Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​ወደፊት እንጂ ወደኋላ አይጋለብም!

ሰላም! ሰላም! ‘ካሚዮን’ አሻሽጬ ኮሚሽኔን ልቀበል የሆነ ካፌ በረንዳ ላይ ተጎልቼ የባጡን የቆጡን አስባለሁ። ለካ አንዱ ከጎኔ ይነድፈኝ ይዟል። መቼም የእናንተ ነገር አይታወቅም። ዘመኑን አስባችሁ እባብ ወይ ጊንጥ የነደፈኝ ይመስላችኋል ብዬ እኮ ነው። ይኼ አስመስሎ መሳል ነገር አለ አይደል? እንደ ፎቶግራፍ? ንድፍ ስል እሱን ነው። ለነገሩ ዘንድሮ ሳይቀነስ ሳይጨመር የማይገለበጥ ነገር የለም። ‘ኮፒ ፔስት’ ይለዋል እንግሊዝኛው። በጥበብ ስም ‘ኮፒ’ መብዛቱ ገርሞን ሳናበቃ ልብ ‘ኮፒ’ ለማድረግ የሚጥርም እያየን ነው። ልብ አውልቁ እኮ በዛ እናንተ።

እናላችሁ ያለፈቃድ ያለኑዛዜ በልሙጥ ወረቀት መገልበጤ ሳይሆን ያናደደኝ በእስክሪብቶ መሳሌ ነው። ቆፍጠን ብዬ “እንዴት አንተ? እግዜር እኮ ሲፈጥረኝ እንድሳሳት ጭምር ነው። እንድሳሳት ብቻ ሳይሆን ተሳስቼ እንድታረም አድርጎ ነው። እንዴት አንተ ላታርም ላታርቅ በእስኪቢርቶ ትቸከችከኛለህ?” እለዋለሁ፣ ‹‹ሥልጣን የለኝማ እርሳስ ከየት አመጣለሁ?›› አይለኝ መሰላችሁ? እንዲያ ሲለኝ ላጲስ መዋጥ አማረኝ በቃ። የት አባቴ ልግባ? ነዶኝ ብቻ “እሺ እንዴት ሳታስፈቅድ ትስለኛለህ?” ብዬ ስደነፋ (ውሸት ምን ያደርጋል ሸጋ አድርጎ ስሎኛል። ቀን አልወጣልኝ እያለ በዚያ ስይዘው በዚህ እየተበተብኝ ለምን እንደሆን እንጃ ፎቶና ሥዕል ይወጣልኛል፤ ኧረ እኔ ምን አውቄ?) ‹‹የመጻፍና የመናገር እንጂ ፈቃድ የሚያስፈልገው ለማየትና ለመስማት ሜዳው ነፃ ነው፤”  ሲለኝ ‘አሃ ይኼ ሰው ከጀርባው ሌላ ተልኮ ይኖረዋል’ ብዬ ብድግ አልኩ። ኋላ የባሻዬን ልጅ ሳገኘው እነግረዋለሁ፣ “ደግሞ ብለው ብለው ፒካሶንም ማኖ አስነኩት?” ብሎ እሱ ብሶብኝ ቁጭ። አሁን ፒካሶ ቢሰማ ምን ይላል? ሸማ አለፈርጁ ተለበሰ ብሎ ያብዳል ወይስ እሱም እንደ እኛ እንደ ዘመኑ ሰዎች ዋናው ቻፓ ነው ብሎ ምን ቸገረኝ ይላል? አንዱንም እንደማይል አውቄው አይደል እኔስ የምለፈልፍ!

እናላችሁ አንድ አዲስ አስፓልት መንገድ ተመረቀና ሥራ ጀመረ አሉ። ወዲያ ወደ ሰሜኑ አካባቢ ነው። ኋላ ሰው ቢታይ ቢታይ በዜብራው አልሻገር ይላል። “ለምንድነው በዜብራ የማትሻገሩት?” ሲባል መልሱ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? “ያልቃል ብለን” – ጉድ እኮ ነው። ታዲያ የማያልቅ ነገር አለ? ሲጨንቀውማ ትራፊክ ፖሊሱ በዜብራ የማይሻገር  60 ብር፣ ግራውን ይዞ የማይጓዘውን አርባ ብር ቅጣት እንዲከፍል ወሰነበት። እኔ ይኼን አላውቅም። አንድ የሚሸጥ ቶርኖ አለ ተብዬ ለማየት ደብረ ማርቆስ ሄጃለሁ። አዲስ አበባ እንደለመድኩት እንዳሻኝ ስሻገር እንዳሻኝ ቀኜን ይዤ ስጓዝ አንድ ትራፊክ ፖሊስ ቁም አለኝ። “ምንድነው የሚለው?” ብዬ ዘወር ብል በአካባቢው ምንም ተሽከርካሪ የለም። አሁንም ስጓዝ ፊሽካ ነፍቶ፣ “አንተን እኮ ነው” ብሎ ጨኸ።

“እንዴት ነው እዚህ አገር የተሽከርካሪ እጥረቱን በእግረኞች ዱካ ነው እንዴ የሚያጣጡት?” ብዬ ቆምኩ። “ግራህን ይዘህ አትሄድም? ስንቴ ይነገራችሁ ግን እናንተ?” ብሎ ተብሰለሰለ። “የምን ግራ?” ግራ ገብቶኛል ለራሴ። ኋላ አተኩሮ ሲያየኝ መጤ እንደሆንኩ ገብቶት፣ “እዚህ እንደ አዲስ አበባ አይደለም። ስትጓዝ ግራህን ይዘህ ካልተጓዝክ ስትሻገር ዜብራ ላይ ካልተሻገርክ…” ብሎ የነገርኳችሁን መቀጫ አብራራና ለቀቀኝ። ገረመኝ። ከዚህ በኋላ ነው ነዋሪው ዜብራው እንዳያልቅ እያለ አልሻገር ብሎ እንዳስቸገረ የሰማሁት። የትራፊክ ፖሊሱን ምሕረት ተቀብዬ በስተግራ በኩል ተሻግሬ ወደፊት ስጓዝ ከመሀል ከተማው ዳር ዳሩ እንዴት እየሠለጠነና ራሱን እየገራ እንደሚጓዝ አስተውል ጀመር። ኋላ አዲስ አበባ ተመልሼ ለባሻዬ ልጅ ሳወጋው፣ “እና የፌዴራሊዝም በጎ ገጽታ ነው እያልከኝ ነው?” ብሎ ነገር ሊጀምረኝ ሞክሮ ነበር። በነበር ቀረ እንጂ!

ያው እንደነገርኳችሁ የሄድኩት ለሥራ ነበር። እናም አንዳንድ ነገሮችን አተኩሬ ማጤኔ አልቀረም። በተለይ ‘የካሽ ፍሎውን’ ነገር። ከምጠብቀው በላይ ነዋሪው እጅ ላይ ያለው ገንዝብ፡፡ ንብረትና መሬት ደህና ደላላ አላገኝ ብሎ እንጂ እየተገላበጠ ለአገር ለወገን በጠቀመ ነበር። “ግን ሰው ተቀምጦበታል” አለኝ አንድ የማቻከል ሊስትሮ ጫማዬን እየጠረገ። “እንዴት?” ስለው፣ “በቃ ተቀምጦ አራጣ ማበደር ነው። አራጣና አራጣ ብቻ ነው ጨዋታው። ለምሳሌ ያ የማነው የጋሽ ማንትሴ ልጅ ብትል፣ እዚያ ታች ያለው ማንትሴ የሚባል ቤት አይተሃል? እነሱ ብትል ኧረ ተወኝ…” ብሎ ዝም አለ። ሊስትሮው የነገረኝን ይዤ ተለቅ ያለ ሰው አገኘሁና ቀስ ብዬ ነገሩን ባነሳው፣ “አራጣውስ ይሁን። አሁን ደግሞ አላስቀምጠን ያለው…” ብሎ ግራ ቀኝ ተገላመጠና “አስማት ነው” አለኝ ወደ ጆሮዬ ጠጋ ብሎ።

“አስማት?” ገርጥቼ ቀረሁ። የአላዲንና የፋኖሱ ዓይነት አስማት ነው? ወይስ ከዛም እልፍ ይላል? እያልኩ በልቤ ማብራሪያ ስጠብቅ፣ “ሰው አሁን ብልጥ ሆኗል። እንደ ድሮው ፊት ለፊት መግደል መገደዳደል እየተወ ነው። እስራቱም እየጠበቀ መጥቷላ። ስለዚህ ምን ተጀመረ አስማት። እከሌን በምናምን እንድፋው ይባላል . . . ማስተብተብ ነው…” ሲለኝ የመጣሁበትን ትቼ በሸዋ በር በኩል አገሬ መግባት አማረኝ። አጠገቤ ተቀምጣ የምትሰለቸኝ ማንጠግቦሽ ከሦስት መቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆኜ ላቅፋትና ጉያዋ ልሸጎጥ አማረኝ። እናስ ስለው ጎልማሳውን፣ ‹‹ምን እናስ አለው? ዋናው አለመቀደሙ ነው። ይልቅ አንተ ምን ልትሠራ መጥተህ ነው?›› ብሎ ወደ እኔ ዞረ። ማንን አምኜ ምን ልለው ነበር ድሮስ? ኧረ ሰው ማመን ናፈቀኝ ጎበዝ!

በስንተኛው ቀን ያን የፈረደበትን ቶርኖ ለማሳየት ባለቤቱ እየመራ ወሰደን። ደንበኛዬን እንደሚገዛው ሳልጠራጠር ይልቅ ቶርኖው ስለሚጫንበት መንገድ እያዋየሁ እንጓዛለን። እንዳልኩት በራስ በጭራው ተገብቶ ማሽኑ ተፈትሾ እንዳበቃ ጥቂት ተከራክረው ገዥና ሻጭ በዋጋ ተስማሙልኝ። ‘ዲል’ ይላል አሉ ፈረንጅ! የሚደረገውን አደራርገን ለማግሥቱ ቀጠሮ ይዘን ተለያየን፡፡ እኔና ደንበኛዬ አንድ ሐራጅ የወጣ ጉደኛ ቤት አለ ተብለን እንዲያው ለማየት ባጃጅ መጠበቅ ጀመርን። አንዱ ደስ ያለኝ ነገር ታዲያ ምን መሰላችሁ? የታክሲ ሠልፍ ማየት እዚያ ይናፍቃችኋል። በየአቅጣጫው ባጃጅ ነው። ጭራሽ አንድ ባጃጅ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር አውሎ ወደፈለጉበት መሄድ ይቻላል። ታዲያ አስተያየት አድርጋችሁ ሁለት ሦስት ብር ጨምራችሁ ትከፍላላችሁ እንጂ፣ ሰው እንዳልጭን ከልክለሃል ብሎ ባለባጃጁ የኮንትራት ሒሳብ አይጠይቅም።

አዲስ አበባ እንኳ ሚኒባሱን ብቻችንን ተቆጣጥረነው ቀርቶ ተቃቅፈን ተሳፍረንም ወያላው መልስ ሊያረሳሳን እንዴት ሲሽኮረመም እንደሚውል አስታውሱ። እኔ አስታውሼ ያስቆምኩት ባጃጅ ላይ ተሰቀልኩ። ወደ ነገርነው አካባቢ (አብማ ማርያም) ወስዶ እንዳደረሰን ያንን የተባልነውን ቤት ፍለጋ አንዱን ልዩ ምልክት ነግረን ብንጠይቀው በኩራትና በደስታ “አላውቀውም!” ብሎ ሳቀ። ኩራቱም ይሁን፣ ደስታውም ደስታ ነው። ሳቁን ምን አመጣው? እያልኩ ግራ ቀኝ እየቃበዝኩ ቤቱን ማሰስ ቀጠልኩ። ላካ ያ አላውቀውም ባዩ መጓዙን ትቶ ጥጉን ይዞ ቆሞ ስንደናበር እያየ ይዝናናላችኋል። “ይኼ የልብ ክፋት ዘር፣ ፆታ፣ ሃይማኖት፣… ሳይለይ በየአቅጣጫው እያደር አይሎ አገር ያለችግር ይለማል ያድጋል ትላለህ?” ብሎ ደንበኛዬ ከእኔ ቀድሞ ታዝቦት ኖሮ ጠየቀኝ። አሁን እስኪ መንገድ መሪነት ፀጋ እንጂ አንሶ መገኘት ነው እንዴ? አንድ ቀን እኮ ሁላችንም መንገድ ተመሪ መሆናችን አይቀርም፡፡ የግል ብሶት መሰለብኝ እንዴ? የገባው ይግባው!

በሉ እስኪ እንሰነባበት። ባሻዬ አደራ ስላሉኝ ብቻ ሳይሆን ዓባይን ተሻግሬ ቅቤና ማር ካልሸመትኩ ጉዞዬ ትርጉም ያጣብኛልና ሸጋ ቅቤና ማር ይዤ አዲስ አበባ ገባሁ። ባሻዬ የቅቤውን ለጋነት የማሩን ወለላነት አሽተውና አጣጥመው ከመረቁኝ በኋላ፣ “እንዲያው አገሩ እንዴት ነው?” ሲሉ ጨዋታ ጀመሩ። “አገሩስ ሰፊ ነበር እኛ እያጠበብነው አስቸገርን እንጂ፤” ብዬ ስለገበሬው ታታሪነት፣ የዋህነት፣ ጥጋብና እጦት ሳወጋቸው ቆየሁ። ስለከተማና ከተሜነት፣ ስለሥልጣኔና ትርጓሜው ባሻዬ ምን አሉ መሳለችሁ ቆያይተው? “እኛ . . .” አሉ ጋቢያቸውን ተጀቡነው እንደተቀመጡ። “ . .. ይኼን ሁሉ ዘመን በታሪክ ህልውና ላይ ስማችን ሲነሳ ይኼው የአዲስ አበባ ዕድሜ እንኳ መቶ ምናምን ዓመት ብቻ ነው። የንጉሥ ተክለ ሃይማኖት መናገሻ የሆነችው ደብረ ማርቆስ በዕድሜ ትበልጣለች። እነጎንደር እነአክሱምን ካልክ ደግሞ ስንት መቶ ዓመታት ስንት ሺሕ ዓመታት ትቆጥራለህ።

ግን . . .” አሉ ባሻዬ “ . . . የፓሪስን ሩብ ክፍለ ከተማ፣ የፕራግን ሲሶ ክፍለ ግዛት፣ የሮምን ሃምሳ ሜትር የኮብልስቶን ጎዳና ያህል ውበት፣ ሥልጣኔና ምቾት ያላት ከተማ የለንም። አይገርምህም? መቼም ዕድገት፣ ከተማና ከተሜነት ነው። ሕግና ሥርዓት ወጥሮ የያዘው የተደራጀ የአኗኗር ሥልት ማለት ነው ከተሜነት። እህ? አለመታደል ሆኖ ይኼው አፍርሰን እየሠራን ነው፤” ሲሉ ቀበል አድርጌ፣“ይኼንንስ ማን አየብን?” አልኩዋቸው። ሳስቼ የደበቅኳቸውን የግብጦ አረቄ አግኝተው ቀማምሰው ይሆን ብዬ መስጋቴም አልቀረ። እስኪ በሆነው ባልሆነው ነገር ከመበሳጨት በሆነው ነገር መደሰት እንወቅ መጀመሪያ። ወደፊት እንጂ ወደኋላ አይጋለብም! አይመስላችሁም? ቺርስ! መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት