Monday, February 6, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የሙስና ዋርካ የሚገረሰሰው ቅርንጫፉን ሳይሆን ግንዱን ሲመቱት ነው!

የፀረ ሙስና ትግል ግቡን የሚመታው በአደባባይ የሚሰሙ መፈክሮች ጋብ ብለው፣ ተግባራዊ ዕርምጃዎች በተጠና መንገድ ሲወሰዱ ነው፡፡ አድርባዮችና አስመሳዮች ሙስናን መታገል አይችሉም፡፡ በሙስና የተነካኩ ደግሞ የትግሉ አካል መሆን አይቻላቸውም፡፡ ሙስና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚጠፋ ባለመሆኑ፣ የንፁኃንና የትጉኃንን ፅናት ይጠይቃል፡፡ የፀረ ሙስና ትግሉ ከመፈክር ጋጋታ ተላቆ ከሥር መሠረቱ እንዲናድ ቁርጠኛ ፍላጎት ካለ፣ ርብርቡ መደረግ ያለበት ቅርንጫፉ ላይ ሳይሆን ግንዱ ላይ ነው፡፡ ግንዱን ከሥሩ መንግሎ መጣል የሚቻለው ደግሞ አገር ወዳድ ዜጎች የትግሉ ግንባር ቀደም ተዋንያን ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሙስና በጣም ከመርቀቁ የተነሳ የሚከናወነው በተናጠል ሳይሆን በቡድን በተደራጁ ኃይሎች ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች በከባድ የጥቅም ቁርኝት የተሳሰሩ በመሆናቸው ሰንሰለታቸውን ለመበጣጠስ ከእነሱ በላይ መደራጀት ያስፈልጋል፡፡ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ያስተሳሰራቸው የዘረፋ ኃይሎች ከበድ ያለ የኢኮኖሚ ጡንቻ ያፈረጠሙ ናቸው፡፡ በየቦታው ከለላ የሚሆኑዋቸው የሚፈሩ ባለሥልጣናትን ጋሻና መከታ በማድረግ ይጠቀማሉ፡፡ ለአገራቸው ጠቃሚ የሆነ ተግባር የሚያከናውኑ ዜጎችን እያዋከቡ፣ ለአገር አሳቢ መስለው በመቅረብ መደናገር ይፈጥራሉ፡፡ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካና ባልተገባ የጥቅም ትስስር በመቧደን ብዙኃኑን እያገለሉ ጥቂቶችን ያበለፅጋሉ፡፡ በዜጎች መካከል አለመታመን እንዲኖር ያደርጋሉ፡፡

ሙስና ያልገባበት ቦታ የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በትምህርት ተቋማት፣ በጤና ተቋማት፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ ሰብዓዊ ተግባራት በሚፈጸምባቸው ሥፍራዎችና በመሳሰሉት ሳይቀር ሥሩን ሰዷል፡፡ በተለይ ከፍተኛ ሀብት በሚመደብባቸው የመንግሥት ፕሮጀክቶችና መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የተንሰራፋው ሙስና ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው፡፡ በነጋ በጠባ በሚዲያም ሆነ በተለያዩ መድረኮች ስለ ሙስና አስከፊነት ቢነገርም፣ ተግባራዊ ዕርምጃው ላይ የሚታየው ዳተኝነት ተጨምሮበት  አስፈሪ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርቶች በተደጋጋሚ የሚጠቀሱት ሕግን ያልተከተሉ ግዥዎችና በአግባቡ የማይወራረዱ ሒሳቦች ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በተለይ ትውልድ በሚቀረፅባቸው ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሙስና መግነን ያሳስባል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ ባለሥልጣናት በየጊዜው ማስጠንቀቂያ የሚሰጡበት ሙስና፣ ተግባራዊ ዕርምጃ ተወስዶ ለምን ውጤቱ አይታይም በማለት በሕዝቡ ውስጥ ዘወትር ጥያቄ ይነሳል፡፡ በእርግጥ ሙስናን ለመዋጋት ጥበብና ብልኃት አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ፣ እያንዳንዱ ዕርምጃ በጥናት ላይ መመሥረት እንዳለበት ዕሙን ነው፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ያገጠጡ ሙስናዎች በቅርብ ርቀት ላይ እየታዩ፣ ሙስና የበረታባቸው መስኮች በትክክል እየታወቁ፣ ሙስናን በበላይነት የሚመሩ አካላት ፊት ለፊት እየታዩ፣ ሕዝቡ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖረው ዕድሉ ከተሰጠ ከመነሻው እስከ መድረሻው የመጠቆም ብቃቱ እያለው፣ የመረጃና የማስረጃ ምንጩ ብዛት ከፍተኛ ሆኖ እያለ ሙስና እንዴት የበላይነት ይይዛል? ቅርንጫፉ ላይ የሚደረጉት ብቅ ጥልቅ የሚሉ ዕርምጃዎች ግንዱን ካላገኙት መፍትሔ እንደሌለ እየታወቀ የምን መወዛገብ ነው?

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት የተወያዩበት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጥናት የአገሪቱን የሙስና ይዞታ በሚገባ ዘርዝሮታል፡፡ በተለይ የሙሰኞች ዋነኛ ምሽግ የሆነው መሬት ላይ ወረራ በመፈጸም የሚዘርፉ ኃይሎች አይታወቁም? ከቀረጥ ነፃ መብትን ላልተገባ ጥቅም የሚያውሉ የተደራጁ ወገኖች የሉም? ከፍተኛ መጠን ያለው ግብርና ታክስ የሚሰውሩት እነማን ናቸው? ጤናማ የግብይት ሥርዓት እንዳይፈጠር ገበያውን የሚረብሹ ኃይሎች የማይታወቁ ናቸው? ሕጋዊውን የግዥና የጨረታ ሥርዓት እየተጋፉ ቢጤዎቻቸውን የሚያበለፅጉት አገር አያውቃቸውም? በመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ሀብት የሚያባክኑትስ አይታወቁም? ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን የሕገወጦች መናኸሪያ ያደረጉ የሉም? የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ከታች እስከ ላይ የጉቦ ማቀባበያ እያደረጉ ያሉትስ? ሕገወጥ ደላሎች የሥርዓተ ኢኮኖሚው ዘዋሪ መሆን የቻሉት እንዴት ነው? የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ እነማን ናቸው የሚጫወቱበት? ሕገወጥ የሀብት ፍልሰት (Capital Flight) ተዋንያን እነማን ናቸው? እነዚህን በቅጡ ሳይፈትሹና የተደራጀ አካሄድ ሳይከተሉ የፀረ ሙስና ትግል አለ ማለት አይቻልም፡፡ ቅርንጫፉ ላይ የሚደረገው ርብርብ እርባና የለውም፡፡

የፀረ ሙስና ትግሉን እንዲመራ ኃላፊነት የተሰጠው ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሰሞኑን በፓርላማ በተደረገ ውይይት ላይ ቅሬታ ቀርቦበታል፡፡ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ‹‹ምክር›› ላይ አተኩረሃል ተብሎ ተገምግሟል፡፡ የፓርላማውና የሕዝቡ ድጋፍ እያለ ዕርምጃ ለመውሰድ አለመቻሉ አስነቅፎታል፡፡ ሕግ አውጪው ፓርላማ ኮሚሽኑን ‹‹አይዞህ በርታ›› ማለቱ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን አስፈጻሚው አካል ግዴታውን በሚወጣበት ጊዜ ከበላይ የሚመጣበትን ጫና ‹‹ዞር በል›› የሚልበት አቅም እንዲያገኝ ማድረግ አለበት፡፡ በአንድ ጀንበር የሚፈጠሩ ሚሊየነሮች በሚታዩበት አገር ውስጥ፣ ፓርላማው የአስፈጻሚውን መንግሥት መሪዎች ጭምር ጠርቶ ማፋጠጥና የሙስናው ግንድ እንዴት እንደሚገረሰስ መመርያ መስጠት አለበት፡፡ በቃል ትዕዛዝና በስልክ ጥሪ ‹‹አርፈህ ተቀመጥ›› የሚባል ተቋም አንቀጽ እየተጠቀሰ ይህንን ዓይነት ዕርምጃ ካልወሰድክ ከማለት በላይ፣ የግንዱን መቁረጫ መጥረቢያ ማቅረብም ተገቢ ነው፡፡ የፓርላማ ወግ ነው፡፡ ይህ በተግባር ካልታየ ግን የሚነገረው ሁሉ ፉርሽ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ፀረ ሙስና ኮሚሽን ውስጡን ማጥራት አለበት፡፡ ግዙፍ የሆኑ ሙስናዎች በሚፈጸሙበት በዚህ ወቅት የሙስና ተቋዳሽ የሆኑ ውስጡ መኖራቸው አሌ አይባልም፡፡ በርካታ ትጉኃንና ንፁኃን እየተገፉ በሙስና ራሳቸውን ‹‹አንቱ›› ያሰኙ ጉዶችን ታቅፎ ሙስናን መከላከል ወይም ማስቆም አይቻልም፡፡ አጉል ቀልድ ነው፡፡ ይኼ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ሌላው ደግሞ ኮሚሽኑ ተጠሪነቱ ለአስፈጻሚው ሆኖ ሙስናን በብቃት ይታገላል ማለትም ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ይልቁንም ተጠሪነቱ ለፓርላማው ሆኖ ጫናዎችን መቋቋም ካልቻለ በስተቀር የፀረ ሙስና ትግሉ ከወሬ ያለፈ ምንም ፋይዳ አይኖረውም፡፡ በአንድ በኩል ውስጡ የመሸጉ ቀበኞችን እያፀዳ፣ በሌላ በኩል ጫናዎችን የሚቋቋምበት ጡንቻ እያፈረጠመ ካልተነቃቃ በስተቀር ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ ማን ምን ዓይነት ሀብት እንዳፈራ በግልጽ ተናግሮ ‹‹የመሸበት ማደር›› የሚቻለው ግንዱን ለመቁረጥ የሚያስችል አቅም ሲኖር ብቻ ነው፡፡

ጡንቻቸው የፈረጠመ ሙሰኞች ተገን ከሚሆኑዋቸው ባለሥልጣናት ጋር ሆነው አገር ሲያስለቅሱ፣ አድርባይና አስመሳይ ካድሬዎች የጥቅም ተጋሪዎች ሆነው ሲያጨበጭቡ፣ በሙሰኞች የተከበቡ የመንግሥት ሚዲያዎች ሲሸፋፍኑ፣ ዕርምጃ መውሰድ ያቃታቸው የሚመለከታቸው አካላት ሲልፈሰፈሱ፣ ሕዝቡ በሚያያቸው አሳዛኝ ድርጊቶች ሲንገፈገፍ፣ ወዘተ እንዴት መተማመን ይኖራል? ‹‹የሙሰኞችን ጣት እንቆርጣለን …›› ሲባል ቢያንስ ለዕርምጃው መቅረብን ማሳያ ነው፡፡ ነገር ግን ዕርምጃው በዘገየ ቁጥር ሕዝቡ ‹‹ለወሬ ያህል ነው›› ብሎ ይተወዋል፡፡ ተደጋግሞ ሲነገረውም ለመስማት አይፈልግም፡፡ የሙስናው ተዋናይ የሆኑ ጉልበተኞችን ማንበርከክ ስለማይቻል ዋጋ የለውም ብሎ ይደመድማል፡፡ ለዚህም ነው የሙስና ዋርካ የሚገረሰሰው ቅርንጫፉን ሳይሆን ግንዱን ሲመቱት ነው የሚባለው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው ከፍተኛ ሀብት ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም ተባለ

በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት የተሰበሰበው የተቀማጭ ገንዘብ መጠን...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...

አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመዋል በተባሉና በኦሮሚያ መንግሥት ላይ ክስ ለመመሥረት ዕግድ ተጠየቀ

የፌዴራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽኖችም ተካተዋል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...