Monday, June 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​ከአፍሪካ በተጭበረበረ መንገድ የሚሸሸውን ከፍተኛ ገንዘብ ለማስቆም ታቦ ምቤኪ የሚመሩት ፓነል የአይኤምፍና የዓለም ባንክ ኃላፊዎችን ያነጋግራል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ኢትዮጵያ ቢሊዮን ዶሮችን ከሚያጡ ዋና ዋና አገሮች ተርታ ትመደባለች

የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ የአፍሪካ አገሮች በውጭ ኩባንያዎችና ኢንቨስትሮች አማካይነት በታክስ ማጭበርበር፣ በወጪና ገቢ ማብዛትና ማሳነስ፣ ሆነ ተብሎ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በማዛባትና በመሳሰሉት አድራጎቶች በየዓመቱ የሚያጡትን በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብ ለማስቆም በከፍተኛ ደረጃ የሚንቀሳቀስ ፓናል ተቋቁሞ ፕሬዚዳንት ምቤኪ እየመሩት ይገኛሉ፡፡

በምቤኪ የተመራው ፓነል ከአፍሪካ በተለያየ የማጭበርበሪያ ሥልት እየሸሸ የሚገኘው ገንዘብ መጠን በዓመት ከ60 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚገመት በፓነሉ ይፋ የተደረገው ጥናት ይጠቁማል፡፡ ይሁንና ባለፉት ሃምሳ ዓመታት ውስጥ ከአፍሪካ ተጭበርብሮ የወጣው ገንዘብ ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ እንደሚገመት ይገመታል፡፡ በአንፃሩ አፍሪካ ለምታካሂደው የመሠረተ ልማት ግንባታ ከ30 እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት በጀት ያስፈልጋታል፡፡ በመሆኑም ይህንን የበጀት ጥያቄ ለማሟላት ከውጭ በሚገኙ ዕርዳታዎችና ብድሮች ላይ ለመደገፍ ስትገደድ ይታያል፡፡ ሆኖም ግን ከአኅጉሪቱ የሚሸሸው የገንዘብ መጠን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎችን በአግባቡ ለማስተናገድ ያስችል እንደነበር ያሳያል፡፡

ከፍተኛ ፓነሉ አምና ይፋ ባደረገው ጥናት መሠረት፣ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. ከ2010 ጀምሮ በየአመቱ ከአሥር ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ በታክስ ማጭበርበር፣ በገቢና ወጪ ንግድ ማጭበርበር፣ የወጪና ገቢ ንግድ ደረሰኞችን ሆነ ብሎ በማዛባትና ወጪን በማናር እንዲሁም ሽያጭን በማሳነስ፣ በውጭ ህልውና ከሌላቸው እህት ኩባንያዎች ግዥ ስለመፈጸሙ፣ ዕዳ ስለመከፈሉ ወዘተ በሚጠቅሱ የተጭበረበሩ ተግባራት ሳቢያ አገሪቱ ከአሥር ቢሊዮን ዶላር በላይ እያጣች መሆኗን ‹‹ትራክ ኢት፣ ስቶፕ ኢት፣ ጌት ኢት›› በሚል ርዕስ ይፋ የተደረገው ጥናት ይጠቅሳል፡፡

በጥናቱ መሠረት ኢትዮጵያ እንዲህ ያለው የተጭበረበረ ተግባር ሰለባ ባትሆን ኑሮ፣ አብዛኞቹን የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ለማሳካት የፈጁባትን 13 ዓመታት ወደ ዘጠኝ ዓመት ያሳጥርላት እንደነበረም ጥናቱ ይጠቁማል፡፡ በመሆኑም በጥናቱ መሠረት ናይጄሪያ ከፍተኛ ገንዘብ የምታጣ ቀዳሚ አገር ስትሆን፣ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ አንጎላ፣ አልጄሪያ፣ ኮት ዲቯር፣ ሱዳን፣ ኢትዮጵያና ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ አሥሩ ዋና ዋና አገሮች ናቸው፡፡ በአንፃሩ ከእነዚህ አገሮች ተጭበርብሮ የሚሸሸውን ገንዘብ ከሚቀበሉ አገሮች አሜሪካ ቀዳሚዋ ሆናለች፡፡ ቻይና፣ ህንድ፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሜክሲኮና የመሳሰሉት አገሮች ይከተላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በቅርቡ ለሚዲያ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት ደግሞ አገሪቱ ከ1996 እስከ 2006 ዓ.ም. በነበሩት አሥር ዓመታት ውስጥ 26 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ ማጣቷን አስታውቋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደረሰኝ በማጭበርበር የታጣው ገንዘብ መጠን 19.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመትም ባለሥልጣኑ ይፋ አድርጓል፡፡ ይህም አገሪቱ በዓመት ከአምስት እስከ አሥር ከመቶ የሚሆነውን የኢኮኖሚዋን ድርሻ በዚህ መንገድ እያጣች እንደምትገኝም ተጠቁሟል፡፡

እንዲህ ያሉትን ችግሮች በማስታወቅ የውጭ ኩባንያዎችና ኢንቨስትሮች የሚያደርጉትን ያልተገባ ተግባር ለማስቆም ቅስቀሳ ላይ የሚገኘው ፓነል ሰሞኑን ወደ አሜሪካ አቅንቷል፡፡ በአሜሪካ ለአራት ቀናት የሥራ ጉብኝት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ በፓነሉ ሰብሳቢ ፕሬዚዳንት ምቤኪ የተመራው ልዑክ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ኃላፊዎችን እንዲሁም የዲፕሎማቲክ ኮር አባላትን እንደሚያነጋግር፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ከአፍሪካ በልዩ ልዩ ዘዴ እየሄደ የሚገኘውን ገንዘብ የማሸሽ ተግባር ሊያስቆም የሚችልና በዓለም አቀፍ ደረጃ ቅስቀሳ የሚያካሂድ ተቋም እንዲመሠርት ኃላፊነት የተሰጠው የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ከአምስት ዓመት በፊት በአፍሪካ የፋይናንስ፣ የዕቅድና የኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮች አራተኛው የጋራ ጉባዔ ላይ በተወሰነው መሠረት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት ይፋ ያደረገው ጥናትም አገሮች እየደረሰባቸውን ያለውን ጉዳት አመላክቷል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች