እሰጣ አገባ
በሞገደኛነታቸው የሚታወቁ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ጉዳትና እልቂት በማድረስ እስከመታወቅ ደርሰዋል፡፡ በነውጠኛነታቸው ሲፈረጁ ከኖሩት መካከል በደቡብ አሜሪካ በአርጀንቲናና ብራዚል የሚገኙ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ሰፊውን ድርሻ ይወስዳሉ፡፡ እጅግ ሰልጥነዋል በሚባሉት አውሮፓውያን በእንግሊዝና መሰል አገሮች ነውጠኛ የእግር ኳስ ደጋፊዎች በተመሳሳይ ጥፋት ሲፈረጁ የቆዩ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ በእነዚህ አገሮች አሁን አሁን በክለቦችም ሆነ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሳይቀር ነውጠኞች ረብሻ በማስነሳት የኖሩበትና ያሳለፉት ጊዜ ፋሽኑ ያለፈበት መሆኑን በመረዳት እየተቀዛቀዘና እየቀረ የመጣበት ወቅት ላይ ይገኛል፡፡
በዚህ ዘመን የነውጠኛ ደጋፊዎች ረብሻና ብጥብጥ ወሬ እምብዛም አይደመጥም፡፡ በእኛ አገር ግን በተቃራኒ የክለቦች ደጋፊዎች የሚያስነሱት ረብሻና ብጥብጥ ቅጥ ያጣ እየሆነ ለአሠልጣኞች ሕልውና ሥጋት እስከመሆን የደረሱ ‹‹ደጋፊ ነን›› ባዮች እየታዩ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ክለቦችን የተጠናወተው ነውጠኛነት ወደ ክልሎችም ተዛምቷል፡፡ በቅርቡ በአዳማ ከነማ እግር ኳስ ክለብ አንዳንድ ደጋፊዎች ዘንድ የታየው ያልተገባ ባሕርይና ከመልካም ስፖርታዊ ጨዋነት ያፈነገጠ ድርጊት ሲያነጋግር ሰንብቷል፤ እያነጋገረም ይገኛል፡፡
ፕሪሚየር ሊጉን እስካለፈው ሳምንት ድረስ ሲመራ የቆየው አዳማ ከነማ በውድድር ዓመቱ ተመልካችን የሚያረካና የተቀናጀ እንቅስቃሴ ከሚያደርጉ ጥቂት ክለቦች አንዱ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ቡድኑ በፕሪሚየር ሊጉ ዘጠነኛ ሳምንት የጨዋታ መርሐ ግብር በሜዳው ድሬዳዋ ከነማን አስትናግዶ 2ለ0 መረታቱ ይታወቃል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ በአንድ ነጥብ ልዩነት በሁለተኛነት ይከተለው የነበረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አርባ ምንጭ አምርቶ አርባ ምንጭ ከነማን 1ለ0 ማሸነፉ በመቻሉ ነጥቡን ወደ 22 ከፍ አድርጎ የመሪነቱን ቦታ ከአዳማ ከነማ እንዲረከብ አስችሎታል፡፡ በሽንፈቱ ምክንያት ቀደም ሲል በነበረው 20 ነጥብ ላይ የተቀመጠው አዳማ ከነማ ሁለተኛ ደረጃን ለመያዝ ተገዷል፡፡ በዚሁ ምክንያት የቡድኑ ደጋፊዎች ዋና አሠልጣኙ አቶ አሸናፊ በቀለን በመቃወም ባስነሱት ብጥብጥና አለመግባባት አሠልጣኙ በገዛ ፈቃዳቸው ኃላፊነታቸው እንዲለቁ የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡
የአዳማ ከነማ ዋና አሠልጣኝ አቶ አሸናፊ ሪፖርተር እንደሚገልጹት ከሆነ የክለቡ ‹‹ደጋፊዎች ነን›› ባዮቹ ችግራቸው ከውጤት ጋር የተገናኝ እንዳልሆነ፣ ይልቁንም እሳቸው ቡድኑን በ2006 የውድድር ዓመት ከብሔራዊ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ካሳደጉበት ጊዜ ጀምሮ እነዚህ ደጋፊዎች ጫና ሲያሳድሩባቸው ቆይተዋል፡፡
የጫናው መነሻ ምንድነው? ለሚለው ቀጣይ የሪፖርተር ጥያቄ አሠልጣኙ፣ ‹‹ደጋፊ ነን ባዮቹ ወደ ክለቡ የሚዘዋወሩ ተጨዋቾች በእነሱ ፍላጎት እንጂ በእኔ ከሆነ በተለይ እኔ በክለቡ በሚኖረኝ ቆይታ ሕይወቴን ሊያሳጣኝ የሚችል አደጋ ሊገጥመኝ እንደሚችል ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሲያስጠነቅቁኝ ቆይተዋል፡፡ የሚደርስብኝ ጫናና ማስፈራሪያ ለክለቡ ኃላፊዎችና ለሚመለከታቸው የፀጥታ ኃይሎች ባሳውቅም ጫናው ከመቅለል ይልቅ ወደ አደገኛ አቅጣጫ እየተቀየረ መጣ፡፡ ይህ እየሆነ ባለበት ቡድኑ በሜዳው በድሬዳዋ ከነማ 2ለ0 ሲሸነፍ ቀድሞ ቂም ይዘው የቆዩት እነዚሁ ደጋፊዎች በሰው ልጅ ላይ ሊነገሩ የማይገባቸው ቃላትን በመናገር ሳይቀር ጫናው እያበረቱብኝ ኃላፊነቴን በገዛ ፈቃዴ መልቀቄን አሳውቄ ክለቡን ትቼ ወጣሁ፤›› በማለት ነው የነበረውን ገጽታ ያስረዱት፡፡
አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ አሠልጣኙ፣ ‹‹ከክለቡ ፕሬዚዳንትና ከአዳማ ከተማ ከንቲባ ጋር እየተፈጠረ ባለው አጠቃላይ ችግር ዙሪያ ተነጋግረን ለሚደርስብኝ ማናቸውም ነገሮች ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ ከስምምነት ደርሰናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ ቀድሞ ኃላፊነቴ ተመልሼ እየሠራሁ እገኛለሁ፤›› ብለዋል፡፡
የአዳማ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ፕሬዚዳንት አቶ ዓለማየሁ ቱሉ በበኩላቸው ‹‹በአሠልጣኙ ላይ አላስፈላጊ ሁከትና ብጥብጥ እየፈጠሩ ያሉት ብዙኃኑን የአዳማ ከነማ ክለብ ደጋፊዎችን የሚወክሉ አይደሉም፡፡ በጣም ጥቂትና የግል ጥቅም ፈላጊዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ደጋፊዎች የአሠልጣኙን ሰብዕና የሚነካ ቃላት ጨምሮ ሥራቸውን ተረጋግተው እንዳይሠሩ ማድረጋቸው እውነት ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ከከተማው የፀጥታ ኃይሎች አቅም በላይ የሚሆኑበት አንዳችም ምክንያት ስለማይኖር ለአሠልጣኙም ይኼው ማረጋገጫና አስተማማኝ የሥራ ዋስትና ጭምር እንዳላቸው ስምምነት ላይ ደርሰን ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ አድርገናል፤›› ብለዋል፡፡
*****
የታዳጊ ወጣቶች ውድድሮችና ሕክምናው
በደረጀ ጠገናው
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በበላይነት ከሚመራቸው የሊግ ውድድሮች ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ወጣቶች የሚያደርጉት የጨዋታ መርሐ ግብር ይጠቀሳል፡፡ በውድድሩ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች እንዲሁም የብሔራዊ ሊግ ክለቦች ተሳታፊ ናቸው፡፡
የታዳጊ ወጣቶቹ ውድድር በዚህ መልኩ መከናወኑ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑንም ሆነ ክለቦቹን የሚያስመሰግናቸው መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ነገር ግን ከጥቂቶቹ ክለቦች በስተቀር ለብዙዎቹ ታዳጊ ወጣቶች ክለቦች የሚመደቡላቸው የሕክምና ባለሙያተኞች በተለይ ወጌሾች የጥራት ጉዳይ ውድድሩን ለሚከታተሉ ሁሉ መነጋገሪያ ሆኖ ይገኛል፡፡ ታዳጊዎቹ በጨዋታ መሐል ጉዳት ሲደርስባቸው ግማሽ አልያም አንድ ሊትር በሚይዝ ሃይላንድ ቀዝቃዛ ውኃ ይዘው ወደ ሜዳ የሚገቡ ወጌሻ የሚመስሉ ግን የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች ተጎጂዎቹ ታዳጊ ወጣቶች እንደመሆናቸው መጠን ሕክምናው አሳዛኝም አስገራሚም በመሆኑ የሚመለከታቸው ሊያስቡት እንደሚገባ ጭምር እነዚሁ የታዳጊ ወጣቶቹ ውድድር ተከታታዮች ትዝታቸውን ይገልጻሉ፡፡
ሰኞ የካቲት 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም ደደቢት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ሐረር ሲቲና አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ዕድሜያቸው ከ17 ዓመት በታች የተደረጉ ውድድሮችን ሲከታተሉ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነገር ግን ማንነታቸው መግለጽ ያልፈለጉ የብሔራዊ ሊግ አሠልጣኝ እንደታዘቡት ከሆነ፣ ‹‹እነዚህ ታዳጊ ወጣቶች የነገዎቹ የፕሪሚዩር ሊግና ብሔራዊ ቡድን ተስፋዎች ናቸው፡፡ እንደምንመለከተው ታዳጊዎቹ በሜዳ ላይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴና ያለመሸነፍ እልህ የፕሪሚየር ሊጉን ጨዋታ የሚያስንቅ ነው፡፡ የሚደረግላቸው ሕክምና ግን በተቃራኒ ነው፡፡ ወጣቶቹ አሁን በሚገኙበት ዕድሜ ጉዳት እንኳ ቢኖርባቸው ለጨዋታ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ከነጉዳታቸው መጫወትን የሚመርጡ ናቸው፡፡ ስለዚህ ትክክለኛውንና ተገቢውን ክትትል የሚያደርግላቸው ሐኪምም ሆነ ወጌሻ መመደብ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ጉዳይ የሚመለከታቸው ተነጋግረው ወደ አንድ የመፍትሔ አቅጣጫ መድረስ ይጠበቅባቸዋል፤›› ብለው፣ ይህ ሳይሆን ባለው ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ የነገዎቹን ተተኪዎች ማፍራት እጅግ ከባድ እንደሚሆን ጭምር ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
*****
ኢትዮጵያውያን በካርዲፍ ግማሽ ማራቶን ይጠበቃሉ
በደረጀ ጠገናው
በዩናይትድ ኪንግደም ሥር የምትገኘው ካርዲፍ ሲቲ ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ የሚካሄደውን ግማሽ ማራቶን ታስተናግዳለች፡፡ ኢትዮጵያውያን በውድድሩ ከሚጠበቁት በግንባር ቀደምትነት ተቀምጠዋል፡፡
የዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር (አይኤኤፍ) ከጊዜ ወደ ጊዜ እጅግ ውስብስብና ለስፖርቱ አደጋ እየሆነ በመጣው የአበረታች መድኃኒት ጉዳይ ግራ ተጋብቶ በሚገኝበት በዚህ ወቅት የሚካሄደው የካርዲፍ ሲቲ ግማሽ ማራቶን ከውድድሩ ይልቅ በችግሩ ዙሪያ እጃቸው አለበት ተብለው የሚጠረጠሩ የቀድሞ የአይኤኤኤፍ ባለሥልጣናት ላይ እየቀረበ ያለው ጉዳይ ሚዛን ደፍቶ ይገኛል፡፡ የተወዳዳሪ አትሌቶች ወቅታዊ አቋምም በዚሁ ሚዛን እየተለካ መነጋገሪያነቱ እንደቀጠለ ነው፡፡
በዘንድሮው የካርዲፍ ሲቲ ግማሽ ማራቶን ከተለያዩ አገሮች የሚወከሉ በርካታ አትሌቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ከእነዚህ አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን ተወካዮቿንም ይፋ አድርጋለች፡፡ ዘንድሮ ለዘጠነኛ ጊዜ በተካሄደው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ የወጡ አትሌቶች አገሪቱን ወክለው የሚቀርቡ መሆኑ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መግለፁ ይታወሳል፡፡ በዚሁ መሠረት በወንዶች ጉዩ አዶሊ፣ ሙሼ ዋሲሁን፣ ታምራት ቶላ፣ አባይነህ አየለ፣ ተሾመ መኰንንና አዱኛ ታከለ ሲጠቀሱ፣ በሴቶች ስንቄ ዱቤ፣ ደኅንነት ደምሰው፣ አስካለ ዓለማየሁ፣ አያንቱ ገመቹና ድንቅነሽ መካሻ ዋና ዋናዎቹ መሆናቸው ታውቋል፡፡