በዓለም ዙሪያ በየዕለቱ የሚሰሙ አብዛኞቹ ዜናዎች ከግጭትና ከትርምስ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ በሶሪያ፣ በኢራቅና በየመን የለየላቸው ጦርነቶች እየተደረጉ ነው፡፡ የሰሜን አፍሪካዊቷ ሊቢያ ሰላም ሊመለስ አልቻለም፡፡ ግብፅ ውስጥ በየጊዜው ፍንዳታዎችና ግድያዎች አሉ፡፡ በመጠኑ እየተረጋጋች የመጣችውን ሶማሊያ አሁንም የጽንፈኛው አልሸባብ ቦምብ ያተራምሳታል፡፡ የደቡብ ሱዳን ግጭት እልባት ባለማግኘቱ አሁንም ሰላም ማስፈን አልተቻለም፡፡ በአፍሪካ፣ በእስያና በአውሮፓ የተለያዩ ሥፍራዎች ግጭቶችና ፍንዳታዎች ይሰማሉ፡፡ ፓኪስታንና አፍጋኒስታን በታሊባን ጥቃቶች ይናወጣሉ፡፡ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ ባለው አስፈሪ ድባብ ምክንያት የዓረብ ሊግ አገሮች የጋራ ጥምር ጦር መሥርተዋል፡፡ ይህ በቅርብ ርቀት ላይ ያለ ሥጋት አገራችንን ኢትዮጵያ አያሳስባትም ማለት የዋህነት ነው፡፡ ስለዚህ እንደ አገር ጠንከር ብሎ መገኘትና የቀውሱ ሰለባ አለመሆን ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ በታሪኳ ከምትታወቅባቸው አኩሪ ተግባራት መካከል ሕዝቧ በምንም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ እንኳ ለውጭ ወረራና ሴራ አለመበገሩ ነው፡፡ ኮሎኒያሊስቶች አፍሪካን ሲቀራመቱ ኢትዮጵያ በብቃት መክታ የወጣችው በጠቅላላ ሕዝቧ ብርቱ ተጋድሎ ነው፡፡ በዓለም ጥቁር ሕዝቦች ዘንድ በአንፀባራቂ ተምሳሌትነቱ ዘመናትን እየተሻገረ በአርዓያነት የሚወደሰው በኢጣሊያ ወራሪዎች ላይ የተገኘው የዓደዋ ድል፣ ኢትዮጵያን እስከ ዛሬ በጀግንነት የሚያስወድሳት ነው፡፡ በዚህ ታሪካዊ ድል ምክንያት ብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት በመጋራት ከነፃነት በኋላ አውለብልበዋል፡፡ በዚህ አኩሪ ታሪክ ምክንያት ኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ መሠረት ሆናለች፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን በተመሠረተው ሊግ ኦፍ ኔሽንስና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ብቸኛዋ የአፍሪካ ተወካይ አባል ነበረች፡፡ ለአፍሪካ ኅብረት መመሥረት ፋና ወጊ ነበረች፡፡ ይህ ሁሉ ክብር የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጋድሎ ውጤት ነው፡፡ አሁንም በከፍተኛ ወኔና ሞራል አገርን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
በአገራችን ኢትዮጵያ 80 ያህል ብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋቸውን፣ ባህላቸውን፣ ሃይማኖታቸውን፣ ልማዶቻቸውንና የመሳሰሉትን ይዘው በልዩነት ውስጥ አንድነትን አንግሠው ይኖራሉ፡፡ በተለያዩ ጨቋኝ አገዛዞች ሥር ሆነው መከራና በደል ሲደርስባቸው፣ የአገራቸውን ህልውናና ጥቅም ለባዕድ አሳልፈው ሰጥተው አያውቁም፡፡ ምንም ያህል ጭቆናውና በደሉ አስከፊ ቢሆንም፣ የአገራቸውን ክብር በደምና በአጥንታቸው ጠብቀው ኖረዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ቱርኮች፣ ግብፆች፣ ጣሊያኖች፣ ድርቡሾችና ሌሎች ወራሪዎች በብርቱ ቅጣት የተመለሱት ሕዝቡ ከልዩነቱ ይልቅ የአገሩ አንድነት ከምንም ነገር በላይ ስለሚበልጥበት፣ ልዩነትን ውበት አድርጎ መስዋዕትነት በመክፈሉ ነው፡፡ የዘር፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት፣ ወይም የተለያዩ አመለካከቶች ልዩነቶች በመከባበርና በመፈላለግ ተበልጠው፣ ኢትዮጵያውያን ለዓለም ምሣሌ የሚሆኑበት ትሩፋት አግኝተውበታል፡፡ ዛሬም መቀጠል ያለበት ይህ አኩሪ አንድነት ነው፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በአንዳንድ ወገኖች በኩል የሚታዩ አላስፈላጊ ተግባራት ፈር ሊይዙ ይገባል፡፡ የራስን የፖለቲካ አጀንዳ ከአገር በማስበለጥና ሕዝቡን በብሔር በማቧደን ለማበጣበጥ መሞከር፣ በማንነት ስም ትልቁን የኢትዮጵያዊነት ምሥል እያደበዘዙ ማጥፋት፣ ሌላው ወገን በደል ያልደረሰበት ይመስል የራስን እያጦዙና እያጎኑ የአገር አንድነትን ማፍረክረክ፣ ዓለም ወደ አንድ መንደር እየተሰበሰበች ባለችበት በዚህ ዘመን የብተና ፖለቲካ ማራመድ፣ በሠለጠነና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ሕዝብን አደራጅቶ በፅናት ከመታገል ይልቅ በባዕዳን ጉርሻ በመደለል አገር ለማፍረስ መንቀሳቀስ፣ በአስተዳደራዊና በሌሎች ምክንያቶች የሚደርሱ በደሎችን ከለላ በማድረግ አገርና መንግሥትን የማይለይ ቀውስ ለመፍጠር መሯሯጥ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ለዘመናት በተካሄደ ትግል በተገነባ ዴሞክራሲ ውስጥ በነፃነት እየኖሩ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እገዛ ከማድረግ ይልቅ የእልቂት ነጋሪት መጎሰም፣ አውሮፓና አሜሪካ ከዜግነት ጋር የሰጡዋቸውን መብቶችና ነፃነቶች በተድላ እያጣጣሙ ለሥልጣን ሲባል ብቻ አገር ለማተራመስ መፈለግ፣ ወዘተ የኢትዮጵያዊነት ባህርይ አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ የራስንና የቡድንን ፍላጎት ብቻ ማዕከል ያደረገ የጥፋት ድግስ ለአገር አይበጅም፡፡ ይልቁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ያዳበረውን ፍቅር፣ መከባበርና መደጋገፍ ማስቀጠል፣ አንዱ የበላይ ሌላው የበታች የሚሆንባት አገር እንዳትፈጠር መታገል፣ ለሁሉም ዜጎቿ እኩል የሆነችና የምትመች ዴሞክራሲያዊት አገር እንድትኖር በጋራ ጉዳዮች ላይ በነፃነት መነጋገር ይቅደም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በዚህ በሠለጠነ ዘመን ለአገራቸው ክብር በግንባር ቀደምትነት የሚሠለፉ ዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሊከበሩ ይገባል፡፡ በአገራቸው ጉዳይ ዋነኛ ተዋንያን መሆን አለባቸው፡፡ ጥቂቶች ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ ማሊየነር የሚሆኑበት ብልሹ አሠራር መወገድ አለበት፡፡ በሙስና የነቀዙ ባለሥልጣናትና አቀባባይ ደላላዎች መጥፋት አለባቸው፡፡ በአገሪቱ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ መኖር አለበት፡፡ የይስሙላ ዴሞክራሲ ተቀባይነት እንደሌለው በተግባር የተረጋገጠ ነው፡፡ ብልሹ አስተዳደር፣ ሙስና፣ ዘረኝነት፣ የሰዎችን መብት አለማክበርና የመሳሰሉት ተቀባይነት የላቸውም፡፡ መንግሥት በሕዝብ ፈቃድ ነው የሚቋቋመው እንጂ፣ በግለሰቦች ወይም በቡድኖች ፍላጎት አይደለም፡፡ ከሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ የሚከናወኑ ድርጊቶች ሁሉ አደጋ ፈጣሪ ናቸው፡፡ ብዙኃኑ እየተጎሳቆሉና መከራ እያዩ ጥቂቶች የሚምነሸነሹባት አገር እንድትኖር ማንም አይፈቅድም፡፡ በሕዝብ ፈቃድና ይሁንታ መሠረት አገር መመራት አለበት፡፡ ይህ ሲሟላ ብቻ ነው አገር እንደ ቀድሞ በኩራት የምትጠበቀው፡፡ ሕገወጥነት እየነገሠና ዘራፊዎች አገር እያመሱ አገርን ከጥቃት መጠበቅ ፈጽሞ አይቻልም፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በመዳፈር ተቃራኒ ሐሳብ የሚያንፀባርቁትን ማንገላታት፣ ማሰርና ለስደት መዳረግ ይቁም፡፡ በአጠቃላይ የፖለቲካ ምኅዳሩ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሲባል ወለል ብሎ ይከፈት፡፡
የአገር ጥቅም ከምንም ነገር በላይ ነው፡፡ ብሔራዊ ደኅንነታችን በአስተማማኝነት የሚጠበቀው ኢትዮጵያዊያን በጋራ ጉዳያችን ላይ የጋራ አቋም ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ ብሔራዊ መግባባቱን ለማምጣት ደግሞ ሁሉም ወገኖች አደብ ገዝተው በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር ዝግጁና ቁርጠኛ መሆን አለባቸው፡፡ አንዱ ሰጪ ሌላው ተቀባይ ሳይሆን፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተና የአገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስቀድም መሆን አለበት፡፡ ላለፉት አርባ ዓመታት በላይ የተደረገው ጉዞ በጭፍን ጥላቻና በክፋት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ካለፈው ስህተት ተምሮ የሕዝባችንን ተምሳሌታዊ አኗኗር በመገንዘብ ተቀራርቦ መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ብዙዎቹ አገሮች ለለውጥና ለነፃነት የቆሰቆሱት አብዮት እንደ ሰደድ እሳት በልቷቸው እየወደሙ ነው፡፡ የማያባራ ጦርነት ውስጥ ገብተው ሕዝባቸውን ለእልቂትና ለአካል ጉዳት፣ ለስደትና እጅግ ከፍተኛ መጠን ላለው የንብረት ውድመት ዳርገዋል፡፡ አሁንም ኃላፊነት በጎደለው መንገድ የሚከናወነው አጉል መጎሻሸም አብቅቶ ለዚህች ታላቅ አገር፣ ለዚህ ታላቅና አስተዋይ ሕዝብ ሲባል ብሔራዊ ጥቅም ይቅደም፡፡ የአገር ህልውና ይከበር፡፡ በአገር ህልውናና በሕዝብ ዘላቂ ጥቅም ላይ አደጋ የሚፈጥር ድርጊት እየፈጸሙ አገርን የአውሬ መፈንጫ ለማድረግ መሞከር ተቀባይነት የለውም፡፡ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› የሚባለው የሥልጣን ጥመኝነት አባዜ ለዚህች አገር አይጠቅምም፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ለዘመናት ከተዘፈቀችበት የድህነት አረንቋ ውስጥ መውጣት አለባት፡፡ ዘወትር የግጭትና የአደጋ መናኸሪያ የሆነው የአፍሪካ ቀንድ አዙሪት ውስጥ እንዳትገባ ጠንካራና አስተማማኝ ኃይል መሆን አለባት፡፡ በቅርብ ርቀት ከየመን እስከ ሶሪያ ባለው እልቂትና ውድመት፣ በጣም በቅርብና በዙሪያዋ ባሉ አገሮች አለመረጋጋትና ትርምስ እንዳትዋጥ መጠንከር አለባት፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች የሚቋሰሉት የአገሪቱ ፖለቲከኞች እከሌ ከእከሌ ሳይባሉ አደብ ገዝተው በሠለጠነ መንገድ ሲነጋገሩ ብቻ ነው፡፡ ከአገር የሚበልጥ ምንም ዓይነት ግላዊም ሆነ ቡድናዊ ጥቅም የለም፡፡ ይህንን ብቻ እያሰሉ ሥልጣንን ዒላማ ማድረግ አገሪቱንም ራስንም የማይወጡበት አዘቅት ውስጥ ይከታል፡፡ ይህ መልዕክት በቀጥታ ገዥውን ፓርቲና ተቃዋሚዎቹን ይመለከታል፡፡ በዘርም ሆነ በፖለቲካ መሳሳብ እየተቧደኑ አገርን የምታህል ትልቅ የጋራ ቤት መርሳት አደጋው የከፋ ነው፡፡ ዙሪያውን እሳት እየነደደ እርስ በርስ እየተናጩ መኖር ማብቃት አለበት፡፡
ሁሌም እንደምንለው ለሕግ የበላይነት ክብደትና ክብር የማይሰጥ ሕገወጥ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ነገር በሕጉ መሠረት ሲከናወንና የሕዝቡም እርካታ በግልጽ ሲታይ፣ አመፅና ብጥብጥ ቦታ አይኖራቸውም፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የያዘ ኃይል አሠራሩ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት መሆን አለበት፡፡ ሥልጣን የሚያዘውም በጉልበት ሳይሆን ነፃና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንደሆነ ማመን አለበት፡፡ ይኼ ለሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የሚሠራ ነው፡፡ በሴራ፣ በተንኮልና በጉልበት ሥልጣን መያዝ መዘዙ የከፋ ነው፡፡ ለባዕዳን ኃይሎች ተላላኪ በመሆን በእነሱ እገዛ ሥልጣን ለማግኘት መሞከርም ውጤቱ ጥፋት ነው፡፡ የግል ወይም የቡድን አጀንዳ ከአገሪቱ ሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ መጓዙን ከቀጠለ፣ ስህተትን በስህተት እያረሙ ወደ ጥፋት መንጎድ ነው፡፡ የአገሪቱና የሕዝቡ ጥቅም ይቅደም፡፡ የዚህች ታላቅ አገር ሕዝብ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለጋራ ብልፅግና በጋራ መነሳት አለበት እንጂ፣ ብትንትኗ ለሚወጣና ለቀውስ ለምትዳረግ ኢትዮጵያ መቀስቀስ የለበትም፡፡ አኩሪ ታሪኩ ይህንን አይናገርም፡፡ አሁንም ደግመን ደጋግመን የምንለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጋራ ብልፅግና እንጂ ለጥፋት ቦታ የለውም ነው!
<span style=”font-size:14.0pt;line-height:200%; font-family:"Ge” ez-1″,”sans-serif”‘=””>