Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ኪንና ባህል​ጥበብ የተለያቸው ሕንፃዎች

  ​ጥበብ የተለያቸው ሕንፃዎች

  ቀን:

  በሰው ዘር መገኛነት የምትታወቀው ኢትዮጵያ በተለይ በአክሱም ሐውልትና በላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት በሌላው ዓለም እንድትታወቅ ሆናለች፡፡ 1700 ዓመታትን ያስቆጠረው የአክሱም ሐውልት 24 ሜትር ርዝማኔ አለው፡፡ 160 ቶን የሚመዝን ሲሆን ወጥ የሆነ ገጽታው ከአንድ ድንጋይ መፈልፈሉን እንዲጠራጠሩ ግድ ይላል፡፡ የኪነ ሕንፃ (አርክቴክቸር) ባለሙያዎችም በዘመኑ የነበሩ አናፂዎች ‹‹ድንጋይን ፈጭተውና አቡክተው የሠሩት ያህል የተስተካከለ ነው፡፡ የሚገርም ሥራ ነው፤›› ሲሉ ያሞካሹታል፡፡

  ጌጠኛ አሠራራቸው በወቅቱ ስለነበረው ጥልቅ የሥነ ሕንፃ ጥበብ ምስክር ነው፡፡ በአሥራ አንደኛው ክፍለ ዘመን የነገሠውና ኢትዮጵያን ለዓመታት ባስተዳደረው የዛጉዌ ንጉሥ ላልይበላ የተሠሩት አሥራ አንዱ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትም በወቅቱ ኢትዮጵያውያን በኪነ ሕንፃ ጥበብ የተካኑ መሆናቸውን ያሳያሉ፡፡ ከአንድ ድንጋይ ተፈልፍለው የተሠሩት ቤተክርስቲያናት ግንባታ 23 ዓመታት ፈጅቷል፡፡ ከምሰሶው አወቃቀር ጀምሮ በጣሪያው፣ በመስኮትና በሮቹ ላይ በተቀረፁት ጌጦች ዘመን ተሻጋሪ ጥበብ ይስተዋላል፡፡

  በጥንታዊው ሥልጣኔ ሕንፃዎች እንደ ምልክት በሐውልት መልክ አልያም ተፈጥሯዊ ከሆኑ አደጋዎች ለማምለጥ ለመሸሸጊያነት ይውሉ ነበር፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የሚሰጡትን አገልግሎት በማስፋት ማራኪ ቅርፅ እንዲይዙና ጥበብ እንዲያጎናጽፉ ተደርገው ይገነቡ ጀመረ፡፡

  ቴክኖሎጂ እንደዛሬ ባልዘመነበት በዚያ ዘመን የተሠሩት የጥበብ ሥራዎች  አጀብ ያሰኙ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በኪነ ሕንፃ የተቀመጡ መሥፈርቶችን በከፊል የሚያሟሉ ሕንፃዎችን ማየት ከባድ የሆነ ይመስላል፡፡

  በተለያዩ ከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ የሕንፃዎች ግንባታ መብዛትን ሕንፃዎች መብቀል ጀምረዋል ከማለት በተሻለ መግለጽ አይቻል ይሆናል፡፡ እየታየ ያለው ለውጥ የሚበረታታ ቢሆንም ሕንፃዎቹ የሚዋቀሩበት መንገድና ገጽታቸው የተዘበራረቀና ወጥነት የጎደላቸው ሲሉ ብዙዎች ይተቻሉ፡፡ ይኽም የዘርፉን ባለሙያዎች እጀ ሰባራ ከማድረጉ ባሻገር በሙያው ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡

  የኪነ ሕንፃ ንድፍና ግንባታ ሥራ ሒደት ክትትል ዘርፍ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይከሰቱ ዘላቂ መፍትሔ ቢሆንም ነገሬ የሚሉት ጥቂቶች ብቻ ናቸው፡፡ ሕንፃዎች እንደሚሠሩበት ቁስና መዋቅራዊ መሰካካት፣ ጥንካሬ፣ የሚያርፉበት ሥፍራ፣ መልከዓ ምድራዊ ገጽታ፣ የአየር ፀባይ፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ ምቾትና በሁለንተናዊ አተያይ ይወሰናሉ፡፡ ሳይንሱን ተንተርሰው የሚገነቡ ሕንፃዎችም ዘመን ተሻጋሪ በመሆን ከትውልድ ትውልድ ይተላለፋሉ፡፡

  የኪነ ሕንፃ ንድፍ ሥራና ክትትል ባለሙያና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህሩ  አርክቴክት ብርሃኑ ሙሳ እንደሚሉት አንድ ሕንፃ በውስጡ ቅርፃ ቅርፅ፣ ፀጥታን የተላበሰ ሙዚቃና  የተለያዩ ጥበቦችን ይይዛል፡፡ ይህንንም ሚዛናዊ ለማድረግ የኪነ ሕንፃን መሥፈርቶች መከተል ያስፈልጋል፡፡

  ኪነ ሕንፃ በአመዛኙ ከቅርፃ ቅርፅ ጋር ይቆራኛል፡፡ ሕንፃ ከሚይዘው ቦታ ባሻገር ከቅርፅ በተቃራኒ በውስጡ ልዩ ልዩ ሁነቶች እንዲካሄዱ ዕድል መስጠቱ ሁለቱ የሚለዩበት ገጽታ ነው፡፡

  ሰዎች ኪነ ሕንፃን በአካላዊና በምናባዊ መዋቅሩ ይረዱታል፡፡ ባለሙያው ደግሞ ፈጠራው የግሉ እንደመሆኑ አዕምራዊ ስሜቱን ጨምሮ ይረዳዋል፡፡ ሕንፃ በቅርፅ፣ በሚሠራበት ቁስ እንዲሁም ውስጡ በሚካተቱ የተለያዩ ሥራዎች በሰዎች ሥነ ልቦና ላይ አሉታዊና አዎንታዊ ተፅዕኖ የማሳደር አቅም አለው፡፡  ‹‹ከባድ በሆኑ ድንጋዮች የተሠራ፣ ትንንሽ መስኮት ያሉት፣ የክፍሎቹ ቁመት አጭር የሆነ በውስጡ የሚገለገሉ ሰዎችን ሥነ ልቦና የመጫን ባህሪ አለው፡፡ እስረኛ ያደርጋል፡፡ በአንፃሩ ግን ለስለስ ባሉ ግብዓቶች ሲሠራ፣ ቀለል ባሉ ድንጋዮች ሲገነባ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ብርሃን እንዲገባ ሲደረግ ቀለል ያለ ስሜት ይሰጣል፤›› በማለት ከሚሰጠው አካላዊ አገልግሎት ባሻገር ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር አርክቴክት ብርሃኑ ይናገራሉ፡፡

  ታዋቂው የታጅ መሀል መስጊድ የኪነ ሕንፃ መዋቅር ሥነ ሕንፃ በሰዎች ሥነ ልቦና ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ ዓይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ታጅ መሀል ሁለት ተመሳሳይ ሕንፃዎች አሉት፡፡ አንደኛው ሕንፃ በነጭ እምነ በረድ የተገነባ ሲሆን፣ ሌላኛው በጥቁር እምነበረድ የተዋቀረ ነው፡፡ ይህም ተቃራኒ የሆኑ ስሜቶችን የመፍጠር አቅም እንዲፈጥር በመካከላቸው ባለው ልዩነትም ሰዎች ከሞት በፊትና ከሞት በኋላ ያለውን ተቃራኒ ስሜት እንዲሰማቸው ለማድረግ ነው፡፡

  ሕንፃዎች ከሚሰጡት ተጨባጭ ጥቅም ባሻገር የአንድን ሕዝብ ባህል፣ አምልኮና ጥበብ በማሳየቱ ረገድም ትልቅ ሥፍራ አላቸው፡፡ ለዚህም ወጥነትና ሊኖራቸው ግድ ይላል፡፡ ግንባታቸውም የአንድን ቦታ መልከዓ ምድራዊ ገጽታ፣ የአየር ባህሪና አጠቃላይ የከተማ ሁኔታን መሠረት ማድረግ ይገባዋል፡፡ ነገር ግን በከተማው ውስጥ የሚታዩ ሕንፃዎች መስፈርቶቹን ምን ያህል  እንደሚያሟሉ አርክቴክት ብርሃኑ ሲገልጹ ‹‹አዲስ አበባ በዝብርቅርቅ ሕንፃዎች ዥጉርጉር ሆናለች፤›› ሲሉ ሕንፃዎቹ ምን ያህል ወጥነት የጎደላቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

  በአሁኑ ወቅት የአገሪቱን የአየር ፀባይ ያላማከሉ ወጥነት የጎደላቸው አልሙኒየምና መስታወት የሸፈናቸው ሕንፃዎችን ማየት ተለምዷል፡፡ ብዙዎቹም የነፋስ አቅጣጫን ከግምት ያላስገቡ በዘፈቀደ የተገነቡ ስለመሆናቸው ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት የአብዛኛዎቹ ሕንፃ ዲዛይን ከባህር ማዶ የተኮረጀ መሆኑ የፈጠረው አለመግባባት እንደሆነ ባለሙያዎች ይስማማሉ፡፡ ሁኔታው በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ሥራ ላይም ሆነ በሙያው ዕድገት ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡

  ‹‹በኪነ ሕንፃ ጥበብ የረዥም ዘመናት ታሪክ አለን፡፡ ይህንንም ማሳየት እንፈልጋለን፤›› የሚለው የዲዛይን ኤንድ ቢውልት ድርጅት ዲዛይነር ኢዮብ ሰለሞን የግንባታ ደንቡን ያልተከተሉ ከባህር ማዶ የሚኮረጁ ሕንፃዎች መብዛት የአገሪቱን የኪነ ሕንፃ ጥበብ ከማሳየት እንዳገዳቸው ይናገራል፡፡

  አንድ ሕንፃ ከመሠራቱ በፊት በቦታው ላይ ምን ዓይነት ሕንፃ ቢሠራ ተስማሚ ስለመሆኑ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስዶ የአካባቢ ጥናት ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ከተገነባ በኋላም የሚሰጠው ውጤት፣ ገጽታና ውበት እንዲሁም የትራፊክ እንቅስቃሴ በአካባቢ ጥናት ከሚካተቱ መሥፈርቶች ይጠቀሳሉ፡፡ መሥፈርቶቹ  ወጥነት ላለው ሕንፃ መሠረት ቢሆኑም ጥቅም ላይ የሚውሉበት አጋጣሚ እምብዛም ነው፡፡ በከተማ ውስጥ የሚታዩት ሕንፃዎች በጥናት ላይ ያልተመሠረቱ ከባህር ማዶ የተቀዱ በመሆናቸው ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ናቸው፡፡

  ሕንፃዎች ምክንያታዊ መሆን አለባቸው የሚለው አርክቴክት ኢዮብ ነገሮችን ከግምት ያላስገቡ ሕንፃዎች ከተማዋን እንዳጨናነቁ ይናገራል፡፡ ከባህር ማዶ ከሚኮረጁ ዲዛይኖች ባሻገር በባለሙያዎች እምነት ማጣት ሕንፃው ከሚኖረው የኪነ ሕንፃ አወቃቀር ሥርዓት በተለየ አንድ ቦታ ከሚኖረው የገንዘብ ጥቅም አንፃር ቦታ ለመቆጠብ ሲባል ቅርፁን መወሰን የኪነ ሕንፃን መሥፈርት ያላሟሉ ሕንፃዎች መብዛት ምክንያት ይጠቀሳል፡፡

  ሁኔታው በአርክቴክቱ የሙያ ነፃነት ላይ ጫና እየፈጠረ ይገኛል፡፡ ‹‹አንድ ባለሙያ የተለያዩ ወጪዎች አሉበት፡፡ እነሱን ለመሸፈን ደንበኛው ያመጣውን ሐሳብ አሜን ብሎ መቀበል ግድ ይላል፡፡ ወይም ደንበኛው ሌላ ባለሙያ ጋር ስለሚሄድ ተጎጂ ይሆናል፤›› በማለት የሚመጣውን የዲዛን ሐሳብ ለመቀበል እንደሚገደዱ ይህም በሙያው አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ አቶ ኢዮብ አልሸሸገም፡፡

  አልፎ አልፎ ሙያዊ ነፃነት የሚሰጡ ደንበኞች የሚያጋጥሙት ቢሆንም ደረጃውን የጠበቀ ዲዛይን ለመሥራት በቂ ጊዜ ስለማይሰጡ ውጤቱ አርኪ አይሆንም፡፡ ‹‹አንድ ጥሩ ዲዛይን ለመሥራት ዓመታት ሊፈጅ ይችላል፡፡ እኛ ጋር ግን ሁሉንም ሕንፃ ዲዛይን በሁለት ወር እንድናደርስ እንታዘዛለን፤›› በማለት የሚሰጠው ምክንያታዊ ያልሆነ ጊዜ በዲዛይን ጥራት ላይ ተፅዕኖ እንደሚፈጥርም ይናገራል፡፡ አልፎ አልፎ የሚታዩ ኪነ ሕንፃ ያስቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉ ሕንፃዎች ቢያጋጥሙም የፓርኪንግ ቦታን ሳያሟሉ የሚቀሩ ይሆናሉ፡፡ በተቀናጀ አወቃቀራቸው በምሳሌነት የሚጠቀሱ ግን አይጠፉም፡፡

  ለዲዛይን የሚሆን በቂ ጊዜ በመስጠቱ ረገድ የመንግሥት ፕሮጀክቶች የተሻሉ መሆናቸውን የሚናገረው የቴልዳ ኮንሰልት ድርጅት ማኔጀርና ስትራክቸራል ኢንጅነር አቶ ዳዊት ታምራት ነው፡፡ ለሙያዊ ድጋፍ ወደ ተቋሙ ከሚመጡ ደንበኞች መካከል የመንግሥት ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡ ምክንያታዊ የሆነ የዲዛይን ጊዜ የሚያገኙትም በዚሁ አጋጣሚ ብቻ ነው፡፡

  በግል የሚመጡ ደንበኞች ከሚሰጡት አጭር የዲዛይን ጊዜ ባሻገር 90 በመቶ የሚሆኑት ቦታ ለመቆጠብ ሲሉ የዲዛይነሩን ነፃነት ይጫናሉ፡፡ ከቦታው ይልቅ ለሕንፃው ውበት ቦታ የሚሰጡ ሰዎች አልፎ አልፎ ቢያጋጥሙም የራሳቸው ዲዛይን በማምጣት የሚያሠሩ ይበዛሉ፡፡

  ቀደም በወረቀት ላይ የሰፈረውን ዲዛይን ለመረዳት የሚቸገሩ አንዳንድ ደንበኞች ያጋጥሙ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ አጠቃላይ የሕንፃውን ገጽታ በአኒሜሽን በማዘጋጀት እንዲረዱት ማድረግ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ውበቱን አድንቆ ከማለፍ ባለፈ ቦታ ለመቆጠብ የሚደረገውን ትንቅንቅ አላስቀረም፡፡ ከቦታ ጋር የሚነሱ ችግሮች በብዛት የሚስተዋሉትም ለቢሮ የሚውሉ ሕንፃዎችን በሚገነቡበት ወቅት መሆኑን ከአማካሪ ድርጅቱ ተሞክሮ መረዳት ይቻላል፡፡

  ሙያው እንደሌሎች የሙያ ዘርፎች ትኩረት አላገኘም፡፡ ብዙዎቹ ደንበኞችም እንደቀልድ ስለሚወስዱት ተገቢውን ክፍያ ለመክፈል ያቅማማሉ፡፡ አልፎ አልፎም ተሠርተው ያለቁ ዲዛይኖች ከዓመታት በኋላ መልሰው የሚያመጡና ‹‹ይህቺን አስተካክልልኝ›› የሚሉ ደንበኞች መኖራቸውን አቶ ዳዊት በምሬት ይናገራል፡፡

  በሙያው ተገቢውን ትምህርት ያልወሰዱ ነገር ግን በልምድ የሚሠሩ ዲዛይነሮች ዘንድ ማሠራት የሚመርጡም አሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ባለሀብቶች ወደ ዲዛይነር ጋር የሚሄዱት የግንባታ ፈቃድ ያለ ዲዛይን ማግኘት ስለማይችሉ ሳይወዱ በግዳቸው እንደሆነ ገጠመኞቻውን ተንተርሰው የሚናሩ ባለሙያዎች አሉ፡፡

  ዲዛይኑና የተሠራው ሕንፃ ፍፁም ተቃራኒ ሆኖ የሚገኝበት አጋጣሚም አለ፡፡ ተመሳሳይ ገጠመኞችን ካስተናገዱ መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአርክቴክቸር ኤንድ ዲዛይን ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ዘገየ ቸርነት ይገኙበታል፡፡ በሥነ ሕንፃና በከተማ ዲዛይን ለዓመታት አስተምረዋል፡፡ የራሳቸውን ቢሮ ከፍተው መንቀሳቀስ ከጀመሩም ቀይተዋል፡፡ ግንባታዎችን በጥናት የተደገፉ ለማድረግ በየጊዜው የተለያዩ ጥናቶች ይሠራሉ፡፡

  ‹‹በአገሪቱ የኪነ ሕንፃ ዕድገት ገና ልጅ ነው፤›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ጥናቶቹን በተግባር ላይ ለማዋል ግን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ እንደሚቸገሩ ይናገራሉ፡፡ ብዙዎቹ ባለሀብቶች ጥናት ላይ የተመሠረተ ሕንፃ የማሠራት ልምዱ የላቸውም፡፡ አልፎ አልፎ ዲዛይን ያደረጓቸው ሕንፃዎችም ግንባታቸው ሲጠናቀቅ የተለየ ገጽታ ይዘው ከሠሩት ዲዛይን ጋር ተዛምዶ የሌላቸው ሆነው አይተዋል፡፡

   ‹‹ከሠራሁት የተለየ ሆነው ያገኘኋቸው ሕንፃዎች አሉ፡፡ በጣም ያሳፍሩኛል፡፡ ባጠገባቸው ላለማለፍ መንገድ አሳብሬ እሄዳለሁ፤›› በማለት እጀ ሰባራ ባደረጓቸው ሥራዎች የሚሰማቸውን ይናገራሉ፡፡ አጋጣሚው የባለቤትነት መብት ጥያቄ እንደሚያስነሳ ቢያውቁም በሁኔታው ከመበሳጨት ባለፈ ጉዳዩን ለፍርድ አቅርበው አያውቁም፡፡

  ‹‹ኪነ ሕንፃ ግዙፍና የማይታለፍ ጥበብ ነው፡፡ በመሆኑም ከውበት ባሻገር ከሚገነባበት አካባቢና የከተማ ሁኔታ አንፃር ሊታሰብበትና በጥንቃቄ ሊገነባ ግድ ይላል፤›› በማለት አንፃራዊ የሆነ ግንባታ ለሁለንተናዊ የከተማ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

  በአዲስ አበባ የሚገኙ ሕንፃዎች ይዘት ከሙያው አንፃር ሲገመገም መቃወስ ይታይበታል፡፡ ይኽም እንደዚሁ የሚታለፍ ሳይሆን ዋጋ እንደሚያስከፍል ‹‹አዲስ አበባ በአሁን ሰዓት በሕንፃ ግንባታ የሙከራ ጊዜ ላይ ትገኛለች፡፡ ሙከራው ሲበቃ ግን እንደገና አፍርሶ ለመሥራት እንገደዳለን፡፡ በዚህም በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ይፈሳል፤›› በማለት አርክቴክት ብርሃኑ ሳይታለም የተሠራው ሥራ ሊያስከፍል ስለሚችለው ዋጋ ያብራራሉ፡፡

  በአሁኑ ወቅት የአርክቴክቶቹ ንድፎች ከወረቀት ላይ ማለፍ አልቻሉም፡፡ ሁኔታው ተገቢውን ትኩረት ካላገኘ የተከማዎች ዕጣ ፈንታ ‹‹ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ›› እንዲሉ መገንባትና ማፍረስ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

     

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img