በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ እንደ ሌሎች አካባቢዎች ሁሉ በአዋሽ ብሔራዊ ፓርክም ክንዱን አሳርፏል፡፡ በፓርኩ፣ ወትሮውንም ቢሆን የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አርብቶ አደሮችና ከርቀት የሚመጡትም ራሳቸውንና የቤት እንስሳቸውን በሕይወት ለማቆየት በሺሕ የሚቆጠሩ እንስሳት ሲያሰማሩበት ቆይተዋል፡፡ በመሆኑም የአርብቶ አደሩ ከብቶች ከዱር አራዊት ጋር የመኖ ሽሚያ ውስጥ ነበሩ፡፡ ድርቁ ሲጨመርበት ደግሞ ፓርኩ ላይ ከባድ ውድመት ደርሷል፡፡
ድርቁ በፓርኩና በዱር እንስሳቱ ላይ ያስከተለውን ችግርና ስለፓርኩ ጠቅላላ ሁኔታ የሪፖርተር ዘጋቢ በቦታው ተገኝቶ የዱር እንስሳትና የተፈጥሮ ቁጥጥር ኦፊሰር የሆኑትን አቶ ሸለመ አብዩን አነጋግሯል፡፡
አቶ ሸለመ እንደሚሉት፣ ችግሩ ስር የሰደደ ነው፡፡ የፓርኩ ግማሽ አካሉ የሚገኘው በአርብቶ አደሮች አካባቢ ነው፡፡ እነዚህ አርብቶ አደሮች በራሳቸው አካባቢ የሚገኘው ተክል በመመናመኑና ከፍተኛ የሆነ ውድመት በመፈጠሩ በሺሕ የሚቆጠሩ የቤት እንስሳቶቻቸውን ሕይወት ለማቆየት የፓርኩን ድንበር አልፈው ገብተዋል፡፡
ፓርኩ ደግሞ በብዛት በውስጡ የያዛቸው ሳር በል የዱር አራዊት ናቸው፡፡ በአካባቢው ከሁለት ዓመት በላይ ዝናብ ባለመኖሩ የዱር እንስሳቱም የቤት እንስሳቱም ያለውን ተክል እየተሻሙ ሲመገቡ ቆይተዋል፡፡ ሆኖም ድርቁ እየከፋ በመምጣቱና የሚመገቡት ሣር ባለመኖሩ የፓርኩም ሆነ የአርብቶ አደሩ እንስሳት እየተመናመኑ ነው፡፡ በውስጡ የሚያልፈው አዋሽ ወንዝም ደርቋል፡፡ እየተንጮለጮለ የሚወርደው ወንዝም በአካባቢው በሚገኙ ፋብሪካዎች በሚለቀቅ ኬሚካል የተበከለ ስለሆነና የዱር አራዊት ውኃውን መጠጣት ስለማይችሉ ችግሩ ድርቁ የፈጠረውን የውኃ እጥረት አባብሶታል፡፡ በዚህ የተነሳ በተለይ የፓርኩ መለያ የሆኑ ሳላዎችና ከርከሮዎች በስደትና በሞት ቁጥራቸው ቀንሷል፡፡ ያሉትም ቢሆኑ ክብደታቸው እየቀነሰ፣ መራመድ እያቃታቸውና ለጅብ ሲሳይ እየሆኑ ነው፡፡ የተሰደዱትም ወደ ፈንታሌ ተራራ አካባቢ በመሄድ ባህሪያቸው እየተቀየረ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ድርቁ ቢቀንስና አካባቢው ለም ቢሆንም የተሰደዱት እንስሳት ይመለሳሉ ወይ? የሚለው በራሱ ትልቅ ሥጋት ሆኗል፡፡
ዝናብ ባለመጣሉ ለብዙ ዘመናት ለዱር አራዊቱ መጠለያ የነበሩት ግራሮች በሕገወጥ ከሠል አክሳዮች በቀላሉ እየተቆረጡ ወደ ከሰል እየተቀየሩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ከፓርኩ ስፋት አንፃር ያሉት የጥበቃ አባሎች ስለማይመጣጠኑ፣ ከሰል አክሳዮችን ለማስቆም እንዳልተቻለና የፓርኩ ኢኮሎጂ ሲስተም እየተዛባ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ የሪፖርተር ዘጋቢ በዚሁ ፓርክ ላይ ጉብኝት አካሄዶ ነበር፡፡ በዛን ወቅት ሳላዎችን ለማየት በረዣዥም ሣር የተሸፈነውን የፓርኩን ክፍል ማጋመስ የግድ ነበር፡፡ በቡድን ተሰብስበው የተቀመጡ ሳላዎችን ማየትም ያጓጓ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ግን ገና ከመግቢያው በር ጀምሮ አንዳንድ የከሱ ሳላዎች ምግብ ፍለጋ ሲዞሩ ያገኟቸዋል፡፡ ያ የሚሰበሰቡበት ቦታ ዛሬ ወደ ቀይ አፈርነት ተቀይሯል፡፡ ለምነቱ ጠፍቷል፡፡ አካባቢውን ቀድሞ ለሚያውቀው ሰው ዛሬ ላይ ያለበት ሁኔታ ያስደነግጣል፡፡
ውስጥ ከነበሩት የዱር እንስሳት ተርፎ በአካባቢው ለሚኖሩ አርብቶ አደሮች የቤት እንሰሳዎች ይመግብ የነበረው ፓርክ፣ ዛሬ ተራቁቷል፣ ደርቋል፡፡ ከዚህ ቀደም ደልበውና ደንደን ብለው ይታዩ የነበሩ የዱር እንስሳትም አጥንታቸው ገጧል፡፡ መሄድ አቅቷቸው እግራቸውን ሲጎትቱም ይታያሉ፡፡ የደረቀውን ሣር ለመንጨት የሚያደርጉትን ትግል ማየት ልብ ይሰብራል፡፡
ከርከሮ በባህሪው በቡድን መሄድ የሚወድ እንስሳ ነው፡፡ ሃቻምና አንድ ከርከሮን ቢያንስ አሥር የሚሆኑ ተከትለውት ይጓዙ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ግን በሕመምና በረሃብ በየቦታው ተበትነውና መንቀሳቀስ አቅቷቸው ያገኙዋቸዋል፡፡
ካችአምና ድምፁን ከርቀት ይሰሙት የነበረው አዋሽ ፏፏቴ ልሳኑ ተዘግቷል፡፡ ከፏፏቴው የሚወጣው የውኃ ፍንጣቂ የሚሠራውን ቀስተ ደመና ለማየት ፏፏቴው ጋር ደርሼ ያስብል የነበረው ትዕይንት ዛሬ ተገፏል፡፡ ፏፏቴው ተሽንፏል፡፡
ከፏፏቴው ስር የነበሩ አዞዎች ላለመሞት ግማሽ አካላቸውን ተራ በተራ ወደ ውኃው በማስገባትና በማስወጣት ገላቸውን ማዳረስ ግድ ሆኖባቸዋል፡፡ ድርቁ በፓርኩ ላይ ያደረሰው ውድመት ከባድ ሲሆን፣ ችግሩን የተካፈለለት የመንግሥት አካል ያለ አይመስልም፡፡
ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አንድ አባወራ ለምን ወደ ፓርኩ ግመሎቻቸውንና ሌሎች የቤት እንስሳቸውን እንደሚያስገቡ ጠይቄያቸው ነበር፡፡ ‹‹ሁለት ሚስቶች፣ ስድስት ልጆች፣ ግመልን ጨምሮ ወደ ሦስት ሺሕ የሚጠጉ የቤት እንስሳት አሉኝ፡፡ እኔ አርብቶ አደር ነኝ፡፡ መሬት አልጠየኩ፣ እነዚህን ሁሉ እንስሶች ምን ላበላ ነው የምትፈልጉት፣ ምን ላጠጣ ነው የምትፈልጉት፣ በአካባቢያችን ደግሞ ብዙ እንደእኔ ከብቶች ያላቸው አሉ፣ ምን እናድርጋቸው፣ ይኼ ፓርክ የምትሉት ለእኛ ምንም የሰጠው ነገር የለም፡፡ ለከብቶቻችን አንድ ጀሪካን ውኃ እንኳን ሰጥቶ አያውቅም፡፡ እኛና ከብቶቻችን ካልኖርን ደግሞ ፓርኩ ለማነው የሚኖረው›› በማለት ከብቶቻቸውን እዚህ ፓርክ ውስጥ ማስገባት በሕይወት የመቆየትና ያለመቆየት እንደሆነ ነግረውኛል፡፡
ይህ ችግር ዓይነቱ ይለያይ እንጂ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ፓርኮች ይታያል፡፡ በአንድ ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደ ሰሜን ፓርክ በመግባት ኑሮዋቸውን እዛው ሲያደርጉ፣ በአካባቢው ያሉ የዱር አራዊቶች ዋሊያን ጨምሮ ነዋሪውን በመሸሽ ተሰደው ነበር፡፡ በተለይ የዋሊያዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ወርዶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሆነው ነበር፡፡ ዛሬ ግን ያ ችግር በመንግሥትና በዓለም አቀፍ ትብብር እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር በተደረገው ተደጋጋሚ ውይይት ለነዋሪዎቹ የሚሆን ቦታ በማዘጋጀትና ችግሮችን በመቅረፍ ነዋሪዎች ፓርኩን ለቀው ወጥተዋል፡፡ በዚህም ዛሬ ላይ የዋሊያዎች ቁጥር ከአራት ሺሕ እስከ ስድስት ሺሕ ሊደርስ ችሏል፡፡
የፓርኩ ባለሙያዎች ስለደረሰው ድርቅ ሲገልጹ፣ በፓርኩ ውስጥ ሣር የሚበቅልባቸው ቦታዎች በማይታወቅ መጤ አረም እየተሞሉ ነው፡፡ ስድስት ሳላዎች ሞተዋል፡፡ ከርከሮዎች ከሣር ወደ ሥጋ በልነት ተቀይረዋል፡፡ ሣር በል የሚበዙበት ፓርክ ዛሬ ሥጋ በል እየበዛበት ነው፡፡ አገር በቀል ዕፅዋቶችም እየጠፉ ዘራቸውም እየተመናመነ ነው፡፡ ከኅብረተሰቡ ጋር ያለው ውዝግብ ካልተፈታም ዝናቡ ቢመጣም፣ ችግሩ ይቀጥላል፡፡
አዋሽ ፓርክ ከአዲስ አበባ 215 ኪሎ ሜትር በምሥራቁ የአገራችን ክፍል የሚገኝ ሲሆን፣ ፓርኩ የተቋቋመው 1958 ዓ.ም. ነው፡፡ በወቅቱ ስፋቱ 756 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የነበረ ሲሆን፣ በ1961 ዓ.ም. ሲከለል፣ አሁን ያየውን 591 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ይዞ ቀርቷል፡፡
ፓርኩ አፋርና ኦሮሚያ ክልሎችም ያዋስኑታል፡፡ ዝቅተኛ የሙቀት መጠኑ 26 ዲግሪ ሲንቲግሬድ ሲሆን፣ ከፍተኛው ደግሞ 42 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይለካል፡፡ በዓመት በአማካይ እስከ 620 ሚሊ ሜትር የሚደርስ ዝናብ ያገኝ ነበር፡፡ በውስጡም 81 አጥቢ እንስሳት 435 የወፍ ዓይነት 43 ሬፕታይልስና ከ400 በላይ የዕፅዋት ዓይነቶች ይዟል፡፡ በተለይ የቱሪስት ቀልብ የሚስበው የፓርኩ መለያ አርማ የሆነው ሳላህ፣ በብዛት ይኖርበታል፡፡ የአዋሽ ፏፏቴ፣ የተፈጥሮ ፍልውኃ፣ እዋሽ ጐርጅ፣ ረዣዥም ሳሮች፣ ከ20 የሚበልጡ የተፈጥሮ መስህቦችን ይዟል ቢባልም፣ ዛሬ ላይ ሁኔታዎች ተቀያይረዋል፡፡ የአዋሽ ፓርክ ምድረ በዳ እየሆነ ነው፡፡
ፓርኩ በሁለት የተከፈለ ሲሆን ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ ሲሄዱ አዋሽ ከተማ ለመድረስ 16 ኪሎ ሜትር ሲቀርዎት በስተቀኝ አዋሽ ፓርክን ያገኛሉ፡፡ ይህ ግቢ ብዛት ያላቸው ሳላዎችን ጨምሮ ሌሎች እንስሳት የሚገኙበት ሲሆን፣ በስተግራ በኩል ደግሞ ከዋናው መንገድ 30 ኪሎ ሜትር ገባ ብሎ ፍልውኃና የተለያዩ የወፍ ዝርያዎች ያሉበትን የፓርኩን ክፍል ያገኛሉ፡፡
በአካባቢው የአርብቶ አደሮች በሕይወት የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ፣ በአዋሽ ፓርክ አስተዳደር ያለው የመንግሥት ኃላፊነትና የሙያ ግዴታ፣ ዘንድሮ የተከሰተው ድርቅ ጥሎት የሚያልፈው ውጤት፣ በፓርኩ ውስጥ አዲስ የተዘረጋው የባቡር መስመር፣ የአዋሽ ወንዝ መበከል፣ በዱር እንስሳቱ ላይ የሚደርሰው ችግር፤ ፓርኩ ከቱሪዝም የሚያስገኘውን ጥቅም አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ጥያቄዎች መቼ፣ እንዴት፣ ተፈትተው አዋሽ ፓርክ የቀድሞውን ግርማ ሞገስ ያገኝ ይሆን?