Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

​‹‹ኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዋጋ የምትተምንበት የሕግ ማዕቀፍ የላትም››

/ ኢንጂነር ውብሸት ዥቅአለ፣ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት

ኢትዮጵያ ከዓመታዊ በጀቷ 60 በመቶ የሚሆነውን በኮንስትራክሽን ሥራዎች ላይ ታውላለች፡፡ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማኅበር በቅርቡ ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ይኸው ተገልጿል፡፡ ይህም የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያመለክት ነው፡፡ ከአገር በጀት 60 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚወስደው የዚህ ዘርፍ አጠቃላይ ገጽታ ሲታይ ግን ብዙ ክፍተቶች ያሉበት፣ ተደጋጋሚ ጥያቄዎች የሚቀርቡበት፣ ለሙስና ተጋላጭነቱም ከፍተኛ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ለዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያት ተደርገው ከሚጠቀሱት ውስጥ ኢንዱስትሪው በዘመናዊ፣ በሙያዊና በሥነ ምግባራዊ ክንውኖቹ ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱ ነው፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሳታፊ በመሆን ከሚታወቁ ጥቂት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ምሁራን መካከል አንዱ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት / ኢንጂነር ውብሸት ዥቅአለ ናቸው፡፡ ኢንዱስትሪው ብዙ መስተካከል ያለባቸው ጉዳዮች አሉት የሚሉት / ኢንጂነር ውብሸት፣ ካላቸው የረዥም ጊዜ ልምድ በመነሳትም መፍትሔውን ያስቀምጣሉ፡፡ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው መስክ መፍትሔ ሊሆን ይችላል በተባለው በጥቅል የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ማኔጅመንት መስክ፣ በዘርፉም እያከናወኗቸው ስለሚገኙ ተግባራት / ኢንጂነር ውብሸት ከዳዊት ታዬ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ በትምህርትዎ ገፋ ብለው እንደሄዱ፣ በዘርፉ በተለያዩ የሥራ መደቦች ላይ እንደሚሳተፉ ይነገራል፡፡ ስለ ራስዎና በሙያዎ አከናውኛለሁ ስለሚሉት ተግባር በአጭሩ ይንገሩን?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- የመጀመሪያ ዲግሪዬን የሠራሁት በሲቪል ምሕንድስና ነው፡፡ የማስትሬት ዲግሪዬን በዩናይትድ ኪንግደም በስትራክቸራል ኢንጂነሪንግ፣ የዶክትሬት ዲግሪዬን ያገኘሁት ደግሞ በኖርዌይ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ማኔጅመንት ነው፡፡ በዚህ ሙያ ውስጥ በባለቤት ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት ኮምሽን በነበረበት ጊዜ ለሁለት ዩኒቨርሲቲዎችና ከአሥር ለሚበልጡ ኮሌጆች የተለያዩ መገልገያ ተቋሞቻቸውን መንገድ፣ የሕንፃ፣ የውኃ አቅርቦትና የመሳሰሉትን የሚያስተባብር ቢሮ ውስጥ ነበር የምሠራው፡፡ እዚህ ቢሮ ውስጥ ከተራ ዲዛይን አድራጊነት እስከ ዝቅተኛው ተቆጣጣሪነት መደብ ከዚያም እስከ ቢሮ አስተዳደር ባለው እርከን ሠርቻለሁ፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ከጀማሪ መምህርነት እስከ ተባባሪ ፕሮፌሰር ደረጃም ደርሻለሁ፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰር ደረጃ ለመድረስ የሚያስፈልገውን አሟልቻለሁ፡፡ የሚጠበቀው የማጽደቅ ሥርዓቱ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የኮንስትራክሽን ዘርፍ አቅም ግንባታ ፕሮግራም የሚባለውንና በአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ሥር በነበረው ተቋም ውስጥ ለአንድ ዓመት ሠርቻለሁ፡፡ ለምሕንድስና አቅም ግንባታ ቢውልዲንግ ፕሮግራም መፈጠር ዋናውን ሥራ ከሠሩት አንዱ ነኝ፡፡ በዚህ ሥራ የትምህርት ማሻሻያ፣ የጥራት መሠረተ ልማት ማሻሻያ፣ የግሉ ዘርፍ ልማትና የምሕንድስና ቴክኖሎጂ ማሻሻያ በሚፈጠርበት ጊዜ ከጀርመኖች ጋር በመሆን ዋና ተዋናይ ነበርኩ ማለት እችላለሁ፡፡ ከዚህም ሌላ በሁለተኛው ዙር ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች ሲቋቋሙ በከፍተኛ ትምህርት ዋና መምሪያ ሥር በነበረው ፊሲካል ፕላን ማስተባበሪያ ውስጥ ጥሩ ሚና ተጫውቻለሁ፡፡ ከዚህ ውጭ በሥራው ዓለም በአራት ዋና ዋና መስኮች ላይ ተሰማርቼ እሠራለሁ፡፡ አንደኛው እንደ ስትራክቸራል መሐንዲስነቴ በዚያ እሠራለሁ፡፡ ሁለተኛ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት አገልግሎት ነው፡፡ ከሌላው በበለጠ የምታውቅበት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ሥራ ነው፡፡ በዚህ ራሱን የቻለ ዕውቅና አለኝ፡፡ ይህ ትልቁና የመጨረሻው ደረጃ ነው ማለት ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የውል ግዴታ የኮንስትራክሽን ግዥ ላይ የሚነሱ ግጭቶች አፈታት ባለሙያ በጣም ጥቂቶች ነን፡፡ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከፈረንጆች ይልቅ ሆነን የምንሠራ ኢትዮጵያውያን ለማሠማራት ባቀደበት ጊዜ ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰዎች መካከል አንዱ ነኝ፡፡ በተለይ በግጭት አፈታት ባለሙያነት ኢትዮጵያ ውስጥ የመጀመሪያው ነኝ ማለት ነው፡፡ 14 ፕሮጀክቶችን በዚህ ረገድ ለማስተዳደር ሞክሬያለሁ፡፡ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ተቋማዊ ይዘት እንዲኖራቸው፣ ዘመናዊ አሠራር እንዲላበሱ ከማድረግ አኳያ ቋሚ አማካሪ በመሆንና ሥልጠና በመስጠትም የምሠራባቸው አምስት ድርጅቶች አሉኝ፡፡ ሌላኛው የምታወቅበት ሥራ ይኼው ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት መስክ እስከ አምና ድረስ ብቸኛው የዶክትሬት ባለሙያ ነበርኩኝ፡፡ አፍሪካ ውስጥም ትንሽ ነን፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ሁለት ቢበዛ ሦስት ዶክተሮችን እያገኘች ነው፡፡ ስለዚህ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ሙያ እያደገ ነው ማለት ይቻላል፡፡ 

ሪፖርተር፡-  ከኮንስትራክሽን ነክ ትምህርቶች ባሻገር በሌሎች ትምህርት ዘርፎችም ተጨማሪ ዲግሪዎች አሉዎት ይባላል?

/ ኢንጂነር ውብሸት– አዎ፡፡ ሁለት ትምህርቶችን ተምሬያለሁ፡፡ አንደኛው በሕግ  ዲግሪ አለኝ፡፡ ሕግ እንድማር ያነሳሳኝ እንግዲህ በግጭት አፈታትና በውል ግዴታ ላይ በምሠራበት ጊዜ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በአደራዳሪነትና በአስታራቂነት ከሕግ ባለሙያዎች ስለምንገናኝ ከእነሱ እኩል ብቁ ሆኖ ጉዳዮችን ለማየትና በገለልተኝነት ጥሩ ፍትሕ ለመስጠት የሚያስችል አቋም እንዲኖረኝ ፍላጐቴ ስለተነሳሳ ነው ሕግ የተማርኩት፡፡ በቅርቡ ደግሞ በትምህርት መርጃ ወይም በፔዳጎጂ ከፍተኛ ዲፕሎማ ወስጃለሁ፡፡ መምህርም ስለሆንኩ የማስተማር ሥራ በትንንሽ ጥረቶችና ኮርሶች ከሚሆን  የተሻለ የማሰተማር ዘዴ ማወቅ ይገባል በማለት የወሰድኩት ነው፡፡ በተለይ በመንገድና ሕንፃ ዘርፍ ላይ ሠርቻለሁ፡፡ በባለቤትነትም በአማካሪነትም በሥራ ተቋራጭ ደረጃ ሠርቻለሁ፡፡ ውኃው ላይ ጥሩ ዕውቀት አለኝ፡፡ እንደ መንገድና ሕንፃ ሥራው የሰፋ አይደለም፡፡ አምስተኛው ሥራ እንግዲህ ምርምር፣ ማማከርና ገምጋሚነት ነው፡፡ ሙያዎቼ በአጭሩ እነዚህ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ባለሙያዎች ማኅበር መሥራችና ፕሬዚዳንት ነዎት፡፡ ይህ ማኅበር እንዴት ተመሠረተከሌሎች ማኅበራት ምን ይለየዋል?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- በዓለም ላይ ሦስት ዓይነት ማኅበራት አሉ፡፡ እኛም ጋ እንደዚሁ ነው፡፡ አንደኛው የባለሙያዎች ማኅበር ነው፡፡ ሁለተኞቹ የቢዝነስ ማኅበራት የሚባሉት ናቸው፡፡ ሦስተኞቹ የብዙኃን ማኅበራት የሚባሉት እንደ የወጣቶች ማኅበር ያሉት ናቸው፡፡ የእኛ ማኅበር የሚመደበው የባለሙያዎች ማኅበር በሚለው ውስጥ ነው፡፡ ከተቋቋመ ስድስት ዓመቱ ነው፡፡ እስካሁን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ነኝ፡፡

ሪፖርተር– ማኅበራችሁ እስካሁን ምን ሠርቷልበተጨባጭ ያስገኘው ውጤትስ እንዴት ይገለጻል?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂና ማኔጅመንት በዓለም ደረጃ የሚታወቀው ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት በሚባል ሙያ ነው፡፡ እኛ ማኅበራችንን ኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንት ብለነዋል፡፡ በአንዳንድ አገሮች ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግና ማኔጅመንት ይሉታል፡፡

በአንድ ሙያ ተመርቆ ሲወጣ የራሱ የሆነ የሙያ ማኅበር ያስፈልገዋል፡፡ የሙያ ማኅበራት ዓላማዎቹ ሁለት ናቸው፡፡ አንደኛው ሙያውን ማሳደግ ነው፡፡ ሙያውን በሥነ ምግባር መምራት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ባለሙያውን በሙያው ሥርዓት እንዲመራ ማስቻል ነው፡፡ ሥነ ምግባሩ እዚህም ይመጣል፡፡ ከዚህ በተረፈ የባለሙያውን መብት ሊያስከብሩ የሚችሉ፣ የባለሙያ ግዴታ የሚጥሉ የተቆጣጣሪ ማዕቀፎች በሚኖርበት ጊዜም ይህንኑ የሚያይ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንትን ከሙያና ከባለሙያ አኳያ የሚያይ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን በሙሉ ይዘን እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት አስፈላጊነት ተደጋግሞ ተገልጿል፡፡ አስፈላጊነቱ ምን ያህል ነውየተለየ አሠራርስ ያመጣል?

/ ኢንጂነር ውብሸት– ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት የስድስት ነገሮችን ነው የሚያስተዳድር ነው፡፡ ኢንዱስትሪውን ይመራል፡፡ ኢንዱስትሪውን ይመራል ሲባል ሦስት ጉዳዮችን በተመለከተ ነው፡፡ እነሱም በአስተዳደር፣ በቁጥጥር ማዕቀፍና በአቅም ግንባታ ነው፡፡ ከዚያ በኋላም የኮንስትራክሽን ፕሮግራምን ያስተዳድራል፡፡ ይኽም ለምሳሌ የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም፣ የከፍተኛ ትምህርት ልማት ፕሮግራም፣ የጤና፣ የውኃና፣ የእርሻ ዘርፍ ልማት ፕሮግራሞች ውስጥ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት የግድ ሊኖር ይገባል፡፡ በነገራችን ላይ ኮንስትራክሽን በሁሉም ዘርፍ ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ከዚያም ባሻገር የመጀመሪያው የኢንቨስትመንት ክፍል ነው፡፡ እሱ ከተሠራ በኋላ ነው ቢዝነሱ የሚመጣው ወይም ልማቱ የሚመጣው፡፡ ስለዚህ የኮንስትራክሽን መድረክ ሁሉንም ነገር ይጐትታል፡፡ ስለዚህ ማነቆ ነው ማለት ነው፡፡

የልማት ፕሮግራሙም ሲቀየስ የኮንስትራክሽን ክፍል ስላለው በጊዜው፣ በትክክል ሊሠራ የታሰበው፣ ልናሠራበት የምንፈልገው የአሠራር ሥርዓት፣ ዋጋውና ጊዜው ካልተተመነ ሊያስከትል የሚችለው ችግር ከፍተኛ ነው፡፡ አገራችን ሁሉን ነገር ትናንት ብትጨርስ ደስ ይላታል፡፡ የተፋጠነ ልማት ነው የምትመኘው፡፡ ግን ደግሞ የራሱ ጊዜና ፍላጐት አለው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ነገሮች አጣጥሞ አቅም በመገንባት ተጠቃሚነትን ማምጣት የተባለውን በደንብ አይተህ፣ አዋጭነቱን በደንብ ዓይተህ የምትሠራበትን ሥራ ማስተዳደር ይፈልጋል፡፡ ወደታች ሲወርድ ደግሞ ፕሮጀክቶች ይመጣሉ፡፡ ስለዚህ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክትን ማስተዳደር ያስፈልጋል፡፡ በቴክኖሎጂ የሚመራ በመሆኑም ይህንንም ማስተዳደር ያስፈልጋል፡፡

የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ማኔጅመንት፣ የኮንስትራክሽን ፕሮግራም ማኔጅመንት፣ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ማኔጅመንት፣ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂ ማኔጅመንትና የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች ማኔጅመንትን አንድ ላይ አድርገህ ስታስተዳድርና ኢንዱስትሪው የተሻለ ደረጃ ይርሳል ማለት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲህ ባለ ዘመናዊ የአሠራርና የአመራር ዘዴ መቃኘት አለበት ከተባለ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲተገበር ማኅበራችሁ ምን ሠርቷልይህንን ለመተግበር ዕድሉን አግኝተናል ብላችሁ ታምናላችሁለምሳሌ የቤቶች ፕሮጀክት አለ፡፡ ይህ ፕሮጀክት መሠራት ያለበት እንዲህ ነው ብላችኋልሙያዊ ድጋፋችሁ ምን ድረስ ነው?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- ማኅበሩ ስድስት ዓመቱ ነው፡፡ በስድስት ዓመቱ ምን ሠራ የሚለውን በመጀመሪያ ልመልስና ወደ አንተ ጥያቄ እመጣለሁ፡፡ ማኅበሩ በተመሠረተ  በመጀመሪያው ዓመት የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ምንድን ነው? የሚለውን ይዘን ቀረብን፡፡ አዲስ ስለሆነ ይህንን ማስተዋወቅ የመጀመሪያ ተግባራችን ሆነ፡፡ ይህንን አድርገናል፡፡ ጠቀሜታውን አስረድተናል፡፡ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ሁሉንም ወገን የሚጠቅም ስለመሆኑ የማስተዋወቅ ሥራ ሠርተናል፡፡

በዘርፉ ለባለሙያዎቻችን የሥራ ዕድል መፍጠር ችለናል፡፡ መንግሥት ስለኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ግንዛቤ መውሰድ ጀምሯል፡፡ የኮንስትራክሽን ችግሮችና የምንሠራበት ቴክኒክ ሳይሆን ማኔጅመንቱ ነው ወደሚለው እንዲያጋድልና እንዲያውቅ የማድረግ ሥራ ሠርተናል፡፡ ይቺ የመጀመሪያዋ ቁልፍ ነገር ነበረች፡፡ ይቺን የሠራናት በእ.ኤ.አ. 2010 ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በዓመቱ የአሥር አገሮችን ልምድ ወስደን ከሥር የታች አመራሩን የአስተዳደር ማዕቀፍ፣ የቁጥጥር ማዕቀፉን፣ አደረዳጀቱን፣ የሕግ ማዕቀፎቹን ካላየን በስተቀር፣ ከላይ ወደታች የሚወርድ ነገር እስካላበጀን ድረስ ወይም እላይ ላለው አካል በደንብ ግንዛቤ እስካልፈጠርን ድረስ ዕድገቱ ይጫጫል የሚል ግንዛቤ ነበረን፡፡ ስለዚህ የአሥር አገሮችን ልምድ ወስደንና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዴት ነው የሚመራው? አደረጃጀቱ እንዴት ነው? ብለን እነዚህን ዋና ችግሮቹን ሊፈታ የሚችል አመራርና አደረጃጀት ምን ይመስላል? የሚለውን ያዝንና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ምሥረታ የሚል ርዕስ ያለው ትልቅ ኮንፍረንስ አደረግን፡፡

አንዳንድ አገሮች የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ምክር ቤት ይሉታል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ቦርድ ይሉታል፡፡
ሌሎቹ ደግሞ ብሔራዊ ኮንስትራክሽን ምክር ቤት ቦርድ ብለው ይጠሩታል፡፡ ከዚህ አንፃር ከሠለጠነው ዓለም፣ መካከለኛ ገቢ ካለውም እንደኛ ካሉ አገሮችም ያለውን ልምድ ዓይን ነው የቀረጽነው፡፡ ለምሳሌ ታንዛንያ ከእኛ በፊት ብሔራዊ የኮንስትራክሽን ምክር ቤት አላት፡፡ ስለዚህ ይህ እንዴት መመራት አለበት ስንል የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ አጋርነትን በመፍጠር መሆኑን ግንዛቤ ፈጠርን፡፡ ስለዚህ በሁለቱ አጋርነት የሚመራ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ልማት ያስፈልጋል የሚል ትልቅ ኮንፈረንስ እንዲካሔድ አደረግን፡፡ በዘርፉ በተለያዩ የሥራ መስክ ላይ ያሉ ባለሙያዎችና ከኢንዱስትሪው ጋር ግንኙነት ያላቸው ማኅበሮች ተካፈሉ፡፡ ይህ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽኑ አካል እንዲሆን በጣም ግፊት ተደርጎበት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ዕቅድ አምና ሲቀረፅም እንደ አንድ መሠረታዊ ይዘት የተወሰደውና በቅርቡ ባካሄድነው ዓውደ ጥናትም የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ያረጋገጠልን ይህንን ጽሕፈት ቤት ለማቋቋም በመንግሥት እንደፀደቀ ነው፡፡ ይኼ ግብዓት ብዙ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ስለዚህ ይህ በማኅበሩ የተሠራ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው መመራት ይኖርበታል ብላችሁ ያቀረባችሁት ሐሳብ  ምንድነው?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- የዚህ አገር ኮንስትራክሽን አሠራር አንዱና ትልቁ ችግር የግንባታው ባለቤት ለብቻው ያቅዳል፣ ፕሮግራምና ፕሮጀክት ያወጣል፡፡ ከዚያ በኋላ ዲዛይነር ይፈልግና ዲዛይን አድርግልኝ ከዚያም የጨረታ ሰነድ አዘጋጅልኝ ይላል፡፡ ጨረታው ይወጣና ሥራ ተቋራጭ ይመጣል፡፡ በሁለቱ መካከል በሚታየው ጐደሎ ነገር ምክንያት ባለቤት ጭቅጭቅ ውስጥ ይገባል፡፡ ለጊዜ መርዘምና ለመሳሰሉት ችግሮች አንዱ ምክንያት ይህ ነው፡፡ ይህ ባህላዊና የተበጣጠሰ የአቅርቦት መንገድ ነው፡፡ ይህንንና ‹‹ዲዛይን ቢድ ቢልድ›› እንለዋለን ዲዛይንና ጨረታ ግንባታ ለየቅል እንደማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር በዓለም ላይ የተተወ ነው፡፡ ለአንዳንድ አገሮች ይሠራል፡፡ ለሁሉም ግን አይሆንምና ዓለም ምን አለው? ስንል አማራጭ የማቅረቢያ ሥርዓት አለው፡፡ አማራጭ የፕሮጀክት መንገዶች አሉት፡፡ እነዚህ ምንድን ናቸው ብለን በዓለም ላይ ያሉትን ልምዶች በስድስት መንገዶች ይዘን ቀርበናል፡፡

የእያንዳንቸው ጥቅምና ጉዳት እንዲታይ አድርገናል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ እየገባና እየወጣ ከዲዛይን ጨረታ ግንባታ ጋር እየተጋጨ ያለው ዲዛይን ቢውልድ  የአቅርቦት መንገድ ነው፡፡ ተርንኪ የምንለው ወይም ዲዛይኑንም ግንባታውንም አንድ ላይ መሥራት ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ ኅብረት ሕንፃ እንደተሠራበት ዓይነት መንገድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃም በተመሳሳይ ነው የሚሠሩት፡፡ እንደነዚህ ያሉ ፕሮጀክቶች ያላቸውን ክፍተቶች ለመሙላት የሚያስችል ነው፡፡ ሌሎች አሠራሮችስ እንዴት ይምጡ የሚለውን አስገንዝበንበታል፡፡

ሪፖርተር፡- ዲዛይንና ግንባታ አንድ ላይ መስጠት የሚያሳየው ክፍተት ምንድነው?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- የሕግ ማዕቀፍ ጥራቱ አንዱ ነው፡፡ ጥሩ ጎኑም አግኝተናል፡፡ ጉዳቱንም እንዲሁ፡፡ እንዴትስ ውጤታማ መሆን አለባቸው ለሚለው ሌሎችም አማራጮች አቀረብን፡፡ እሱን ይዘን ዲዛይንና ግንባታ ላይ ትኩረት ሰጥተን ሐሳቡን ለመንግሥት አቀረብን፡፡ ከዚያ በኋላ የዲዛይን ቢውልድ መንገድ እንደ እንጉዳይ ተበራከተ፡፡ ይህ ደግሞ ሌሎች እንዲመጡ በር ከፈተ፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ትልቁን ቁልፍ ነገርና ጭቅጭቅ ያመጣው አፈጻጸሙ ነበር፡፡ ችግሩ አፈጻጸም ከሆነ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንትን መገንባት ማድረግ ነው፡፡ ኩባንያዎችና ባለሙያዎችም እንዲገነዘቡት አደረግን፡፡ ከዚያ ነገሩን አሁን ካለው ሒደት ጋር አስተያየነው አገር የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አውጥታ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ልግባ ብላ እየተንደረደረች ከሆነ እያንዳንዱ ዘርፍ ለዚያ ግብዓት ነው፡፡

የዘርፉ መዋቅር ካልተለወጠ ካላደረገ አገር አትለወጥም፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዴት ነው መለወጥ ያለበት ብለን መጨነቅ ጀመርን፡፡ ሰሞኑን ያደረግነውም ዓውደ ርዕይ ይህንን ጥያቄ ሊመልስ በሚችል ደረጃ የተዘጋጀ ነው፡፡   የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትራንስፎርማሽን ከየት ወዴት? ይህም በአስተዳደር፣ በቁጥጥር መዋቅር፣ በሕግ ማዕቀፎችና በመሳሰሉት ከየት ወዴት ይሂዱ ብለን ያደረግነውና አዲስ ከተቋቋመው የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ጋር አብረን እንሥራ ብለን የሠራ ነው፡፡

አዲስ እንዲመጣ ያቀረብነው ሐሳብ ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ግብዓት ይሆናል፡፡ እኔ የመጀመሪያ የዶክትሬት ዲግሪዬን ሰሠራ በመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራምና በከፍተኛ ትምህርት ልማት ፕሮግራም 108 ፕሮጀክቶችን አጥንቼ፤ ችግሮቹ ምንድንናቸው ብዬ ነበር፡፡ አሁን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ተብሎ የወጣውንና የእኔን የመመረቂያ ጽሑፍ ብታነበው ምናልባት እነዚህ ነገሮች አንድ ናቸው ልትል ትችላለህ፡፡ በጥቅል ሲታይ ግን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው መለወጥ ያለበት ቀድሞ ነው፡፡ ለምን ቢባል ኮንስትራክሽን ዘርፍ የመጀመሪያው የኢንቨስትመንት መስክ ስለሆነ ነው፡፡ ስለዚህ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ባለሙያዎች ዋናው ሥራቸው ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ማስተዳደር ነው፡፡ ኮንስትራክሽን ፕሮግራሙን መምራት ነው፡፡ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን የመምራት ሥራቸው ዲዛይን ማድረግ አይደለም፡፡ ስለዚህ የኮንስትራክሽን ቴክኖሎጂውን እንዴት መርተን እናሻሽላለን? ለሚለውና ከየት ወዴት መሄድ እንዳለበትም አሳይተናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ትልቅ ዘርፍ ነው፡፡ ብዙ የሚባልለትም ነው፡፡ እስከዛሬ ያለውን አካሄድ እንዴት ያዩታልኢንዱስትሪው ምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አሁን ባለበት ደረጃ በአስተዳደር፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ለመሥራት ዝግጅት ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ወደዚህ ለመግባት 24 ዓመት ፈጀበት ማለት ነው፡፡ ከ11 ዓመታት በፊት ማድረግ የምንችልበት ዕድሎች ነበሩ፡፡ ብናደርገው ኖሮ የት ይደርሳል የሚለውን ማየት ይጠይቃል፡፡ ይህ ማለት ዘገየ ማለት ሳይሆን አሁንም ተረባርበንበት ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡  ቁልፍ ነገር ነው፡፡ ሁለተኛ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በፕሮግራም ደረጃ ሲታይ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በፕሮግራም ደረጃ ዝቅተኛ ሲባል እንዴት ነው?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- ፕሮግራም ስንል የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራም ዓይነት ነው፡፡ የጤና ዘርፍ ልማት ፕሮግራም እንደምንለው ዓይነት ነው፡፡ እነዚህ ፕሮግራሞች ሲቀረጹ የባለቤት ፍላጐት ብቻ ያለበት ስለሆነ ተፅዕኖውም ከፍተኛ  ነው፡፡ ለምሳሌ የግንባታ ጊዜን እንውሰድ፡፡ እዚህ አገር በትክክለኛ ሣይንሳዊ መንገድ የአንድ ፕሮጀክት የግንባታ ጊዜ አይወሰንም፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት አይወሰንምእናይ የለም እንዴኮንትራት በጊዜ ገደብ ይቀመጣል አይደለም እንዴ?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- በትክክለኛው መንገድ አይደለም የሚወሰነው፡፡ ስለማይወሰንም ዘገየ ብትለው፣ አልዘገየም ብትለው ምንም የሚያነጋግር ነገር የለም ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግን ኮንትራት ሲፈረም በዚህን ጊዜ ሥራው ይጠናቀቃል ተብሎ ነው፡፡ ውሉም በዚሁ መሠረት ይፈጸምና ወደ ግንባታ ይገባል፡፡ ዘገየ ፈጠነ የሚባለውም ለዚህ አይደል እንዴ?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- ስለፈረምክ ብቻ ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡ ሁለት የማያውቁ ሰዎች ትክክለኛ ባልሆነ ጊዜ ላይ ቢፈራረሙ ምንም ጥቅም የለውም፡፡ ግን ሳይንሳዊ ጊዜው ወይም ግንባታው ሊፈጅ የሚችለው ጊዜ በሳይንሳዊ መንገድ የሚወሰንበት አካሄድ አለ፡፡ ስለዚህ ወርደን ይሄ ፕሮጀክት የዘገየው በኮንትራክተሩ ጥፋት ነው፣ ይህኛው ሥራ የተበላሸው በሠራተኛው ችግር ነው፣ ያኛው ደግሞ በእከሊት ምክንያት ነው ብንል ምንም ዋጋ የለውም፡፡ መሠረታዊው ነገር ፕሮግራሙ ሲቀረጽ ሳይንሳዊና ሊታመኑ የሚችሉ የኮንስትራክሽን ባለሙያዎች በትክክል ተምነውታል ወይ? የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ይህ ቁልፍ ነገር ነው፡፡ በዚህ ደረጃ ካየናት አገራችን ዝቅተኛው ደረጃ ላይ ናት፡፡ ሁለተኛው አስገራሚ ነገር እዚሁ ላይ ዋጋ ይተመናል፡፡ በምንድነው የሚተመነው? ስንል ግምቱ የሚሠራው እንዲሁ በግምት ነው፡፡ አንዳንዴም በፍላጐት ዋጋ ይተመናል፡፡ ይህ ሊሆን አይችልም፡፡ መጀመሪያ በትክክል መተመን አለበት፡፡ የራሱ የመተመኛ መንገድ አለ፡፡ በነገራችን ላይ የኮንስትራክሽን ግንባታ ዋጋ ተመንን በተመለከተ የሚያሳዝንህ ነገር ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች የኮንስትራክሽን ዋጋን የምትተምንበት የሕግ ማዕቀፍ የሌላት መሆኗ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለግንባታዎች ዋጋ ትመና የሚያስፈልግ ሕግ አለ ማለት ነውአገሮች ይጠቀሙበታል?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- በሁሉም አገር አለ፡፡ እዚህ አገርም እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማምጣት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት እንደ መንገድ ልማት ያሉ ፕሮግራሞች ላይ የተወሰኑ ባለሙያዎች ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ባለሙያዎች ዋጋውን ይዘው በምን አባዝተው ይሥሩት? በካሬ ሜትር ይህንን ያህል አባዛው ከማለት በቀር ትክክለኛው ሕግ የለም፡፡ የተወሰኑ ጅምሮች አሉ፡፡ ነጥሮ የወጣ ነገር ግን የለም፡፡ ፕሮግራሙ ሲቀረጽ እዛ ጋር የሚመጣው ውሳኔ በኋላ ላይ ፕሮጀክቶቹ ሲሠሩ ወደኋላ ቀረ፡፡ ትክክል ናቸው አይደሉም ለማለት ከጅምሩ ፕሮግራሙ መስተካከል አለበት፡፡ የፕሮጀክት ማኔጅመንት የፕሮጀክቱን የማብቂያና ማጠናቀቂያ ጊዜ የምንለካበት ሥርዓት የግድ ያሻዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ሌላው ችግር በቴክኖሎጂ ካለመታጠቅ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑም እየገለጻችሁ ነው፡፡

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- ቴክኖሎጂው ላይ በክምችትና በግንባታ ቦታ ነው የምንሠራው፡፡ ዘጠና ዘጠኝ በመቶው ታች ነው ያለነው፡፡ መሠረታዊው ችግር ጉልበት ተኮር የሚባለው ጽንሰ ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ጉልበት ተኮር የሚባለው ነገር በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ትክክል ነው፡፡ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ይጠቅማል፡፡ ግን የሥራ ዕድል የሚፈጥረው የት ነው? የሚለው ላይ መስማማት ይገባል፡፡ ሳይት ላይ ነው? ወይም ሳይት ላይ ከመድረሱ በፊት ግብዓቱ ላይ ነው? ግንባታዎችን በፍጥነት ማጠናቀቅ ለዕድገት መሠረት ነው፡፡ ስለዚህ ሳይት ላይ በፍጥነት ነው መሄድ ያለበት፡፡ ለእሱ ግብዓት የሚሆኑ ሰንሰለቶች በሙሉ ሌላ ቦታ ልንሠራው እንችላለን፡፡ ጉልበት ተኮርነቱ ሳይጠፋ ማለት ነው፡፡

ይህንን ተግባራዊ የሚያደርጉት ሰዎች ትርጉም ሁሉም ነገር ሳይት ላይ፣ ቤቶች ሳይት ላይ እየተሠራ ሊያሳድገን አይችልም፡፡ ሌሎች አገሮች እኮ 500 ሺሕ ሁለት ሚሊዮን፣ ሦስት መቶ ሺሕ ቤቶች በዓመት ይሠራሉ፡፡ እኛ እኮ እየሠራን ያለነው 10 ሺሕ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- 10 ሺሕ ቤቶች መወሰኑ እርስዎ አሁን ካሉት ጋር ይገናኛል?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- ኮንስትራክሽን በግንባታ ቦታ ላይ ነው ቴክኖሎጂያችን፡፡ ባለሙያዎቻችንና አመራሩ አይገናኙም፡፡ እንዲያውም ኮንስትራክሽን ባለሙያ በጣም ብቁ ነው፡፡ የማናውቀውን ነገር አናውቅም፡፡ ግን ያወቅን ይመስለናል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ነው ያለነው፡፡ ወይም ደግሞ እያወቅን ስንግባባ እንሠራለን፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁለት ነገሮች ተደምረው ነው አመራሩና አሠራሩ የተለያዩት፡፡ ይኼ መቀየር ካልቻለ በባለሙያ የማይመራበት፣ በባለሙያ የማይሠራበት፣ በባለሙያው የዕድገት ደረጃ የማይመጣበት ከሆነ ያለው ይቀጥላል፡፡ ለምሳሌ የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ከጀመርን በአሥራ ሁለት ዓመት ይሆነናል፡፡ እስካሁን ድረስ ከ13 ሺሕ ቤቶች በላይ ሠርተን አናውቅም፡፡ ሒደቱ በዚህ መቀጠል አለበት ወይ? በመንገድም ረገድ ቢሆን በዓመት ከሦስትና ከአራት ሺሕ ኪሎ ሜትር ያለፈ አይደለም፡፡ ስለዚህ በዚህ መንገድ ነው መቀጠል ያለብን?

ይህንን ነው ማየት ያለብን፡፡ የውጭ ኮንትራክተሮች ወይም ኢንቨስተሮች ለምን ዓይነት ፕሮጀክት ነው የሚገቡት፡፡ ከገቡስ እንዴት ነው ቴክኖሎጂውንና ማኔጅመንቱን አስተላልፈው መውጫ ስትራቴጂ የምንቀርጸው? ይህ ሁሉ ታስቦበት ነው መሠራት ያለበት፡፡ ስለዚህ ግልጽ የሆኑ አካሄዶች ያስፈልጋሉ፡፡ አንድ ነገር ቅድመ ዝግጅት ይፈልጋል፡፡ ፕሮግራም ሲቀረጽ ትልቅ ሥራ እንሠራ እንላለን ያልኩህ ለዚህ ነው፡፡ ፕሮጀክቶች ላይ እንዲህ ያሉ ችግሮች አሉ፡፡ ወደ ኩባንያዎች ስንሄድ በአንድ ግለሰብ ወይም እና በቅንጅት ተፅዕኖ የሚያደርጉበት፣ ተቋም ያልተፈጠረበት የኩባንያ ደረጃ ነው ኢትዮጵያ ያላት፡፡ ከዚህ ወደ ተቋምነት በመሄድ ተወዳዳሪ ለመሆን ያለመ የኩባንያ ዕድገት እንዲኖር ነው እንደ ትራንስፎርሜሽን የምንመኘው፡፡  

ሪፖርተር፡- ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ክፍተት ሲታሰብ የባለሙያ ብቃትም ጥያቄ ውስጥ የሚገባበት ጊዜ አለ፡፡ ይህ ለምን ተፈጠረ ይላሉ?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- የባለሙያውም ደረጃ ዕውቀቱን በደንብ የሚያውቅ የሚሠራና ሁልጊዜ በቀጣይነት ራሱን የሚያሳፍግ የሚያደርግ፣ ነው ትራንስፎርም ያድርግ የምንለው፡፡ የዚህን ዓይነት ሥርዓት እስካልፈጠርን ድረስ ተነስተን በሬዲዮና ቴሌቪዥን እያንዳንዷን የምንናገራትና ፕሮጀክቱ ዘገየን እነሱ ናቸው ጥፋተኞች ወዘተ፣ የሚለው ነገር ለእኔ ትርጉም የለውም፡፡ አንዱ ሌላውን መውቀሱና መወነጃጀሉ ለኢንዱስትሪውም ለአገርም ጥቅም የለውም፡፡ ስለዚህ የተጣመረ አካሄድ ይፈልጋል፡፡ ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም ይህንን የተረዳው ይመስለኛል፡፡  

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ብዙ ነገር ይባላል፡፡ ሙስና ያለበት ዘርፍ ነው ይባላል፡፡ በተለይም ግንባታን በወቅቱ አጠናቆ ያለማስረከብ ችግር አለ፡፡ የአሠራርና የማኔጅመንት ችግርም ይታያል፡፡ ዘርፉ ዘመናዊ አሠራርና ማኔጅመንት ያስፈልገዋል የማለታችሁን ያህል የኢንዱስትሪው ተዋንያን ይህንን እየተገበሩ ነውያያችሁትስ ለውጥ አለ?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- አዎ፡፡ እንግዲህ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት በጣም እየታወቀ፣ የራሱን  ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት እስከማለት፣ በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት በማስትሬት ዲግሪ ደረጃ እንዲማሩ ማድረግ፣ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንትን እንደሙያ የመቁጠር፣ ሌሎች ባለሙያዎችም ማስተርሳቸውን በዚህ ለመማር መፈለግ ነገር አለ፡፡ እንቅስቃሴው ይህንን ያሳያል፡፡ ሙያው መከበሩን ያሳያል፡፡ መጥቀሙን ያሳያል፡፡ ከዚያ በኋላ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ አጋርነት ከተመራ ግልጽነትን ያመጣል፡፡ ግልጽነትን አመጣ ማለት ሥነ ምግባር የጎደላቸውን አሠራሮች ለመዋጋት ትችላለህ ማለት ነው፡፡ ሰነድ አያያዝንም ያመጣል፡፡ ሰነድ በአግባቡ መያዝ ሲመጣ ደግሞ ግልጽ የሆነ አሠራርን ያመጣል ማለት ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ ነው ይዞ የሚመጣው፡፡ ለእኔ በሰነድ የተደገፈ፣ ግልጽነት የሰፈነበት፣ ሥነ ምግባሩን የጠበቀ አሠራር የሚመጣው በዚህ መንገድ ነው፡፡ መንግሥትና የሕዝብ ክንፍ ብሎ ነው ያስቀመጠው፡፡ ስለዚህ ሕዝባዊ ናቸው፡፡ የሕዝብ ክንፍ የምንባለው እኛ ነን፡፡ ባለሙያዎች ነን፡፡ የቢዝነስ ማኅበራት ሁሉ የሕዝብ ክንፍ ነው፡፡ ምክንያቱም አደረጃጀት ነው፡፡ በውክልና ነው የሚመጣው፡፡ መንግሥትም በውክልና ነው የመጣው፡፡ የግሉ ዘርፍም አለ፡፡ ስለዚህ የግልና የመንግሥትን አጋርነት ስትፈጥር የሁሉም ፍላጐት ይንፀባረቅበታል፡፡ ይሄ መሠረታዊ ነገር ነው፡፡

ሁለተኛ እዚህ አገር ያለው ትልቅ ችግር የተማከለና ያልተማከ አሠራር ልዩነትን በደንብ የተረዳን አይመስለኝም፡፡ እያንዳንዱ አገር ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ የተጣጣመና ማዕከላዊ ሥርዓት የሆነ ሥርዓት አለ፡፡ ማዕከላዊነት የሚጠላ ነገር አይደለም፡፡ የግዥ አሠራራችን በተጣጣመ መንገድ የተማከለ ሥርዓት ሊኖረው ይገባል፡፡ እንደ አገር የአመራር ሁኔታችንም ስትራቴጂካዊ ጥምረት የክልልና ፌዴራል ብለህ የምትለቀው አይደለም፡፡ ስለዚህ ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ መጣጣም መሆን አለብን፡፡

እርስ በርሳችን አንረዳዳም፡፡ ወደ መካከለኛ ገቢ እንግባ ስንል ከሌላ አገር ጋር ነው የምንወዳደረው፡፡ የውጭ ምንዛሪያችንን እናሳድግ ስንል ከሌላ አገር ነው የምንወዳደረው፡፡ ጨዋታው ከሌላው ጋር አገር ነው፡፡

እኔ የምወዳደረው ከጋና፣ ከኡጋንዳና ከመሳሰሉት እንጂ ከአማራና ከትግራይ ጋር አይደለም፡፡ ይሄ በስትራቴጂካዊ አካሄድ መጣመር የሚመጣበት ስሜት እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ሲታይ የታክቲክና የኦፕሬሽን ደረጃው ያልተማከለ መሆን አለበት፡፡ በዘርፉም ያልተማከለ መሆን አለበት፡፡ ሁሉን በጨረታ ግዥ ነገር ብሎ መኖር አይቻልም፡፡ የፌደራል መንግሥትም እንደዚያ ሆኖ ሊኖር አይችልም፡፡ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም ሊኖር አይችልም፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያለ ትራንስፎርሜሽን ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ ይህን ነው ሰሞኑን ያሳወቅነውና አቅጣጫውንም የሚያሳይ መረጃ የሰጠነው፡፡ ይህንን ከዚህ ወደዚህ ውሰደው ግን እንዴት ይወሰድ ነው የምንለው፡፡

ሪፖርተር፡- በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በተለይ በመንገድ ሥራ በተደጋጋሚ ከሚነሱ ችግሮች አንዱ ዲዛይን ነው፡፡ መንገድ ዘገየ ሲባል ዲዛይኑ ስለተቀየረ ነው ይባላል፡፡ የግንባታ ጥራት ችግርም አሳሳቢ እየሆነ ነው፡፡ በከተሞች ሕንፃዎች ዲዛይንም ላይ ችግሮች አሉ፡፡ እርስዎ ይህንን እንዴት ያዩታል?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- እነዚህ ነገሮች ሊታሠሩ የሚችሉት በቁጥጥር መዋቅርና በኩባንያ ብቃትና በባለሙያ ዕውቀት ማረጋገጥ ነው፡፡ ዲዛይንን እንዲመሠረት ይዘህ ስትሄድ እኛ የምንጠቀምበት ዲዛይን የተለመደው የዲዛይን አሠራር ነው፡፡ ኋላቀር ነው፡፡ የተለመደው የዲዛይን አሠራር ወደ ተጣመረው የግንባታ ዲዛይን አሠራር መሄድ ያስፈልጋል፡፡ አንድ ዲዛይን የሚመራበት የራሱ አተገባበር አለው፡፡ ያንን አተገባበር አጣምሮ መጠቀም አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የቁጥጥር ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ መስታወትን እንውሰድ፡፡ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር የመስታወት ዓይነት አለ፡፡ ከርቴልዎል የሚባለውን ትንሹን ዓይነት ብንወስድ አራት ዓይነት ከርቴልዎል አሉ፡፡

ትንሽ ምሳሌ ብሰጥህ አንደኛው ደረጃ እና የመጨረሻው ደረጃ (በካሬ ሜትር) በአንድ ሚሊዮን ብር ይለያያሉ፡፡ እንግዲህ እንዲህ ዓይነቱን ነገር ትክክለኛ የቁጥጥር ማዕቀፍ ከሌለው የፈለግከውን ታመጣለህ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በጨረታ አነስተኛ ዋጋ ያቀረበ ብለህ አትስጠው ዝቅተኛውን ያመጣልሃል፡፡ ዓይንህን የሚያጠፋ መስታወት ይሰጥሃል፡፡ ካጠፋህ በኋላ ሕግ ታወጣለህ፡፡ ይህ ሲሆን ኢንቨስተሩንም ትጐዳለህ፡፡ የተሰቀለውን መስታወት አውርድ ብትለው ሕዝቡንም አገርንም ትጐዳለህ፡፡ ስለዚህ ቀድመህ መገኘት አለብህ፡፡ የቁጥጥር ማዕቀፍ ቀድሞ መገኘት ይፈልጋል፡፡ ሕግ ከጨረታ ቀድሞ መገኘት አለበት፡፡ ሕጉ በእያንዳንዱ በሚወጣው የደረጃ መሥፈርት መሠረት ቀድመህ መገኘት አለብህ፡፡

ዲዛይን ማለት የምትጠቀምበት የዲዛይን ሥርዓት ማለት ነው፡፡ ቅድም ወደ ኩባንያ ወደ ባለሙያ ይወርዳል ያልኩት ለዚህ ነው፡፡ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ባለሙያ በዚህ ሰዓት ሳይፈተሽ በምቾት ዞን ውስጥ ያለ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህንን አባባል ሊያፍታቱልኝ ይችላሉ?

/ ኢንጂነር ውብሸት፡- ሳይፈተሽና ሳይፈተን ማለት ሙያውን የሚፈትን ነገር የተጠየቀበት ጊዜ የለም፡፡ በምቾት ዞን ውስጥ ይኖራል ማለት ጥሩ ይከፈለዋል፤ ተዝናንቶ የሚኖር ነው ማለት ነው፡፡ ለምን? አመራሩ ካልን በፈጠረው ችግር ምክንያት ማለት ነው፡፡ ከዕውቀት ነፃ በሆነ መንገድ አመራር ይሰጣል፡፡ በልምድ ከሚኖረው ግንበኛና አናፂ ጋር ሥራ ይሠራል፡፡ ባለሙያው አመራር ውስጥ ሊገባ ይገባል፡፡ ባለሙያው እነዚህን ሥራዎች ሊመራ ይገባል፡፡ አለበለዚያ የባለሙያው አለመፈተንና ምቾት ዞን ውስጥ መቀመጥ አገርን ይጐዳል እንጂ ማንንም አይጠቅምም፡፡ በአገር ደረጃ በሙያ ዕውቀት ያላቸውን ሰዎች መጠቀም መቻል የአገርን ዕድገት ያፋጥናል፡፡ ሳይፈለጉ መሀል ሰፋሪ ሆኖ በምቾት ዞን ውስጥ አስቀምጠኸው የምትመራው ከሆነ፣ አገርን እየገደልክ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እዚህ ላይ መሠራትና መታሰብ አለበት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

ሲሚንቶ በዲጂታል መንገድ ለማገበያየት የክፍያ አማራጮች ልየታ ተጀመረ

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሲሚንቶ ግብይትን በዲጂታል መንገድ ለማከናወን...