ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለማጥናት በቀረበላቸው የቴክኒክ ሰነድ ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው፣ ባልተስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ቀጠሮ መያዛቸው ተሰማ፡፡
የሦስቱ አገሮች ብሔራዊ የቴክኒክ ቡድኖች በሱዳን ካርቱም ካለፈው ሳምንት እሑድ ጀምሮ በቀረበላቸው የቴክኒክ ፕሮፖዛል ላይ ውይይት አድርገው፣ በአንዳንድ ነጥቦች ላይ ስምምነት ላይ ባለመድረሱ ነው በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ ላይ ለመገናኘት የወሰኑት ሲሉ የውኃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በሱዳን ካርቱም ውይይት ሲደረግ የቆየው ጥናቱን ለማከናወን የተመረጡት የፈረንሣዮቹ ኩባንያዎች ዋናው አጥኚ ቢአርኢል ኢንጂነርስና ኤርቴሊያ የተባሉት ኩባንያዎች፣ ባቀረቡት የተሻሻለ የቴክኒክ ፕሮፖዛል ላይ የሦስቱን አገሮች አስተያየትን ለማካተት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ኩባንያዎቹ ባቀረቡት ዋጋ ላይ ለመወያየትና የጥናቱ የሕግ አማካሪ ሆኖ የተቀጠረው የለንደኑ የሕግ አማካሪ ከርቤት የተባለ ኩባንያ የቴክኒክ ሰነዱን ተመልክቶ፣ የኮንትራት ውሉን ማዘጋጀት የሚችልበትን ሁኔታ እንዲያመቻች መሆኑን አክለዋል፡፡
በሱዳን በተካሄደው ውይይትም ስምምነት የተደረገባቸው ጉዳዮች መኖራቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ስምምነትን የሚጠይቁ ቀሪ ጉዳዮች በየአገሮቹ እንዲታዩና በተቻለ መጠን አጭር ጊዜ ውስጥ የውል ስምምነቱ በአዲስ አበባ እንዲፈረም ተስማምተዋል፡፡
የአዲስ አበባውን ቀነ ቀጠሮም እንዲቆርጡ የየአገሮቹ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴዎች ተነጋገርው እንዲወስኑ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡
ሱዳን ትሪቡን እንደዘገበው ቀጣዩ ውይይት ግፋ ቢል በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡
ይህ ውይይት ተካሂዶ ስምምነት ላይ መድረስ ከተቻለ፣ ሁለቱ ኩባንያዎች የህዳሴው ግድብ ሁለት የተፅዕኖ ሥጋቶች ላይ ጥናታቸውን ማካሄድ ይጀምራሉ፡፡
አንደኛው ጥናት የግድቡ ኃይድሮሎጂ ሲመሌሽን ማለትም የግድቡ ውኃ አያያዝና አለቃቀቅን የሚመለከት ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ግድቡ በሁለቱ የታችኛው አገሮች ላይ ሊያደርስ የሚችለው አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖን መገምገም ነው፡፡