Saturday, December 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አለ በጅምላ ለመፈጸም ካቀደው ግዥ 60 በመቶውን ሳይፈጽም ቀረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ሽያጩ ግን ከዕቅዱ በላይ ሆኗል

ገበያው ውስጥ ያለውን ክፍተት ለማቃለል እገዛ ያደርጋል በሚል በመንግሥት ወደ ሥራ ከገባ ከሁለት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው አለ በጅምላ፣ በ2008 ግማሽ በጀት ዓመት የዕቅዱን ያህል ግዥ ማከናወን አለመቻሉ ተገለጸ፡፡

ድርጅት በስድስት ወራት ውስጥ ለመፈጸም አቅዶ የነበረው ግዥ 330.1 ሚሊዮን ብር ቢሆንም፣ 196.1 ሚሊዮን ብር ብቻ የሚያወጣ ግዥ መፈጸሙን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ይህም የዕቅዱን 60 በመቶ ያላሳካ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአለ በጅምላ ሥራ አስኪያጅ አቶ ኑረዲን መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በስድስት ወራት ውስጥ የግዥ ክንውኑ የዕቅዱን ያህል ያልሆነው ግዥውን ለመፈጸም ያስፈልገው የነበረውን የውጭ ምንዛሪ በወቅቱ ባለማግኘቱ ነው፡፡ የተወሰነ የበጀት እጥረት ምክንያት እንደነበር የጠቆሙት አቶ ኑረዲን፣ ይህ ክፍተት በዕቅዱና በክንውኑ መካከል ልዩነት እንዲፈጠር አድርጓል፡፡

በግማሽ በጀት ዓመቱ የተፈጠረው ክፍተት በሁለተኛው ግማሽ በጀት ዓመት ይቀረፋል የሚል እምነት እንዳላቸው የጠቆሙት አቶ ኑረዲን፣ በተለይ የውጭ ምንዛሪ ችግሩ አሁን እየተቀረፈ በመሆኑ የሚፈለገውን ግዥ መፈጸም ይቻላል የሚል እምነት አላቸው፡፡

በግማሽ የበጀት ዓመቱ በግዥ ደረጃ ያለው አፈጻጸም የተፈለገውን ደረጃ ባይደርስም አጠቃላይ ሽያጭ ላይ ግን ዕድገት መታየቱን ጠቁመዋል፡፡ እንደ አለ በጅምላ መረጃ በግማሽ በጀት ዓመት 269.6 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ለመፈጸም አቅዶ የ355.1 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ማከናወኑ ከዕቅዱ በላይ ሆኗል፡፡ አለ በጅምላ የሚያቀርባቸውን ምርቶች ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለመግዛት ባልቻለበት ሁኔታ ሽያጩ ከፍ ያለው ከበጀት ዓመቱ በፊት በእጁ ብዙ ምርቶች ስለነበሩ ነው ተብሏል፡፡

በቀደመው ዓመት መጨረሻ ላይ ከ260 ሚሊዮን ብር በላይ ስቶክ ስለነበረው ይህንን መሸጥ በመቻሉ ሽያጩ ከዕቅዱ በላይ ሊሆን መቻሉን አቶ ኑረዲን ገልጸዋል፡፡ ከጠቅላላው ሽያጭ ውስጥ 41 በመቶውን የያዘው የፓልም የምግብ ዘይት እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ አለ በጅምላ በስድስት ወራት ውስጥ ካሰባሰበው የሽያጭ ገቢ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው ፓልም ዘይትን ጨምሮ ሌሎች የምግብ ዘይቶች ሽያጭ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በስድስት ወራት ከተገኘው 269.6 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ውስጥ የምግብ ዘይቶች ገቢ 197.1 ሚሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡ ይህም የሌሎች ምርቶች ሽያጭ አነስተኛ መሆኑን አሳይቷል፡፡

ከምግብ ዘይት ሌላ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘው የለስላሳ መጠጦችና የታሸገ ውኃ 29.1 ሚሊዮን ብር፣ ስኳር 22.7 ሚሊዮን ብር፣ ፓስታና መኮሮኒ 16 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ተከናውኗል፡፡

በአለ በጅምላ መረጃ መሠረት በአሁኑ ወቅት ካሉት ሰባት መደብሮች ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ሽያጭ የተከናወነው ደግሞ በባህር ዳር መደብር ነው፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት የባህር ዳር አለ በጅምላ መደብር 67.4 ሚሊዮን ብር ሽያጭ በማከናወን ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ከባህር ዳር ቀጥሎ ከፍተኛ ሽያጭ አከናውነዋል ተብለው የተጠቀሱት ደግሞ ሻሸመኔ 64.6 ሚሊዮን ብርና ሐዋሳ 61.8 ሚሊዮን ብር ሸጠዋል፡፡

የአለ በጅምላን ምርት ተቀብለው የሚቸረችሩ ነጋዴዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው ተብሏል፡፡ እንደ አቶ ኑረዲን ገለጻ እስከ ታኅሳስ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ 12,995 የሚሆኑ ቸርቻሪ ነጋዴዎች ከአለ በጅምላ ጋር እየሠሩ ነው፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 5,259 አዳዲስ ቸርቻሪ ደንበኞችን በአባልነት መያዝ ሲችል፣ ከዚህ ውስጥም በስድስት ወራት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቸርቻሪዎች የተመዘገቡበት የባህር ዳር ቅርንጫፍ ሆኗል ተብሏል፡፡

በስድስት ወራት ብቻ በባህር ዳር ከ1,700 አዳዲስ ደንበኞች ተመዝግበዋል፡፡ በሐዋሳ ደግሞ 1,300 አዳዲስ ደንበኞች የአለ በጅምላ ምርትን ተቀብለው መቸርቸር ጀምረዋል፡፡

አለ በጅምላ በአሁኑ በሥራ ላይ ካሉት ሰባት መደብሮች ሌላ በቀጣይ አራት መደብሮችን በመቐለ፣ በድሬዳዋ፣ በአዳማና በጅማ እንደሚከፍት ተገልጿል፡፡

እነዚህን ቅርንጫፎች በዚህ በጀት ዓመት ሥራ ለማስጀመር ያቀደ ቢሆንም፣ ከአራቱ መደብሮች ግንባታው የተጀመረው የጅማው ብቻ ነው፡፡ ይህም ድርጅቱ ገጠመኝ ካለው የበጀት እጥረት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በበጀት ዓመቱ 354.9 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ስድስት መጋዘኖችን የመገንባት ውጥን እንደነበረው ይታወቃል፡፡

በአሁኑ ወቅት አለ በጅምላን ጨምሮ አራት የመንግሥት ተቋማት በአንድ ኮርፖሬሽን ሥር ሆነው እንዲተዳደሩ መደረጉ ግን በተለይ የበጀት እጥረቱን ይቀርፋል የሚል እምነት አለ፡፡

የኮርፖሬሽኑ መቋቋም ተጨማሪ ካፒታል የሚፈጥር በመሆኑ፣ የበጀት እጥረትን ለመቅረፍ ስለሚችል አለ በጅምላ በሙሉ በበጀት ዓመቱ የያዘውን ዕቅድ እንደሚያሳካ የአቶ ኑረዲን ገለጻ ያስረዳል፡፡

አለ በጅምላ በ2008 ሙሉ በጀት ዓመት 802 ሚሊዮን ብር ግዥና የ695.7 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ለማካሄድ ማቀዱ ይታወሳል፡፡ የሠራተኞቹን ቁጥር ደግሞ 730 የማድረስ ውጥን እንዳለው የበጀት ዓመቱ ዕቅድ ይጠቁማል፡፡ አለ በጅምላ አሁን 370 ሠራተኞች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች