በአፍሪካ ብቻ የሚገኘውና “አፍሪካን ጎልደን ካት” በሚል የሚታወቀው ድመት፣ መጠኑ በቤት ውስጥ ከሚኖሩት ለማዳ ድመቶች በሁለት እጥፍ ይበልጣል፡፡ ኑሮው በደን ውስጥ ሲሆን አይጥ፣ ነፍሳትንና ወፎችን ይመገባል፡፡
በምዕራብና በመካከለኛው አፍሪካ በሚገኙ ደኖች የሚገኘው ድመት፣ ወርቃማ በቡናማ፣ ወርቃማ በጥቁር፣ ወርቃማ በቀይ የተቀላቀለ ፀጉር አለው፡፡ አንዳንዶቹ ነጠብጣብ ያላቸው ሲሆን ምንም ነጠብጣብ የሌላቸው መኖራቸውንም ኪድስ ባዮሎጂ በድረ ገጹ አስፍሯል፡፡
የሰውነቱ ርዝመት ከ61 ሴንቲ ሜትር እስከ አንድ ሜትር፣ ጭራው ከ16 ሴንቲ ሜትር እስከ 46 ሴንቲ ሜትር ይረዝማል፡፡ የጭንቅላቱ መጠን ከሰውነቱ መጠን ጋር ሲነፃፀር ሊኖረው ከሚገባው ልኬት አነስተኛ ነው፡፡ ክብደቱ ከስድስት እስከ 16 ኪሎ ግራም ይመዝናል፡፡ እስከ 12 ዓመት ድረስም ይኖራል፡፡
“አፍሪካ ጎልደን ካት” በጫካ ውስጥ ብቻ መኖር መለያው ነው፡፡ አንድ የአፍሪካ ወርቃማ ድመት የሚወለደው ከ75 ቀናት ወይም ከሁለት ወር 15 ቀናት የእርግዝና ጊዜ በኋላ ነው፡፡ ተወልዶ ዓይኑን ለመግለጥ የሳምንት ጊዜ የሚፈጅበት ሲሆን፣ ከጡት በተጨማሪ ጠንካራ ምግብ ለመብላት ከስድስት እስከ ስምንት ሳምንታት ይወስድበታል፡፡ ከ11 ወራት በኋላ ለግንኙነት የሚደርስ ቢሆንም፣ ወንዶቹ ግንኙነት የሚጀምሩት 18 ወራት ሲሆናቸው ነው፡፡