Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትእግር ኳሱ የ‹‹ሁከት›› መንስኤ መሆኑ ለምን?

እግር ኳሱ የ‹‹ሁከት›› መንስኤ መሆኑ ለምን?

ቀን:

ዓለም ላይ የሰዎችን ቀልብ በመግዛት ቀዳሚ ከሆኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እግር ኳስ ተጠቃሽ ነው፡፡ ይኼው ስፖርታዊ እንቅስቃሴ በምንገኝበት ዘመን ከመዝናኛነቱም አልፎ አማራጭ የሌለው የኢንቨስትመንት ዘርፍ ሆኗል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን መንግሥታት በማኅበራዊና ፖለቲካዊ ረገድ ያለውን ጠቀሜታና ድርሻ በመረዳት ይመስላል ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

የስያሜው መጠሪያ ‹‹ይመጥነዋል አይመጥነውም›› የሚለው አከራካሪ ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከተመሠረተ ሁለት አሠርታትን ለማስቆጠር ከጫፍ የደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተለይም እግር ኳሱ በሚገኝበት በዚህ ዘመን ከዕድገቱ ይልቅ የ‹‹ሁከት›› መንስኤ መሆኑ ለምን? በሚል ሰዎችን ማነጋገሩ ቀጥሎበታል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ዘጠነኛ ሳምንት የውድድር መርሐ ግብር (ጥር 29 ቀን 2008 ዓ.ም.) በተለይም በአንዳንድ የክልል ከተሞች የታዩ የዲሲፕሊን ክፍተቶች ለዚህ ትልቅ ማሳያ ስለመሆናቸው ጭምር የሚናገሩ አሉ፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በበላይነት ከሚመራቸው ውድድሮች ውስጥ ቁጥራቸው እስከ 80 የሚደርሱ የብሔራዊ ሊግ ክለቦች፣ 32 ክለቦች የሚሳተፉበት ከፍተኛ ሊግ (ሱፐር ሊግ) እና 14 ክለቦች የሚሳተፉበት ፕሪሚየር ሊግ ይገኙበታል፡፡ የፌዴሬሽኑ የጨዋታ መርሐ ግብር እንደሚያስረዳው ከሆነ፣ ባለፈው ቅዳሜና እሑድ ብቻ ከ62 በላይ ጨዋታዎች በሦስቱም ሊጎች ተከናውነዋል፡፡ ጨዋታዎቹ በአብዛኛው ሥነ ምግባር በጎደለው ሁኔታ የተጠናቀቁ መሆኑ ደግሞ የጉዳዩን አሳሳቢነት እንደሚያጎላው የሚናገሩ አሉ፡፡

የአገሪቱ የእግር ኳስ ደረጃ እያሽቆለቆለ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ‹‹በእንቅርት ላይ …›› እንዲሉ በችግሮቹ ዙሪያ ፌዴሬሽኑና የሚመለከተው አካል በቅርበት ተነጋግረው ከወዲሁ የመፍትሔ አቅጣጫ ሊያስቀምጡለት እንደሚገባ የእግር ኳስ ዳኞችና የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች እንዲሁም ተመልካቾች ሥጋታቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ጨዋታዎች በሰላም ተጀምረው በሰላም መጠናቀቅ ይችሉ ዘንድ የእግር ኳስ ዳኞች ሚና ትልቅ ድርሻ እንዳለው የሚናገሩ ተመልካቾች በሌላ በኩል፣ እስከዛሬ ድረስ በተለይ በጨዋታ መሀል ለሚፈጠሩ ሁከቶችና የዲሲፕሊን ጉድለቶች የዳኝነት ጉዳይን በመንስኤነት ይጠቅሳሉ፡፡ ቅሬታውን አስመልክቶ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የእግር ኳስ ዳኞች በበኩላቸው፣ በእንቅስቃሴ መሀል የሚፈጠሩ ስህተቶች አሁን አይደለም ወደፊትም ሊታረሙ እንደማይችሉ፣ ሆኖም መግባባቱና መተማመኑ ካለ ስህተቶቹን መቀነስ እንደሚቻል ግን ያስረዳሉ፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን አስመልክቶ እስካሁን ድረስ የሰጠው መግለጫ ባይኖርም፣ አንዳንድ ማንነታቸው እንዲገለጽ የማይፈልጉ አመራሮች ለሁከቱ መፈጠር ምክንያት እየሆኑ የሚገኙ ክለቦችና ደጋፊዎቻቸው ለእግር ኳሱ ሰላም ሲባል ከፌዴሬሽኑ ጋር ተባብረው መሥራት እንደሚኖርባቸው ነው የሚያስረዱት፡፡

ከውጤት ጋር ተያይዞ የሚነሱ ተጠያቂነቶችን ለመሸሽ ሲባል ሁከትን እንደ ብቸኛ ማምለጫ የሚጠቀሙ የክለብ አመራሮች፣ አሠልጣኞች፣ ተጫዋቾች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካሎች ለሙያው ሥነ ምግባር ተገዢ ሊሆኑ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ በተለይ ለሁከት መነሻነት የክለቦች ስያሜዎች ከትውልድ ማንነት፣ ከሠራዊት መጠርያ ጋር መያያዙ ላለመተሳሰሩ ማረጋገጫ አለ ወይ የሚሉ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ፡፡

በ1950ዎቹ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች መጠርያ ለምሳሌ ሐማሴንና አከለ ጉዛይ ወደ አስመራና እምባይሶራ፣ ጦር ሠራዊትና ፖሊስ ወደ መቻልና ኦሜድላ፣ አየር ኃይልና ሸዋ ፖሊስ ወደ ንብና ዳኘው፣ ሶዶ ምንጭ ወደ አዋሽ ምንጭ እንዲሁም ሌሎች የተለወጡበት ምክንያት በወቅቱ ከነበው ሁከት በመነሳት በመሆኑ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፈጣን እርምጃ መውሰዱ ይታወቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...