የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አዲስ አበባን ጨምሮ ከሚገኙበት አካባቢ ውጭ የርቀት ትምህርት እንዳይሰጡ መመሪያ መተላለፉን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ለሪፖርተር አስታውቋል፡፡
ይህ ከትምህርት ሚኒስቴር የወረደው መመሪያ በኤጀንሲው በኩል ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ እንዲተላለፍ የተደረገው በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ሲሆን፣ መመሪያው ከአካባቢያቸው ውጭ በርቀት ትምህርት (በመጀመሪያ ዲግሪ መርሐ ግብር ዘንድሮ ምንም ዓይነት አዲስ ተማሪ እንዳይቀበሉ ያሳስባል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት አግባባነትና ጥራት ኤጀንሲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ገረሡ እንደገለጹት፣ እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ዩኒቨርሲቲዎቹ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የርቀት ትምህርት በመስጠት ትርፍ ተኮር እንዳይሆኑና ይህ ደግሞ በመደበኛው ትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ሥጋት በመፈጠሩ ነው፡፡
ምንም እንኳ የትምህርት ተቋማቱ ከአካባቢያቸው ውጭ ዘንድሮ በርቀት ትምህርት አዲስ ተማሪ እንዳይቀበሉ መመሪያው ከወራት በፊት የተላለፈ ቢሆንም፣ አዲስ አበባ ውስጥ በ2008 ዓ.ም. አዲስ ተማሪ የተቀበሉ ዩኒቨርሲቲዎች መኖራቸውን የሚጠቁሙ ማስረጃዎች አሉ፡፡
አብዛኛውን ጊዜ የቢሮዎች የተደራጁ አለመሆንና ለተማሪዎች እንደ አስፈላጊነቱ ተደራሽ አለመሆን ከርቀት ትምህርት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ የሚነሡ ችግሮች ናቸው፡፡ በ2003 ዓ.ም. በኤጀንሲው በተደረገ አጠቃላይ ግምገማ ስድስት ከፍተኛ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት አዲስ አበባ ውስጥ የርቀት ትምህርት እንዳይሰጡ መደረጋቸውን አቶ ታረቀኝ ያስታውሳሉ፡፡ በተመሳሳይ ዕርምጃ የተወሰደባቸው የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም ነበሩ፡፡ በወቅቱ የተደረገውን ግምገማ ተከትሎ ቀደም ሲል የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የኤጀንሲው ዕውቅና ሳያስፈልጋቸው የርቀት ትምህርት የሚሰጡበት አሠራር ተቀይሮ በመጀመሪያ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው የኤጀንሲውን ፈቃድ ይዘው ወደሥራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
አርባ ምንጭ፣ ባህርዳር፣ ሀሮማያና ጅማ አዲስ አበባ ውስጥ የርቀት ትምህርት ሲሰጡ የነበሩ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሆኑ፣ መመሪያው እነዚህን ጨምሮ ለሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ተላልፏል፡፡
በሌላ በኩል የርቀት ትምህርት አገልግሎት በሚሰጡ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይም የተለያዩ ችግሮች የሚስተዋሉ ሲሆን፣ እነዚህን ተቋማት ለመቆጣጠር ድጋፍ ለማድረግም የክልል ማዕከላትን ለማቋቋም እየተሠራ እንደሆነ አቶ ታረቀኝ ገልጸዋል፡፡
ዘንድሮ መግቢያ ላይ የኤጀንሲው ሠራተኞች፣ የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በተገኙበት ውይይት ማካሄዳቸውና የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲን ለረዥም ጊዜ ያገለገሉት ዶ/ር ተስፋዬ ተሾመ ከኅዳር 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸው ይታወሳል፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የርቀትና ተከታታይ ትምህርት ፕሮግራም ዳይሬክተር የነበሩት ዶ/ር ተስፋዬ ሙህዬ ደግሞ ከጥር 26 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ኤጀንሲውን ለመምራት ኃላፊነት መረከባቸውን ኤጀንሲው ለሪፖርተር አረጋግጧል፡፡