Saturday, June 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቲማቲም ማቀነባበሪያ ለማቋቋም የአጋርነት ስምምነት ተፈረመ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሙሉዓለም ወሰነ እርሻ የተባለ የግል ድርጅት ከ60.1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚጠይቅ የቲማቲም ማቀነባበሪያ ለመገንባት የሚያስችለውን የቴክኒክ እገዛ ለማግኘት ከኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ ጋር ስምምነት አደረገ፡፡

በደቡብ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ የሚገነባው ይህንን የቲማቲም ማቀነባበሪያ ግንባታ ለማካሄድ ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ የሚሳተፈው የማቀነባበሪያውን አጠቃላይ ዕቅድ ጨምሮ በራሱ ወጪ የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት ነው፡፡ ማቀነባበሪያው ለባለአነስተኛ ማሳ አርሶ አደሮች የሚሰጠውን ወሳኝ ጠቀሜታዎች በማጤን ጭምር ለማቀነባበሪያው ፋብሪካው ውጤታማ እንዲሆን ከሙሉዓለም ወሰነ እርሻ ጋር ለመሥራት እንደተዋዋለ ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ የላከው መረጃ ያስረዳል፡፡

የማቀነባበሪያው መቋቋም እስከ 25 በመቶ የሚደርሰውን የቲማቲም ድኅረ ሰብል ብክነት በማዳን፣ ቲማቲም አቅራቢዎች የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ ያስችላል ተብሏል፡፡ አስተማማኝ ባልሆነ ግብይት የተነሳ አርሶ አደሮች የሚያጡትን ገቢ እንዲያገኙ ማስቻል እንዲሁም የድርድር አቅማቸውን መጨመር የሚሉት ሌሎች ተጠቃሽ ጠቀሜታዎች ሲሆኑ፣ እነዚህ እንዲፈጸሙ ለማስቻል ከጥናት ጀምሮ ያለውን ሥራ ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ ይሠራዋል ተብሏል፡፡

የእርሻ ድርጅቱ  አቅራቢያ ባሉ ማሳዎች ላይ የሚገኙ 5,703 ባለአነስተኛ ማሳ አርሶ አደሮችን በአምርቶ አቅራቢነት እንደሚያደራጅ ታውቋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ተገቢ የሆነ የእሴት ሰንሰለት ሥርዓት በመዘርጋት በባለአነስተኛ ማሳ አርሶ አደሮችና በቲማቲም ማቀነባበሪያው መካከል ዘላቂ የግብይትና የአቅርቦት ትስስሮሽ እንዲፈጠር ማስቻል የኢንተርናሽናል ፓርትነርስ የሥራ ድርሻ ይሆናል ተብሏል፡፡ በዚህም በመጀመርያው ዓመት ብቻ እያንዳንዱ ምርት አቅራቢ አርሶ አደር በነፍስ ወከፍ 1,300 ብር ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝበትን ዕድል የሚፈጥርም ስለመሆኑ የተላከው መረጃ ያስረዳል፡፡ በቀጣይ ዓመታት ደግሞ የተጠቀሰው ገቢ ቢያንስ በአምስት በመቶ እያደገ የሚሄድ አሠራር ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በአጠቃላይ ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ ለማቀነባበሪያው በሚውሉ ማሽኖች ግዢና ተከላ ሒደት ቴክኒካዊ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡ የለጋ ቲማቲም አቅርቦት ላይ የእሴት ሥርዓትን ለመንደፍ፣ ሙከራ ለማካሄድና ለመዘርጋት ቀጥሎም የማቀነባበሪያ አመራር ሥርዓትን ለመቅረፅና ለመዘርጋት፣ የድኅረ ሰብል አያያዝና የግብይት ስትራቴጂ ለመተግበር የሚያስፈልገውን የገንዘብና የቴክኒክ እገዛም በኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ በኩል የሚቀርብ ይሆናል፡፡ ስምምነቱ እስከ ታኅሳስ 2009 ዓ.ም. ድረስ የሚቀጥል ሲሆን፣ ማቀነባበሪያው በየካቲት 2009 ዓ.ም. ድረስ ሥራ እንደሚጀምር መረጃው ያስረዳል፡፡

የሙሉዓለም ወሰነ እርሻ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉ ዓለም ወሰነ እንደገለጹትም፣ የማሽነሪ ግዢ በመካሄድ ላይ ነው፡፡ የማቀነባበሪያው መቋቋምም ከ440 ላላነሱ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል፡፡ የኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ የቡድን መሪ አቶ ነቢል ኬሎ እንደጠቀሱት፣ ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ የቢዝነስ ተቋማት መዋዕለ ንዋያቸውን እንዳያፈሱ የሚያደርጓቸውን ተግዳሮቶችና ሥጋቶች በመለየትና በፍጥነት ሊያድጉ የሚችሉ አዋጭ የቢዝነስ ሞዴሎችን እንዲተገበሩ እገዛ ያደርጋል፡፡ እንዲህ ያሉ ቢዝነሶችን ኪሳራን በመጋራት መርህ የፈጠራ አካል ከሆኑ አካላት ጋር ተጣምሮ በመሥራት ግብይቶች የሚቃኑበትን አሠራር እንደሚያመቻችም ገልጸዋል፡፡

የዚህ ስምምነት ዋነኛው ፋይዳ በድህነት የሚኖሩ ሴቶች ምርታቸውን በሚያቀነባብረው ድርጅት ውስጥ ወሳኝ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማስቻል የተሻለ ግብይት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግና የድርድር አቅማቸውን ማጎልበት እንደሆነም ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ ገልጿል፡፡ አቶ ሙሉዓለም ለሪፖርተር እንደገለጹትም፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እርሻ ላይ የተሰማራው ድርጅታቸው እንዲህ ባለው ድጋፍ ወደ ማቀነባበሪያ መግባቱ ውጤታማ ያደርገዋል፡፡ ድርጅቱ በ43 ሔክታር ላይ ምርት እያመረተ ቢሆንም፣ ለምርቱ የሚወጣው ወጪና የሽያጭ ዋጋው የተስማማ አለመሆን ወደ ማቀነባበሪያው እንዲገባ አድርጎታል ተብሏል፡፡

ማቀነባበሪያው  ድርጅቱ በራሱ የሚያመርታቸውን አትክልትና ፍራፍሬዎችንም ጨምሮ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችን ምርት በመቀበል ከቲማቲም ሌላ የሌሎች ፍራፍሬዎች ማቀነባበሪያዎችን ለማስፋፋት ያግዛል፡፡

ለፋብሪካው ግንባታ የሚሆን 3,600 ካሬ ሜትር የተዘጋጀና የማቀነባበሪያው የአዋጪነት ጥናት በመጠናቀቁ ወደ መሣሪያ ተከላ በቅርቡ የሚገቡ መሆኑን አቶ ሙሉዓለም ገልጸዋል፡፡ ማቀነባበሪያውም በሰዓት ሁለት ቶን የማምረት አቅም ይኖረዋል ተብሏል፡፡

ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ በኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ በማጎልበት የሀብት ፈጠራን ለማበረታታት፣ በዚህም ለሴቶችና ለድሆች ይበልጥ የሥራ ዕድል እንደሚያስገኙ በሚታወቁት ጥጥ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ የቁም እንስሳት፣ ቆዳ፣ አትክልት፣ ፍራፍሬና የፋይናንስ ተደራሽነት ላይ የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡

ኢንተርፕራይዝ ፓርትነርስ ከላይ በተጠቀሱት ዘርፎች ውስጥ ከተሰማሩ የግል ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ በመሥራትና አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ የግል ድርጅቶቹ አቅም እንዲጨምር ብሎም ሥራ አጦችንና ሴቶችን እንዲቀጠሩ የማድረግ ተግባር ለማከናወን የሚሠራ ነው ተብሏል፡፡ በተለይም የግሉ ዘርፍ ሀብቱን ለማፍሰስ ደፍሮ በማይሳተፍባቸው ወይም በማያዋጣውና ከላይ እንደተጠቀሱት ዘርፍ ተኮር ማነቆዎች ላይ በወጪ መጋራት መርህ ከፊል ወጪውን በመሸፈንና የቴክኒክ እገዛ በመስጠት እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች