Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት​ለስፖርቱ ዕድገት ሁለንተናዊ ለውጥ ማድረግ የሚያስችል ጥናት መጀመሩ ተሰማ

​ለስፖርቱ ዕድገት ሁለንተናዊ ለውጥ ማድረግ የሚያስችል ጥናት መጀመሩ ተሰማ

ቀን:

የስፖርቱ ዘርፍ አቅምና ክህሎት እንዲሁም ጊዜ ኖሯቸው ስፖርቱን ማገዝ በሚችሉና በፕሮፌሽናል ሙያተኞች ለመምራት እንዲቻል፣ ቱባ የመንግሥት ባለሥልጣናት ምድብ ሥራቸውን ከመምራት ወጪ በትርፍ ጊዜያቸውና ባላቸው የተጣበበ ጊዜ ወደ ስፖርቱ እንዳይገቡ የሚያደርግ ጥናት ማካሄድ መጀመሩ ተሰማ፡፡

በቅርቡ በአዲስ መልክ ከተዋቀረው ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው፣ በስፖርቱ መስክ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ዘርፉን የሚመሩ ኃላፊዎች ብቻም ሳይሆን፣ በየተዋረዱ ባሉት እርከኖች ላይ ለውጥ ያመጣል የተባለ የመዋቅርና የአደረጃጀት ማስተካከያ የሚያመጣ ጥናት በተለይም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አካባቢ ጥናት እየተደረገ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

እንደ መረጃው ከሆነ ጥናቱ በመሠረታዊነት የሚመለከተው የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች የሥራ አስፈጻሚ ጥንቅርና ብዛት እንዲሁም የመምራት ብቃት፣ ክህሎትና ጊዜው ኖሮት ስፖርቱን የማገዝ አቅም ያለው ሰው እንዲሆን ለማድረግ ያለመ ነው፡፡ እስካሁን በዘለቀው የስፖርቱ ተሞክሮ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና በየዕርከኑ ያሉ መዋቅሮችን ለመምራትና ለማስተዳደር ምርጫዎች ሲቃረቡ ሒደቱ ‹‹በኔትወርክ›› እንደሚጠናቀቅ፣ ከዚህ ባልተናነሰ ሌላው የሚስተዋለው ችግር ደግሞ ለምርጫ ራሳቸውን የሚያቀርቡ እጩዎች ለውኃ ዋና ፌዴሬሽን አልያም ለኢትዮጵያ እግር ኳስና ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለመወከል የተለያዩ ክልሎችን ድጋፍ መጠቀም እየተለመደ መምጣቱ ስፖርቱ ላይ ለሚስተዋለው የአሠራር ክፍተትና ግድፈት ተጠቃሽ ተደርጎ በጥናቱ እየታየ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከ26 በላይ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑና አሶሼሽኖች ሕጋዊ ሰውነት ኖሯቸው እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ይታመናል፡፡ ሁሉም ማለት በሚያስችል መልኩ ስፖርቱ ከመንግሥት ድጎማና ድጋፍ ወጥቶ በሒደት ሕዝባዊ አደረጃጀት እንዲኖረው የመንግሥት ፍላጎት መኖሩ በ1990ዎቹ መጀመሪያ በአገር አቀፍ ደረጃ የወጣው የስፖርት ፖሊሲ ማሳያ ነው፡፡ ይሁንና አሁን መሬት ላይ ያለውና እየሆነ የሚታየው በተቃራኒ መሆኑ በአብዛኛው የስፖርቱ ተቋማትና አመራሮች ስፖርቱ በሒደት ራሱን ችሎ መሄድ ይችል ዘንድ የተለያዩ ስትራቴጂካዊ እቅዶች ከመንደፍ ይልቅ ውድድሮችን መምራት ብቻ እንደ ዋና ሥራ አድርገው መቁጠራቸው፣ በአገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ደረጃ እቅድ ተይዞላቸው ያለ ውጤት የቀሩ በርካታ ፕሮጀክቶች ለምንና በእነማን ሊሳኩ አለመቻላቸው ሳይታወቅ ተድበስብሶ የሚቀር አሠራር መኖሩ፣ ለዚህ በቅርቡ እውን ይሆናል ተብሎ ለሚጠበቀው የመዋቅርና የአደረጃጀት ማስተካከያዎች ጥናት በዋና መነሻነት መቅረቡም እየተነገረ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጓዳኝ እያንዳንዱ የፌዴሬሽን አመራርና በየዕርከኑ የተቀመጡ ሙያተኞች ከእንግዲህ መመዘን የሚኖርባቸው በሚያቀርቡት ሪፖርት ሳይሆን መሬት ላይ ባለው ነገር ሊሆን እንደሚገባ ጭምር መረጃው ያመለክታል፡፡ ለዚህ ደግሞ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በጉዳዩ ከባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረኮችን በማመቻቸት ለተግባራዊነታቸው እውን መሆን የአንበሳውን ድርሻ ሊወስድ መዘጋጀቱ ተሰምቷል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኖችን የሚመሩ አካላት ምንም ዓይነት ክፍያ ሳይኖራቸው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚሠሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን በስፖርቱ ባለውና በሚስተዋለው ተጨባጭ ሁኔታ ‹‹ነፃ አገልግሎት›› ለመስጠት በመጡ የስፖርቱ አመራሮች መካከል ‹‹ልቀቅ አለቅም›› በሚል እልህ አስጨራሽ እሰጣ ገባዎች ውስጥ መገባቱ በውስጡ ምን ዓይነት ጥቅም ቢኖር ነው? ወደ ሚል ድምዳሜ ሊያደርሰው መቻሉና ለሚኒስቴሩ የትኩረት አቅጣጫ እየሆነ መምጣቱ እየተነገረ ይገኛል፡፡

በአቅም ችግር ምክንያት መንቀሳቀስ ለማይችሉ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች በሚመለከት ሚኒስቴሩ ድጋፍና የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥም መረጃው አመልክቷል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በሚኒስቴሩም ሆነ በብሔራዊ ፌዴሬሽኖችና ሌሎች በሚመለከታቸው አካላት እቅድ ተይዞላቸው ‹‹እየተሠራባቸው ነው›› ተብሎ የሚነገርላቸው የተለያዩ የፕሮጀክት ጣቢያዎች ያሉበትንና የሚገኙበትን ደረጃ በመመልከትና በመከታተል እውነተኛውን መረጃ ለሕዝብ ማድረስ ለሚፈልጉ መገናኛ ብዙኃንም ቅድመ ሁኔታዎች የሚያመቻች እንደሆነ መረጃው ይፋ አድርጓል፡፡

*******

የደጋፊው ፍላጎትና የፀጥታ አጠባበቁ ገፅታ

በደረጀ ጠገናው

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ባለ ብዙ ሺሕ ደጋፊዎች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ፣ በአዲስ አበባም ሆነ በክልል የሚያካሂዳቸው ጨዋታዎች ከትንሽ እስከ ከፍተኛ ደረጃ የሚደርስ የፀጥታ ችግር እንደሚገጥመው ብዙዎችን ያስማማል፡፡ ይህ ዓመታትን ያስቆጠረ እውነታን በሁለት መልኩ መገንዘብ እንደሚገባ የሚገልጹ የስፖርቱ ቤተሰቦች፣ የፀጥታ አጠባበቁን ከደጋፊ ልባዊ ፍላጎት ጋር ማጣጣም እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡ ይህም ደጋፊው ለቡድኑ ካለው ጥልቅ ስሜት የሚመነጭ መሆኑን ማረጋገጥ ከረብሻና ከብጥብጥ የፀዳ እንዲሆን ማድረግ የፀጥታ ኃይሉ ብቃት ሊሆን እንደሚገባም ያክላሉ፡፡

በብዙ ውጣ ውረድ እያለፈ ባለው እግር ኳስ፣ የብሔራዊ ቡድኑን ያህል በውጤት ማጣትና በደጋፊ ብዛት የሚገለጸው የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ለዓመታት ከሚተችበት የድጋፍ አሰጣጥና ችግሮችን ማረም ያለመቻል ታሪኩ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በማድረግ የተቀናጀ ሥራ ሊስተካከል እንደሚችልም እነኚሁ የስፖርቱ ቤተሰቦች ይገልጻሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በጉዳዩ ላይ ሊወስደው የሚገባው ጠንካራ አቋም የመፍትሔው መጀመሪያ ሊሆን እንደሚገባም ያክላሉ፡፡ የፀጥታ ኃይሉም ቢሆን ካለበት አገራዊ ተልዕኮ ጎን ለጎን ስታዲየም ውስጥ የሚታደሙ ደጋፊዎች የሚመለከቱት እግር ኳስ ነውና በእንቅስቃሴ መሐል አላስፈላጊ የቃላት ልውውጦች እንደሚኖሩ ግምት ውስጥ በማስገባት ድርጊቱ ወደ አላስፈላጊ ነገር እንዳይለወጥ የጥበቃውን ሁኔታ ብልሃት፣ ጩኸትና ትርምስ በማይፈጥር መልኩ ማከናወን እንደሚጠበቅበትም ይጠቁማሉ፡፡ ደጋፊዎች መሐል ገብቶ ድርጊቱን ለማቀዝቀዝ ከመጣር ይልቅ በአቅራቢያው ሆኖ ክትትሉንም ሆነ ቁጥጥሩን ማድረግ ቢቻል የመፍትሔው አካልና ተመራጭ ሊሆን እንደሚችል ጭምር ይገልጻሉ፡፡

ለዚህ የደጋፊዎች ፍላጎትና የፀጥታ አጠባበቅ ገፅታን አስመልክቶ ለተነሳው ሐሳብ መነሻ የሆነን፣ ባለፈው ሐሙስ የካቲት 3 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብና በሃዲያ ሆሳዕና እግር ኳስ ክለብ መካከል የተደረገው የኢትዮጵያ ከለቦች ጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላይ የተፈጠረው ‹‹ሁከት›› ነው፡፡ ደጋፊዎች ክለባችን እየደገፍን ሳለ የፀጥታ ኃይሎች ለምን መሐላችን ይገባሉ በሚመስል መልኩ የዕለቱ ጨዋታ እየተከናወነ በሚገኝበት ሰዓት ስታዲየሙን ለቀው ሲወጡ የታዩ ተመልካቾች ታይተዋል፡፡ የሪፖርተር ዝግጅት ክፍልም በቦታው የነበረ በመሆኑ በደጋፊዎችና ፀጥታ ኃይሎች መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት አስመልክቶ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የፀጥታ ሥነ ምግባርና ስፖርታዊ ጨዋነት ኮሚቴ ሰብሳቢ ለሆኑት ዶ/ር ነስረዲን አብዱራህማን ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ሰብሳቢው እንደተናገሩት ከሆነ፣ በዕለቱ ጨዋታ የተፈጠረውን ሁኔታ አስመልክቶ ለፌዴሬሽኑ ሪፖርት እንዲቀርብ፣ ከዚያም ከሪፖርቱ በመነሳት አስፈላጊውን ማብራሪያ የሚሰጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በፀጥታ ኃይሉ በኩል ያለውን ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡ በሌላ በኩል ግን በጉዳዩ ዙሪያ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ የደጋፊዎች ማኅበር ኃላፊዎች፣ የክለቡ የቦርድ አመራሮች፣ ፌዴሬሽኑና ከፀጥታ ኃይሎች የሚመለከታቸው ኃላፊዎች በሚገኙበት እሑድ የካቲት 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በክለቡ የስብሰባ አዳራሽ ተገናኝተው በጉዳዩ ለመነጋገርና የመፍትሔው አካል ለመሆንም ቀጠሮ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማኅበርስ ምን እያለ ነው?

አቶ ክፍሌ አማረ በመደበኛ ሥራቸው የሕግ አማካሪ ሲሆኑ፣ ከግል ሥራቸው በተጓዳኝ ደግሞ የኢትዮጵያ ቡና የደጋፊዎች ማኅበርን ለረዥም ዓመታት በአመራርነት ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ማኅበሩ በቅርቡ ባካሄደው አዲስ የአመራሮች ምርጫ በፕሬዚዳንትነት ተመርጠው በማገልገል ይገኛሉ፡፡

የክለቡ የደጋፊዎች ማኅበር ወቅታዊ አቋምና በቀጣይ ስለሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎችና እቅዶች ሪፖርተር ላቀረባላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ማኅበሩ ሕጋዊ እውቅና አግኝቶ መንቀሳቀስ የጀመረው ከጥር 3 ቀን 1990 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ ከክለቡ የደጋፊዎች ማኅበር ምሥረታ አኳያ ቀዳሚና የመጀመሪያ ያደርገዋል፤›› ብለው፣ ዓላማውን አስመልክቶ አቶ ክፍሌ ሲያስረዱ፣ በማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ አምስት መሠረት የደጋፊ ማኅበሩ በዋናነት የክለቡ ደጋፊዎች የሆኑትን ሰዎች ወይም ድርጅቶችን በማስተባበር ክለቡን በሞራል፣ በቁሳቁስና በልዩ ልዩ መንገዶች በመደገፍ ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ አንዱና ዋናው መርሁ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ክለቡ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ሁሉ ደጋፊዎቹ በስታዲየሞች በመገኘት ስፖርታዊ ጨዋነት በተላበሰ መልኩ ቡድናቸውን ማበረታታት እንዲሁም ክለቡ ወደ ዘመናዊ አደረጃጀት እንዲሸጋገር ከክለቡ ሥራ አመራር ቦርድ ጋር በመሆን ጥናት በማድረግና ወደ ተግባርም እንዲለወጥ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡

ማኅበሩ በቀጣይ ሊሠራቸው ያቀዳቸውን በተመለከተም ቀደም ሲል ለመግለጽ ከተመለከተው ጎን ለጎን በአደረጃጀቱ ከአፍሪካ ቀዳሚና ታላላቅ ክለቦች ተርታ እንዲቀመጥ ማስቻል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ዘመናዊ አደረጃጀት ሲባልም ከምኞትና ፍላጎት ባለፈ የአጭር፣ የመካከለናኛ የረዥም ጊዜ እቅዶችን በመንደፍ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡

ከእቅዶቹ ቅድሚያ ተሰጥቷቸው እየተሠራባቸው ከሚገኙት ውስጥ ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ መሆናቸው እንደተጠበቀ፣ በዋናነት በመላው ዓለም በተለይም በደቡብ አፍሪካ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በዱባይና በመሳሰሉት አገሮች በብዛት ስለሚገኙ ወጥና አሳታፊ የሆነ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ማስተሳሰር የደጋፊ ማኅበሩ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጭምር ያስረዳሉ፡፡ ለዚህ እንቅስቃሴ እውን መሆን የስትራቴጂክ እቅድ ዝግጅት ትልቁን ስፍራ ይይዛልም ብለዋል፡፡ ዘመን ተሻጋሪ የቡና ማኅበረሰብና ደጋፊዎችን ለማፍራት እንዲሁም ከአፍሪካ በጠንካራ ቡድንነት እንዲሁም በበርካታ የደጋፊ ቁጥር ማዋቀር ሌላው ግቡ ነው፡፡

 ኢትዮጵያ ቡና ካሳለፋቸው አራት አሠርታት የምሥረታ ዕድሜና አሁን ለደረሰበት እውቅናና ተወዳጅነት ደጋፊው የጎላ ድርሻ እንዳለው የሚናገሩት አቶ ክፍሌ ይህ ዝም ብሎና ለይስሙላ ሳይሆን ‹‹ደጋፊዎቹ ገንዘባቸውንና ጊዜያቸውን ጭምር መስዋዕት በማድረግ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ለዚህ እንደማሳያ የሚያነሱት ደግሞ ኢትዮጵያ ቡና በ1980ዎቹ አጋማሽ መንግሥት የመዋቅር ለውጥ አድርጎ በነበረበት ወቅት፣ የክለቡ ባለቤት የነበረው የቡና ገበያ ኮርፖሬሽን በፈረሰበት ጊዜ ክለቡም አብሮ እንዳይፈርስ በወቅቱ ከነበሩት የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በመሆን ደጋፊው የከፈለውን መስዋዕትነት ያስታውሳሉ፡፡ ክለቡን የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች በባለቤትነት እስኪረከበው ድረስ ከተጨዋች የደመወዝ ክፍያ ጀምሮ የተለያዩ ወጪዎችን በመሸፈን ረገድም የደጋፊው ድርሻ እንዲህ በቀላሉ የሚነገር አለመሆኑን ጭምር ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ የጎላ ድርሻው በመነሳትም በክለቡ የሥራ አመራር ቦርድ ውስጥ ማኅበሩ በሁለት አባላቱ ተወክሎ ያለበት ሁኔታ መኖሩን የሚናገሩት የደጋፊ ማኅበሩ ፕሬዚዳንት፣ ኢትዮጵያ ቡና ካለፉት አሥራ አምስት ዓመት ጀምሮ በሜዳ ገቢ ደረጃ አብላጫውን ይዞ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡

ክለቡ እንደሌሎች ክለቦች የዋንጫ ባለቤት ባልሆነባቸው ወቅቶች ሳይቀር የደጋፊዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ይታመናል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ አቶ ክፍሌ ‹‹ምንም ምስጢር የለውም ክለቡ የሚከተለው ማራኪ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ነው››  ብለው፣ ሕዝባዊነቱም ለዚህ ትልቅ ቦታ እንዳለው ያስረዳሉ፡፡ በመጨረሻም አቶ ክፍሌ ለደጋፊው መጨመር ሁለተኛው በምክንያትነት የሚጠቅሱት፣ ‹‹የክለቡ ደጋፊዎች ቁጥር ለመጨመሩ አንዱ ሕዝባዊ መሠረት ያለው መሆኑ፣ ከዚሁ ባልተናነስ ደግሞ የደጋፊ ማኅበሩ ክለቡን የሚመለከት ማናቸውም ውሳኔዎች ላይ ተሳታፊ መሆኑ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በችሎታቸው ከፍተኛ ደረጃ የደረሱና የዘመኑ ድንቅ ተጫዋችን የራሱ ያደረገ መሆኑ፣ ከነዚህ ተጨዋቾች ውስጥ ሙሉጌታ ወልደየስ፣ ሚሊዮን በጋሻው፣ መንግሥቱ ቦጋለ፣ አሰግድ ተስፋዬ፣ ካሳዬ አራጌ፣ አሸናፊ ግርማና ዮርዳኖስ ዓባይ የመሳሰሉትን ይዞ የራሱን አሻራ ማስቀመጡ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከክለቡ ደጋፊዎች ምን ይጠበቃል? ለሚለው ነጥብ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፣ ‹‹እስከዛሬ በነበረው ሁኔታ የክለቡ ደጋፊዎች ለክለባቸው ባላቸው የፀና ፍቅር የአካል ጉዳትና ለተለያየ ማኅበራዊ ቀውሶች የተዳደረጉ አሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከክለቡም አልፎ እግር ኳሱን መውደድ ነው፤›› ብለው ከዚህ ጎን ለጎን የክለቡን ዕድገትና ውጤቱን ለሚጎዳ ነገር መስዋዕትነት ለመክፈል የተዘጋጀ ደጋፊ መሆኑ፣ ሆኖም ለአገሪቱ እግር ኳስ ሲባል መቻቻሎችን ለመፍጠር በሚደረጉ ማናቸውም ተግባር ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑንና በዚህ አርአያነት ባለው ተግባሩ ወደፊትም እንደሚቀጥልበት የፀና እምነታቸው መሆኑን ይናገራሉ፡፡

‹‹በምንገኝበት ዘመንና በዘመናዊ እግር ኳስ ውስጥ የገንዘብ አቅም ዋናው ጉዳይ ነው፤›› የሚሉት አቶ ክፍሌ፣ ‹‹በዚህ ረገድ የአገሪቱ እግር ኳስ እጅግ ኋላ ቀር ነው›› ይላሉ፡፡ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ ሌት ተቀን እየተጋ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና በቅርቡ በኢትዮጵያ ክለቦች ታሪክ የመጀመሪያ የሆነ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ የስፖንሰርሺፕ ስምምነት ከሐበሻ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ጋር ያደረገውን ስምምነት በዋቢነት ያስቀምጣሉ፡፡ ለዚህም ትልቁን ድርሻ ለተወጡት የክለቡ ኃላፊዎች ያላቸውን ልባዊ ምስጋና በማቅረብ አቶ ክፍሌ አስተያየታቸውን አጠቃለዋል፡፡

******

የግማሽ ማራቶን ውድድር በሰበታ ይካሄዳል

  • በዘንድሮ ውድድር የሚሳተፉ ክለቦች ቁጥር ቀነሰ

በዳዊት ቶሎሳ

ዘጠነኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር እሑድ የካቲት 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስታወቀ፡፡

አዋሽ ድልድይ መነሻውን አድርጎ መድረሻውን ዲማ ፍላሚንጎ የአበባ እርሻ ፋብሪካ እንደሚያደርግ የገለጸው ፌዴሬሽኑ ውድድሩ የካቲት 18 ቀን 2008 ዓ.ም. እንግሊዝ ካርደፍሲቲ ለሚደረገው የዓለም ግማሽ ማራቶን ውድድር አገሪቱን ወክለው የሚወደዳሩ አትሌቶች ለመምረጥ ቀዳሚ ግቡ እንዳደረገ አስረድተዋል፡፡

ሰባት የክልልና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም 21 ክለቦች የሚሳተፉ ሲሆን፣ 383 ወንድ፣ 123 ሴት አትሌቶች እንደሚወዳደሩም ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

ለአሸናፊ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች ለቡድን አሸናፊዎች የዋንጫ ሽልማትና በግል ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ለሚወጡ አትሌቶች ከ10,000 እስከ 1,000 ብር እንዲሁም ከአንድ እስከ ሦስተኛ ለሚወጡ አትሌቶች በሁለቱም ጾታ የሜዳሊያ ሽልማት ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡

በውድድሩ ከሚሳተፉት ታዋቂ አትሌቶች መካከል አበራ ኩማ፣ ፀጋዬ ከበደ፣ አፀዱ ፀጋዬና እንዲሁም በሴቶች ሶሌ አቱራ፣ ነፃነት ጉደታና ሌሎችም እንደሚገኙ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ግማሸ ማራቶን ላይ የሚሳተፉት ክለቦች ቁጥር ከአምናው ጋር ሲነፃፀር በቁጥር ያነሰ ሆኗል፡፡ እንደፌዴሬሽኑ መግለጫ በዚህም መሠረት በዘንድሮ ውድድር የክለቦች ቁጥር ከ32 ወደ 21 ዝቅ ብሏል፡፡

የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ እንደገለጹት፣  በዘንድሮ ውድድር ላይ ለክለቦች ቁጥር መቀነስ ክለቦቹ በተገቢው መንገድ አለመዘጋጀትና የምዝገባ ወቅትን አለማክበር እንደ ምክንያት አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም የክልሎች በርቀቱ ያለመሳተፍና የአንዳንድ ክለቦች ወጣ ገባ ማለት ወይም መሠረት ማጣት የችግሩ መንስዔ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል፣ ትግራይና ድሬዳዋ ያልተሳተፉ ክልሎች መሆናቸው ተጠቅሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግማሸ ማራቶን ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ በየዓመቱ አልፎ አልፎም በየሁለት ዓመቱና አንዳንዴም ከዓለም የግማሽ ማራቶን የውድድር መርሐ ግብር ጋር እንዲጣጣም በማድረግ የተለያዩ ስያሜዎችን በመያዝ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ወጥ ስያሜ ተሰጥቶት እንደ አዲስ ‹‹የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን›› በሚል እየተካሄደ ይገኛል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...