Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል​አገራዊው ቴሌቪዥን በኢዮቤልዩው ማግስት

​አገራዊው ቴሌቪዥን በኢዮቤልዩው ማግስት

ቀን:

‹‹ለሕዝባችን በበለጠ ትምህርትና ዕውቀት ለማካፈል የሚችልበትን ዘዴ በመሻት ለምናደርገው ጥረት ቴሌቪዥን ተጨማሪ መሣሪያ ስለሚሆን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መርቀን ስንከፍት ደስ ይለናል፤ ትምህርት ለወጣቶችና ለሕፃናት ብቻ ሳይሆን ለሸመገሉም ነው፡፡ የቴሌቪዥን ጣቢያ አገልግሎቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አነስተኛ ቢሆንም ወደፊት ድርጅቱ ተስፋፍቶ የሚሰጠው ጥቅም መላውን ሕዝባችንን እንደሚያደርስ ተስፋ አለን፡፡ ካልተጀመረ አይጨረስም!››

ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በንጉሠ ነገሥትነታቸው ዘመን (1923-1967) ከ51 ዓመት በፊት ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያን መርቀው ከከፈቱ በኋላ የተናገሩት ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ መደበኛ ሥርጭቱን ጀምሮበታል፡፡

ኢትዮጵያ ከቴሌቪዥን ጋር መተዋወቅ የጀመረችው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ 25ኛው የንግሥና በዓል በማስመልከት በተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ አማካይነት እንደነበር ታሪክ ያመለክታል፡፡

በጥቅምት 1948 ዓ.ም. የቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የዘውድ በዓልን አስመልክቶ በአሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ (ብስራተ ገብርኤል) አካባቢ ተዘጋጅቶ በነበረው ኤግዚቢሽን ላይ ቢቢሲ ያቀረበው የቴሌቪዥን ትርዒት እንደ በኩር ሙከራ ይወሰዳል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሲኒማ ጥበብ ሲተዋወቅ ሕዝቡ የሰጠው ምላሽ ለቴሌቪዥንም ተደግሟል፡፡ ‹‹የሰይጣን ሥራ ነው›› ብሎታል፡፡

በቀጣይም ደጃዝማች ዳንኤል አበበ የተባሉ ባላባት የቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም በ1952 ዓ.ም. ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥያቄ ቢያቀርቡም፣ በግለሰብ ደረጃ ለማቋቋም አልተፈቀደላቸውም፡፡ ከዛ በኋላ ብስራተ ወንጌል ሬዲዮና የቴሌኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ጨምሮ የቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም የጠየቁ ተቋሞች አልተሳካላቸውም፡፡

በመጨረሻ ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም. ምሽት ላይ በንጉሠ ነገሥቱ የተመረቀውና በ247,000 ብር የተቋቋመው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሥርጭቱን የጀመረው በፊሊፕስ ኢትዮጵያና ቶምሰን ቴሌቪዥን ኢንተርናሽናል አማካይነት ነበር፡፡ ጣቢያው በብዙ ውጣ ውረዶች አልፎ ዘንድሮ በ51ኛው ዓመት ላይ 50 ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩውን (ከጥር አጋማሽ ጀምሮ        ) በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እያከበረ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሕንፃ አራተኛ ፎቅ ላይ በ27 ኢትዮጵያውያንና አምስት እንግሊዛውያን ሠራተኞች ሥራውን ሲጀምር የሥርጭት ጊዜው ከ40 ደቂቃ ያልበለጠ 80 በመቶ የሚሆነው የሥርጭት ሰዓት የሚሸፈነው ደግሞ በውጪ ፊልሞች መሆኑ ድርሳናቱ ያመለክታሉ፡፡

በአነስተኛ ስቱዲዮ፣ በጥቂት መሣሪያ ሥራ የጀመረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሚያስተላልፋቸው መርሐ ግብሮች ጥያቄና መልስ፣ ኅብረ ትርኢትና ውይይት ይጠቀሳሉ፡፡ ጣቢያው በመሣሪያ፣ በአቀራረብና በሙያተኞች ብቃት እየተሻሻለ እንደመጣ ያገኘናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የአገር ውስጥ ዝግጅቶች እየጨመሩ፣ በአገሪቱ ያሉ የሥርጭት ቦታዎች እየሰፉ ከመምጣታቸው ባሻገር ባለቀለም ምስል በ1977 ዓ.ም. ተጀመረ፡፡

የወርቅ ኢዮቤልዩውን በማስመልከት በኦሮሞ ባህል ማዕከል የተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ጥናት ያቀረቡት አቶ መኩሪያ መካሻ፣ ጣቢያው በፓን አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው አመልክተዋል፡፡ የድርጅቱ 50ኛ ዓመት መሪ ቃልም ‹‹ፓን አፍሪካኒዝምን ያቀነቀነ የመጀመሪያው ሚዲያ›› የሚል ነው፡፡ ጣቢያው ከ1966-1983 ዓ.ም. ለልዩ ልዩ ፕሮፓጋንዳ ማሠራጫ ይውል እንደነበር ጥናታቸው ያሳያል፡፡ የ1977 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ረሀብ ለማጋለጥ የነበረውን ሚና ጠቅሰዋል፡፡ በወቅቱ ቅድመ ምርመራ ያደርስ የነበረውን ጫናና ሙያዊ ሥራዎች ለማቅረብ የነበረውን ፈተና ተናግረዋል፡፡

‹‹ዓይናችን››፣ ‹‹ዐውደ ሰብ›› እና ‹‹ስኬት›› ተወዳጅ ዝግጅቶች ነበሩ፡፡ በተለይ ‹‹ዓይናችን›› የመልካም አስተዳደር እጦትና የሚታዩ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የሚታወቅ መርሐ ግብር ሲሆን፣ በፓናል ውይይቱ ላይ መቋረጥ አልነበረበትም የሚል አስተያየት የሰነዘሩ ነበሩ፡፡ በ1990 ዓ.ም. ኢቲቪ 2፣ በ2003 ዓ.ም. ደግሞ ኢቲቪ 3 ተከፈቱ፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቲቪ) የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢብኮ) ሆኖ ከድርጅትነት ወደ ኮርፖሬሽንነት የተቀየረው በ2006 ዓ.ም. ሲሆን፣ የጣቢያው ኤዲቶሪያል ፖሊሲ የወጣውም በዚያው ዓመት ነው፡፡ ኢብኮ አሁን 74 ማሠራጫ ጣቢያዎች በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ያሉት ሲሆን፣ አገራዊ ሽፋኑ 86 በመቶ እንደደረሰ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ሌላው ጥናት አቅራቢ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ፣ ጣቢያው በፌዴራሊዝም መምጣት፣ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነትና በሌሎችም አገራዊ ጉዳዮች የነበረውን ሚና ‹‹እንደ ትምህርት ቤት ነበር›› በማለት ገልጸውታል፡፡ የጣቢያው አቋም በብዙዎች እይታ በአሉታዊ መንገድ እንደሚያስፈርጀው ጥናታቸው ያሳያል፡፡ እሳቸው ግን ‹‹ጣቢያው እውነትን ግብአት አድርጎ የሚያቀርብ፣ የገጽታ ግንባታ የሚሠራና እኩልነትን የሚያሳይ ሥራ ሠርቷል፤›› ብለዋል፡፡

ጣቢያው ላይ የሚቀርቡ ትችቶችንም ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት ላይ የሰላ ትችት አለማቅረቡ፣ ፈጠራ የተሞላባቸውና የሚስቡ ዝግጅቶች አለመኖራቸው፣ ‹‹የብዝኃነት ድምፅ›› ቢባልም የሙያ፣ የብሔር፣ የሃይማኖትና የጾታ ስብጥር በሙያተኞቹ አለመታየቱ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ዶ/ር ነገሪ በበኩላቸው፣ በጣቢያው ያሉ ክፍተቶችን ለማሻሻል እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጣቢያው ተስፋ የሚጣልበት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ድምፅ ለመሆን መሥራት እንዳለበት በጥናታቸው መደምደሚያ አስቀምጠዋል፡፡

በውይይቱ ላይ አስተያየታቸውን ከሰነዘሩ ግለሰቦች መካከል ጣቢያው ማደግ የሚገባውን ያህል አለማደጉንና በአስተዳደር ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለሕዝቡ በማቅረብ ረገድ ያለውን ክፍተት የተቹ ነበሩ፡፡ በኢዮቤልዩው፣ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በሥራ ላይ ሳሉ ሕይወታቸውን ላጡ የጣቢያው ባለሙያዎች መታሰቢያ ተደርጓል፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ግን ሕይወታቸውን ያጡት ባለሙያዎች በአጠቃላይ እንዳልተገለጹ ተችተዋል፡፡

በዓሉ በተከበረበት የኦሮሞ ባህል ማዕከል ለሳምንት የዘለቀ ዐውደ ርዕይ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ጣቢያው ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የነበሩ ባለሙያዎችና የተለያዩ የቀረጻ መሣሪያዎች ለእይታ ቀርበዋል፡፡ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡ ጎብኚዎች ዐውደ ርዕዩ የወርቅ ኢዮቤልዩን ጥቅል ጉዞ የማያሳይ ክፍተቶች ጎልተው የሚታዩበት እንደሆነ፤ ምስላቸው መካተት የነበረባቸው ነገር ግን የተዘለሉ የጣቢያው ባለሙያዎች መኖራቸው ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህም ከመጀመሪያዎቹ ዜና አንባቢዎች አንዷ የነበረችው ሮማንወርቅ ካሳሁን እንዲሁም ‹‹ከማጀት እስከ አደባባይ›› ፕሮግራም አዘጋጅ የነበረችወ  ብዙ ወንድምአገኘሁ፣ ህሊና ተረፈና ሰለሞን ክፍሌን ይጠቅሳሉ፡፡     

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...