የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ በመሆን ሲያገለግሉና አወዛጋቢ ነበር በተባለ የሥራ መልቀቂያ ኃላፊነታቸውን በለቀቁት በአቶ ጋሻው ደበበ ምትክ አዲስ ዋና ጸሐፊ ተሰየመ፡፡
ከንግድ ምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ እንዲሆኑ የተሰየሙት አቶ እንዳልካቸው ስሜ ናቸው፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ጥር 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የንግድ ምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ አድርጎ የሰየማቸው አቶ እንዳልካቸው፣ የቀድሞው ዋና ጸሐፊ ከሥራ ከለቀቁ በኋላ በተጠባባቂ ዋና ጸሐፊነት ተመድበው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ የቦርዱን ውሳኔ ተከትሎም ጥር 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት በተፈረመና በዋና ጸሐፊነት እንዲያገለግሉ መመደባቸውና መቀጠራቸውን የሚያመላክት ደብዳቤ ደርሷቸዋል፡፡
አዲሱ ዋና ጸሐፊ ከሁለት ወራት በላይ በተጠባባቂ ዋና ጸሐፊነት ቀደም ብሎም የንግድ ምክር ቤቱ ምክትል ዋና ጸሐፊ በመሆን ከአራት ዓመታት በላይ ሲያገለግሉ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አቶ እንዳልካቸው ከሐሮሚያ ዩኒቨርሲቲ በአግሪካልቸራል ኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የማስትሬት ዲግሪያቸውን በመማር ላይ ናቸው፡፡ ንግድ ምክር ቤቱን ከመቀላቀላቸው በፊት በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ሠርተዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅና ጋርመንት አምራቾች ማኅበር ዋና ጸሐፊ በመሆን ከአምስት ዓመታት በላይ ማገልገላቸው ይጠቀሳል፡፡ የጉለሌ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅም ነበሩ፡፡ በኖሪላ ኢንጂነሪንግ የማርኬቲንግና ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት ሥራ አስኪያጅ፣ በአደይ አበባ ድርና ማግ ፋብሪካ ውስጥ ደግሞ የገበያ ጥናት ኃላፊና የገበያ ጥናትና ፕሮሞሽን ኃላፊ በመሆን ሠርተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ የኦሮሚያ ክልል የኅብረት ሥራ ፕሮሞሽን ቢሮና የኢትዮጵያ የእንስሳት ገበያ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች ውስጥ በኤክስፐርት ደረጃ መሥራታቸው ተጠቅሷል፡፡
አቶ እንዳልካቸውን በዋና ጸሐፊነት ለመሰየም ቦርዱ ተከታትይ ስብሰባዎች የተቀመጠና አከራካሪ ውይይቶችን በማካሄድ ቅጥሩ እንዲፈጸም ዓርብ ጥር 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ውሳኔ ላይ የደረሰው በድምፅ ብልጫ መሆኑን ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡ ጉዳዩን በቅርብ ሲከታተሉ ከነበሩ ወገኖች መረዳት እንደተቻለው፣ አቶ እንዳልካቸው ዋና ጸሐፊ ሆነው እንዲመደቡ ለማድረግ ለቦርዱ ጥያቄውን ያቀረቡት የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ ናቸው፡፡
እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ ሐሳቡን ለቦርዱ ያቀረቡት አቶ እንዳልካቸው ለቦታው ይመጥናሉ በሚል ሲሆን፣ ማስታወቂያ አውጥቶ ቅጥር እስኪካሄድ የሚፈጀውም ጊዜ ታሳቢ ተደርጎ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ከሥር ያሉ ሠራተኞችን ማሳደጉ የበለጠ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ፣ ሌሎች ሊጠቆሙ የሚችሉ ካሉ ቦርዱ እንዲጠቁምም ዕድል መሰጠቱንም ይጠቅሳሉ፡፡ በፕሬዚዳንቱ በቀረበው ሐሳብ መሠረት ቦርዱ ሰፊ ውይይት ያደረገ መሆኑንም አስታውሰው መጨረሻ ላይ በድምፅ ብልጫ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ከአሥራ አንዱ የቦርድ አባላት ውስጥ ሦስቱ የአቶ እንዳልካቸውን በዋና ጸሐፊነት መሰየም ሳይደግፉ ቀርተዋል ተብሏል፡፡ እንደ ምንጮች ገለጻ ድምፅ ለመስጠት ያልፈለጉት የቦርድ አባላት በማስታወቂያ ቅጥር መፈጸም ይሻላል በሚል ነው፡፡
ከዚህም ሌላ የአቶ እንዳልካቸው በዋና ጸሐፊነት መሰየም ላይ ጥያቄ የሚያነሱ ወገኖች የቦርዱ ውሳኔ በንግድ ምክር ቤቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ዋና ጸሐፊ ሆኖ ለመቅጠር የሚያስፈልጉ መስፈርቶችን ያሟላ አይደለም የሚል ነው፡፡
ንግድ ምክር ቤቱን በዋና ጸሐፊነት ለመምራት የሚቀጠረው ዋና ጸሐፊ የትምህርት ደረጃው በዓለም አቀፍ ንግድ ወይም በቢዝነስ አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው ወይም ዶክትሬት ዲግሪ ያለው የሚል ነው፡፡ አዲሱ ዋና ጸሐፊ ግን ይህንን የሚያሟሉ አይደሉም ብለው የሚከራከሩ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ ግን ይህ ከእውነት የራቀ ነው ይላሉ፡፡ ውሳኔው የተሰጠው በንግድ ምክር ቤቱ አሠራር ደንብን ተከትሎ የትምህርት ደረጃቸውና ብቃታቸው ታይቶ መሆኑንም ያስረዳሉ፡፡ ለዋና ጸሐፊነት የሚጠየቀውንም መስፈርት የሚያሟሉና ለዚህም እስከዛሬ የሠሯቸው ሥራዎች ተመዝኖ እንጂ መስፈርቱን ሳያሟሉ የተሰጠ ውሳኔ ያለመሆኑንም ተናግረዋል፡፡ የቦርዱ ውሳኔ በበርካታ መመዘኛዎች ሲታይ ዋና ጸሐፊ ሆነው እንዲሠሩ መሰየማቸው ትክክል ስለመሆኑ የሚገልጹት አቶ ሰለሞን፣ በተለይ ጽሕፈት ቤቱን በሚገባ የሚያውቁና አቅምም ያላቸው ስለሆነ አዲስ ቅጥር አካሂዶ ሥራን ከማጓተት የሚታደግ ጭምር በመሆኑ ውሳኔው አግባብ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ አዲስ ዋና ጸሐፊ ከውጭ መቅጠሩ የሥራ ክፍተትን የሚፈጥርና የልምምድ ጊዜውም ሥራ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ታሳቢ ተደርጓልም ተብሏል፡፡