Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልአፍሪካዊነት የተንፀባረቀበት የቦብ ማርሌ ልደት

አፍሪካዊነት የተንፀባረቀበት የቦብ ማርሌ ልደት

ቀን:

ራስ ሥዩም፣ ቀድሞ ይዘፍን ከነበረው አርቲስት መድረኩን እንደተረከበ “ከኢትዮጵያ ወጥታችሁ ወደየትም አትሂዱ፤ ኢትዮጵያ መኖር ይሻላል፤ ከአፍሪካም ወደየትም አትሽሹ፤” እያለ ማቀንቀን ጀመረ፡፡ በሙዚቃዎቹ ኢትዮጵያን በአጠቃላይ አፍሪካን ከአውሮፓ ጋር በማነጻጸር “ወደ አውሮፓ ለመሄድ በመመኘት ሕይወታችሁን በቀይ ባህር አትጡ፤” እያለ በኢትዮጵያ ወይም በሌሎች የአፍሪካ አገሮች መኖርን ያወድስ ነበር፡፡ “ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አፍሪካ” በማለት በአህጉረ አፍሪካ ያሉ አገሮች መካከል አንድነት እንዲፀና የሚያሳስብ ሙዚቃ ያስደመጠው ደግሞ ቴዲ ዳን ነበር፡፡

የቦብ ማርሌን 71ኛ ዓመት የልደት በዓል ለመዘከር ጥር 28 ቀን 2008 ዓ.ም. ምሽት ላይ በአምባሳደር ፓርክ “ሬጌ ሙቭመንት ቡክ 1” በሚል የተዘጋጀው ኮንሰርት ብዙ የሬጌ ሙዚቀኞችን አስተናግዷል፡፡ በሙዚቃዎቻቸው የኢትዮጵያን ምድር ከፍ ከፍ የሚያደርጉ መልዕክቶች ተደምጠዋል፡፡ ኢትዮጵያን ከሚያወድሱ ሙዚቃዎች በተጨማሪ ስለፍቅር፣ ሰላምና አንድነት የሚሰብኩ ዘፈኖች ተሰምተዋል፡፡

በኮንሰርቱ በኢትዮጵያ ሬጌ ሙዚቃ ስማቸው ከሚጠቀስ ድምፃውያን መካከል ጆኒ ራጋ፣ ጃ ሉድና ራስ ጃኒ እንዲሁም ወጣቶቹ ዳጊ ሻሽ፣ ራስ አቤል፣ ራስ ኢቾ እና አቤል ራስታ አቀንቅነዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ውጪ የመጡት ራስ ስዩም፣ ቴዲ ዳን፣ ላቮስቲና ጃ ፔላም ሙዚቃዎቻቸውን አስድምጠዋል፡፡ ጆኒ ራጋ፣ ጃ ሉድና ራስ ጃኒ እንዲሁም ወጣቶቹ ድምጻውያን ከራሳቸው ዘፈኖች በተጨማሪ የቦብን፣ የጀንትልማንንና ሌሎችም በሬጌ ሙዚቃ ዕውቅ የሆኑ ዘፋኞችን ሥራዎች አቅርበዋል፡፡ ኮንሰርቱ ከመጀመሩ አስቀድሞና ከአንድ ሙዚቀኛ ወደ ሌላ ለመሸጋገር በሚኖረው ክፍተትም የነዚህን ድምፃውያን ሥራዎች ዲጄ አቢሲኒያና ኤምሲ ራስ ቦይ ያስደምጡ ነበር፡፡ የኢዮብ መኮንን፣ የጃማይካዊው ፕሮቴዤና የሌሎችም ሬጌ አቀንቃኞች ተወዳጅ ዘፈኖችም ተለቀዋል፡፡ የኮንሠርቱን የመጀመርያ ግማሽ ግዕዝ ሩትስ ባንድ ሁለተኛውን ደግሞ መሀሪ ብራዘርስ አጅበዋል፡፡

በመድረኩ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ያተኮሩ ሙዚቃዎች ቢደመጡም፣ ስለፍቅርና አንድነት የሚያወሱት ያመዝናሉ፡፡ “ወንድም ወንድሙን ለምን ይገላል?” እና “በሰላም እንኑር፤ እንቻቻል፤ እንዋደድ፤” ጎልተው ከተደመጡት መልዕክቶች ውስጥ ናቸው፡፡ ነፃነትና እኩልነት እንዲኖር፣ ዘርን መሠረት ያደረገ አድልዎ እንዲቀረፍ የሚያሳስቡ ሙዚቃዎችም ከመድረኩ ተደምጠዋል፡፡ በሬጌ መነሻቸውን በጥቁር ሕዝቦች ታሪክና የቅኝ ግዛት ተፅዕኖ ያደረጉና ስለነፃነት የሚያወሱ ሙዚቃዎችን መስማት የተለመደ ነው፡፡ በራስተፈሪያኒዝም የሚታመንባቸው፣ ለምሳሌ ሥጋ አለመብላትን (ቨጀቴሪያን መሆን) የመሰሉ ጉዳዮችም ተነስተዋል፡፡ ታዳሚዎቹ የሙዚቀኞቹን ግጥሞች እየተከተሉ አብሮ ከማቀንቀን ጎን ለጎን ለሚነሱት ሐሳቦች ያላቸውን ድጋፍ ያሳዩ ነበር፡፡

ላየን ኦፍ ጁዳና የቦብ ምስል የሰፈረባቸው የኢትዮጵያ ባንዲራዎችን የሚያውለበልቡ ታዳሚዎች ነበሩ፡፡ ላይተራቸውን ለኩሰው ከፍ በማድረግ ድጋፋቸውን ያንፀባረቁትንም መጥቀስ ይቻላል፡፡ በኮንሰርቱ ከተገኙት ታዳሚዎች አብዛኞቹ ወጣቶች የሬጌ ሙዚቃ አፍቃሪዎች ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት የተዘጋጁ ልዩ ልዩ አልባሳትና መዋቢያዎች፣ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ምስሎች በብዛት ተስተውለዋል፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡን ታዳሚዎች መካከል አንድ ኮንሰርት ይጀመራል ተብሎ ከሚተዋወቅበት ሰዓት ዘግይቶ መጀመሩ የተለመደ ቢሆንም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሳይጀመር የሚቆይበት ሰዓት እየረዘመ እንደመጣ የጠቆሙ ነበሩ፡፡ መዘግየት እንደ መልካም ገፅታ የሚታይ እስኪመስል ድረስ በብዙ ኮንሠርት አዘጋጆች መለመዱን ተችተዋል፡፡

ሌላው የሬጌ ሙዚቃ ካለው አድማጭ አንጻር በኮንሠርቱ ላይ የተገኙት ታዳሚዎች ቁጥር ውስን የመሆኑ ጉዳይ ነው፡፡ የኮንሰርቱ መግቢያ ዋጋ 300 ብር ነበር፡፡ የጤና ይስጥልኝ ኢንተርቴመንት ኤንድ ኢቨንትስ ኃላፊ ዘላለም አምባዬ (ራስ ቦይ) ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ከተዘጋጀው ቦታ አንፃር ብዙ ታዳሚዎች ተገኝተዋል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ዋጋው ላይ ቅሬታ ማሰማታቸውን ተናግረዋል፡፡ ኮንሠርቱን በሚያዘጋጁበት ወቅት ከገጠሟቸው ችግሮች አንዱ የማስተዋወቂያ ሥራ የተሠራበት ጊዜ ማጠሩ መሆኑንም አያይዞ ጠቅሷል፡፡

ኮንሠርቱ ላይ ወጣት የሬጌ ድምጻውያን እንዲዘፍኑ የጋበዙበትን ምክንያት ሲያስረዳም፣ ‹‹ሬጌ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነትን ይሰብካል፡፡ ወጣቶች መልዕክቱን ተገንዝበው ሬጌን እንዲወዱ ለማድረግ ታስቦ ነው፤›› ብሏል፡፡ የተቀሩት ድምፃውያንም ያዘጋጁትን በጥሩ ሁኔታ እንዳቀረቡ ያምናል፡፡

ድርጅታቸው ከዚህ ቀደም ለቦብና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ልደት በተለያዩ ክለቦች የሙዚቃ ዝግጅት በማሰናዳት ቢታወቅም፣ ይህ የመጀመሪያ ኮንሠርታቸው ነው፡፡ በቀጣይ በአዲስ አበባ እንዲሁም በክልሎች ትልልቅ የሬጌ ኮንሠርቶች የማዘጋጀት ዕቅድ እንዳላቸው ኃላፊው ተናግሯል፡፡

በ1960ዎቹ በጃማይካ የተጀመረውን ሬጌ፣ ለመላው ዓለም በስፋት ካስተዋወቁ አንጋፋ ሙዚቀኞች የቦብ ስም ጎልቶ ይነሳል፡፡ ሙዚቃዎቹ የነፃነት ትግልን፣ የሰው ልጅ እኩልነትን፣ የአፍሪካ አንድነትን እንዲሁም በርካታ ንቅናቄዎችን አስተጋብተዋል፡፡ ሙዚቃዎቹ ዓለም አቀፍ ተወዳጅነትና ተደማጭነት ከማትረፋቸው በላይ በተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው ይታወቃሉ፡፡ ለፓን አፍሪካኒዝምና ራስተፈሪያኒዝም እንቅስቃሴዎች ባደረገው አስተዋጽኦ የሚታወሰው ቦብ፣ እ.ኤ.አ በ1981 በካንሰር ሳቢያ በ36 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡ ሙዚቃዎቹ ግን ፍቅር፣ ነፃነትና ኅብረትን እየሰበኩ ከትውልድ ትውልድ ይሸጋገራሉ፡፡ ፈለጉን የተከተሉና ዴሚያን ማርሌና ስቴፈን ማርሌ ያሉ ድምጻውያን ልጆቹም፣ ከሙዚቃዎቹ በተጨማሪ ለዓለም ያበረከታቸው ስጦታዎች ናቸው፡፡

የቦብ ልደት በጃማይካ፣ በኢትዮጵያ (በተለይም የተስፋ ምድር እንደሆነች በራስተፈሪያኖች በሚታመንባት ሻሸመኔና) ሌሎችም አገራት በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡ የመላው ዓለምን ትኩረት የሳበውና ብዙ ሺዎች የታደሙት 60ኛ ዓመት የልደት በዓሉን ምክንያት በማድረግ በመስቀል አደባባይ የተዘጋጀው ኮንሰርት አይዘነጋም፡፡ አምና 70ኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ የተመረቀው ሐውልትም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...