ይወተውታሉ፡፡ ሀብታሙ ግን አይቆጥብም፡፡ ሀብታሞቹ አይደሉም ቆጥበው ባጃጅ እንዲሸለሙ የሚወተወቱት፤›› በማለት የባንኮቹን የወቅቱን ውትወታ እንዲህ ገልጸውታል፡፡
‹‹ቁጠባ አላሳለፈልንም እንጂ እንደ እኛ የሚቆጥብ የለም፡፡ ኑሯችን ሁሉ ቁጠባ ነው፡፡ በዕድርና በዕቁብ አማካይነት እንቆጥባለን፡፡ ለክፉ ጊዜ በማለት ራስጌ ሥር ገንዘብ እንቆጥባለን፡፡ በቀን አንድ ጊዜ እየተመገብን ከምግባችን እንቆጥባለን . . . ›› ብለዋል፡፡
በአገሪቱ የሚታየው የባንኮች የቁጠባ ወለድ ክፍያ ወይም ምጣኔ ከአገሪቱ ወቅታዊ የዋጋ ንረት አኳያ ሲታይ፣ ‹‹አክሳሪ የቁጠባ መጣኝ›› ይዘት እንዳለውም በመጽሐፋቸው ስለቁጠባ በሚያወሳው ምዕራፍ ዘጠኝ ውስጥ በስፋት አብራርተዋል፡፡
እንዲህ ያሉ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ጽንሰ ሐሳቦችና አተገባበሮች የተብራሩበትን ይህንን መጽሐፍ ጨምሮ በ2007 ዓ.ም. ‹‹ግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚያችን፤›› በሚል ርዕስ ያሳተሙት፣ እንዲሁም በ1987 ዓ.ም. ‹‹የኢትዮጵያን ትኩረት የሚሹ ሦስት መሠረታዊ የኢኮኖሚ ጥያቄዎች፤›› በሚል ርዕስ ያሳተሙት መጽሐፍ በአብዛኛው ፖለቲካል ኢኮኖሚ ላይ ያጠነጠኑ ሥራዎች ሆነው ይገኛሉ፡፡ ወቅታዊ አገሪቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች በመከታተልና በመተቸት በርካታ መጣጥፎችን ያስነበቡት አቶ ጌታቸው፣ በግል ማማከር ሥራ የተሰማሩ ናቸው፡፡