Tuesday, December 5, 2023

ፓርላማው በሥራ አስፈጻሚው መዋቅር ውስጥ የለያቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስፈጻሚ አካላት የዕቅድ አፈጻጸም ላይ ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ እንዳለበት፣ በሕገ መንግሥቱና በምክር ቤቱ የአሠራርና የአባላት ሥነ ምግባር ደንብ ተደንግጓል፡፡ ይህንን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ፣ እንዲሁም ሥራ አስፈጻሚው መንግሥት የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ይፋዊ መግለጫና አገራዊ ዕቅድ አዘጋጅቶ ሥራ ውስጥ ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩን መሠረት በማድረግ፣ ምክር ቤቱ አሥር ልዩ ቡድኖችን አዋቅሮ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ እንዲያከናውኑ አድርጓል፡፡

እነዚህ ቡድኖች በተመረጡት የመንግሥት መዋቅሮች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርን ጨምሮ በመመርመር ሪፖርታቸውን አጠቃለው አውጥተዋል፡፡ ቡድኖቹ ምርመራውን ያደረጉት ተገልጋዩን በተናጠል በማነጋገር፣ የውይይት መድረክ በማዘጋጀትና በማወያየት፣ የተለያዩ ሰነዶች በማየት፣ ሒደቱንና ግኝቱን አስፈጻሚ አካላትም እንዲያውቁት በማድረግ መሆኑን የቡድኖቹ ጠቅላይ ሰብሳቢና የሪፖርቱ አዘጋጅ አቶ ታደሰ ወርዶፋ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል፡፡

በሥራ አስፈጻሚው መዋቅር ውስጥ ከተለዩ ችግሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ተሰናድተዋል፡፡

የፍትሕ አካላት

የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶች የክህሎትና የአቅርቦት ችግሮች መኖራቸው በፍትሕ ሚኒስቴር፣ በዓቃቤ ሕግና በሲቪል ሠራተኞች ተገልጋይን የማንገላታት፣ ሰዓት አለማክበርና የመከራከር ብቃት ማነስ ችግሮች እንዳሉ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡

ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች አንፃር ሰዓት አክብረው የሚሠሩ ዳኞችና ሠራተኞች ቢኖሩም፣ አብዛኛው ችሎት የሚጀመረው ከረፋዱ አራት ሰዓት በኋላ መሆኑና ዳኞች ከሰዓት በኋላ ተመልሰው የማይመጡ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

አንዳንድ ዳኞች ከደላላ በፀዳ መንገድ አገልግሎት የማይሰጡ መሆኑና ከብቃትም አንፃር ችግር እንዳለ የፓርላማው ቡድን መገንዘቡን ለምክር ቤቱ ይፋ አድርጓል፡፡ አራዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ማኅተም በየቀኑ በሠራተኛ ቦርሳ የሚመላለስ መሆኑ ለኪራይ ሰብሳቢነት አደጋ የተጋለጠ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

ከፍትሕ ሥራ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ደላሎችን በፍርድ ቤቶች አካባቢ መበራከታቸውና ይህንን ችግር አለመታገል፣ እንዲሁም በሰበር ችሎት በአንድ ጉዳይ ሦስት ዓይነት የሕግ ትርጉምና ውሳኔ የተሰጠበት ሁኔታ መኖሩን ገልጿል፡፡

የኤሌክትሪክና የውኃ አገልግሎት

በኤሌክትሪክ አገልግሎት ዘርፍ ተገልጋዩ ለሚጠይቀው አገልግሎት በአግባቡ የማይስተናገድ መሆኑ፣ ኃላፊዎችም ሥራውን በአግባቡ እንደማይከታተሉ በሪፖርቱ ተቀምጧል፡፡

ደንበኞች ለሚከፍሉት ማንኛውም ክፍያ ፕሪንተር ስለተበላሸ በሚል ደረሰኝ የማይሰጡ መሆኑ፣ ከአንዳንድ ማዕከላት የሚገዙ ኃይል ቆጣቢ አምፑሎች ለማንና አድራሻው የት እንደሆነ ሳይለይ በጠየቁት መጠን ልክ አምፑሎች ሲሸጡ መታየቱን ይጠቅሳል፡፡

አገልግሎት እየሰጠ ያለ ትራንስፎርመርን ባለሙያዎች መጥተው ፊውዝ ፈተው ወደ ሌላ ማዛወር የተለመደ መሆኑ፣ ፊውዙ የተወሰደባቸው የመስመሩ ተጠቃሚዎች ለጨለማ እንደሚዳረጉ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 በቀጣና 2 ነዋሪዎች ቅሬታ መቅረቡን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

ለቆጣሪና ለኤሌክትሪክ ፖል ተገቢውን ክፍያ ፈጽመው ለረዥም ጊዜ ወረፋ የሚጠብቁ ግለሰቦች መኖራቸውን፣ የመብራት ንባብ ለመውሰድ በር ቶሎ አልከፈታችሁም በሚል ሰበብ ጥለው እንደሚሄዱ፣ አለበለዚያ ገንዘብ እንዲከፈላቸው እንደሚጠይቁ ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡

የአርሴማ ቁጥር ሁለት የልማት ተነሺዎች መሬታቸውን ለልማት፣ እንዲሁም ቀደም ሲል ይጠቀሙበት የነበረን ቆጣሪ አስረክበው ከተነሱ ስምንት ዓመት ቢሆንም እስካሁን በኩራዝ እንደሚኖሩ ሪፖርቱ ይዘረዝራል፡፡

የውኃና ፍሳሽን በተመለከተ የክትትል ሥራው ያተኮረው በአዲስ አበባ ላይ ብቻ ሲሆን፣ የብረት ቱቦ በፕላስቲክ ቱቦ ለመቀየር ከ4,000 ብር እስከ 14,000 ብር እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ነዋሪዎች እያማረሩ ስለመሆኑ፣ ከቧንቧ የሚለቀቅ ውኃ የጥራት ችግር ያለበት መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡

የውኃ ፈረቃ ጊዜ ለሕዝብ በውል ካለመታወቁ ጋር ተያይዞ ኅብረተሰቡ ሌሊት ሲጠባበቅ እንዲያድር መገደዱም በሪፖርቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የውኃ ችግር ሳይኖር የተቋሙ ባለሙያዎች ሆን ብለው በመዝጋት የሚፈጥሩት ችግር መኖሩ ተንፀባርቋል፡፡

ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን

የገቢዎችና ጉምሩክ ሥራዎች ከብዙ አቻ መሥሪያ ቤቶች ጋር የሚያገናኝ ቢሆንም፣ ከእነዚህ ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ ባለመሥራቱ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት አለመቻሉን ጠቅሷል፡፡

የቀረጥ ተመላሽ መረጃ በወቅቱ አዘጋጅቶ ሲላክ በደረሰው መረጃ መሠረት አጣርቶ ገንዘቡን ተመላሽ ከማድረግ አንፃር ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በወቅቱ ተመላሽ የማይደረግ መሆኑ፣ የቫት ተመዝጋቢ መሆናቸው ሳይገለጽ የተርን ኦቨር ታክስ ገቢ ብቻ በየሦስት ወሩ እየተቀበሉ ያስተናገዱት የነበረን ግብር ከፋይ በዓመቱ መጨረሻ ላይ ቫት በየወሩ አልተከፈለም በሚል ከፍተኛ ቅጣት መጣልና ከንግድ የማስወጣት ተግባር እንደሚታይ ጠቁሟል፡፡

ተቆጣጣሪዎች ሕጉን ማስከበር ሲገባቸው ነጋዴዎች የሚፈጥሩትን ስህተት በመጠቀም የጉቦ መሰብሰቢያ ማድረጋቸው፣ የሚጋፈጣቸውን ደግሞ በሐሰት የሚወነጅሉ መሆኑን ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡

አንድ ባለሙያ በወሰነው የታክስ ኦዲት ቅር የተሰኘ ተገልጋይ ቅሬታውን ቀጥሎ ላለው አካል ሲያቀርብ፣ ቅሬታው የቀረበለት ለማሻሻል የሚያስችል መመርያ ባለመኖሩ ከተጠያቂነት ለመሸሽ ውሳኔ ለመስጠት መፍራትና መገፋፋት ሌላው ችግር መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በኮንትሮባንድ የሚገቡ ዕቃዎች በተለይም ጨርቃ ጨርቅ፣ ኤሌክትሮኒክስና የመዋቢያ ዕቃዎች ከቁጥጥር በላይ መሆናቸው፣ ሐሰተኛ ደረሰኞች በስፋት መርካቶ ውስጥ ታትመው እየተሠራጩ መሆኑ፣ የጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ ላይ ክትትሉ ዝቅተኛ ስለሆነ በሕጋዊ መንገድ ከብሔራዊ ባንክ ከሚሸጠው በላይ የውጭ ምንዛሪ ስለሚያገኙ በኮንትሮባንድ የሚያስገቡት ዕቃ በመኖሩ፣ ሕጋዊ አስመጪዎች መወዳደር አለመቻላቸውን በተመለከተ እሮሮ እያሰሙ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶች

ፕሮግራሙ በርካታ የመኖሪያ ቤት ችግር ያለባቸውን ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎችን የቤት ባለቤት ያደረገ፣ የሴቶችን፣ የመንግሥት ሠራተኞችን፣ አቅመ ደካሞችንና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ስኬታማ አፈጻጸም የታየበት መሆኑን ከነዋሪዎች በተሰጡ አስተያየቶች ለመገንዘብ መቻሉን የፓርላማው ቡድን በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡

ይሁን እንጂ ከጥራት ጋር በተያያዘ ችግሮች መኖራቸውን ቡድኑ ተዘዋውሮ በጎበኛቸው የኮንዶሚኒየም ቤቶች መገንዘቡን በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ አንዳንዶቹ ጣሪያቸው የሚያፈስ፣ ቆርቆሮዋቸው በንፋስ የተገነጠለ፣ የሳኒተሪ ቱቦዎች በአግባቡ ባለመገጠማቸው ከላይ መፀዳጃ ቤት በመፈንዳት ታች ያሉትን በማጥለቅለቅ ለነዋሪዎች ጤንነት ጠንቅ መሆናቸውን በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡

ቤቶችን ከማስተላለፍና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ ዕጣ የደረሳቸው ነዋሪዎች ቤታቸውን ለመረከብ በብዙ ቀጠሮ እንደሚመላለሱ፣ ቤቶቹን በፍጥነት ባለማግኘታቸው ለሚኖሩበት ቤት ኪራይና ለባንክ ተደራራቢ ወጪ መዳረጋቸውን ሪፖርቱ ይጠቅሳል፡፡

ሕገወጦች ዕጣ የደረሳቸው በማስመሰል ቁልፍ ሰብሮ መግባት መታየቱ፣ የጋራ መገልገያ ቤቶች በሳይት ፕላኑ መሠረት አለመገንባታቸው፣ ዋጋው ግን በተጠቃሚው ላይ የሚታሰብ መሆኑ በሪፖርቱ ይፋ ሆኗል፡፡

በሌላ በኩል ለብሎኮች የተሰጠው ቁጥርና በተጨባጭ የተገነባው ሕንፃ ቁጥር ልዩነት ያለው በመሆኑ፣ በነዋሪዎች ዘንድ የት ገባ የሚል ጥርጣሬ እንዲፈጥር ያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ለተጠቃሚዎች ሳይተላለፉ ተዘግተው የተቀመጡ በርካታ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸውና በርና መስኮታቸው እየወለቀ መሆኑን ለመረዳት መቻሉን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡

በማጠቃለያነትም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት የሚወሰደው ዕርምጃ በየደረጃው ያለው አመራር የየራሱን ድርሻ በመውሰድ ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መልኩ መፈጸምና ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እንደሚገባ፣ የሱፐርቪዥን ቡድኖቹ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ወርዶፋ ገልጸዋል፡፡

ሪፖርቱ ከቀረበ በኋላ አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ በምክር ቤቱ ለተገኙ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የሥራ አስፈጻሚው አካላት መመርያ ሰጥተዋል፡፡ በዚህም መመርያ መሠረት ማንኛውም የሥራ አስፈጻሚው ተወካይ በቀረበው ሪፖርት ላይ ጥያቄ ማንሳት እንደማይፈቀድለት፣ ዕድሉ የሚሰጠው ተቋማቱ የተገለጹትን ችግሮች ለመመለስ ምን ዓይነት ዕቅድ እንዳስቀመጡና ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እንደጀመሩ እንዲያብራሩ ብቻ መሆኑን አሳስበዋል፡፡

በዚሁ መሠረት በምክር ቤቱ የተገኙት የሥራ አስፈጻሚ አመራሮች የተጠቀሱባቸውን ችግሮች ሙሉ በሙሉ አምነው በይፋ ተቀብለዋል፡፡ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን በተመለከተ ከሕዝብ ክንፍ ጋር ውይይት መጀመራቸውን፣ ወደ ዕርምጃ እየቡ ስለመሆኑ፣ ከሥራ እንዲታገዱ የተደረጉ ሠራተኞች ስለመኖራቸው ማብራሪያ ከሰጡት መካከል የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ፍትሕ ሚኒስቴር እንዲሁም የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ይገኙበታል፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ በማጠቃለያ በሰጡት ማሳሰቢያ ምክር ቤቱ ከዚህ በኋላ የተለያዩ ማጓተቻ ምክንያቶችን እንደማይሰማ ለአመራሮቹ ግልጽ አድርገው ያሳሰቡ ሲሆን፣ ቀጣዩ ዕርምጃ በሕግ ተጠያቂ መሆን ወይም የአስተዳደራዊ ዕርምጃ ሰለባ መሆን እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -