Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜና​ፍትሕ ሚኒስቴር በትራንስፎርመር ጥራት የተወዛገቡ መንግሥታዊ ተቋምና የህንድ ኩባንያ እያደራደረ ነው

​ፍትሕ ሚኒስቴር በትራንስፎርመር ጥራት የተወዛገቡ መንግሥታዊ ተቋምና የህንድ ኩባንያ እያደራደረ ነው

ቀን:

ከግዢ መሥፈርቱ የወረደ ጥራት ታይቶባቸዋል በተባሉ 765 ትራንስፎርመሮች ሳቢያ ውዝግብ ውስጥ የገቡትን መንግሥታዊ ተቋምና የህንድ ኩባንያ ሲያደራድር የቆየው ፍትሕ ሚኒስቴር፣ የመጨረሻውን የመደራደሪያ ሐሳብ ማቅረቡን አስታወቀ፡፡

በመንግሥት ግዢ አስተዳደርና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አማካይነት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ግዢ ተፈጽሞባቸው ወደ አገር ውስጥ የገቡት ትራንስፎርመሮች፣ ከህንድ ኩባንያ የተገዙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴር የማደራደሪያ ሐሳቡን ረቡዕ የካቲት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ለሁለቱም ወገኖች የላከ ሲሆን፣ ከበላይ አመራሮቻቸው ጋር መክረው የውሳኔ ሐሳባቸውን በ15 ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቁ ማሳሰቡን ፍትሕ ሚኒስቴር ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

በአገሪቱ ውስጥ ከሁለት ዓመታት በፊት ተፈጥሮ የነበረውን የኃይል እጥረት ለመቅረፍ የትራንስፎርመር ግዢ ለመፈጸም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የግዢ መሥፈርቱን ለመንግሥት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ከሰጠ በኋላ፣ አገልግሎቱ ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ፌደረር ሎይድ የተባለ የህንድ ኩባንያ አሸንፎ ነበር፡፡

- Advertisement -

አሸናፊው ኩባንያም ከአገልግሎቱ ጋር ወዲያው ውል ፈጽሞ በስምምነቱ የተጠቀሱትን 2,065 ትራንስፎርመሮች ወደ አገር ውስጥ ቢያስገባም፣ ከገቡት ውስጥ 765 ያህሉ ከሚፈለገው የጥራት መሥፈርት በታች በመሆናቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደማይረካባቸው አስታውቋል ተብሏል፡፡ ይልቁንም ካሳ ሊከፈለው እንደሚገባ በማስታወቁ በአቅራቢው የህንድ ኩባንያና የግዢ ትዕዛዝ በፈጸመው መንግሥታዊ ድርጅት መካከል ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር፡፡

ባለፈው ሳምንት የግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የበጀትና የፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ በጠራው ስብሰባ ላይ የመሥሪያ ቤታቸውን የስድስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ ከምክር ቤቱ አባላት ትራንስፎርመሮቹ ለምን ይህን ያህል ጊዜ በወደብ ያለሥራ እንደተቀመጡ ተጠይቀው ነበር፡፡ እሳቸውም በሰጡት ምላሽ በውዝግቡ ምክንያት በፍትሕ ሚኒስቴር የግልግል ዳኝነት እየታየ በመሆኑ ትራንስፎርመሮቹ አለመነሳታቸውን ገልጸው ነበር፡፡

ነገር ግን ጉዳዩን በግልግል ይዞታል የተባለው የፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሐ ብሔር ዳይሬክቶሬት ጉዳዩ ‹‹የግልግል ጉዳይ›› ሳይሆን ‹‹የማደራደር ሥራ›› ተሰጥቶት ላለፉት ዘጠኝ ወራት ሲመረምርና ሁለቱን ወገኖች ልዩነታቸውን ለማቀራረብ እየሠራ መቆየቱን፣ ዳይሬክተሩ አቶ ሙሉጌታ አያሌው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ለትራንስፎርመሮቹ በወደብ መቆየት የፍትሕ ሚኒስቴር አደራዳሪነት እንደ ምክንያት ሊጠቀስ እንደማይገባው አመልክተዋል፡፡

ፌደረር ሎይድ የተባለው የህንድ ኩባንያ ትራንስፎርመሮቹን ህንድ ውስጥ በሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ጥራታቸው ተረጋግጦ ያስገባቸው በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በተካሄደው ምርመራ የተገኘው ውጤት በስምምነቱ መሠረት የተዘረዘሩ መሥፈርቶችን አላሟሉም መባሉን አለመቀበሉ ተገልጿል፡፡

የማደራደር ሒደቱን ከሌሎች ሁለት የፍትሕ ሚኒስቴር ባልደረቦች ጋር እየመሩ ያሉት አቶ ሙሉጌታ እንደገለጹት፣ ሁለቱ ወገኖች በሦስት ጉዳዮች ላይ ባለመግባባታቸው ምክንያት ነበር ድርድሩ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደው፡፡

ሲከራከሩባቸው ከቆዩባቸው ጉዳዮች መካከል በዋነኛነት ሊግባቡ ያልቻሉት በትራንስፎርመሮቹ የኃይል መጠን ቅነሳ (Loss of Capitalization) በሚባለው ሲሆን፣ ይህም እያንዳንዱ ትራንስፎርመር ኃይል ማመቅ ሲጀምር የኃይል ብክነት መጠኑን በሚመለከት ልኬት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ የተጣራ የጉዳት ካሳ (Liquidated Damage) እና የዲመሬጅ ክፍያን በተመለከተ እንደነበሩ አቶ ሙሉጌታ አብራርተዋል፡፡

‹‹ሁለቱንም የማስማማት ሥራው እየተገባደደ ነው፡፡ የሁለቱም ተቋማት የበላይ ኃላፊዎቻቸው ባቀረብንላቸው ሐሳብ መሠረት በየግላቸው ተወያይተው እስከ የካቲት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. አቋማቸውን እንዲገልጹ አሳውቀናቸዋል፡፡ ባቀረብንላቸው ሐሳብ ከተስማሙ ጉዳዩ በዚያው እንዲያልቅ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን በዚህም መስማማት ካልቻሉ ጉዳዩ ቀድሞ ተቋርጦ ወደነበረው መደበኛ ፍርድ ቤት ይሄዳል፤›› ሲሉ አቶ ሙሉጌታ አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ የመጨረሻ ሐሳብ የተባለውን የድርድር ሐሳብ ከሁለቱም ወገኖች መልስ እስከሚመጣ ድረስ ሊገለጽ እንደማይችል አደራዳሪው ገልጸዋል፡፡

ትራንስፎርመሮቹ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ የኃይል ብክነት መጠናቸውን ምርመራ ያከናወነው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን መሆኑን፣ የግዢ ሥራው ህንድ ውስጥ ሲከናወን ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተወክለው እንዲታዘቡ የተላኩ ባለሙያዎች ተልከው እንደነበር የሚሉ ነጥቦች ተነስተውላቸው፣ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ራሱ ትራንስፎርመር እያመረተ፣ በሌላ ኩባንያ ተገዝተው አገር ውስጥ የገቡ ትራንስፎርመሮችን የመመርመር ሥራ በምን የሕግ አግባብ እንዳከናወነና የጥቅም ግጭትን በተመለከተ ተጠይቀው ነበር፡፡

የድርድር ሥራው ገና ያልተጠናቀቀ በመሆኑ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት የተቆጠቡት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹ኮርፖሬሽኑ እንደዚያም ቢሆን እንኳ (ትራንስፎርመር ቢያመርትም) የግዢ ጨረታው ወጥቶ ግዢ እስከተፈጸመበት ጊዜ ድረስ የራሱን ትራንስፎርመር ማምረት አልጀመረም፤›› በማለት መልሰዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በወቅቱ የትራንስፎርመር ግዢ ያስፈለገው በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ የኃይል እጥረት በመኖሩ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡ አስቸኳይ ግዢ ተደርጐ ከውጭ አገር ማስገባት ማስፈለጉም ሌላው ጉዳይ መሆኑን አክለዋል፡፡

እንዲሁም የግዥ ሒደቱን ለመታዘብ ወደ ህንድ እንደሄዱ የተገለጹት ባለሙያዎች፣ ከጥራት በታች ተገዝተዋል በተባሉ ትራንስፎርመሮች ጉዳይ ሊኖራቸው የሚገባ ተጠያቂነት ካለ የሚል ጥያቄ ሲነሳላቸውም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ነገር ግን የግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ውሉን ከመፈራረሙ በፊት ፍትሕ ሚኒስቴርን አማክሮ ቢሆን ኖሮ፣ ውዝግቡ እዚህ አይደርስም ነበር ሲሉ አቶ ሙሉጌታ ገልጸዋል፡፡  

ባለፈው ሳምንት ለቋሚ ኮሚቴው ማብራሪያ የሰጡት አቶ ይገዙ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአምስት ሚሊዮን ዶላር ካሳ መጠየቁን አስታውሰው፣ የህንዱ ኩባንያ ግን ከ2.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለመክፈል ፈቃደኛ አለመሆኑን መጥቀሳቸው ይታወሳል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...