የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሁለት ሳምንት በፊት ያረቀቀውና በውጭ ምንዛሪ ንግድ ላይ ግልጽነት እንዲሰፍን የሚያደርግ ነው የተባለለት መመርያ፣ ከዛሬ የካቲት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን አስታወቀ፡፡
የፀደቀው መመርያ በረቂቁ ላይ ያልተካተቱ ማሻሻያዎች የያዘ ሲሆን፣ በዋነኝነት በገቢ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ለአንድ ወደ አገር ውስጥ ለሚገባ የገቢ ዕቃ ከአንድ ባንክ በላይ የባንክ መተማመኛ ሰነድ (Letter of Credit) መክፈት እንደማይችሉ ይደነግጋል፡፡ በተለይ አገር ውስጥ ባለው የውጭ ምንዛሪ ችግር ምክንያት የገቢ ንግድ የሚያከናውኑ ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሪ የማግኘት ዕድላቸውን ለማስፋት በተለያዩ ባንኮች በአንድ ጊዜ ተመሳሳይ የምንዛሪ ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ መመርያው ከዚህ በኋላ ይህ አሠራር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በማስታወቅ፣ ይህን ለመቆጣጠርም ባንኮች በየሳምንቱ የቀረበላቸውን የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ለብሔራዊ ባንክ ማሳወቅ እንዳለባቸውም ይደነግጋል፡፡
የውጭ ምንዛሪ መመርያው በዋነኝነት ባንኮች ‹‹በቅድሚያ የመጣ በቅድሚያ ያገኛል›› በሚለው መርህ መሠረት ደንበኞቻውን ማስተናገድ እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡ ይህንም በዋነኝነት ባንኮች ለደንበኞቻቸው የምንዛሪ ጥያቄ ቅድሚያ የሚሰጡበትን አሠራር የሚያስቀር ነው፡፡ በቀድሞ አሠራር መሠረት በተለይ በወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ ደንበኞች በየባንኮቻቸው የውጭ ምንዛሪ ጥያቄያቸው ቅድሚያ ይሰጠው የነበረ ሲሆን፣ ይህንን የሚከለክል መመርያም ያልነበረ መሆኑን የባንክ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ረገድ መመርያው የመጫወቻ መደላደሉን የማስተካከል ኃይል ያለው መሆኑም እነዚሁ ባለሙያዎች አክለው ይገልጻሉ፡፡
መመርያው በተጨማሪ እያንዳንዱ የባንክ መተማመኛ ሰነድ ጥያቄ ሲቀርብ፣ በትንሹ የምንዛሪውን 30 በመቶ በብር ማስቀመጥ እንደሚጠበቅባቸው የሚገልጽ ሌላ ማሻሻያ ያካተተ ሲሆን፣ ባንኮች የየሳምንቱ የምንዛሪ ንግድ መረጃቸውን ለብሔራዊ ባንክ መላክ እንዳለባቸውም ይደነግጋል፡፡ ከቁጥጥር ጋር በተያያዘ ብሔራዊ ባንክ የባንክ አመራርና ቦርዱ በአንድነት የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ንግድ ጤናማነትን የመፈተሽ፣ የመከታተልና ሪፖርት የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ያሳስባል፡፡ ከባንኩ አመራሮች ጎን ለጎን በውስጥ ኦዲተሮች ቁጥጥር እየተደረገ ስለመሆኑና የባንኩ የውጭ ምንዛሪ ንግድ በተቀመጠው መመርያ መሠረት መከናወኑን እንዲያረጋግጡ፣ ለዚህም ድንገተኛ ፍተሻም ጭምር ማድረግ እንዳለባቸው መመርያው ያዛል፡፡
የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ አቅራቢዎችን በተመለከተም ለአንድ የገቢ ዕቃ በተለያየ ባንክ የምንዛሪ ጥያቄ ማቅረብ በብሔራዊ ባንክ ጥቁር መዝገብ ላይ እንደሚያሰፍር፣ ብሎም ከስድስት ወራት እስከ ሁለት ዓመታት ከምንዛሪ ንግድ ተሳትፎ ሊያሳግድ እንደሚችል መመርያው ያስረዳል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ንግድን በተመለከተ መንግሥት በተደጋጋሚ በኢኮኖሚው ‹‹የተጋነነ›› የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጥያቄ መኖሩ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ ይህም እውነተኛ የምንዛሪ ፍላጐትን እንደማያሳይ በመጥቀስ ሲከራከር ቆይቷል፡፡
ከሦስት ሳምንት በፊት የአገሪቱ ትልቁ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአንድ ጊዜ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ የምንዛሪ ጥያቄን ለማስተናገድ ፈቃደኛ መሆኑን ተከትሎ፣ በባንክ ዘርፉ ውስጥ የብር እጥረት መፈጠሩን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አንድ ባንክ ከአጠቃላይ ካፒታሉ 15 በመቶ ያልበለጠ የውጭ ምንዛሪ መያዝ እንዳለበት የሚደነግግ ሲሆን፣ አዲሱ መመርያ ባንኮች ከዚህ መመርያ በተቃራኒ የውጭ ምንዛሪ ንግድ እንዳያካሂዱ ያሳስባል፡፡