Friday, March 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ነገረ ቻይና

በዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ

ርካሽ ነገር ውድ ነው

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ‹‹ርካሽ ነገር ውድ ነው›› ይላሉ። ይህ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የቻይና ምርቶችን ጥሩ አድርጎ ይገልጻቸዋል። አንድ ጥራቱን ያልጠበቀ ሸሚዝ በርካሽ ገዝቶ ያለ እርካታና ያለምቾት ለአምስት ወር ከመልበስ ጥሩ ሸሚዝ በውድ ዋጋ ገዝቶ በምቾትና በእርካታ ዓመት ሁለት ዓመት መልበስ የሚመርጡ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች (የመግዛት አቅማቸው እንዳለ ሆኖ) ‹‹ርካሽ ነገር ውድ ነው›› የሚለው ብሂል የገባቸው ይመስላል። በእርግጥ አሁን አሁን የቻይና ምርቶች ከመብዛታቸው የተነሳ የጥሩ ዕቃ ጣዕሙ እየጠፋን፣ ጥሩ ዕቃ ፈልጎ ማግኘቱም በቻይና ዕቃዎች እየተሸፈነ ፍለጋውን ከባድ ስላደረገው፣ ዕቃ ሁሉ የቻይና ብቻ የሆነ ያህል ከማመን ደረጃ ደርሰናል።

በርካሽና ጥራት አልባ የቻይና ዕቃዎች የተማረሩ ዜጎች በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ተቃውሞ አሰምተዋል። በሴኔጋል የሆነው ቻይናውያን ነጋዴዎች ዓላማቸውን ለማሳካት የት ድረስ እንደሚሄዱ በሆዋርድ ፍሬንች ‹‹China’s Second Continent: How a Million Migrants Are Building a New Empire in Africa›› መጽሐፍ ውስጥ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡  በጥራት አልባ የቻይና ዕቃዎች የተማረሩ ሴኔጋላውያን የቻይና ዕቃ ወደ አገራቸው እንዳይገባ የተቃውሞ ሠልፍ ያደርጋሉ። ጥቅማቸው ሊነካባቸው የሆነው የቻይና ነጋዴዎች የተቃውሞ ሠልፉን እንዲቃወሙ የሴኔጋል ሸማቾች ማኅበር አባላትን አደራጅተውና ብር ከፍለው የተቃውሞ ሠልፉን እንዲቃወሙ ሠልፍ ያስወጧቸዋል። አንዳንድ ታዛቢዎች ገንዘቡን የከፈሉት ቻይናውያን ሳይሆኑ የሴኔጋል መንግሥት ነው ይላሉ።

በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የሚገኙ ዜጎች ቻይናዊያንን ከሚቃወሙባቸው ምክንያቶች አንዱ የቻይና ድርጅቶች የቀን ሠራተኞችን ጨምሮ በዝቅተኛና በመካከለኛ የሙያ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሠራተኞችን ይዘው ይመጣሉ የሚለው አንዱ ነው። ይኽም በአፍሪካውያን ሊሠራ የሚችለውን ሥራ ለቻይና ሥራ አጦች በመስጠት በአፍሪካ የሥራ አጥነት እንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መጨመር ነው ይላሉ። ተጨማሪ መከራከሪያ የሚያቀርቡ ተንታኞች፣ በቻይና ዕገዛ አፍሪካ ውስጥ በሚደረጉ ፕሮጀክቶች ውስጥ ከትንሽ እስከ ትልቅ ደረጃ ያሉ የሥራ ዘርፎች በቻይና ሠራተኞች የሚያዙ ከሆነ አፍሪካ አጥብቃ የምትፈልገው የዕውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ልታገኝ አትችልም ይላሉ። በኢትዮጵያም የተደረጉ ጥናቶች የሚያሳዩት በቻይና ድርጅቶች የሚፈጠሩ ብዙዎቹ ሥራዎች ከቀን ሠራተኛነት ያልዘለሉ መሆናቸው ነው። ይህም የሚፈለገውን የቴክኒክ ዕውቀት ለኢትዮጵያውያን እንዳይደርስ እንቅፋት ይሆናል።

ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች በቻይና ድጋፍ የሚደረጉ መሆኑ ደግሞ የቻይና ድርጅቶች በቀን ሠራተኝነትም ሆነ በጊዜያዊነት ለሚቀጥሯቸው አፍሪካውያን አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዳያደርጉና ተገቢውን ክፍያ እንዳይፈጽሙ ያግዛቸዋል። ይኽም ሠራተኞችን ከመበዝበዝ አልፎ ለአደጋ ያጋልጣል። ዛምቢያ በሚገኝ በአንድ የቻይና ኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ 50 ዛምቢያውያን ሠራተኞች በጥንቃቄ ጉድለት በተፈጠረ ፍንዳታ ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል። አደጋው ሊፈጠር እንደሚችል ቀድመው የተረዱት ቻይናውያን ቀጣሪዎች ለዛምቢያውያኑ ሳይነግሯቸው ራሳቸው ብቻ ማዳናችውን ሆዋርድ ፍሬንች እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል፡፡

‹‹ውጥረቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከማጉረምረም አልፎ ሌላ መልክ ያዘ። ዛምቢያ ውስጥ የሚገኝ የቻይና ኬሚካል ማምረቻ ፋብሪካ ሥራ በጀመረ ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በደረሰ ፍንዳታ 50 የሚደርሱ ዛምቢያውያን ሠራተኞችን ሕይወት ቀጥፏል። ይህም በአገሪቱ የኢንዱስትሪ ታሪክ ትልቁ አደጋ ነው። ነገሩን የበለጠ አስቀያሚ የሚያደርገው ደግሞ ፍንዳታው ከመከሰቱ ጥቂት ደቂቃዎች በፊት ቻይናውያን የፋብሪካው አስተዳዳሪዎች ዛምቢያውያን ሠራተኞችን ከዕቁብ ሳይቆጥሯቸውና አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሳያስጠነቅቋቸው፣ ለራሳቸው ከለላ ፍለጋ ሲሸሹ መታየታቸው ነው፡፡›› 

የትኞቹ ቻይናውያን ናቸው በብዛት ወደ አፍሪካ የሚገቡት?

አንድ ሚሊዮን የሚገመቱ ቻይናውያን በአፍሪካ እንደሚገኙ የተለያዩ የመረጃ ምንጮች ያሳያሉ። ይህን ያልህ ቻይናውያን ወደ አፍሪካ የገቡት በአሥር ዓመት ውስጥ እንደሆነም ይገልጻሉ። የቻይናውያኑ ብዛትም ሆነ የተጠቀሰው ዓመት ያንሳል ብለው የሚከራከሩ ወገኖች አሉ። የመረጃ አያያዝ ችግር ስላለና መረጃ ሆን ተብሎ ስለሚደበቅ የተጠቀሰው ቁጥር ግምት ነው። እንዲያም ሆኖ አሁን አፍሪካ ውስጥ ካሉት ቻይናውያን በላይ ሊያሳስብ የሚገባው ወደፊት ሊመጡ ያሰቡትና በመምጣት ላይ ያሉት ብዛትና ጥራት ነው። እ.ኤ.አ. በ2011 የቻይና ፓርላማ አባላት ባደረጉት ዓመታዊ ስብሰባ የቻይና ወጣቶችን የሥራ ችግር ለመቀነስ አንድ መቶ ሚሊየን ለሚጠጉ ቻይናውያን በአፍሪካ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዳቀዱ በስብሰባው ላይ የቀረበ ትልመ ጥናት (ፕሮፖዛል) ያሳያል። ዛኦዝኻይ የተባለ ትልመ ጥናቱ እንዲሰምር አጥብቆ የሚከራከር የፓርላማ ተወካይ ጉዳዩን አስመልክቶ ‹‹ሕዝባችን በሥራ አጥነት ችግር ውስጥ ባለበት ሁኔታ ቻይና ለሥራ አጥ ዜጎቿ አፍሪካ ውስጥ ሥራ በማግኘት ተጠቃሚ ትሆናለች። አፍሪካም ቻይና የትኛውንም መሬትና ዕፀዋት በማልማት ካላት ልምድ ተጠቃሚ ትሆናለች፤›› በማለት ተከራክሯል። አንድ የአፍሪካ አገርም ቻይና ለምታደርግላት የዕዳ ስረዛ 5,000 የሚሆኑ ቻይናውያን ወደ አገሯ እንዲገቡ መፍቀዷ በአሉባልታ ደረጃ ተወርቷል። እነዚህ ኩነቶች ታዛቢዎችን ‹‹ቻይና ወደ አፍሪካ የምትልከው ርካሽ ሸቀጦቿን ብቻ ሳይሆን ሥራ አጥ ዜጎቿንም ጭምር ነው፤›› እንዲሉ አድርጓቸዋል። ወደ አፍሪካ ከሚመጡ ቻይናውያን ውስጥ ብዙዎቹ በዕውቀት የበለፀጉና የዳበረ የሥራ ልምድ ያላቸው አይደሉም። የብዙዎቹ መነሻም በድህነታቸው ከሚታወቁና ለመታረስ እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑ እንደ ‹‹ፉጂያን›› ካሉ ገጠራማ የቻይና ክፍሎች ነው። ወደ አፍሪካ ከሚመጡ ቻይናውያን ውስጥ የሕግ ታራሚዎች እንደሚገኙበትም ይነገራል። እነዚህ ቻይናውያን አገራቸውን ለቀው ወደ አፍሪካ አገሮች እስኪደርሱ ድረስ የአገራቸው መንግሥት ምን ያህል ጨቋኝ እንደሆነና የድህነታቸው መጠንም ምን ያህል ብርቱ እንደሆነ አያውቁትም። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ እንግዳ ተቀባይ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ራሳቸውን ሲያገኙ ደግሞ፣ የነፃነታቸው መጠን ይጨምራል። እንደዚህ ላሉ ቻይናውያንን በአፍሪካ አገሮች ውስጥ መኖር በሙቀት ብዛት እየፈላ ታፍኖ ቆይቶ ግጣሙ እንደተነሳለት ድስት ያህል ነው። አፍሪካ ደርሰው ያለውን አንፃራዊ ነፃነትና የሥራ ዕድል በሚመለከቱበት ጊዜ ለራሳቸው ተጠቅመው ጋደኞቻቸውን በጋብቻም፣ በሥራ ሰበብም፣ በሙስናም ጭምር ወደ አፍሪካ ለመሳብ ጥረት ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ መቀመጫ በመሆኗ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ለሚሄዱ ቻይናውያን የመግቢያ በር ከመሆን በተጨማሪ በአኅጉር ደረጃ ለሚከናወኑ ግንባታዎች፣ የልማት ሥራዎችና ፖለቲካዊ ግንኙነቶች የሚመጡ ቻይናውያን መቆያ ናት። የቆይታ ጊዜያቸውን ጨርሰው ወደ አገራቸው ከመመለስ ይልቅ ጊዜ ወስደውና ሥር ሰደው በመኖር ግዛታቸውን ማስፋት ይመርጣሉ።

ምን ዓይነት ሥጋት አለ?

በአፍሪካና በቻይና መንግሥታት መካከል ከሚደረገው ይፋዊ ግንኙነት ባሻገር በግለሰብ ደረጀ የሚደረግ የመረጃ ልውውጥና መስህብ የበርካታ ቻይናዎችን ልብ እያማለለ ወደ አፍሪካ እያመጣቸው ነው። ይህ ደግሞ ቻይና ሕዝቧን ወደ ሌሎች አገሮች ልኮ የቻይና ማኅበረሰብን በመፍጠር ካላት የቆየ ታሪክ፣ በአብዛኛው አፍሪካውያንና ኢትዮጵያውያን ዘንድ ካለው ስንፍናና የሥራ ዕድል መኖር እንዲሁም እንግዳ ተቀባይነትና የቻይና መንግሥት ዜጎቹ ወደ ውጭ አገር ሄደው እንዲሠሩ ከማበረታታቱ ጋር ሲወዳጅ ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ ሥጋት ነው።

ይህን ሥጋት የሚያጠናክሩ የተለያዩ አገሮች ልምዶች አሉ። ማሌዥያ የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ መሆኗን ከዚህ ቀደም የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ። የተለያዩ አገሮች ልምድም እንደሚያሳየው፣ የውጪ አገር የንግድ ሰዎች በተለይም ቻይናውያንና ህንዳውያን በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በመስፈር ጥቃቅንና አነስተኛ የንግድ ዘርፎችን በመቆጣጠር ነዋሪውን ለድህነትና ሥራ አጥነት ዳርገዋል። በጊዜ ሒደትም የኢኮኖሚ ቅኝ በመያዝ ነፃነቱን ሊያሳጡት ይችላሉ። ይህንን በተመለከተ ከመቶ ዓመታት በፊት ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ያነሳውን ሐሳብ ደግሞ ማንሳቱ ግድ ነው፡፡

‹‹እስኪ አሁን እኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርነት አለን ሊባል ነውን? አርነት ያለው ሕዝብ ማለት ትርጉሙ ለብቻው መንግሥት ያለው ሕዝብ ማለት አይደለም፡፡ ራሱንም የቻለ ሕዝብ ማለት ነው እንጂ። የኢትዮጵያ ሕዝብ እስከ ዛሬ ድረስ ገና ራሱን አልቻለም። እስኪ የለበስነውን እንይ፤ ከወዴት የተሠራና ማን ያመጣው ነው? የምንለብሰው ልብስ የምንጠጣበትና የምንበላበት ምግባችንንም የምናበስልበት ዕቃና መሣሪያ ሁሉ ፈጽሞ ከውጪ አገር የመጣ አይደለምን? ከዚህም ቀደም በአገራችን ራሳችን ለመሥራት ስንችለው የነበረው ሥራ ሁሉ ዛሬ ተረሳ፤ ቃጫና በፈረንጅ አገር የተሠራ ሸማ ፈትልም የአገራችንን ብሉኮና ጋቢ ያማረውንም ሸማችንን የሴቶቻችንንም ቀጭን ፈትል ከገበያው አባረረው፣ ዋጋውንም ወሰዱት። የዶማውንና የመጥረቢያውን ነገርማ ዛሬ ምን ብለን እናውጋው?

 . . . የአውሮፓ ሰዎች በአገራችን ከመጡና ከገቡ ወዲህ እንኳን ዕውቀት ልንጨምር አባቶቻችንም ያቆዩልንን ሥራ ሁሉ ግማሹን ዛሬውኑ ረስተነዋል። . . . በኢትዮጵያም ሕዝብ ውስጥ ያለው የእያንዳንዱ ሰው የዛሬው ጥረቱ በደህና ለመኖር ሰውነቱንና ቤቱን ለማስጌጥ ነው። በማናቸውም ሕዝብ ልብ ውስጥ እንደዚሁ ያለ ጥረት ቢኖር ሕዝቡ ዕውቀት ፈላጊ እንደሆነ ይመሰክራልና እጅግ ያስመሰግነዋል። ይህንንም ጥረት ዓይቶ መንግሥት በደህና መንገድ ከመራው እንደዚህ ያለ ተጣጣሪ ሕዝብ ከፍ ወዳለው የዕውቀት ደረጃ ለመድረስና ትልቅ ሀብት ለማግኘት ይችላል። ደህናውን መንገድ መንግሥት ለክቶ ካልሰጠውና ካላሳየው ግን እንደዚህ ያለ ጌጥና ምቹ ኑሮ የሚወድ ሕዝብ መጨረሻው ክፉ ነው። ብዙ ነገርም ይለምዳል፤ ነገር ግን የለመደውን ነገር ለማድረግ ግን አቅም ያጣል። ይህም ብቻ አይደለም፤ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ዕውቀት ባላቸው አገሮች በመኪናና በተሻለ መሣሪያ ተሠርቶ ሲመጣ ዋጋው በአገሩ ከተሠራው ይረክሳልና ለዋጋው ሲል በአገሩ የተሠራውን ትቶ ከውጪ አገር የመጣውን ዕቃ ይገዛል፤›› (መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር፣ ገጽ 102 እስከ 103)

ቻይናም ቅድመ ሁኔታ ታስቀምጣለች

በፖለቲካና በምጣኔ ሀብት መካከል ያለውን ድንበር ለመለየት ቢያስቸግርም የኢትዮጵያና የቻይና ግንኙነት በፖለቲካውም መስክ በግልጽ ይታያል። ከቻይና መንግሥት ለኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ የሚደረገው የገንዘብና የብድር ድጋፍ የኢትዮጵያ መንግሥት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት፣ ‹‹ልማታዊ መንግሥት›› እንዲመሠርት አግዞታል። ከዚህም በተጨማሪ ከምዕራባውያን መንግሥታት ጋር ያለውን ወደ አንድ ወገን ያጋደለ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንኙነት ሚዛኑን እንዲጠብቅ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል። ቻይና ለላንቲካም ቢሆን በአፍሪካ አገሮች የውስጥ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ አልገባም፣ የዴሞክራሲን ጥያቄ እንደ ቅድመ ሁኔታ አላነሳም፣ በምሰጠው ብድርም ቅድመ ሁኔታ አላስቀምጥም ማለቷ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የታዳጊ አገር መግሥታት መሪዎች ምቹ በመሆኑ፣ እነዚህ አገሮች ለቻይና ባለሀብቶች በራቸውን እንዲከፍቱ አድርጓቸዋል።

ቻይናውያንም ይህን የፖለቲካ ግንኙነት ሽፋን አድርገው የገበያ ፍላጎታቸውን በማሟላት ላይ ይገኛሉ። እንደ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያና ሌሎች የአፍሪካ አገሮች የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት በአመርቂ ሁኔታ ያልተጠናና በቅጡ ያልተለየ ቢሆንም፣ ቻይናዎች በኢትዮጵያም በተፈጥሮ ሀብት ፍለጋ ተሰማርተዋል። ኢትዮጵያ አፍሪካ አገሮች ላይ ያላትን የፖለቲካ የበላይነትና መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ በመጠቀምም ወደ አፍሪካ አገሮች መግቢያ አድርገዋታል። በዋናነት ግን ከመቶ ሚሊዮን በላይ የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥራቱን ያልጠበቀ ሸቀጥ በማራገፍ ህልውናቸው በውጪ ንግድ ላይ ለተመሠረተ የቻይና ፋብሪካዎች የገበያ ፍላጎት ማርኪያ አድርገዋቸዋል።

ቻይና በምታደርገው ዕርዳታ ላይ ማዕቀብ አላደርግም፣ በአገሮች የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ አልገባም ትበል እንጂ በተግባር የሚታየው ከዚህ የተለየ ነው። እንደ ምዕራባውያን መንግሥታት ሁሉ የራሷን ጥቅም የሚያስከብርላትን አገዛዝ ከመደገፍ ወደ ኋላ አትልም። ከዚህም በተጨማሪ በቻይናና በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች መንግሥታት መካከል የሚደረጉ የልማትና የንግድ ስምምነቶች ለሰፊው ሕዝብ ግልጽ አይደሉም። ይህም ሙስናን ለማስፋፋትና ምዝበራን ለማስፈን ክፍተት ይፈጥራል። ተገቢው ጥንቃቄ ካልተደረገበትም የጥቅም ፖለቲካን በማራመድ ጥቂት ጉልበተኛ አፍሪካውያን ባለሀብቶችንና የቻይና ድርጅቶችን እየጠቀመ የሰፊውን ሕዝብ ጉልበት እንዲሁም የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት የሚመዘብር ሥርዓትን ሊፈጥር ይችላል።

ቻይና የምትሰጠው ብድርም ከቅድመ ሁኔታ ነፃ አይደለም። በእርግጥ ‹‹ዴሞክራሲ ይኑር›› የሚል ቅድመ ሁኔታ አታስቀምጥም። ይህ ደግሞ ለራሷ የሌላትን ሥርዓት በሌሎች ላይ መጫን ትርጉም ስለማይኖረው ነው። ከምታራምደው ርዕዮተ ዓለም ጋርም ይጋጫል። ስለዚህ ከቻይና ብድር የሚያገኙ የአፍሪካ አገሮች የሚቀመጥባቸው ቅድመ ሁኔታ ኢኮኖሚያዊ ነው። በምትሰጠው ብድር የሚሠሩ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የሚከውኑት የቻይና ድርጅቶች እንዲሆኑ የምታደርግ ሲሆን፣ ለግንባታ የሚያስፈልጉ ግብዓቶች የቻይና እንዲሁም ሥራውን የሚከውኑት ሰዎች ቻይናውያን እንዲሆኑ ታደርጋለች። በአፍሪካ ለሚደረጉ ግንባታዎች ጨረታዎችን የቻይና ኩባንያዎች እንዲያሸንፉም ከቻይና መንግሥት ድጎማ ይደረግላቸዋል። ይህም በብድር መልክ ያወጣችውን ገንዘብ መልሳ ወደ አገሯ እንድትወስድ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላታል።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በርካታ የቻይና ድርጅቶችና ቻይናውያን ትልልቅ የልማት ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ። ይህ ለጊዜው ልማትን የሚያፋጥን ቢመስልም፣ ፈረንጆች ‹‹Some Relations Grow Better Before they Grow Worse›› እንዲሉ በጊዜ ሒደት ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ሊታሰብበት ይገባል። የቻይና ድርጅቶችና ኮንትራክተሮች በሚሠሯቸው ትልልቅ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ላይ በስፋት መሳተፋቸው የኢኮኖሚ አቅማቸውን በማደራጀት ቀስ በቀስ ፖለቲካውም ላይ ተፅዕኖ ማድረግ ከሚያስችላቸው ደረጃ ሊያሸጋግራቸው እንደሚችል የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስጠነቅቃሉ።

በዋና ዋና የንግድና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ባላቸው የሥራ ዘርፎች ላይ ለመሰማራት አቅምና ዕድሉን ስለሚፈጥርላቸው የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ ሊጥሉ ወደ ሚችሉ ሴክተሮች ሊያሸጋግራቸው ይችላል። ቀስ በቀስም ጥገኝነትንና የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን ሊያስከትል ይችላል። የቻይናን ያለፈ ታሪክ አስመልክቶ ፒተር ዱስ የተባለ ጸሐፊ ‹‹The Abacus and the Sword›› በሚል መጽሐፉ ውስጥ ጃፓን እንዴት ቻይናን ቅኝ እንደገዛች ሲያስረዳ ‹‹Imperialism Requires an Available Victim- a Weaker, Less Organized, or Less Advanced Society or State Unable to Defend Itself against outside Intrusion›› ይላል።

ቻይና ከአፍሪካ አገሮች ጋር እያደረገችው ያለው የንግድ ልውውጥ የተፈጥሮ ሀብትን በገንዘብ መግዛት ብቻ አይደለም። እንደ መንገድ፣ ስታዲየም፣ የባቡር ሐዲድና መሠል መሠረተ ልማቶችን ገንብቶ በልዋጩ የተፈጥሮ ሀብትን በመውሰድ የድሮውን የ‹‹ባርተር›› የንግድ ሥርዓት በአፍሪካ መልሳ አስተዋውቃለች። ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ለኮንጎ ወደ ስድስት ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት የመሠረተ ልማት ግንባታ በራሷ ወጪ አደረገች። በልዋጩም የኮንጎን የተፈጥሮ ሀብት ለ22 ዓመታት ያህል ማውጣትና መውሰድ የሚያስችላትን መብት አገኘች። በጎንዮሽ የምታገኘውን ጥቅማ ጥቅም ሳይጨምር፣ ከኮንጎ የምታገኘው የተፈጥሮ ሀብት ዋጋ ወደ 12 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይገመታል።

ኢትዮጵያም ለባቡር ሐዲድ ግንባታና ሌሎች የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከቻይና ለተበደረችው ዕዳ በሰሊጥና በፖታሽ ጭምር እየከፈለች እንደሆነ ይነገራል። ማንኛውም አገር ከሌላው አገር ጋር የሚያደርገው ግንኙነት የጥቅም እንጂ የልግስና ወይም የዕርዳታ አይደለም። ከሰጠው በላይ መጠቀም ይፈልጋል። ቻይናም ከአፍሪካ አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት እንደምትለው አፍሪካን ለመርዳት ሳይሆን የራሷን ጥቅም ለማስከበር ነው። ለአፍሪካ አገሮችም እየሰጠች ያለው ለአፍሪካውያን የሚያስፈልገውን ሳይሆን የራሷን ጥቅም የሚያስከብርላትን ነው።

ቻይና አደገኛ ወዳጅ

በእርግጥ ቻይና ለተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የቀድሞ ቅኝ ገዥዎቻቸው አሁንም ድረስ ለሚያደርሱት ብዝበዛ አማራጭ ሆናለች። የአውሮፓ ደሃ አገር ከሆነችው ፖርቱጋል ጋር ባላት ከቅኝ ግዛት የቀጠለ እጅግ ሚዛን አልባዊ የንግድ ግንኙነት፣ የቻይና እንደ አማራጭ መቅረብ ሞዛምቢክን ትልቅ ዕረፍት ሰጥቷታል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሞዛምቢክ ወደ ፖርቱጋል ለምትልካቸው ዕቃዎች የዋጋ ተመን የሚወጣው ከሊዝበን ነበር። ቻይና እንደ አማራጭ መምጣቷ ለሞዛምቢክና መሰል የአፍሪካ አገሮች  አማራጭ ስለሆናቸው የዴሞክራሲ ጥያቄ ካለማንሳቷ ጋር ተያይዞ እጃቸውን ዘርግተው እንዲቀበሏት አደረገ። ሆኖም ቻይና የመጣችው ሞዛምቢክን ነፃ ልታወጣ ሳይሆን የራሷን ጥቅም ለማስከበር በመሆኑ፣ የሞዛምቢክ ዕጣ ፈንታ ከቀድሞው የተሻለ አልነበረም። ቻይና የሞዛምቢክን የደን ሀብት በመጨፍጨፍ ወደ አገሯ ልካለች። ሕዝቧን ለመመገብ የሚያስፈልጋትን ለም መሬትም ከሞዛምቢክ አግኝታለች።

ቻይና የዓለምን ሃያ በመቶ የሚሆን ሕዝብ ያላት ሲሆን፣ የመሬት ስፋቷ ደግሞ ዘጠኝ በመቶ ነው። የመሬት ስፋቷና የሕዝቧ ብዛት ስለማይመጣጠን እንዲሁም እያካሄደች ላለችው ትልልቅ የኢንዱስትሪና ግንባታዎች የሚያስፈልጓትን ጥሬ ዕቃዎች ለማግኘት በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተለይም በአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያላትን እንቅስቃሴ አጠናክራ ቀጥላለች። የተፈጥሮ ሀብትን ወደ ቻይና ከመውሰድና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎቿን ወደ አፍሪካ አገሮች ከማምጣትም በተጨማሪ ሞዛምቢክ፣ ማሊ፣ ላይቤሪያና ሴኔጋል በመሳሰሉት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የመሬት ቅርምት እያካሄደች ነው። ምንም እንኳን የቻይና ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ትልልቅ የእርሻ መሬቶችን ባይወስዱም፣ ቻይናዎች በዚህ ረገድ በሌሎች አገሮች ካላቸው ተሞክሮ አንፃር እንዲሁም ኢትዮጵያ መሬትን ለኢንቨስተሮች በመስጠትና በማስፈጸም ሒደት ውስጥ ካሉባት የተለያዩ ችግሮች ወደዚህ ዘርፍ የሚገቡ ከሆነ ጥንቃቄ ሊደረግባቸው ይገባል።

ቻይናዎች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር በሆነው የቴሌኮም ሴክተር በስፋት መግባታቸው መንግሥት እንደ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ጭምር የሚጠቀምበትንና የመረጃ ቋት የሆነውን ሴክተር ለቻይናዎች መክፈቱ የአገሪቷን ሉዓላዊነት ለአደጋ ሊያጋልጠው ይችላል። አሁን ባለው የካፒታሊዝም ኢኮኖሚ ሥርዓት መሠረት ቋሚ ወዳጅም፣ ቋሚ ጠላትም ስለማይኖር በልማትና ንግድ ሽፋን ወደ አገራችን የሚመጡ ቻይናዎች ተገቢው ቁጥጥር ካልተደረገባቸው፣ ጥቅም እስካገኙበት ድረስ የትኛውን ሕግና ደንብ ለመተላለፍ ወደ ኋላ አይሉም። መንግሥት በአሸባሪነት ስም ለሚከሳቸው የአገር ውስጥና የውጪ አካላት ቅጥረኛ ከመሆን አይቆጠቡም። ቻይናዎች ደግሞ ዕቅዳቸው የረዥም ጊዜ ነው። ከቻይና ጋር ያለውን ግንኙነት መጥኖ መደቆሱ ኋላ ቁጭ ብሎ ከማልቀስ ስለሚያድን ያንኑ ማድረግ ይሻላል።

የኢትዮጵያ ሕግ በብዙኃን መገናኛ ዘርፍ መሰማራት የሚችሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ እንደሆኑ ይደነግጋል። የትልልቅ የቻይና የብዙኃን መገናኛ ሠራተኞች (ኮርስፖንደንት) እና ቢሮዎች አዲስ አበባ ውስጥ አላቸው። የዥንዋ ሙሉ ጊዜ ሠራተኞች ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከናወኑ ሁነቶችን ለቻይናውያን በየዕለቱ ይዘግባሉ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሲጂቲቪ ዋና ቢሮውን ኬንያ ላይ አድርጎ በአፍሪካ ውስጥ የሚከናወኑ ሁነቶችን በየዕለቱ በመዘገብ ላይ ይገኛል። ይህ በብዙኃን መገናኛ በኩል የተቀመጠውን የኢትዮጵያ ሕግ ባይጥስም፣ ቻይናውያን የሚፈልጉትን መረጃ ከማግኘት የከለከላቸው አይመስልም። በዚህም የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ለረዥም ዓመታት በአፍሪካ ያደርጉት የነበረውን የበላይነት በመዋጋት የቻይናን ጥቅም ለማስከበር የሚዲያ ጦርነቱን ተያይዘውታል። ከዚህ ቀደም በርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ይደረግ እንደነበረው ሁሉ የፕሮፓጋንዳ ጦርነቱ በአፍሪካ ምድር ላይ በመካሄድ ላይ ነው።

ጦርነቱ ከፕሮፓጋንዳ አልፎ በባህልና በቋንቋ ዘርፍም ይታያል። ቻይናም ለረዥም ዓመታት በኢትዮጵያ የቆዩ እንደ የአሜሪካው ‹ፒስ ኮርፕስ›፣ የእንግሊዙ ‹ብሪቲሽ ካውንስል›፣ የፈረንሣዩ ‹አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ› እና የጀርመኑ ‹ጎተ ኢንስቲቲዩት› የመሳሰሉትን የባህልና የቋንቋ ተቋማትን የሚገዳደር የኮንፊሺየስ ኢንስቲቲዩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አቋቁማለች። የቻይና ቋንቋ የሆነው ማንዳሪንም በተለያዩ የቋንቋ ትምህርት ቤቶች ውስጥ በመሰጠት ላይ ይገኛል። የኮንፊሺየስ ኢንስቲቲዩት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲመሠረት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ተቋም ተማሪዎች የሚገለገሉበት ቤተ መጻሕፍት ቦታን ነበር የነጠቀው። ትርጉሙ ከሆነ የሕንፃ አካልነት እጅግ ይበልጣል። ደራሲ እንዳለ ጌታ ከበደ ግርምቱን በግጥም እንደሚከተለው ገልጾ ነበር፡፡

‹‹. . .  እንደ ቻይና ልርቀቅ ብዬ

ደሃነትን ለመደፍጠጥ

በቋንቋዋ ስመጥቅበት

ሩጫውን በግሬ ስሮጥ

ስፍጨረጨር ስውተረተር

ጥዬ ላልፈው ድሃነቴን

ራሴን ኖሯል የቀደምኩት

ባህል ቅርስ ማንነቴን!

እኔም ሐዘንሽ አመመኝ

ሕመም ስቅየትሽ ምነው በዛ

ደሃ ገድሽ አይወረዛ፡፡

ታደርጊው ነገር ብታጪ

አስተማርሽኝ ቅልውጥና

አሳደርሽኝ ከባዕዳን

አድርገሽ ላክሽኝ ባዶ ቁና፡፡. . .››

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ በኢሜይል አድራሻቸው   [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles