Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​የኢትዮጵያውያኑ ተሞክሮ በጃፓን ዩኒቨርሲቲዎች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የጃፓን መንግሥት ከአፍሪካ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ላለፉት 20 ዓመታት የቆየና በየአራት ዓመቱ ሲካሔድ የከረመ ጉባዔ በጃፓን ሲያካሒድ ቆይቷል፡፡ በጃፓኗ ዮኮሃማ ከተማ ከሁለት ዓመት በፊት በተካሔደው አምስተኛው የቶኪዮ ዓለም አቀፍ የአፍሪካ ልማት – ቲካድ›› ጉባዔ ወቅት በተወሰነው መሠረት በየአምስት ዓመቱ ሲካሔድ የቆየው የመሪዎች ጉባዔ በየሦስት ዓመቱ ተደርጓል፡፡

በጃፓን ብቻ ሲስተናገድ የነበረውም ከእንግዲህ ለአፍሪካውያንም እንዲደርሳቸውና በዙር ጉባዔውን የማስተናገድ ዕድል እንዲሰጣቸው ጠይቀው በዚያው መሠረት ስምምነት መደረጉን በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሔደው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ወቅት ይፋ ተደርጓል፡፡

በቅርቡ በጃፓን ጉብኝት ያደረጉ ጋዜጠኞችም ስለዚሁ ተገልጾላቸዋል፡፡ በጃፓን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋባዥነት ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከደቡብ አፍሪካ እንዲሁም ከፈረንሣይ የተውጣጡ አምስት ጋዜጠኞች በነበራቸው ቆይታ በጃፓን ከተሞች ተዘዋውረው ጃፓን ከአፍሪካ ስላላት ግንኙነትና ስለምታከናውናቸው የትብብርና የድጋፍ ተግባራት ለመመልከት ተችሏል፡፡

በመሠረተ ልማት ግንባታ መስክ የጃፓን ኩባንያዎች በመንግሥታቸው በሚያገኙት ድጋፍ ታግዘው በአፍሪካ ፋብሪካዎችን፣ ወደቦችን፣ መንገዶችንና ሌሎችንም እየገነቡ ይገኛሉ፡፡ የኬንያውን ሞምባሳ ወደብ ማስፋፊያን የሚገነባው የቶዮታ ግሩፕ ኩባንያ አካል የሆነው ቶዮታ ቱሾ የተባለው ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡ በናይጄሪያ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በግብፅ፣ በሞዛምቢክና በሌሎችም አገሮች የጃፓን ኩባንያዎች እንቅስቃሴ ጎልቶ ይታያል፡፡

በአንፃሩ በኢትዮጵያ ይህ ነው የሚባል የጃፓን ኩባንያ ባይኖርም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ አሉ፡፡ ከዚህ ይልቅ በኢትዮጵያ የጃፓን ትኩረት በመሠረተ ልማትና በሰው ሀብት ልማት መስክ ላይ ያነጣጠረ ይመስላል፡፡ ለዚህም ማሳያው በጃፓን ዕርዳታ የተገነቡ ድልድዮች፣ መንገዶች፣ አነስተኛ ትምህርት ቤቶች፣ የውኃ ጉድጓዶች ወዘተ ይጠቀሳሉ፡፡ በአንፃሩ በሰው ሀብት ልማት መስክ ከሁለት ዓመት በፊት በዮኮሃማ በተወሰነው መሠረት ለአንድ ሺሕ አፍሪካውያን ወጣት ባለሙያዎች የትምህርት ዕድል መስጠት የሚለው ይገኝበታል፡፡ ‹‹አፍሪካ ቢዝነስ ኤዱኬሽን ኢኒሼቲቭ›› በምጽኃረ ቃሉ ‹‹አቤ ኢኒሼቲቭ›› የሚባለውና ከጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ጋር የገጠመው የትምህርት ዕድል ለሁለተኛው ዙር በመቶዎች የሚቆጠሩ አፍሪካውያንን ከወዲሁ ተጠቃሚ አድርጓል፡፡

ለ54 የአፍሪካ አገሮች ለሚሰጠው የትምህርት ዕድል የግል፣ የመንግሥት ኃላፊዎችና የአካዴሚ ሰዎችን የሚያሳትፍ ነው፡፡ ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ተኩል በሚቆይ ጊዜ ውስጥ ከኢንተርንሺፕ እስከ ማስትሬት ዲግሪ ባለው እርከን ነፃ የትምህርት ዕድል በጃፓን መንግሥት እየቀረበ ይገኛል፡፡

ከትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል፡፡ በጃፓን በተደረገው ጉብኝት ትምህርታቸው በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመከታተል ላይ ከሚገኙት መካካል ሪፖርተር ያነጋገራቸው አሉ፡፡ በናጋሳኪ ዩኒቨርሲቲ፣ ‹‹ትሮፒካል ሜዲስን ኤንድ ግሎባል ሄልዝ›› ትምህርት ክፍል ውስጥ የማትስትሬት ዲግሪውን መከታተል ከጀመረ አምስት ወራት ያስቆጠረው አወት ዓለም ተክለ ሚካኤል ይጠቀሳል፡፡

አወት በአገር ቤት የምግብ፣ መጠጥና መድኃኒት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ባልደረባ ሆኖ ያገለግላል፡፡  ወጣቱ አወት በናጋሳኪ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ መንፈቀ ትምህርት ቆይታው ካገኛቸው ጥቅሞች መካከል የፋርማሲ ሙያን ከዚህ ቀደም ከሚያውቀው ይልቅ በተግባር፣ በተራቀቁ መሣሪያዎችና በዘመናዊ ላቦራቶሪ የተደገፈ ትምህርት መቅሰም መጀመሩን ይናገራል፡፡ ከትምህርቱ ጎን ለጎን የጃፓን ኩባንያዎችን የሚመሩ ሰዎች በየጊዜው ወደ ዩኒቨርሲቲው በመምጣት ከተማሪዎች ጋር የሚያደርጉትን ውይይትም ከጠቃሚነት በላይ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ አወት እንደሚለው ይህንን አጋጣሚ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ ሊሠራ ላቀደው ተግባር ትልቅ ግብዓት ሆኖ አግኝቶታል፡፡

የኩባንያዎቹ ተማሪዎችን መጎብኘት በኸርባል ወይም በስራስርና ቅጠላቅጠሎች መድኃኒት ቅመማ መስክ የመሥራት ፍላጎቱን የሚያሳካበት አጋጣሚ ሊፈጥር የሚችል ግንኙነት ለመፍጠር እንደሚያግዘው ይናገራል፡፡

ከአወት ባሻገር ከቶኪዮ ከ800 ኪሎ ሜትር በላይ ርቃ፣ ፓስፊክ ውቅያኖስን በምትንተራሰው፣ ደቡብ ኮሪያንና ፉኮካ ደሴትን በምትዋሰነው ደቡባዊቷ የጃፓን ግዛት ኦይታ ትባላለች፡፡ በዚህች የገጠር ግዛት ውስጥ ቤፑ የተባለች ከተማ ትገኛለች፡፡ በፍልውኃ ሀብቷ በምትታወቀው ትን ኦይታ ግዛት ውስጥ በጃፓን ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዩኒቨርሲቲ ይገኛል፡፡ ሪቲሱሚካን ኤሽያ ፓስፊክ ዩኒቨርሲቲ ይሰኛል፡፡ በጃፓን ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ ከዓለም የተውጣጡ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ፈር ቀዳጅ ነው፡፡

ከአሥር ዓመት በፊት የጀመረው የውጭ ተማሪዎችን ተቀብሎ የማስተማር ተግባር ዛሬ ላይ በጃፓን ትልቅ ቦታ እንዳሰጠው የሚገልጹት ኢቶ ኬንጂ፣ በዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት የአስተዳደር ኃላፊ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ከ30 ሺሕ ያላነሱ ጃፓናውንና የውጭ አገር ተማሪዎችን ከመጀመርያ ዲግሪ እስከ ዶክትሬት ባለው መስክ ያስተምራል፡፡ ቤፑ ከተማ በዩኒቨርሲቲው ምክንያት ከሞመት መዳኗን የሚገልጹት ኬንጂ፣ በአሁኑ ወቅት ከሚቀበላቸው የውጭ ተማሪዎች መካከል በርከት ያሉት ከአፍሪካ የሚሔዱ ናቸው፡፡

ጃፓን በኢትዮጵያውያኑ ዓይን

በኤሽያ ፓስፊክ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ከሚገኙት ሁለቱ ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ካሊድ ዩሱፍ አህመድ ነው፡፡ ካሊድ ወደ ዩኒቨርሲቲው ያቀናው ከአሥር ዓመታት በፊት ሲሆን፣ ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ አሁን እስከሚገኝበት የዶክትሬት ዲግሪ ደረጃ ድረስ ትምህርቱን በዚሁ ዩኒቨርሲቲ ተከታትሏል፡፡ አብሮት በዩኒቨርሲቲው የማስትሬት ትምህርቱን በመከታተል ላይ የሚገኘው ኢዮብ የተባለው ወጣት ‹‹ካሊድ ጃፓናዊ ነው ማለት ይቀላል፤›› ሲል ይገልጸዋል፡፡

ካሊድ በጃፓን በቆየባቸው ዓመታት ለተለያዩ ኩባንያዎች ተቀጥሮ ሠርቷል፡፡ በድኅረ ምረቃ ትምህርት ቤት ኢኖቬሽን ኢኮኖሚክስ የተባለውን ትምህርት ካጠናቀቀና የዶክትሬት ዲግሪውን ከሠራ በኋላ በኢትዮጵያ የራሱን ኩባንያ የማንቀሳቀስ ሐሳብ እንዳለው ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ ይሁንና ጃፓኖች ሙያቸውንና ዕውቀታቸውን ለማጋራት ወደ ኋላ የማይሉ፣ ከትምህርት ከሚገኘው ዕውቀት ይልቅ በጃፓን ኩባንያዎች የሥራ ተሞክሮ የሚገኘው ዕውቀት የላቀና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን አብራርቷል፡፡

ኢዮብ በበኩሉ ስለጃፓኖች እንዲህ ይላል ‹‹ስለጃፓኖች ማወቅ ግማሽ መንገድ ሔዶ እነሱን ለመቀበል ያስችላል፡፡ ለመወሰን ቀርፋፋና ቀዝቃዞች ቢሆኑም አንዴ ከወሰኑ ግን ወደ ኋላ አይሉም፤›› የሚለው ኢዮብ፣ እስከ 1500 ዓመት ያስቆጠሩ ትልልቅ ድርጅቶች እንዳሏቸውም ይገልጻል፡፡

‹‹ካይዘን የሕይወት ዘይቤ ነው፤›› የሚለው ካሊድ፣ ቀስ በቀስ በየጊዜው ለውጥ ለማምጣት ሳያቋርጥ የሚተገበር ሥርዓት መሆኑን ያስረዳል፡፡ በካይዘን ከእያንዳንዱ ሠራተኛ የሚመነጭ ሐሳብ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጠው፣ ግንኙነቱም ከላይ ወደ ታች ብቻም ሳይሆን ከታች ወደ ላይ እንደሆነ አብራርቶታል፡፡ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የካይዘን ሥርዓት ጥሩ ጅምር መሆኑን ካሊድ ገልጾ፣ ይበልጥ ግን ከጃፓኖች ጋር የሚስተካከል ሥርዓት ቢዘረጋ በርካታ የጃፓን ኩባንያዎችን ማምጣት እንደሚያስችል ያምናል፡፡ ዕምነትና የረጅም ጊዜ ግንኙነት እንደሚፈልጉም ጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ካይዘን ጅማሮው ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ በወጥነትና በቀጣይነት እንዲጓዝ ማድረግ እንደሚገባ የሚመክረው ኢዮብ ሲሆን፣ ከታች ጀምሮ ያላደገና ያለባህርይ የሚሠራበት ሲሆን ደግሞ ይበልጥ ትዕግሥት እንደሚጥይቅም ያሳስባል፡፡ ካይዘንን በምሳሌ የሚያስረዳው በኤሽያ ፓስፊክ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በአንድ ጊዜ አንድ ሺሕ ተማሪዎችን የሚያስተናግድ ካፊቴሪያ እንዳለ ጠቅሶ፣ አንድም ቀን ግን ግፊያም ሆነ ሰልፍ እንደማይታይበት፣ ሁሉም የተመገበበትን ቁሳቁስ ወደየሥፍራው የመመለስ ባህል እንዳለው ይህም በሌሎች ሬስቶራንቶችም የሚተገበር ልማድ መሆኑን ያብራራል፡፡ አንድም ቀን የመኪና ጥሩምባ ሲጮህ አለመስማቱ ከሚያስገርሙት ነገሮች ውስጥ አንዱ መሆኑን የሚናገረው ኢዮብ፣ በምግብ ቤቶች፣ በባቡር ጣቢያዎች፣ በየመንገዱና በመሳሰሉት ሁሉ የሚያየው ንፅህናም መገረምን ይፈጥርበታል፡፡

‹‹ዘመናዊነትና ባህል ተጋብተው የሚኖሩባት አገር›› ሲል የሚገልጻት ጃፓን ልክ እንደ አገር ቤቱ ሁሉ ጃፓናውያንም እንደምን አደርክ፣ እንደምን ዋልክ ሰላምታ ለጥ ብሎ እጅ ከመንሳት ጋር የሚዘወተርባት፣ ይሉኝታ፣ ዝምተኛነት ወይም ቁጥብነት፣ ጭምትነትና አድማጭነት  ከሰፈነባቸው ሕዝቦቿ ጋር ከኢትዮጵያ ጋር የሚያመሳስሏት ሆነው እንዳገኟቸው ገልጿል፡፡

እንዲህ ባለው ተዛምዶ የሚገለጹትን ጃፓናውያን ባለሀብቶች መንግሥት ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ኢንቨስት እንዲያደርጉ በተደጋጋሚ እየጋበዘና መምጣታቸውንም እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች