Friday, April 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

​የስደት መባባስን ለመግታት ምን ይበጃል?

በሪፖርተር ጥር 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ዕትም ያሲን ባህሩ የተባሉ ጸሐፊ ‹‹ኢትዮጵያውያን ለምን ይሰደዳሉ?›› በሚል ርዕስ ያስነበቡትን ጽሑፍ ተመልክቻለሁ፡፡ ጸሐፊው ‹የዕድገት አለ ስደት በዛ› እንቆቅልሹን በመበርበር በአገሪቱ በዋናነት የኢኮኖሚ ስደተኞች በዝተው እንደሚገኙ፣ በፖለቲካ መዘዝም የሚሰደዱ እንዳልጠፉ ተችተዋል፡፡ ይሁንና ጸሐፊው ለአገራችን ወጣቶች ስደት መነሻ የሆኑ ሌሎች ምክንያቶችን ካለማንሳታቸውም ባሻገር፣ መፍትሔ ማመላከት ላይ የሚጎድሉት ነጥቦች ያሉ ይመስለኛል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ደግሞ በእኔ እምነት የሚሰሙኝን ነጥቦች ለመጨመር እወዳለሁ፡፡

ለነገሩ በዚህ አንገብጋቢ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እንዳተኩር ያደረገኝ የአውሮፓ ኅብረትን እያስጨነቀ የመጣው የስደተኞች ጉዳይ ነው፡፡ በተለይ ባሳለፍነው ሳምንት የቢቢሲ ‘‘ሃርድ ቶክ’’ አዘጋጅ ስቴፈን ሳከር አስጨንቆ ያፋጠጣቸውን በፈረንሣይ የአውሮፓ ኅብረት ዋና ጸሐፊ አርለም ዴሳይ ንግግርን ማዳመጤ ነው፡፡

ኃላፊው ደጋግመው እንዳስረዱት የአውሮፓ ኅብረት በሕጋዊም ሆነ በሕገወጥ ስደተኞች አያያዝና አቀባበል ላይ ወጥ የሆነና ነባሩን የየአገሮች ዜጎች ጥቅምና ፍላጎት በጠበቀ መንገድ ሊተገብሩ ይገባል፡፡ በሰብዓዊነትና በመንቀሳቀስ መብት ስም በተለይ ከአፍሪካና ከመካከለኛው ምሥራቅ በስፋት እየተካሄደ ያለው ፍልሰት ሥርዓት ካልተበጀለት ግን ከሽብርተኝነት፣ ከደኅንነት ማጣትና ከሥራ ዕድል መጣበብ ጋር የተያያዙ ችግሮች ሊባባሱ ይችላሉ ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አውሮፓም ሆነ በሌላው ያደገው ዓለም የሰው ልጅ ከቦታ ቦታ ዝውውር የማይቀር ቢሆንም፣ በየአገሩ ለዜጐች ተስማሚ የሆነ ልማትና ዴሞክራሲያዊነት ብሎም የተረጋጋ ሰላም እንዲኖር ማገዝ እንዳለበት ምክር ለግሰዋል፡፡

ይህን ወቅታዊ የዓለም አጀንዳ ወደ አገራችን በማምጣት ለመመልከት በአትኩሮት መታየት ያለባቸው ነጥቦችን ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ይኼውም ዕውን አሁን በአገሪቱ ስደትና ወደ ውጭ ማማተር ተባብሷልን? ከሆነስ መሠረታዊው ምክንያት ምን ይሆን፣ መንግሥትና የግል ባለሀብቱስ ይህን ችግር ለማስታገስ ምን እየሠሩ ነው? ወደፊትስ ምን ቢደረግ ችግሩ ሊረግብ ይችላል? እያልኩ ትዝብታዊ ዕይታዬን ለመሰንዘር እሞክራለሁ፡፡

የስደቱ መባባስ ሌላኛው መንስዔ

ቀደም ሲል የጠቀስኩዋቸው ጸሐፊ ለአገራችን ወጣቶች ሕገወጥ ስደት መባባስ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መልክ እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡ የእኔ ሐሳብም ከዚሁ ጋር ቢያያዝም፣ በአገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ ቁጥሩ እየጨመረ የመጣው ሕዝብ አንዱ መንስዔ መሆኑ በማንሳት ልከራከር እወዳለሁ፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የሥነ ሕዝብ ተመራማሪ በዚህ ላይ ያነሱልኝ አሳማኝ ነጥብ አለ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ግልጽ የሥነ ሕዝብ ፖሊሲ ከኢኮኖሚ ጋር የተመጣጠነ የውልደት ምጣኔንና የሚያስገድድ ስትራቴጂን የሚከተል አይደለም፡፡ ይልቁንም ሕዝብ ኃይልና ዕድል (Opportunity) ነው ብሎ ስለሚያምን ላለፉት 30 ዓመታት የአገሪቱ የውልደት ምጣኔ (Birth Rate) ከሦስት በመቶ በታች ሊሆን አልቻለም፡፡ በዚህ ደግሞ ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የመሸከም አቅም በላይ የአገሪቱ ሕዝብ 95 ሚሊዮን ያህል ሊደርስ ችሏል፡፡ ከዚህ ሰፊ ቁጥር ያለው ሕዝብ እስከ 60 በመቶ የሚደርሰው ወጣትና ‹‹አምራች ኃይል›› መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለኑሮው ሥራ፣ ለሕይወቱ መቀጠል ደመወዝ፣ ቤትና ምቹ አካባቢን የሚፈልግ ነው፡፡ ስለሆነም አዲሱ ኃይል ከነባሩ ዜጋም የበለጠ ፍላጐት ያለው፣ የማይረካና ኑሮን ለማሸነፍ የትም አገር ድረስ ለመሄድ (ለመሰደድ) የሚያመነታ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ አሁን የደረሰችበት የኢኮኖሚ ደረጃ የሚታወቅ ነው፡፡ ምንም እንኳን ከ12 ዓመታት ላላነሱ ጊዜ ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገት መመዝገቡ ባይታበልም፣ ከዝቅተኛ ደረጃ የተነሳ ምጣቤ ሀብት በመሆኑ የነፍስ ወከፍ ገቢው በዓመት ከ700 ዶላር አልበለጠም፡፡ ይህም ቢሆን በፍትሐዊነት ለሁሉም ተከፋፍሏል ማለት አይደለም፡፡ ዛሬ በከተሞች አብዛኛው ነዋሪ የሆነው ተቀጣሪ (ደመወዝተኛ) ከደመወዙ ግማሽ በላይ ለቤት ኪራይ የሚያወጣ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ብቻ እንኳን 34 በመቶ ነዋሪ (1.8 ሚሊዮን) የግሉ የመኖሪያ ቤት የሌለው መሆኑ በጥናት ተረጋግጧል፡፡ በዚህ ላይ አልባሳት፣ የትምህርት ክፍያና ዋና ጉዳይ የሆነውን ምግብ በቤተሰብ ደረጃ የመሸፈን ፈተና ትግል የሚጠይቅ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በገጠር ያለው ግብርና መር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴም በየመንደሩ እየተተራመሰ ካለው ወጣት አንፃር የብዙኃኑ የሕይወት መሠረት መሆን አልቻለም፡፡ ምርታማነቱ በከፍተኛ ደረጃ ባልጨመረበት ሁኔታ፣ የመሬት እጥረት እንቅፋት በመሆኑም ሆነ ወደ ኢንዱስትሪ የሚደረገው ሽግግር (በተለይ በገጠር እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ) የሥራ አጡ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡

በእርግጥ መንግሥት በፈጠራቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ በግል ባለሀብቶችና በአንፃሩ ኢኮኖሚው በፈጠረው እንቅስቃሴ ምክንያት ሰፊ ቁጥር ያለው ወጣት የሥራ ዕድል እየተፈጠረለት መጥቷል፡፡ ነገር ግን የሥራ ፈላጊውና ተፈላጊው መሳሳብ በከተሞች ላይ ያተኮረ ሆኖ ቀርቷል፡፡ (በአዲስ አበባ ከጫፍ ጫፍ የተሰገሰጉት ከተለያዩ ክልሎች የመጡ የገጠር ወጣቶች ይመለከቷል) ከዚህም ባሻገር በአገሪቱ የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች የሚያስገኙት ጥቅም ለዕለት ጉርስና ለመጠለያ እንኳን በወጉ ስለማይበቁ፣ እግር ወደ መራው ለእንጀራ ፍለጋ መንጎድ አማራጭ ሆኖ ቀርቷል፡፡

ከዚህ አንፃር እየተጠናከረ የመጣውን አሳሳቢ የአምራች ኃይል ስደት ለማስታገስ፣ ፈጣንና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድገት ይበልጥ እንዲረጋገጥ ከማድረግ በላይ የሥነ ሕዝብ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

በመሰደድ የሚገኝ ገቢ እዚህ ካለው ይሻላል

በቅርቡ የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ (VOA) የአማርኛው ክፍለ ጊዜ እንደዘገበው፣ ከአውሮፓውያን አዲስ ዓመት (2016) መግባት ወዲህ በታንዛኒያ በኩል በሕገወጥ መንገድ የተሰደዱ ወጣት ኢትዮጵያውያን ተይዘዋል፡፡ በተመሳሳይ በእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ባለቸው የመን እንኳን ራሳቸውን ለአደጋ አጋልጠው እየገቡ ካሉ ስደተኞች አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን የየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች መርጃ ድርጅት የቅርብ ጊዜ መረጃዎች አመላክተዋል፡፡

ስደተኞች ከአገር ለመውጣታቸው ዋነኛ መንስዔ የሚሉት በአገር ውስጥ ሥራ የለም ነው፡፡ ሥራ ቢኖርም ራስን ለመቀየር የሚያስችል ገቢ ማግኘት ከባድ ነው የሚልም ምክንያት ይቀርባል፡፡ ስለሆነም ምንም ያህል ከባድ ቢሆንም አስፈላጊውን መስዋዕትነት ከፍሎ ከአገር በመውጣት ኑሮን ለማሸነፍ ጥረት ማድረጉ ብቸኛ አማራጭ ሆኗል፡፡

አበበ ጭሉ የተባለ በታንዛኒያ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ፣ ‹‹ከደቡብ ኢትዮጵያ ከንባታ አካባቢ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመሄድ ስነሳ ከዚህ ቀደም ወደ ፕሪቶሪያ አቅንቶ የተሻለ ኑሮ መኖር የጀመረውን የአጎቴን ልጅ ሕይወት አይቼ ነው፡፡ ወጣቱ ሱቅ በደረቴ በውጭ አገር በመሥራት የራሱን ገቢ ከማሻሻል በተጨማሪ፣ ለቤተሰቦቹ መኖሪያ ቤትና ከብት እስከ መግዛት ደርሷል፡፡ እህቶቹንም እየደገፈ ማስተማር ችሏል፡፡ ስለዚህ እኔስ እዚህ ምን እሠራለሁ በማለት ጥያቄ በማንሳት ጉዞ ጀመርኩ፤›› ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ለተባባሰው ስደት፣ ሕገወጥ ስደትና ይህንኑ ድርጊት የሚተባበሩ የመንግሥት አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረጉን ይገልጻል፡፡ ለሥራ ወደ ውጭ (በተለይ መካከለኛው ምሥራቅ) የሚደረግ ጉዞን አግዶ በመቆየት በማሻሻያ አዋጅ ደግሞ እንዲጀመርም አድርጓል፡፡ ይህ ብቻም አይደለም፡፡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደረጃ ከአንዳንድ አገሮች ጋር በተደረገ ስምምነት ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈላጊዎች ጥቅማቸውና መብታቸው ተከብሮ በየአገሮቹ የሚሠሩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ጥረት መደረጉም ይሰማል፡፡

ይህ ሁሉ ተደርጎ ግን አሁንም ከስደት ተመላሹንም ሆነ ገና ወደ መሰደድ እያኮበኮበ ያለውን ኃይል በአገር ውስጥ ወደ ሥራ እንዲሰማራ የማድረግ ፈተናው ከባድ ሆኗል፡፡ ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ገደማ በስፋት እየተነገረለት ያለው የጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ዘርፍ ልማት ቀድመው ማምረቻና የመሸጫ ሼድ በያዙ ‘ጁንታዎች’ እንደተጠለፈ ነው፡፡ እንደ አዲስ ተደራጅቶ ቦታ፣ ማሽነሪና ገበያ ማግኘትም እንዲህ እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራን የሚደግፉና የሚያስተባብሩ ሕዝባዊ ተቋማት በስፋት እየመጣ ያለውን ተመራቂና አዲስ ኃይል ሥራ ከመስጠት ይልቅ፣ ነባሩን ባለሥራ መደገፍ ይቀላቸዋል፡፡ ለምን ሲባሉም መስኩ ተጣቧል፣ በአንዳንድ መስኮች የጥቃቅን አንቀሳቃሾች ውጤታማ አይደሉም ይላሉ፡፡ በአነስተኛ ሥራ ፈጠራ (ንግድም ሆነ አገልግሎት) ተሰማርተው ያሉ ዜጎች በበኩላቸው በንግድ ጽሕፈት ቤቶች፣ በገቢዎችና ደንብ አስከባሪዎች ብሎም በፖሊስና መሰል መንግሥታዊ አካላት የሚደርስባቸውን እንግልትና ድጋፍ አልባ ጫና በተስፋ አስቆራጭነት ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህም ስንቶች የጀመሩትን ሥራ ትተው ተሰደዋል በማለት?!

የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ዋስትና ያስጨንቃል

የሰው ልጅ በየትኛውም ዓለም ተንቀሳቅሶ፣ በሽብርና በጦርነት ቀውስ ውስጥ ያሉ አካባቢዎች መሰደድ ባይመከርም ሕጋዊ መስመርን ተከትሎ የመንቀሳቀስ መብት አለ፡፡ ያም ቢሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገሮች እያንገራገሩበት ያለ ጉዳይ መሆኑን ግን በመግቢያችን ላይ የአውሮፓውያንን ሁኔታ አንስተናል፡፡

ኢትዮጵያውያን ስደት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ በጋራና በተናጠል የሚገጥሟቸው ችግሮች አሉ፡፡ ከሁሉ የከፋው ግን በ2006 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ‹‹ሕገወጥ ናችሁ›› በማለት ያባረራቸው ከ125 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ነው፡፡ እርግጥ በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ አንዳንድ ከተሞች በሁሉም አፍሪካውያን ስደተኞች ላይ የተፈጸመው አረመኔያዊ፣ አግላይና ዘረኛ ዕርምጃም ብዙዎች ማዘናቸው የሚታወቅ ነው፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ደቡብ ሱዳን ጁባ ውስጥ በተፈጠረው የሥልጣን ሹክቻም ዘጠኝ ኢትዮጵያውያን ከመሞታቸው በላይ ንብረታቸው መውደሙን ሰምተናል፡፡ በሊቢያ ጠረፍ የባህር ዳርቻ  በአይኤስ የታረዱ ወጣቶች ሐዘንም አልወጣልንም፡፡ በየጊዜው ከመካከለኛው ምሥራቅ የአካልና የአዕምሮ ጉዳት ደርሶባቸው የሠሩበት ሀብትና ጥሪት ተዘርፎ ወደ አገራቸው የሚመለሱ በተለይ ሴቶች እህቶቻችን ጉዳይም እስኪበቃን የሰማነው ነው፡፡

ከዚህ አንፃር መንግሥት ተጨማሪ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ግን ማጤን ተገቢ ነው፡፡ በአንድ በኩል በየትኛውም አገር ያሉ ዜጎቻችን ሕጋዊ ጉዞንና አኗኗርን እንዲፈጽሙ በማድረግ ጥበቃ እንዲያገኙ መደረግ አለበት፡፡ በሌላ በኩል በተቻለ መጠን በአገር ውስጥ ፍትሐዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የሥራ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት፣ ብሎም የአገር ፍቅር ስሜትና የመረዳዳት ባህልን መገንባት ያስፈልጋል፡፡ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግርን የመፈታቱ ጉዳይም ከዚሁ ጋር ይያያዛል፡፡

እንደ መቋጫ

የስደት መኖር አለመኖር ጉዳይ ከአገሮች የኢኮኖሚ አቅም፣ ፖለቲካዊ መረጋጋት፣ አገራዊ ደኅንነት ጋር የሚያያዝ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ዓለም ወደ አንድ መንደር የተቀየረበት የመረጃና የግንኙነት መሠረተ ልማት መቀላጠፍም የሰው ልጅን ከቦታ ቦታ ተዟዙሮ የመሥራት ዕድል አስፍቶታል፡፡

የኢትዮጵያውያን ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ ሥራ ፈላጊ ወጣቶችና ሌሎች ስደት የሚታየውም ከዚሁ አንፃር ነው፡፡ ነገር ግን ቻይናውያንን ጨምሮ በርካቶች ረጅም ርቀት አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ በስፋት ሲመጡ፣ ‹‹ሰላም የለም ጦርነት የለም›› በሚባልበት ሁኔታ ውስጥ ካሉት ኤርትራና ኢትዮጵያ አንፃር እንኳን ችግር ሳይገጥማቸው፣ አዲስ አበባን እየሞሏት ያሉት የአስመራ ልጆች ቁጥር እየጨመረ እንዴት ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ትተው በስፋት ይሰደዳሉ የሚለው ጉዳይ ነው የሚያስጨንቀው፡፡

በተለይ ከአንዳንድ ክልሎች ባለማቋረጥ እየፈለሰ ያለው ወጣት በስቃይና በእንግልት ውስጥ፣ በመከራና ሞት ጥላ ሥር እያለፈ መሆኑ ሲታሰብ ነገ የታሪክ ተጠያቂነት እንዳይመጣ ሊፈተሽ የሚገባው ነው፡፡ ለዚህ ተጠያቂነትና ወቀሳ ደግሞ መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ በአገሪቱ የምንኖር ባለሀብቶች፣ ምሁራንና ዜጎች ጭምር ራሳችንን ማዘጋጀት አለብን፡፡ በመንግሥት በኩል ደግሞ ፍትሕ የማስፈን፣ አስተዳደራዊ በደሎችን የማስወገድ፣ ሕገወጥና ብልሹ አሠራሮችን የማረም፣ ሙስናን ድምጥማጡን ማጥፋት፣ ሰብዓዊ ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበር፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ማስፈን፣ ትምክህተኝነትን፣ እንዲሁም ጠባብ ብሔርተኝነትን መፋለም የግድ መሆን አለበት፡፡ እነዚህ የአገር ጠንቅ የሆኑ ጠላቶች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያውያን ስደትና ውርደት ማብቃት አለበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

በሒሩት ደበበ

       

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles