ኢትዮ ቴሌኮም ከሚተገብራቸው አሠራሮች ውስጥ ከውጭ የሚገቡ የእጅ ስልኮች በአገር ውስጥ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስቻል ነው፡፡ የተዘጉ ስልኮችን በመክፈት አገልግሎት ላይ እንዲውሉ እያደረገ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን አገልግሎት በተለያዩ ቅርንጫፎቹ የሚሰጥ ሲሆን፣ ይህም በሕገ ወጥ መንገድ የሚገቡ የሞባይል ስልኮችን ለመቆጣጠርና የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት ያለመ አሠራር ነው፡፡
ስልካቸው አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የግድ የቴሌ ባለሙያዎችን እገዛ የሚሹት ግን የአገሬው ዜጎች ብቻ አይደሉም፡፡ የውጭ ዜጎችም ስልኮቻቸውን ለማስከፈት የቴሌን ደጅ ይጠናሉ፡፡ ይህንን አገልግሎት ለማግኘት በተለያዩ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ማዕከላት የሚታየውን ወረፋ ልብ ብሎ ያስዋለው አካል ያለ አይመስልም፡፡ ችግሩ አገልግሎቱን ለማግኘት የሚወስደው ጊዜ ብቻ ሳይሆን፣ ለተለያዩ ሥራዎችና ለአጭር ወይም ለረዥም ጊዜ ቆይታ ወደ ኢትዮጵያ የሚወጡ የውጭ ዜጎችን የሚጎረብጥ እየሆነ መታየቱም ነው፡፡
በዚሁ መሠረት አገልግሎት ለማግኘት ወደ ኢትዮ ቴሌኮም የሚያቀኑ የውጭ ዜጎች፣ ስልካቸውን ለማስከፈት የሚወስድባቸው ጊዜ ከሚገመተው በላይ እያስመረራቸው ስለመምጣቱ እየታዘብን ነው፡፡ እኛስ ለምደነዋልና እንቻለው ብንል እንኳ፣ የውጭ ዜጎችን በተለመደው ቢሮክራሲና አዝጋሚ የአገልግሎት አሰጣጥ ተቋዳሽ እንዲሆኑ ማድረግ ግን ከባድ ነው፡፡ ነገሩን ሰፋ አድርገን ከተመለከትነው የአገር ገጽታን የሚጎዳ መጥፎ አዝማሚያ ነው፡፡
ለምሳሌ ለሦስት ቀናት ቆይታ ብቻ የመጣ የውጭ ኢንቨስተር በአገር ውስጥ በሚያደርገው ቆይታ ወቅት የግድ ሞባይሉን መጠቀም ስላለበት፣ ይዞ የመጣውን ስልክ በአገር ውስጥ መጠቀም ካስፈለገው ማስከፈት ይኖርበታል፡፡ ሆኖም ወረፋ ጠብቆ ስልኩን ለማስከፈት አንድ ቀን ሙሉ መጠባበቅ ካስፈለገው፣ ዋናውን ሥራ በየትኛው ጊዜው ሊያከናውን ነው? የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ ዓለም ስንት በሚራበት ወቅት ስልክ ለማስከፈት ሰው እንዲህ ያለ ወረፋ መጠበቅ ካስፈለገው፣ ወደ ኢትዮጵያ የሚጋበው የውጭ ዜጋ መጀመርያ የሚያገኘው እንዲህ ያለ አማራሪ አገልግሎት ከሆነ፣ በቆይታው ወቅት ያሰባቸውን ሥራዎች እንዴት ሊያከናውን እንደሚችል ሥጋት ቢገባው አያስገርምም፡፡ እንዲህ ያለው ችግር እንዲህ በሚንፀባረቅ ምሬት የሚቀር አለመሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም አማራሪውን የአገልግሎት አሰጣጥ ወደ አገሩ ሲመለስ የሚገልጽበትና ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ሰዎች የሚያብራራበት መንገድ ይኖራል፡፡ ስለዚህ አሰልቺው የአገልግሎት አሰጣጥ በአገር ገጽታ ላይ የሚፈጥረው መጥፎ ሁኔታ እንደ ቀላል ነገር መታየት የለበትም፡፡
የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብ የሚደረጉ ጥረቶች ስንት ዋጋ እንደሚከፈልባቸው በሚነገርበት ወቅት፣ እንዲህ ያለ ቢሮሞክራሲያዊና የተንዛዛ የአገልግሎት አሰጣጥ መምጣቱ ያውም የቴክኖሎጂ አግልግሎት የሚሰጥ ተቋም፣ ኋላቀር አሠራር መተግበሩ ጉራማይሌ ነው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ የውጭ ዜጎችን በፍጥነት የሚስተናገዱበት መስኮት ማዘጋጀት ችግሩን ለማቃለል ይረዳል፡፡ በተለመደው አሠራር ከቀጠልን ግን ጉዳቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገንዘብ ያሻል፡፡ አንድ የውጭ ኢንቨስተር ኢትዮጵያን ሲረግጥ ጉዳዩን በስልክ ለመከወን እንዲሁም እንደ ኢንተርኔት ያሉ ለሥራው ወሳኝ አገልግሎቶችን ለመጠቀም የግድ የእጅ ስልኩ መከፈት ይኖርበታል፡፡ ስልኩን ለማስከፈት የሚወስድበት ጊዜ የመጣበትን ዓላማ እንዳያሳካ ብቻም ሳይሆን፣ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን የተሳሳተ ውሳኔ አድርጎ እንዲያስብ ሊያስገድደውም ይችላል፡፡ እንዲህ ያሉ ክፍተቶች ዞሮ ዞሮ ጉዳታቸው ቀላል ስለማይሆን ሊታሰብበት ይገባል፡፡
በአብዛኛዎቹ የአገራችን ተቋማት በአመዛኙ ዘመናዊና ቅልጥፍና የተላበሰ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችል ደረጃ ያልተዋቀሩ፣ ለብልሹ አሠራር የተጋለጡ፣ እንደ ድሮው የቴሌ ስልክ ሳንቲም ወይም ጉቦ ካልጎረሱ የማይሠሩ ናቸው፡፡ ይህ በተገልጋዩ ዘንድ ብቻም ሳይሆን፣ በመንግሥት ደረጃም የታመነ ችግር ነው፡፡ ብልሹ የመልካም አስተዳደር ውጥንቅጥ የወለዳቸው ችግሮች ስለመሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን እንመልከት ካልን ስለአገልግልሎት አሰጣጣቸው ‹‹እሰየው በርቱ››፣ እንትፍ እንትፍ የሚያስብሉ የመኖራቸውን ያህል የመሻታችንን የማይሞሉት ግን ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ስለዚህ ተገልጋዩን የሚያረካ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲዳብር ብዙ መልፋትና መትጋት ያስፈልጋል፡፡
የውጭ ዜጎችን የሚያስተናግዱ ተቋማትም ብርቱ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ በእርግጥ አገልግሎት አሰጣጥ ለአገሬውና ለውጭው ተብሎ መለየት ባይኖርበትም፣ ቢያንስ እንግዶቻችንን በለመድነው አሠራር በማስተናገድ ስማችንን ማስነሳት እንደሌለብን ግን መገንዘብ ግድ ይላል፡፡
እንደቀደመው ጊዜ ቴሌን የምንጠቅስበት ብዙ የአሠራር ጉድለቶች ባይኖሩም፣ እንደ ሰሞኑ ያሉትን አገልግሎቶቹን ግን ማስቀረት፣ ቀሪዎቹን አሠራሮቹን ምቹና ቀልጣፋ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ መጠቀስ ያለበት ጉዳይ፣ ዜጎች አንድ አገልግሎት ለማግኘት በፀሐይ እየተንቃቁ ወረፋ እንዲጠብቁ ማስገደድ በራሱ የችግሩ አንድ አካል ነው፡፡ አገልግሎት ሰጪው ደንበኞቹን ለማስተናገድ በሚያደርገው ጥረት ወረፋ የሚያስጠብቃቸው ከሆነ፣ ምናለ ከፀሐይ የሚከላከሉበት ምቹ ቦታ ማዘጋጀት ቢችል? የአገልግሎት አሰጣጥ ሲታሰብ እንዲህ ያሉ ነገሮችም ሊታሰቡ ይገባል፡፡ ተገልጋይ እስኪስተናገድ አረፍ የሚልበት ቦታ ያላዘጋጁ ተቋማትን እንቁጠር ከተባለ በርካታ ናቸውና ተገልጋይን በአግባቡ የማስተናገድ ባህላችን ሊጎለብት ይገባል፡፡