የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአይሻ የንፋስ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታን ለማካሄድ፣ ከቻይናው ግዙፍ ኩባንያ ደንግ ፋንግ ጋር የ265 ሚሊዮን ዶላር የኮንስትራክሽን ኮንትራት ተፈራረመ፡፡
የአይሻ ፕሮጀክት አንድ ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል አቅም እንዳለው በጥናት የተረጋገጠ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከደንግ ፋንግ ጋር ውል የገባው 120 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና በደንግ ፋንግ መካከል ከአንድ ሳምንት በፊት ስምምነት መፈረሙን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራው ኤሌክትሪክ ሥራ አመራር ቦርድ፣ ደንግ ፋንግ ከራሱ የገንዘብ ምንጭ በብድር የሚመለስ ፋይናንስ የሚያመጣ ከሆነ ሥራው እንዲሰጠው፣ ይህንንም ሥራ ከአገር በቀሉ ኩባንያ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ጋር በጋራ እንዲያካሂድ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ውሳኔ ማሳለፉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በዚሁ መሠረት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ደንግ ፋንግ ፋይናንስ ይዞ መምጣቱን ከማረጋገጡም በተጨማሪ፣ ከዚህ ቀደም የደንግ ፋንግን የቴክኒክ ብቃት ገምግሞ ስለነበር ሥራውን ሊያስረክበው እንደቻለ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
ደንግ ፋንግ በበኩሉ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ሥራዎችን እንዲያከናውን ከመስፍን ኢንዱስትሪያል ጋር በቅርቡ ይፈራረማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በአገር ውስጥ የሚመረቱ መሣሪያዎች በሙሉ ከውጭ መግባት እንደሌለባቸው፣ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉና ለወደፊት ራሳቸውን ችለው ግንባታዎች እንዲያካሂዱ አቅም መገንባት አለባቸው የሚል መመርያ መሰጠቱም ተጠቁሟል፡፡ በዚህ መሠረት መስፍን ኢንዱስትሪያል ከደንግ ፋንግ ለጊዜው ግምቱ ያልታወቀ ክፍያ እንደሚያገኝ ተገልጿል፡፡
በሶማሌ ክልል አይሻ ወረዳ ከባህር አካላት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ንፋስ በሰፊው የሚነፍስ በመሆኑ፣ ፕሮጀክቱ ከተጠነሰሰ ረዥም ጊዜ አስቆጥሯል፡፡
በዚህ አካባቢ ከንፋስ ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት ለማካሄድ የጀርመን ኩባንያ ላፍቶ፣ አገር በቀሉ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንና ደንግ ፋንግ ፍላጎት በማሳየት፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ድርድር ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡
በመጨረሻ ከዓመታት ውጣ ውረድ በኋላ ፕሮጀክቱ ዕውን እንዲሆን የመንግሥትን ይሁንታ በማግኘቱ ደንግ ፋንግ ሊፈራረም እንደቻለ ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከንፋስ ኃይል ብቻ 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም አላት፡፡ እስካሁን አሸጎዳና አዳማ የንፋስ ኃይል ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ሆነዋል፡፡
የአይሻን ፕሮጀክት የተረከበው ደንግ ፋንግ በጊቤ ሦስት ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጨት ፕሮጀክት የኃይድሮ ሜካኒካል ሥራዎችን ያከናወነ ኩባንያ ነው፡፡