Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​ብዙዎች የማይመርጡት ፈውስ

​ብዙዎች የማይመርጡት ፈውስ

ቀን:

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ ከሚታወቁ ዝነኛ ሰዎች ተቀዳሚው ናቸው፡፡ አገርን መምራት፣ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች መሳተፍ፣ ቤተሰብን ማስተዳደርና ሌሎችም ብዙ ኃላፊነቶች የተደራረቡባቸው ፕሬዚዳንቱ፣ ባሉበት ቦታ ሆነው ዘወትር ስፖርት እንደሚሠሩ በርካታ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

ኦባማ በዋይት ሐውስ ውስጥ፣ ለእረፍት ወይም ለሥራ ወደተለያዩ አገሮች ሲጓዙም ስፖርት ለመሥራት ጊዜ አያጡም፡፡ የተለያዩ ስፖርታዊ ጨዋታዎችንም ያዘወትራሉ፡፡ በአንድ ወቅት ዘ ጋርዲያን በአንድ ጂም ውስጥ ክብደት ሲያነሱ የሚያሳይ ቪዲዮ ለቆ ነበር፡፡ የፕሬዚዳንቱ የስፖርትና አመጋገብ እቅድን እንደ መመሪያ ካቀረቡ ድረ ገጾች ኸልዚ ሰለብ (Healthy Selb) ይጠቀሳል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ባለቤት ሚሼል ኦባማም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማዘውተር ይጠቀሳሉ፡፡ ሐፊንግተን ፖስትም በባልና ሚስቱ መካከል ስለሚደረጉ ስፖርታዊ ውድድሮች ዘግቧል፡፡

ከኦባማ በበለጠ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚታወቁት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ናቸው፡፡ ስድስተኛ ዳን ያላቸው ፕሬዚዳንቱ፣ የጁዶና ሳምቦ ማስተርም ናቸው፡፡ በዓለማችን ላይ እጅግ የተጣበበ ጊዜ ካላቸውና በሥራ ከሚወጠሩ ሰዎች በቀዳሚነት የሚጠቀሱት እኚህ ሰዎች፣ ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ፡፡ ጊዜም አያጡም፡፡

በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በእኛ አገር የነበረ ቡድን ነው፡፡ አባላቱ አውሮፕላን አብራሪዎች ሲሆኑ፣ ቦሌ መንገድ ላይ ሰብሰብ ብለው የእግር ጉዞ ያደርጉ ነበር፡፡ ቡድኑ ከዓመታት በፊት ‹‹ልወዝወዘው በእግሬ›› በሚል መጠሪያ ይታወቅ ነበር፡፡ ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የሚታወሱት የ‹‹ልወዝወዘው በእግሬ›› አባላት ዛሬ ባይታዩም፣ በቡድን ተመሳሳይ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎች አሁንም ይስተዋላሉ፡፡

ከቀናት በፊት ቅዳሜ ንጋት ሰባ ደረጃ አካባቢ ነው፡፡ ወደ ደረጃው በሚወስደው አስፋልት የስፖርት ትጥቅ ለብሰው ዱብ ዱብ የሚሉ ጎልማሶች ይታያሉ፡፡ ከወገባቸው ዝቅ እያሉ ወደ ግራና ቀኝ እየተወዛወዙ ሰውነታቸውን ያፍታታሉ፡፡ ከመካከላቸው ሰባ ደረጃን የሚወጡና የሚወርዱም አሉ፡፡ በተመሳሳይ ሰዓት ጃንሜዳ ወይም መስቀል አደባባይ አካባቢ ወጣቶች ጎልማሶችም በተናጠልና በቡድን ስፖርት እንደሚሠሩ ይታወቃል፡፡ መስቀል አደባባይ እግር ኳስ የሚጫወቱ፣ ደረጃ እየወጡ ከአንድ ጥግ እስከ ሌላው የሚሮጡ፣ ገመድ የሚዘሉ፣ ብረት ላይ እየተንጠላጠሉ ፑል አፕ የሚሠሩ፣ መሬት ላይ ፑሽ አፕ ወይም ሲት አፕ የሚሠሩ ብዙዎች ናቸው፡፡

እንደ ሰባ ደረጃና መስቀል አደባባይ ያሉ አካባቢዎች መሄድ ሳይጠበቅባቸው፣ ቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፉ የአካል ብቃት እንቅሰቃሴዎችን በመከታተል ስፖርት መሥራት የሚመርጡም አይታጡም፡፡ ወደ ጂምናዚየም (ጂም) የሚያመሩም አሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በየቦታው ጂሞች እየተከፈቱ ነው፡፡ የተጠቃሚዎቻቸው ቁጥርም እንደዚሁ እየጨመረ ነው፡፡ ከቀበሌ አዳራሾች እስከ ኮንዶሚኒየም ግቢና ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች ድረስ አገልግሎቱ ይሰጣል፡፡

ክብደት ለመቀነስ፣ ቅርፅን ለማስተካከል፣ በሽታን ለመከላከልና የጤና እክል ከገጠመ በኋላ በሰውነት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ፊታቸውን ወደ ስፖርት ያዞሩ ቢኖሩም፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን የሕይወታቸው አካል ያላደረጉ በርካቶች ናቸው፡፡ ባለንበት ክፍለ ዘመን የከተሜነት መስፋፋት (ኧርባናይዜሽን) ተከትሎ የመጣው የአኗኗር ዘይቤ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግድ እየሆነ መመጣቱን የሚናገሩ ነገሮችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እየተለመዱ የመጡት ፈጣን ምግቦች (ፋስት ፉድ) ብዙዎችን ለበሽታ በሚያጋልጡበት እንዲሁም ተላላፊ ያልሆኑ እንደ ልብ፣ ስኳርና ካንሰር ያሉ በሽታዎችም የብዙዎችን ሕይወት በሚቀጥፉበት በዚህ ወቅት ስፖርት መሥራት የማያወላዳ መፍትሄ እንደሆነ የሕክምና ባለሙያዎችም ይናገራሉ፡፡

ወደ ጂም ማምራት ወይም በቴሌቪዥን የስፖርት መርሐ ግብሮችን  መከታተል ብቸኛ አማራጮች ናቸው ብሎ መደምደም ግን አይቻልም፡፡ በየቀኑ ለተወሰነ ሰዓት የእግር ጉዞ ማድረግን በመሰሉ መንገዶችም ጤናን መጠበቅ ይቻላል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ የአኗኗር ዘዬ ስንቶች የአካል ብቃት እንቅስቃሴን አስፈላጊነት ተገንዝበው የሕይወታቸው ክፍል ያደርጉታል? የሚለው ጥያቄ ይሆናል፡፡ የበርካቶች ኑሮ በሥራ፣ በትምህርትና በሌሎች ጉዳዮች የተወጠረ በመሆኑ ደቂቃዎች ከመቼውም በላይ ውድ ናቸው፡፡ ስለዚህም አጭርም ይሁን ረዥም ርቀት ለመሄድ ትራንስፖርት መጠቀም ይመረጣል፡፡ ካላቸው የጊዜ ጥበት አንፃር አንድ ፌርማታ እንኳን በእግራቸው የማይሄዱ፣ በቀን ከመኪናቸው ወጥተው 20 ሜትር እንኳን በእግር የማይንቀሳቀሱ ሰዎች ቁጥር ብዙ ነው፡፡ ስፖርት መሥራትን እንደ ቅንጦት የሚመለከቱም አይታጡም፡፡

የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አንድ ሰው ያለበትን የሰውነትና የጤና ሁኔታ ከግምት በማስገባት በተለያዩ መንገዶች ይከናወናል፡፡ ጤናማ ለመሆን፣ አዕምሮን ማፍታታትና ሥራን በተሻለ ብቃት ማከናወን በተደጋጋሚ የሚጠቀሱት ጥቅሞቹ ናቸው፡፡ የተለያየ የሰውነት ክፍል ላይ ትኩረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎች ከአመጋገብ ሥርዓት (ዳይት) ጋር በሐኪም ወይም የስፖርት ኢንስትራክተር አማካሪነት ይከናወናሉ፡፡

ሩጫ፣ ዋናና ክብደት ማንሳት ከሚዘወተሩ እንቅስቃሴዎች ጥቂቱ ናቸው፡፡ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ማለትም ደም ብዛት፣ ደም ግፊት፣ ከነርቭ ጋር የተያያዙ በሽታዎችና ስኳርን ለመከላከልና ከተከሰቱ በኋላም ጉዳታቸውን ለመቀነስ ስፖርት ይመከራል፡፡ በጡትና ሳንባ ካንሰር የመያዘ ዕድልን ዝቅ ለማድረግም የስፖርትን ፍቱንነት የሚያመላክቱ ጥናቶች አሉ፡፡ የኮሌስትሮል መጠንን ለመቀነስ፣ ለአጥንትና መገጣጣሚያ ጥንካሬ፣ ለረዥም ዕድሜና ለተስተካከል አቋም ያለው ጠቀሜታም ቀላል አይደለም፡፡

ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስለ ስፖርት ያለው ግንዛቤ አድጎ ብዙዎች እንቅስቃሴን የሕይወታቸው አካል እያደረጉ ቢሆንም አሁንም በቂ አይደለም፡፡ በርካቶች የሕይወትና የሞት አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ ብቻ ስፖርት መሥራት ሲጀምሩ ይስተዋላል፡፡ ተሞክሯቸውን ያካፈሉን የ45 ዓመቱ አቶ ብርሃኑ ሁምኔሳ፣ ስፖርት መሥራት የጀመሩት ደም ብዛት እንዳለባቸው በሐኪም ከተነገራቸው በኋላ ነው፡፡ በንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ ብርሃኑ፣ ሕይወታቸው ባጠቃላይ በሩጫ የተሞላ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

በፊት ጂም ገብቶ ስፖርት የመሥራትን ነገር አስበውት እንደማያውቁ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ለልጆቼ ቅሪት የሚሆን ነገር ለማስቀመጥ ላይ ታች ስል ራሴን ዘንግቼ ነበር፤›› ይላሉ፡፡ አሁን አመጋገባቸውን ከማስተካከል በላይ፣ ስፖርት ይሠራሉ የእግር ጉዞም ያደርጋሉ፡፡ በተመሳሳይ ሥራ የተሰማሩ ጓደኞቻቸውንም እንደሚመክሩ ይናገራሉ፡፡ ብዙዎች ስፖርትን ጊዜ ከተትረፈረፋቸው ሰዎች ጋር እንደሚያያይዙትና እውነታው ግን ለጤናው የሚሆን ጊዜ የሌለው ሰው አለመኖሩ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

የ27 ዓመቷ ኬብሮን ዳዊት ጂም የገባችው ክብደቷ ስለጨመረ ነበር፡፡ ጠዋት መሥሪያ ቤት የምትገባበት ሰዓት ሲረፍድባት ማታም እንደ ልቧ አልመች ሲላት ስፖርቱን አቋረጠች፡፡ ጠዋት ለጥቂት ደቂቃዎች መሮጥና ኢንተርኔት ላይ ያሉ የስፖርት ቪዲዮዎችን እየተመለከተች በሚመቻት ሰዓት መሥራትን መርጣለች፡፡

ስፖርት የምትሠራው ለመቀነስ እንጂ የጤናዋ ሁኔታ እስከዚህም አሳስቧት እንደማያውቅ ትናገራለች፡፡ ‹‹ክብደትን መቀነስ ማለት በተዘዋዋሪ ጤናን መጠበቅ ነው፡፡ ቢሆንም በእኔ ዕድሜ የብዙዎቹ ፍላጎት የሰውነት ቅርፅን ማስተካከል ነው፤›› ትላለች፡፡

አንድ ወጣት በየቀኑ በጠዋት ብረት እንደሚገፋ፣ ፑሽ አፕ እንደሚሠራና ማር በሎሚ በጥብጦ እንደሚጠጣ ገልጾልናል፡፡ ከዕድሜ መጨመር ጋር ተያይዞ የሚመጣ በሽታን ለመከላከል በሚል ጠዋትና ማታ የእግር ጉዞ የሚያደርጉ ሴት ወይዘሮና የስፖርት ማሽን ገዝተው ቤታቸው ስፖርት የሚሠሩ ጥንዶችም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በጥሩ አቋም ላይ ስለሚገኝ ስፖርት እንደማያሻው የገለጸልን ወጣትም አለ፡፡ በቢራና በድራፍት የመጣ ቦርጭን አጥፍቶ የተስተካከለ ሆድ (ሲክስ ፓክ) ከማውጣት በዘለለ ስፖርት እንደማይሠሩ የገለጹልንም ነበሩ፡፡

የጂምና የውኃ ዋና ኢንስትራክተር ደሳለኝ ባየ፣ ባላቸው አቅምና በአካባቢያቸው ባለው ግብዓት ስፖርት የሚሠሩ ሰዎች ቁጥር ቢጨምርም፣ አቅም እያላቸው የማይንቀሳቀሱ ብዙ ናቸው ይላል፡፡ ገዳይ (ሳይለንት ኪለር) የሚባሉት እንደ ደም ግፊትና ስኳር ያሉ በሽታዎች ቢስፋፉም አኗኗራቸውን ለመለወጥ የወሰኑ ጥቂት ናቸው፡፡ አላስፈላጊ የሆነ ውፍረት በተለይም በሕፃናት መታየቱ አንድ ምሳሌ ነው፡፡

‹‹በቀን ለተወሰኑ ደቂቃዎች እንቅስቅሴ ማድረግ ያለው ጠቀሜታ በማኅበረሰቡ ገና አልሰረጸም፤›› ይላል አቶ ደሳለኝ፡፡ ሰዎች የሚያገኙትን ገንዘብና የሚገነቡትን ሕይወት ለማጣጣም ረዥም ዕድሜ የሚያገኙት በስፖርት ሆኖ ሳለ ችላ መባሉ አግባብ አለመሆኑን ያስረዳል፡፡

አንዳንዶች ስፖርት ለአጭር ጊዜ ሠርተው ይተዋሉ፡፡ እሱ እንደሚናገረው፣ ለሠርግ፣ ወይም ለሆስተሲንግ ፈተና ብለው በጥቂት ቀናት ክብደት ለመቀነስ ወደሱ የሚያመሩ አሉ፡፡ ‹‹ለዓመታት የተከማቸ ውፍረት በቀናት አይወገድም፤ ሰው ሕይወቱን በሙሉ በተስተካከለ አቋም ለመኖር መሥራት አለበት፤›› ይላል፡፡

ሌላው በተለያዩ ነገሮች እየተወጠሩ ለእንቅስቃሴ ጊዜ አለመመደብ ነው፡፡ ኢንስትራክተሩ ቀደም ባሉ ጊዜያት ሰዎች በእግር የመጓዝ ልማድ ስላላቸው ሳያውቁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ያደርጉ ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ መንገዶች የተጨናነቁ ከመሆናቸው በላይ ደኅንነቱን የጠበቀ የእግረኛ መንገድ ባለማግኘትም በእግር የሚጓዙ ጥቂት ናቸው፡፡ ከተማ ቀመስ አካባቢዎች የሚታየውን የጤና እክልና የክብደት መጨመር ችግር ገጠራማ አካባቢዎች ካለው የተስተካከለ አቋም ጋር ያነጻጽረዋል፡፡

በሌላ በኩል እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሰዎችም ጥንቃቄ መውሰድ እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ ለምሳሌ እንደ ሰባ ደረጃ ወይም መስቀል አደባባይ ባሉ አካባቢዎች ያለ አሠልጣኝ ስፖርት የሚሠሩ ሰዎች፣ የሚያከናውኗቸው እንቅስቃሴዎች ስላላቸው ተፅዕኖና ጠቀሜታ ሳይገነዘቡ ከሠሩ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ የሕክምናና ስፖርት ባለሙያዎችን በማማከር ከዕድሜ፣ ከጤና ሁኔታና ከሰውነት አቋም አንፃር መንቀሳቀስ ተገቢ መሆኑንም ያሳስባል፡፡

ከጎበኘናቸው ጂሞች የአራት ኪሎው የአዲስ አበባ ስፖርትና ትምህርት ሥልጠና ማዕከል አንዱ ነው፡፡ የጂሙ አገልግሎት የሚጀመረው አመሻሽ ላይ ቢሆንም ብዙ ተገልጋዮች ቀደም ብለው ተገኝተዋል፡፡ ስድስተኛው የመላው አዲስ አበባ ጨዋታዎች ስለሚካሄድ አዳራሹ ሞልቷል፡፡ በግቢው ያሉት አብዛኞቹ ተገልጋዮች በዕድሜ የገፉ ናቸው፡፡ ሰብሰብ ሰብሰብ ብለው የሞቀ ጨዋታ ይዘዋል፡፡ የስፖርት ትጥቆቻቸውን የያዙ ቦርሳዎች ደግሞ በአንድ ላይ ተከምረዋል፡፡

የቀድሞው ወወክማ (ወጣቶች ወንዶች ክርስቲያን ማኅበር) የነበረበት ጂም ከዕድሜ ጠገብ ጂሞች አንዱ ነው፡፡ የማዕከሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታሁን ለዓለም ማዕከሉ በ1968 ዓ.ም. ወደ ስፖርት ዘርፎች ከዞረ ጀምሮ ልዩ ልዩ ስፖርት ነክ ክንውኖች ይካሄዱበታል ይላሉ፡፡  ጂሙ ከ18 ዓመት በላይ ለሆኑ በሙሉ ለኤሮቢክስ 250 ለማሽን 350 ብር በማስከፈል አገልግሎት ይሰጣል፡፡ አሁን 1,024 ተገልጋዮች ያሉ ሲሆን፣ ቅርጫት ኳስ፣ ቴኒስ፣ ባድሜንተን የመሰሉ ጨዋታዎችም አሉ፡፡

ስለ አካል ብቃት እንቅስቃሴና የጤና አጠባበቅ መረጃ የሚሰጡ በራሪ ወረቀቶችን ለተገልጋዮቻቸው በማደል ግንዛቤ ለመፍጠር ይሞክራሉ፡፡ ስለ አመጋገብ ሥርዓትና ከስፖርት ጋር ስለሚሄዱ የምግብ ዓይነቶችም መረጃ ይሰጣሉ፡፡ በብዛት እንደ ችግር የሚነሳው ስፖርት ጀምሮ ማቋረጥ ሲሆን፣ ይህ በሰውነት ላይ የሚያደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ  ሥራ አስኪያጁ ያስረዳሉ፡፡

የማዕከሉ ሥልጠናና ተሳትፎ ኬዝ ቲም ኦፊሰር አቶ ገናናው ዓለሙ ወደ ማዕከሉ ከሚያመሩ ብዙዎቹ የጤና እክል ገጥሟቸው በሐኪም ትዕዛዝ የሚሄዱ እንደሆኑና ለመዝናናናት የሚሄዱም እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ ስፖርት መሥራት እየተለመደ ቢመጣም ስለ ጤና ሁኔታቸው ግንዛቤ የሌላቸውና በማንኛውም አጋጣሚ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተነሳሽነት የሚጎላቸው ብዙ ናቸው ይላሉ፡፡ ‹‹ወጣቶች በጣም ቀላል የሚባለውን ነገር ሳይቀር በማሽን ታግዘው ማከናወን ይመርጣሉ፡፡ በሌላ በኩል በእግር ከመሄድ አንስቶ በተለያየ መንገድ ጤናቸውን የሚጠብቁም አሉ፤›› ይላሉ፡፡

በማስከተል ያመራነው ወደ ካፒታል ዌልነስ ነው፡፡ የሚዋኙና በዘመን አመጣሽ መሣሪያዎች ስፖርት የሚሠሩ ሰዎችን ተመልክተናል፡፡ በተለያየ ዕድሜ ክልል ያሉ ተገልጋዮች ያሉ ሲሆን፣ ከ2,500 ብር ጀምሮ እንደተጠቃሚው ቆይታ ብዛት ያስከፍላሉ፡፡ ተጠቃሚዎች ስፖርት ከመጀመራቸው በፊት ያሉበት የጤና ሁኔታ በባለሙያዎች ተመዝኖ ተገቢው እንቅስቃሴ ይታዘዝላቸዋል፡፡

የካፒታል ዌልነስ ማናጀር፣ ሲኒየር ኢንስትራክተርና የስፖርት ሳይንስ ባለሙያ አቶ ኃይለሰማዕት መርሐጥበብ ‹‹የሰውን ልጅ ውሳጣዊ ደኅነነት ከሚጠብቁ ዋነኛው የሆነው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በኛ አገር ትኩረት አልተሰጠውም፤›› ይላል፡፡ የስፖርት ሳይንስ በዓለም ላይ ቀዳሚ ከሆኑ ሳይንሶች ዋነኛው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ተገቢው ቦታ እንደሌላው ያክላል፡፡ ‹‹ስፖርት የማያልቅ ሂደት ነው፤›› በማለት ሰዎች የጤና ችግር ከመከሰቱ አስቀድሞ በመላ ሕይወታቸው ሊተገብሩት እንደሚገባ ያሳስባል፡፡

‹‹የሰው ልጅ ቤቱ ሰውነቱ ነውና ከሁሉም አስቀድሞ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፤›› የሚለው ባለሙያው፣ በዓለም ላይ በተለያዩ ኃላፊነቶች የተወጠሩ ሰዎች እንኳን እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን በማጣቀስ፣ ለስፖርት የሚሆን ጊዜ የለም የሚለውን የተለምዶ ምክንያት ያጣጥላል፡፡ ከአመጋገብና አኗኗር ለውጥ ጋር ተያይዘው ለሚመጡ ችግሮች መፍትሄ የሰውነት እንቅስቃሴ መሆኑንም ከሌሎች አስተያየት ሰጪዎችን ጋር ይስማማበታል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው መረጃ ዓለም ላይ በየዓመቱ ወደ 38 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የ6 ሚሊዮን ሰዎች ሞት የሚከሰተው ከ70 ዓመት በፊት ሲሆን፣ ድርጅቱ መኖር ከሚችሉት ጊዜ በጣም ያነሰ እንደሆነ ያትታል፡፡ ከመንስኤዎቹ መካከል ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ ሱሶች (መጠጥ፣ ሲጋራና አደንዛዥ እፆች) እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ይጠቀሳሉ፡፡ ወደ 3.2 ሚሊዮን ሰዎች የሞታቸው መንስኤ እንቅስቃሴ ያለማድረግ ነው፡፡

እጅግ በጣም ድሀና ሃብታሞችም ለእነዚህ በሽታዎች ያላቸው ተጋላጭነት ሰፊ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለሁለተኛው የምእት ዓመት ግቦች እንቅፋት ከሆኑ መካከል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ይጠቅሳል፡፡ ከግለሰብ አልፎ በአንድ አገር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁናቴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያደርሰውና የዓለም ራስ ምታት የሆነውን ይህን ችግር ለማስተካከል ቀዳሚው መፍትሔ  ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚያስችል የአኗኗር ዘዬን መከተል ነወ፡፡                   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...