Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምየቱርክ አውሮፓን በስደተኞች የማጥለቅለቅ ዛቻ

የቱርክ አውሮፓን በስደተኞች የማጥለቅለቅ ዛቻ

ቀን:

በሶሪያ ከአምስት ዓመታት በፊት የተጀመረውን የእርስ በርስ ጦርነት ተከትሎ፣ ወደ አውሮፓ የሚሰደዱ ሶሪያውያን ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ አሻቅቧል፡፡ አዲሱ የአውሮፓውያን ዓመት ከገባ ወዲህ ደግሞ ቁጥሩ እያሻቀበ ነው፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በሩሲያ የሚደገፈው የሶሪያ መንግሥት ብዙ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው የነበሩትን አማፅያንና የአይኤስ ቡድን አባላትን ከአገሪቱ ጠራርጐ ለማስወጣት የጀመረው መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደሆነ ግሎባል ፖስት ዘግቧል፡፡

የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መሄድ በቅድሚያ የሚያጨናንቀው የሶሪያን ድንበር ተጋሪ ቱርክን ቢሆንም፣ ከቱርክ አልፈው ግሪክ ከዚያም ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገሮች የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ ከአራት ሚሊዮን በላይ ሶሪያውያን ሲሰደዱም የአብዛኞቹ መዳረሻ አውሮፓ ነበር፡፡ ባህር የሚበላቸውም ስደተኞች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡

ከአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ውስጥ እንደ ጀርመን በሩን ለስደተኞች ክፍት ያደረገ የለም፡፡ ጀርመን እ.ኤ.አ. በ2015 ከሶሪያ ስደተኞች እስከ አንድ ሚሊዮን ለሚጠጉት መጠለያ እንደምትሰጥ በማሳወቅ ካቀደችው በላይ ስደተኞች የተቀበለች ቢሆንም፣ የስደተኞችን ሸክም ሁሉም የኅብረቱ አባል አገሮች መካፈል አለባቸው ስትል እየወተወተች ነው፡፡ ሆኖም አውሮፓውያኑ እንደሚፈለገው በራቸውን ክፍት አላደረጉም፡፡ ስደተኞችም ከአገር ከመውጣት አልተቆጠቡም፡፡

- Advertisement -

አውሮፓውያኑ ይህን ችግር ለመፍታት ስደተኞች በሶሪያና በቱርክ ድንበር የሚቆዩበትን ዕቅድ ነድፈው፣ ለቱርክ ሦስት ቢሊዮን ዩሮ በዓመት ለመለገስና ቱርክ ድንበር የሚደርሱ የሶሪያ ስደተኞችም ባሉበት ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲያገኙ የተስማሙት ባለፈው ዓመት ማብቂያ ነበር፡፡ የቱርክ ባለሥልጣናት የኅብረቱ አባል አገራት ጉባዔ ላይ እንዲሳተፉ፣ ቱርክ የአውሮፓ ኅብረት አባል ለመሆን ያቀረበችው ጥያቄ በአፋጣኝ እንዲታይ የሚሉ ስምምነቶችም ይገኙባቸዋል፡፡

ሆኖም የአውሮፓ ኅብረት እ.ኤ.አ. በ2015 ኅዳር ላይ ለቱርክ ለማድረግ ቃል ከገባው ሦስት ቢሊዮን ዩሮ በዓመት ለመለገስ የሚለውን አለመፈጸሙ ውጥረት ፈጥሯል፡፡ የቱርክ ፕሬዚዳንት ሪሴፕ ኤርዶጋን፣ በቱርክና በሶሪያ ድንበር የሚገኙትን ከ50 ሺሕ ያላነሱ፣ እንዲሁም በየቀኑ እየጎረፉ የሚገኙትንና በአገሪቱ የሚገኙ ከሁለት ሚሊዮን ተኩል በላይ ስደተኞችን እንደሚለቁና አውሮፓን በስደተኞች እንደሚያጥለቀልቁ በመግለጽ የአውሮፓ ኅብረት መሪዎችን አስፈራርተዋል፡፡

ሚስተር ኤርዶጋን ባለፈው ዓመት በሶሪያ ስደተኞች ዙሪያ ከአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ያደረጉትን ውይይት የያዘ ቃለ ጉባዔ ሰሞኑን አፈትልኮ መውጣቱን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንገላ መርከል ሰኞ ጥር 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በቱርክ አንካራ በመገኘት ከቱርክ ባለሥልጣናት ጋር በስደተኞች ጉዳይ ከመምከራቸው አስቀድሞ ያፈተለከው ቃለ ጉባዔ፣ ኤርዶጋን የኅብረቱ አባል አገሮች ባለሥልጣናትን ያንቋሸሹበት፣ ስደተኞችን በድንበር ለማቆየት ሦስት ቢሊዮን ዩሮ ሳይሆን፣’ ስድስት ቢሊዮን ዩሮ ሊሰጥ እንደሚገባ የተከራከሩበት እንደነበር ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ አባል አገሮቹ ግን ባለፈው ዓመት ያፀደቁት ሦስት ቢሊዮን ዩሮ ለመለገስ ነው፡፡ ሆኖም ተፈጻሚ አልሆነም፡፡

እ.ኤ.አ. በ2015 ብቻ ከአንድ ሚሊዮን በላይ በሚሆኑ የሶሪያ ስደተኞች የተጨናነቀችውን ጀርመን ለማስተንፈስ አንገላ መርከል ቱርክ በመገኘት ስምምነቱ ወደ ተግባር በሚለወጥበት ጉዳይ ላይ መክረዋል፡፡

ሆኖም ያፈተለከውንና ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን በቃለ ጉባዔው ላይ ተናገሩ የተባለውን ጠቅሶ ዘ ቴሌግራፍ እንደዘገበው፣ ‹‹ቱርክ የአውሮፓ ኅብረትን ገንዘብ አትፈልግም፡፡ በማንኛውም ሰዓትም ወደ ቡልጋሪያና ቱርክ የሚያስኬደውን በሯን ትከፍታለች፡፡ ስደተኞችንም በአውቶቡስ ጭና ትልካለች፤›› ብለዋል፡፡

ኤርዶጋን ባለፈው ዓመት ከአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች መሪዎች ጋር በነበረው ልዩና አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል ስለመባሉ የተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘግቡት፣ የአውሮፓ ኅብረትም ሆነ የቱርክ መንግሥት አላስተባበሉም፡፡ አስተያየትም አልሰጡም፡፡ ይህም ቃለ ጉባዔው እውነት እንደሆነ፣ የአውሮፓ ኅብረት ለቱርክ እሰጣለሁ ያለው የሦስት ቢሊዮን ዩሮ ስምምነትም አደጋ ላይ መሆኑን ዘ ቴሌግራፍ አትቷል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ለቱርክ ለመለገስ ቃል የገቡትን ገንዘብ ዕውን ለማድረግና ቱርክም ስደተኞችን ባሉበት እንዲቆዩ እንድታደርግ ለመምከር ወደ ቱርክ ያቀኑት አንገላ መርከል፣ ከቱርክ ጠቅላይ ሚኒስትር አህመት ዳቩቱግሉ ጋር በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ሩሲያ በሶሪያ ውስጥ እያካሄደች ባለው የአየር ድብደባ መሳቀቃቸውን፣ ኅብረቱ ለቱርክ ሦስት ቢሊዮን ዩሮ ለመለገስ የደረሰበትን ስምምነት ወደ ተግባር የመለወጫ ጊዜው አሁን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከ50 ሺሕ በላይ የሶሪያ ስደተኞች ቱርክ ድንበር፣ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ደግሞ ቱርክ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ቱርክ ካቅሜ በላይ ነው ብላ ስደተኞቹን ከለቀቀች ጫናው የአውሮፓ ነው፡፡ ሆኖም አብዛኞቹን ስደተኞች ራሷ እያስተናገደች ትገኛለች፡፡ በቱርክ የሚገኙ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶችም እገዛ እያደረጉ ነው፡፡

አፈተለከ የተባለው ቃለ ጉባዔ የሚስተር ኤርዶጋንን ዳተኝነት ቢያትትም፣ የቱርክ ባለሥልጣናት ከአንገላ መርከል ጋር በነበራቸው ቆይታ የአውሮፓ ኅብረት ለቱርክ ቃል የገባውን የሦስት ቢሊዮን ዩሮ ዕርዳታ ተግባራዊ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡ የገንዘቡ መገኘት በቱርክ የሚገኙ ስደተኞችን ለመታደግና የፖለቲካ ጥገኝነት ጠያቂዎችንም ለመቀበል ያስችላል ብለዋል፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው እ.ኤ.አ. በ2016 የመጀመሪያዎቹ አምስት ሳምንታት ብቻ 68 ሺሕ ስደተኞች ወደ ግሪክ አቅንተዋል፡፡ ከእነዚህ ግማሽ ያህሉ ሶሪያውያን መሆናቸውንም ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ዘግቧል፡፡

የአውሮፓ ኅብረትም ቱርክ ለሶሪያ ስደተኞች በሯን ክፍት እንድታደርግ ጫና እየፈጠረ ነው፡፡ ይህም በአገሪቱ የተለያዩ አመለካከቶች እንዲንፀባረቁ አድርጓል፡፡

የኤርዶጋን ተቃዋሚዎች፣ ‹‹የአውሮፓ አገሮች ለደኅንነት በማለት በሮቻቸውን ለስደተኞች ዝግ ሲያደርጉ በተቃራኒው ቱርክ እንድትቀበል ይገፋፋሉ፤›› ሲሉ፣ ደጋፊዎች ደግሞ፣ ‹‹በአውሮፓ ለስደተኞች ያለው ክብር ኢሰብዓዊነት የተሞላበት ስለሆነ ስደተኞች ቱርክ እንዲቀሩ ይፈልጋሉ፤›› ብለዋል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ፣ ‹‹ዓለም በሶሪያ ጉዳይ ጽንፍ ይዟል፡፡ የሁሉም መልዕክት ግን አንድ ነው፡፡ ሶሪያውያን ወደ አውሮፓ አትምጡ፣ ባላችሁበት ሙቱ፤›› የሚል እንደሆነ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡        

 

                                                           

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...