Tuesday, November 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ወደ ሀብት የሚሮጡትን ተንጠባጥበው የሚቀሩትን ጭንቀት አለባቸው››

ዶ/ር ሰለሞን ተፈራ፣ የኢትዮጵያ የአእምሮ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት

ዶ/ር ሰለሞን ተፈራ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአእምሮ ሕክምና ጥናት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ የአእምሮ ሕክምና ስፔሻሊስት ሲሆኑ፣ በአእምሮ ሕክምና ጥናት ፒኤችዲ ዲግሪ አላቸው፡፡ የሰብ ስፔሻላይዜሽን ሥልጠና የወሰዱት በካናዳ ቶሮንቶ ነው፡፡ በጥቅሉ ያለፉት 16 ዓመታትን በአገልግሎትና በትምህርት አሳልፈዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በማስተማር፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡ በበጐ ፈቀደኝነት ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ የኢትዮጵያ የአእምሮ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበርን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአገሪቱ የአእምሮ ጤና ሕክምና፣ አጠቃላይ ሁኔታ፣ የሕክምና አገልግሎት ተደራሽነትና ስለማኅበሩ እንቅስቃሴ ምሕረት አስቻለው ከዶ/ር ሰለሞን ተፈራ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡  

ሪፖርተር፡- ማኅበሩ የተቋቋመው እንዴት ነው?

ዶ/ር ሰለሞን፡- ከአሥር ዓመት በፊት ማኅበሩን የማቋቋም ጥረቶች የነበሩ ቢሆንም በአዲስና በተደራጀ መልኩ ማኅበሩን ያቋቋምነው በ2006 ዓ.ም. ነው፡፡ ማኅበሩ እንዲቋቋም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ካደረጉ መካከል አንዱ ነኝ፡፡ በመላ አገሪቱ የሚገኙ ሳይካትሪስቶችን በማንቀሳቀስና መሥራች ጉባኤ እንዲካሔድ በማድረግ ነው ማኅበሩ ሊቋቋም የቻለው፡፡ ከማኅበሩ መሠረታዊ ዓላማዎች አንዱ በአገሪቱ በሚገኙ የአእምሮ ሕክምና ባለሙያዎች መካከል መቀራረብ እንዲፈጠርና የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ማስቻል ነው፡፡ የውይይት መድረኮች መዘጋጀት የሥልጠናዎች መሰጠት በየጊዜው ባለሙያው እውቀትና ልምዱን እንዲያዳብር ያግዛል፡፡ ሁለተኛው በአገሪቱ የአእምሮ ሕክምና አገልግሎት ያልዳበረ ስለሆነ፣ ያለው ግንዛቤም የዚያኑ ያህል በመሆኑ፣ አገልግሎቱም ከፍተኛ ክፍተት ስላለበት በማኅበረሰቡ ዘንድ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ፣ በፖሊሲ አውጪዎች በኩልም የአእምሮ ጤና ትኩረት እንዲያገኝ በተደራጀ መልኩ ድምፃችንን ማሰማት እንድንችል ነው፡፡ የአእምሮ ሕሙማን መገለል፣ ለሙያው ለባለሙያውም የሚሰጠው ቦታ ዝቅተኛ በመሆኑ ጉዳዩ ቅስቀሳ (አድቮኬሲ) እንደሚያስፈልገው እሙን ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ በተደራጀ መንገድ ነው፡፡ አዳዲስ ሳይንሳዊ እውቀቶችን መቀበል ከመሰል አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠርን የመሰሉ ሌሎች ዓላማዎችም አሉ፡፡ ጥናትና ምርምር ማካሔድ የተፈተኑ ሕክምናዎችን ከአገራችን የአእምሮ ሕክምና እውነታ ጋር በማዛመድ ጥቅም ላይ የሚውሉበትን መንገድ መፍጠርም ትልቁ የማኅበሩ ትኩረት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለሙያው ትኩረት ባልተሰጠበት ሁኔታ በመላ አገሪቱ ያሉ ባለሙያዎችን ለመድረስ የምታደርጉት ጥረት ምን ይመስላል?

ዶ/ር ሰለሞን፡- የባለሙያ ቁጥር ትንሽ ነው፡፡ ግን ይህ ቁጥር ሲጠቀስ መነሻውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት የነበሩት ባለሙያዎች ከአሥር የማይበልጡ ነበሩ፡፡ ከዚያ ተነሥቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስልሳ የሚጠጉ ሳይካትሪስቶች አሉ፡፡ ስፔሻላይዝ ያደረጉ ከዚህም አልፎ ሰብ ስፔሻላይዝ ያደረጉ ባለሙያዎች አሉ፡፡ አሁንም ቁጥራችን አነስተኛ ቢሆንም ወደተለያዩ አገሮች ሔዶ ሙያውን ከፍ ወዳለ ደረጃ የማድረስ ጥረትም እየተደረገ ነው፡፡ በሰብ ሳህራ አፍሪካ ያለው የሳይካትሪስት ቁጥር አንድ ሺሕ አይሞላም፡፡ ይህ ማለት ወደ አንድ ቢሊዮን ለሚጠጋ ሕዝብ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 500 የሚሆኑት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ናቸው፡፡ 200 ናይጄሪያ ቀጥሎ ሊጠሩ የሚችሉ አገሮች ኢትዮጵያ፣ ኬንያና ሱዳን ናቸው፡፡ እንደ ጋና ባለ አገር እንኳ የሳይካትሪስት ቁጥር ስድስት ብቻ ነው፡፡ ሳይካትሪስት የሌላቸው፣ አንድ ሁለት ያላቸውም ብዙ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ሙያው ከሰሐራ በታች ባሉ አገሮች ያደገ አይደለም፡፡ ስለዚህ እኛ አገር የታየው ለውጥ ትልቅ ነው፡፡ ለምሳሌ በእኛ ዩኒቨርሲቲ በሥልጠና ላይ ያሉ ሀያ የሚሆኑ ሳይካትሪስቶች አሉ፡፡ በዚህ ሙያ በጅማ ዩኒቨርሲቲና በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ኮሌጅ ሥልጠና ተጀምሯል፡፡ የቁጥራችን ማነስ እንዳለ ሆኖ አባላት ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ጊዜው አጭር ቢሆንም በዚህ ጊዜ (በሁለት ዓመት) ውስጥ ወሳኝ የሚባሉ የማኅበሩ ዕርምጃዎች?

ዶ/ር ሰለሞን፡- ማኅበሩን ሕጋዊ ዕውቅና እንዲኖረውና እንዲንቀሳቀስ ማስቻል ለብዙዎች እንደ ትልቅ ተራራ የታየ ነገር ነበር፡፡ ስለዚህም ዕውቅና ለማግኘት ያሉ ፈተናዎችን ማለፍ የመጀመሪያው ዕርምጃ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ወሳኝ በሆኑ የአእምሮ ጤና ጉዳዮች ላይ የውይይት መድረኮችን አድርገናል፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተሳተፈበት የአገሪቱን የአእምሮ ጤና ሁኔታ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የዳሰሱ ጥናቶች የተደረጉበት፣ ውይይቶችና ክርክሮች የተደረጉባቸው መድረኮች ነበሩ የተዘጋጁት፡፡ እነዚህ መድረኮች ምን መሆን አለበት? ምን መደረግ አለበት? በሚባሉ የአእምሮ ጤና ጉዳዮች ላይ በአንድ ድምፅ አቅጣጫ እንድናመለክት እረድተዋል፡፡ ጤና ጥበቃ እንደ አንድ ዋና ባለድርሻ ተሳትፎውን አድርጓል፡፡ እኔን ጨምሮ አብዛኞቻችን ሳይካትሪስቶች የአገሪቱን የአእምሮ ጤና በሚመለከቱ ጉዳዮች ቀደም ሲልም ከፍተኛ ተሳትፎ ያለን ነን፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት የመጀመሪያው የአገሪቱ የአእምሮ ጤና ስትራቴጂ ሲቀረጽ የቴክኒክ ቡድኑን የመራነው እኛ ነን፡፡ በወቅቱ የተሳተፍነው ለምሳሌ እኔ እንደ ባለሙያና እንደ ዩኒቨርሲቲ ማኅበረሰብ አባልነቴ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህን ተሳትፎ በማኅበሩ ስም አጠናክረን እያስቀጠልን ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ውስጥ በአእምሮ ጤና ላይ የባለሙያዎች አማካሪ ቡድን ውሰጥ እየተሳተፍን ነው፡፡ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አገር አቀፍ የአእምሮ ጤና ሲምፖዚየም እየተካሔደ ነው፡፡ አምና አዲስ አበባ የዘንድሮው መቀሌ ነበር የተደረገው፡፡ የሲምፖዚየሙ ሳይንሳዊ ቅርፅ የሚመለከተውን ቡድን መርቻለሁ፡፡ ይህ ማኅበሩን ወክዬ ያደረግኩት ተሳትፎ ነው፡፡ ለሕክምና ባለሙያዎች በየጊዜው ፍቃድ ለማደስ ተከታታይ ሥልጠና መውሰድ አስፈላጊ መሆኑ ለሕክምና ታምኖበት ይህን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡ ይህንን የባለሙያዎች ሥልጠና የመስጠት ኃላፊነት በዋናነት ለሙያ ማኅበራት የተሰጠ ሲሆን፣ ማኅበራችን ይህንን የሙያ ሥልጠና የመስጠት ፍቃድ ማግኘቱን እንደ ትልቅ ስኬት ነው የምንመለከተው፡፡ ምክንያቱም ሌላ አካል አሠልጥኖ ዕውቅና የሚሰጠን ሳይሆን ራሳችን ለሙያችን ኃላፊነት መውሰድ ችለናል፡፡ ሁሉም ማኅበራት ይህን ዕድልም አላገኙትም፡፡ ማኅበራችን ከተቋቋመ በኋላ ከሀምሳ ዓመት በላይ ዕድሜ ካለው ከኢትዮጵያ ሕክምና ማኅበር ጋር እየሠራ ነው፡፡ የዓለም የሳይካትሪስቶች ማኅበርም (World psychiatric association) አባል ነን፡፡ ይህ ምን ያህል እየተንቀሳቀስን እንደሆነ ያሳያል፡፡ ሌላው በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረግንበት ያለው ሁነት ሰኔ ውስጥ ከአፍሪካ ሳይካትሪ ማኅበር ጋር በመሆን ትልቅ አህጉራዊ ጉባኤ ማካሔድ ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- እንደዚህ ያለ የአእምሮ ጤና ላይ የሚያተኩር አህጉራዊ ጉባኤ ሲደረግ የመጀመሪያ ነው? የሚነሱ ርዕሰ ጉዳዮችስ ምንድን ናቸው?

ዶ/ር ሰለሞን፡- የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ በጥቂት ሳይካትሪስቶች ጥረት ተመሳሳይ ጉባኤ ተደርጐ ነበር፡፡ ስለዚህ ይህ ሁለተኛው ሊባል ይችላል፡፡ አባል አገር በመሆናችን እንዲሁም ይህን ጉባኤ ለማካሔድ አቅሙና ዝግጅቱ አለን በማለታችን ጉባኤውን ለማዘጋጀት ዕድሉን አግኝተናል፡፡ መጀመሪያ ጉባኤው ሊካሔድ የታሰበው ታንዛኒያ ውስጥ ነበር፡፡ ይህንን ዓይነት ጉባኤ ማካሔድ በሌሎች አገሮች የተደረጉ ምርምሮችን፣ አዳዲስ አሠራሮችን በሚመለከት ልምድ ለማግኘት ይረዳል፡፡ ብዙ ጥናቶችም የሚቀርቡበት ጉባኤ ነው፡፡ እንደ አገርም ከውጭ ብዙ ሰዎች ሲመጡ ለቱሪዝሙም ለገጽታ ግንባታውም የሚያበረክተው አስተዋጾ አለ፡፡  

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ የአእምሮ ጤና ሁኔታ እንዴት ይገመገማል?

ዶ/ር ሰለሞን፡- ችግሩ ብዙዎች ከሚገምቱት በላይ ሰፊ ነው፡፡ እዚህ አገር ባንድም ይሁን በሌላ መንገድ 15 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የአእምሮ ችግር አለባቸው፡፡ ይህ ሕፃናትንም የሚጨምር ሲሆን፣ እስከ 20 ሚሊዮንም ሊደርስ ይችላል፡፡ ይህ በተለያዩ አካባቢዎች የተሠሩ የተለያዩ ጥናቶች ተጨምቀው በአገር አቀፍ ደረጃ የተሠራ ስሌት ነው፡፡ ይህ ቁጥር ከአሥር ዓመት በፊት የተቀመጠ ነው፡፡ አሁን እስከ 20 ይደርሳል ያልኩትም ለዚሁ ነው፡፡ ይህ ማለት ከአምስት ሰዎች አንዱ ላይ ችግሩ ይታያል ማለት ነው፡፡ እንደ ስኪዞፍሬኒያ ከበድ ያሉትን ያየን እንደሆነ ከግማሽ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ችግሩ አለባቸው፡፡ ስኪዞፍሬኒያ ከባዱ የአእምሮ ሕመም ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ያሉት እንደ ድብርት፣ ጭንቀትና የተለያዩ ሱሶች ተጨማምረው ቁጥሩን ከፍ ያደርጉታል፡፡

ሪፖርተር፡- ሰዎችን ለአእምሮ ሕመም ተጋላጭ የሚያደርጉ የተለዩ አገራዊ ሁኔታዎች እንዴት ይታያሉ?

ዶ/ር ሰለሞን፡- የአእምሮ ጤና ችግሮች መነሻን እኛ ብዙ ጊዜ በሦስት ከፍለን ነው የምንመለከታቸው፡፡ የመጀመሪያው ተፈጥሯዊ ተጋላጭነት ወይም ሰዎች በራሳቸው ውሳኔ የሚገቡበት ሱስ አንዱ ነው፡፡ ሁለተኛው ሥነ ልቦናዊ ጫና ነው፡፡ ይህ ጭንቀትና ውጥረት ነው፡፡ ሦስተኛው ማኅበራዊ ሲሆን፣ የተለያዩ ሽግግሮችን፣ ማኅበራዊ ግጭቶችን፣ ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ይጨምራል፡፡ በተለይም እንደ እኛ በሽግግር ላይ ያለ ማኅበረሰብ ለሥነልቦናዊና ማኅበራዊ ቀውሶች የተጋለጠ ነው፡፡ ወደ ሀብት የሚሮጡት፣ በውጥረት ተንጠባጥበው የሚቀሩትም ጭንቀት አለባቸው፡፡ እንደዚህ ያለ ለውጥ ውስጥ ባለ ማኅበረሰብ ውስጥ ማንም ከጫና ነፃ ነች ሊል አይችልም፡፡ እኔም ባልደረቦቼም ያየናቸው ስኬታማ የሚባሉ ግን የአእምሮ ችግር ያለባቸው ብዙ አሉ፡፡ የአንዳንዶቹ ኬዝ ለማመን የሚቸግር ሁሉ ነው፡፡ በጥቅሉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ ሽግግር ላይ ባለ ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር ጫናው ከባድ ነው፡፡ ለምሳሌ ባህላዊ ሽግግሩን ብንመለከት ቀደም ሲል ሰዎች የጠበቀ ማኅበራዊ ትስስር ነበራቸው፡፡ የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥም ለጓደኛ፣ ለዘመድ ለሃይማኖት አባት ይነገር ነበር፡፡ አሁን ሰዎች በራሳቸው የሕይወት ሩጫ የተወጠሩበት በመሆኑ አንዱ የሌላውን ችግር ሰምቶ ድጋፍ ለማድረግ የሚቸገርበት ጊዜ ነው፡፡ ማንም ጊዜ የለውም፡፡ ይህ አንድ ትልቅ ሥነልቦናዊ ጫና ነው፡፡ ችግር ያለባቸው ሰዎች በነፃነት ሔደው አገልግሎት የሚያገኙባቸው ተቋማት በስፋት አለመኖር ብዙዎች ችግራቸውን ተሸክመው ቤታቸው እንዲቀመጡ የግድ ብሏል፡፡ ለምሳሌ ድብርት የተባለው የአእምሮ ሕመም ላይ አገራዊ ጥናት ለማድረግ ሞክረን ነበር፡፡ ውጤቱ በይፋ ያልወጣ ቢሆንም ቀላል የማይባል ቁጥር ያለው ሰው በሕመሙ እንደሚጠቃ ያሳያል፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የግንባታ ሠራተኞች የሚያስፈልገውን ክህሎት እንዲያሟሉ ትምህርታቸው በሥራ ላይ ልምምድ የታገዘ መሆን አለበት›› አቶ ሙሉጌታ ዘለቀ፣ የናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት መሥራች

ናሽናል ኮንስትራክሽን ሪልስቴት የተመሠረተው በ2003 ዓ.ም. ነው፡፡ ላለፉት 13 ዓመታትም በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት የሚውሉ ሕንፃዎችን ለደንበኞቹ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢንጆይ ጀነራል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል...

‹‹የኤድስ በሽታ ከ10 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ባሉ ልጆች በሁለት እጥፍ እየጨመረ ነው›› ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ፣ በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኤችአይቪ ኤድስ ዘርፍ...

የኤችአይቪ ኤድስ ሥርጭት ከቦታ ቦታ ቢለያይም እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡ አዲስ አበባም የችግሩ ሰለባ ከሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች አንዷ ናት፡፡ ሲስተር ፈለቀች አንዳርጌ በአዲስ አበባ ጤና...

‹‹የዋጋ ግሽበቱ እንደ አቅማችን እንዳናበድርና ተበዳሪዎችም እንዳይከፍሉ እያደረገ ነው›› አቶ ፍጹም አብረሃ፣ የአሚጎስ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ

አሚጎስ የቁጠባና ብድር ኅብረት ሥራ ማኅበር፣ በተቋም ደረጃ ለመመሥረቱ መነሻው ጓደኛሞች በየወሩ በቁጠባ መልክ የሚቆርጡት ተቀማጭ ገንዘብ ነው፡፡ በ20 ሺሕ ብር ካፒታል በ20 ጓደኛሞች...