Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየቅድመ አደጋ መከላከል ብሔራዊ መረብ ማቋቋም ያስፈልጋል ተባለ

የቅድመ አደጋ መከላከል ብሔራዊ መረብ ማቋቋም ያስፈልጋል ተባለ

ቀን:

የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ጎርፍ፣ ድርቅ፣ ሰደድ እሳት በመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች ዙሪያ የቅድመ ማስጠንቀቂያና የነፍስ አድን ሥራ የማከናወን አቅም ያለው የቅድመ አደጋ መከላከል ብሔራዊ መረብ (ሲቪል ፕሮቴክሺን ፍሬምወርክ) መመሥረት አስፈላጊ መሆኑን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ፡፡

  የዩኒቨርሲቲው የጂኦፊዚክስ፣ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት ኃላፊና የመሬት መንቀጥቀጥ ሳይንስ ባለሙያው ዶ/ር አታላይ አየለ ገለጻ፣ አገራዊ ሽፋን ያለው ይህ ዓይነቱ መረብ በሳይንስና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ፣ ብቁ ተመራማሪዎችን ያቀፈ፣ በተፈጥሮ አደጋዎች ዙሪያ ምርምር የሚሠራበትና ቅድመ ጥናት የሚከናወንበት ነው፡፡

በቅርቡ በሐዋሳ ከተማ የተከሰተውን የመሬት መንቀጥቀጥ በተመለከተ ከሪፖርተር ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ የመሬት መንቀጥቀጥ በሚያዘወትርበት አካባቢ የትንበያ ሥራ የመሥራት፣ የመንቀጥቀጡ ሁኔታ በተተነበየበት አቅጣጫ አደጋ ለመከላከል ቅድመ ማስጠንቀቂያ የመስጠት ኃላፊነትም አለው፡፡

በተለይ በሆስፒታሎች፣ በትምህርት ቤቶች በአጠቃላይ ሕዝብ በብዛት በሚያዘወትርባቸው አካባቢዎች፣ አደባባዮችና መኖሪያ ሥፍራዎች ላይ ልዩ ትኩረትና ጥንቃቄ እንዲደረግላቸው፣ በአደጋ ሥጋት በሚጠረጠሩ አካባቢዎች ምን ዓይነት ሕንፃዎች መገንባት እንዳለባቸውም አቅጣጫ የማስያዝ ጭምር አጠቃሎ ሊሠራም ይችላል፡፡

እንደ ኃላፊው ማብራሪያ፣ መረቡ ተጠሪነቱ ለአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን መሆን ይገባዋል፡፡ ይህ እንዲሆን ያስፈለገበትም ምክንያት በቅድመ ማስጠንቀቂያው ዙሪያ የተከናወኑትን ተግባራት በየወቅቱ ለማሳወቅና አደጋውም እንደተከሰተ ጊዜ ሳይፈጅና ካላስፈላጊ ቢሮክራሲ ውጭ ፈጣን የሆነ የነፍስ አድን እንዲሁም አደጋው በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ተጨማሪ ጉዳት ከማድረሱ በፊት የመከላከል ዕርምጃ ለመውሰድ እንዲያስችል ነው፡፡

በነፍስ አድን ሥራዎችም ላይ ሁልጊዜ በተጠንቀቅ የቆመ የመከላከያ ኃይልን መጠቀም ግድ ይላል፡፡ ይህ ኃይል የተሟላና በቂ የሆነ ሎጂስቲክ ስላለው በፍጥነት ለመንቀሳቀስ ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ ከዚህም ሌላ የሠለጠኑ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችም ሊኖሩ ይገባል፡፡

የቅድመ አደጋ መከላከል ብሔራዊ መረብ ከኢትዮጵያ በስተቀር በሌሎች አገሮች በብዛት እየተሠራበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተሠራ ያለው ግን አደጋው ከደረሰ በኋላ ለተጎዳው ኅብረተሰብ ምግብና አልባሳትና መድኃኒትና ውኃ በማቅረብ ላይ ያተኮረ ነው፡፡

“ሐዋሳ ከተማ ውስጥ በቅርቡ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ እንደማስጠንቀቂያ ደወል ነው፡፡ ይህም ማለት ብዙዎቹ ከተሞቻችን በስምጥ ሸለቆ ዙሪያ እንደመሆናቸው መጠን በየትኛው አካባቢ ባለ ስንት ፎቅ ሕንፃ መገንባት አለበት? ግንባታውስ ምን ያህል ጥንካሬ ሊኖረው ይገባል? አደጋው በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ቢያደርስ ይህን ችግር ለመቋቋም የሚያስችል አቅም አለን ወይ? ብሎ ማሰብና ለዚህም ቅድመ ዝግጅት ማድረግን አስተምሮን ወይም አሳይቶን አልፏል፤” ብለዋል ዶ/ር አታላይ፡፡

አንድ ሕንፃ ግንባታ የሚካሄድበት ሥፍራ ከመሬት መንቀጥቀጥ ነፃ መሆንና አለመሆኑን፣ ከተገነባ ደግሞ በምን መልኩ መከናወን እንዳለበት የሚያሳይ መረጃ የመስጠቱ የኢንስቲቱዩቱ ግዴታና ኃላፊነት አይደለም? ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄም ዶ/ር አታላይ ሲመልሱ፣ “መረጃ የሚፈልግ ድርጅትም ሆነ ባለሀብት ሲመጣ ሊሠራበት በመረጠው ቦታ ወይም አካባቢ ያለው የመሬት እንቅስቃሴ መጠን ምን ያህል ነው? የሚለውን ከቀመርንና ከአለቱ በላይ ያለው የአፈሩን ውፍረት ከለየን በኋላ የደረስንበትን ድምዳሜ ለተጠቃሚው ወገን እናቀርባለን፤” ብለዋል፡፡

ይህ ዓይነቱን መረጃ የማግኘት ጥያቄ ከአዲስ አበባ በስተቀር ከየክልሎች ቀርቦ እንደማያውቅ፣ አዲስ አበባም ቢሆን የመረጃ ፈላጊ ወይም ተጠቃሚዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ እንደሆነና ይህም ሆኖ በተሰጠው መረጃ መሠረት ሕንፃው መገንባቱና አለመገንባቱ እንደማይታወቅ፣ ይህንን አካሄድ የመከታተልና የመቆጣጠር ሥልጣን ኃላፊነት ኢንስቲትዩቱ እንደሌለው አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በፊት ትልቁ የመሬት መንቀጥቀጥ የደረሰው ከ110 ዓመት በዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት ነሐሴ 1898 ዓ.ም. ሲሆን፣ በውጭ አገር የጂኦፊዚካል ኦብዘርቫቶሪ ጣቢያዎች የተመዘገበው መጠን በሬክተር ስኬል 6.8 ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ጂኦፊዚካል ኦብዘርቫቶሪ ጣቢያ በ1943 ዓ.ም. የተቋቋመው አራት ኪሎ በሚገኘው በቀድሞው ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና የአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳይንስ ፋኩልቲ ቅጥር ግቢ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር ሒደት እገዛ ከማድረጉ ውጪ፣ በርካታ የምርምር ተግባር እንዳላካሄደ ዶ/ር አታላይ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ጣቢያውም ሊቋቋም የቻለው ፈረንሳይ ውስጥ ይካሄድ የነበረው ኢንተርናሽናል ሲምፖዚየም በምድር ወገብ አካባቢ የመሬትን መግነጢስ (ማግኔት) ለመመዝገብና በምዝገባውም ላይ ተመሥርቶ ምርመራ ለመሥራት የሚያስችል ጣቢያ በአፍሪካ ውስጥ እንዲቋቋም በመወሰኑና ለዚህም ተስማሚ ሆኖ የተገኘው አዲስ አበባ በመሆኑ ነው፡፡ አዲስ አበባ ተመራጭ የሆነችውም ከምድር ወገብ ስምንት ዲግሪ ያህል ርቃ መገኘቷ ነው፡፡

ጣቢያው በአሁኑ ጊዜ የጂኦፊዚክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ኢንስቲትዩት በሚል መጠሪያ በዘመናዊ መሣሪያዎች መደራጀቱንና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አሥር የምርምር ጣቢያዎች እንዳሉትም ዶ/ር አታላይ ተናግረዋል፡፡ ከጣቢያዎቹም መካከል የሠመራ፣ የደሴ፣ የአንኮበር፣ የሐረር፣ የወራቤ፣ የአዲስ አበባ ፉሪ ተራራ ተጠቃሾች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...