Tuesday, October 3, 2023

​እስራኤልና ጀርመን በጋራ የናዚ ጭፍጨፋን ያወገዙበት የአዲስ አበባ መድረክ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የዘር ማጥፋትና የጅምላ ጭፍጨፋ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተለያዩ አገሮች ውስጥ ተፈጽሟል፡፡ በሶቭየት ኅብረት፣ በአሜሪካ፣ በደቡብ አፍሪካና በሌሎች አገሮች ውስጥ የተፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ በተለያዩ መዛግብቶች ተዘርዝሮ ይገኛል፡፡ የጅምላ ጭፍጨፋ በተለያዩ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ምክንያት በአንድ ዘር፣ ብሔር ወይም በአንድ ቡድን ላይ የሚካሄድ የተደራጀ ሲሆን፣ በይበልጥ የዘር ማጥፋት ድርጊት (Genocide) ተብሎ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትም ‹‹በዘር ማጥፋት ወንጀል›› የሚጠየቁ ሲሆን ቅጣቱም ከፍተኛ የሚባል ነው፡፡

በኢትዮጵያ በአንዳንድ መዛግብት እንደተገለጸው ደቂቀ እስጢፋኖስ በመባል የሚታወቀውን ቡድን ለማጥፋት የተወሰደው ዕርምጃ እንደ ዘር ማጥፋት ወንጀል  ይወሰዳል፡፡ በዘመነ ደርግ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር በሚሉ ስያሜዎችም የተከሰተው ዕልቂትም የጅምላ ጭፍጨፋ ሌላኛው መገለጫ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲወሳ ነበር፡፡ በአገራችን ለተፈጸሙ የጅምላ ጭፍጨፋዎች አንዳንድ ማስታወሻዎች የቆሙ ሲሆን፣ ከመካከላቸው በመቐለ የሚገኘው የሐውዜን አደባባይና የሰማዕታት ሐውልት፣ እንዲሁም በአዲስ አበባ የሚገኘው ‹‹መቼም እንዳይደገም›› በሚል የቀይ ሽብር ሰለባ ለሆኑ የቆመው ሐውልት ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ስድስት ኪሎ የሚገኘው የሰማዕታት ሐውልትም በግራዚያኒ የተመራው የፋሽስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በተለይ ደግሞ በአዲስ አበባ ነዋሪዎች ላይ ለፈጸመው የጅምላ ጭፍጨፋ ማስታወሻ የቆመ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ለተፈጸሙ የዘር ማጥፋት ለሚመስሉ ወንጀሎችና የጅምላ ጭፍጨፋዎች አንዳንድ ማስታወሻዎች ሲቆሙና በፈጻሚዎች ላይ ሕጋዊ ዕርምጃ ሲወሰድ የሚስተዋል ቢሆንም፣ በቂ ምርምር እየተደረገበት ትምህርት ሲወሰድበት እንደማይታይ በብዙዎች ዘንድ ይወሳል፡፡

ይኼ ለሰው ልጆች ክፉና አስነዋሪ ድርጊት ተደርጐ የሚወሰደውና በተለያዩ አገሮች ይፈጸም እንጂ፣ በጀርመንና በሩዋንዳ የተፈጸሙ አሰቃቂ ድርጊቶችን ግን የሚስተካከል ያለ አይመስልም፡፡ የጥላቻና የዘረኝነት ውጤት የሆነው ይኸው ድርጊት፣ የናዚ ጀርመኖች በስደተኛ እስራኤላውያን በፈጸሙት የጅምላ ጭፍጨፋ ስድስት ሚሊዮን ንፁኃን ሰዎች ሲያልቁ፣ በሩዋንዳም የሁቱ ጎሳ አባላት የመንግሥትን ሥልጣንና ጉልበት በመጠቀም፣ ለወራት በዘለቀ ጥቃት አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ቁጥር ያላቸው ለዘብተኛ ሀቱቲዎችና የቱትሲ ተወላጆች ዕልቂት ተፈጽሞባቸዋል፡፡

የፀጥታው ምክር ቤትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶችና የዓለም መንግሥታት፣ በተለይ የሩዋንዳን አሰቃቂ ፍጅት በወቅቱ በመድረስ ማስቀረት እየቻሉ በዳተኝነት የሰው ልጅ በከንቱ እንዲያልቅ አድርገዋል ተብሎ ወቀሳ የሚቀርብባቸው ሲሆን፣ ከድርጊቱ ትምህርት ለመቅሰም በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ይውላል፡፡

በየዓመቱ ጥር 18 ቀን በጀርመን ናዚ ያለቁ አይሁዶችን ለማስታወስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የተወሰነ ዓለም አቀፍ ቀን ነው፡፡ ዘንድሮ የእስራኤል መንግሥትና የጀርመን ኤምባሲ በጋራ በትብብር በዓሉን በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኮሚሽን የስብሰባ አዳራሽ አዘጋጅተዋል፡፡

በዓሉ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ አገሮች ከፍተኛ ዲፕሎማቶች፣ የእስራኤል የሃይማኖት መሪዎች፣ አምባሳደሮችና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ተከብሮ ውሏል፡፡ “Holocust Memorial Day” በመባል የሚከበረው ይኼው ዓለም አቀፍ ሥነ ሥርዓት በቅርቡ በጎረቤት ሱዳን ዳርፉርና በኬንያ የተፈጸሙትን፣ እንዲሁም አሁንም ድረስ በደቡብ ሱዳን ውስጥ በመፈጸም ላይ ያለውን ድርጊት የሚመለከት ነው፡፡

በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር በላይነሽ ዚቫይዳ ባደረጉት አጭር ንግግር፣ በሰው ልጅ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ. ከ1941 እስከ 1945 ሰውን ለመግደል ኢንዱስትሪዎች ተቋቁመው እንደነበር በማስታወስ ነበር የጀመሩት፡፡ በዚሁ ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች በተገደሉበት ዘመቻ፣ ስድስት ግዙፍ የመግደያ ካምፖች መገንባታቸውን፣ እንዲሁም ሰዎች የሚገደሉባቸው ረጃጅም የጋዝ መተላለፊታ ቱቦዎች ተዘርግተው አገልግሎት እንደሰጡ ገልጸዋል፡፡

አሌክሳንደር ውርዝ የተባለ ጋዜጠኛ፣ ‹‹ሴቶችና ሕፃናት ወንዶች ዕርቃናቸውን ከኮንክሪት በተሠሩ ሳጥኖች ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ በእያንዳንዱ ሳጥን ከ200 እስከ 250 ሰዎች ይታሰራሉ፡፡ ሙሉ ለሙሉ ጨለማ ነው፡፡ ጋዝ ከላይ እንዲርከፈከፍ ይደረጋል፡፡ ከዚያም ውኃ ሰማያዊ ቀለም ያላቸው መስቀያዎች ከላይ ወርደው ከፍተኛ ሙቀት ያለው አየር እንዲተንባቸው ይደረጋል፡፡ ከሁለት እስከ አሥር ደቂቃ ባለው ጊዜ ውስጥ የታፈነው ሰው ይሞታል፤›› በማለት የሁኔታውን አሰቃቂነት ገልጾታል፡፡

ይህንን የጋዜጠኛውን ማስታወሻ የጠቀሱት አምባሳደር በላይነሽ ከዚህ ግድያ ያመለጡ አይሁዶችን ግን፣ ‹‹ብቀላን አላሰቡም፣ አዲሲቱን እስራኤል መልሶ መገንባት እንጂ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ከሰባት አሥር ዓመታት በኋላ ታሪክ ያስተማረንን እንዳንረሳው ዛሬም እናስታውሳለን፡፡ አሰቃቂ ውጤቱንም እንዘክራለን፡፡ የጅምላ ጭፍጨፋው ለቀጣይ ከማንቂያም ደወል በላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በእስራኤልና በጀርመን መካከል ስላለው ግንኙነት አስተያየት የሰጡት አምባሳደር በላይነሽ፣ እ.ኤ.አ. በ1956 ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ፣ የላቀ ትብብር እያደረጉ እንደሆነና ከሁለትዮሽ ግንኙነትም በዘለለ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ አገሮች (ኬንያ፣ ጋና፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ካሜሮንና ብሩንዲ) ጋር በርካታ የልማት ፕሮጀክቶች በጋራ እንደሚያከናውኑ ገልጸዋል፡፡

ንግግራቸው ሲያጠቃልሉም፣ ‹‹የናዚዎችን ጭካኔ ስናስታውስ የይቅር ባይነትና የበጎ አሳቢነትን ኃይል መዘንጋት የለብንም፤›› ብለዋል፡፡          

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ጆአኪም ስክሚድት በበኩላቸው፣ ‹‹ጀርመናውያን በሕዝቡ ላይ የፈጸሙትን ስቃይ ስመለከት፣ ይህንን ውሳኔ በመወሰንዎ በጀርመን ሕዝብ ስም ላመሰግንዎት እወዳለሁ፤›› በማለት የአምባሳደር በላይነሽን ጥረት አድንቀዋል፡፡

የተፈጸመውን እብደት ለመግለጽ ቃል እንደሌላቸው የተናገሩት አምባሳደሩ፣ ‹‹ከሰው ልጅ ህሊና የማይፋቅና ለዘለዓለም ለሰው ልጅ ማስጠንቀቂያ መሆን ያለበት ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ጀርመንና ጀርመናውያን ለተፈጸመው ጥፋት ሙሉ ኃላፊነት እንደሚወስዱ ገልጸው፣ ‹‹በሰው ልጅ ታሪክ የተፈጸመውን ይኼንን የጨለማ ምዕራፍ መቼም አንረሳውም፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹የዚህ ወንጀል ሰለባ የሆኑትንም ሆነ የዚህን ወንጀል ፈጻሚ የሆኑትን ልጆቻችን መቼም ሊረሱዋቸው አይገባም፤›› በማለት አክለዋል፡፡

በቅርቡ ‹‹አብርሃም ጋይገር›› በመባል የሚታወቀው ሽልማት የተሰጣቸው የጀርመን መርሒተ መንግሥት አንገላ መርከልን ንግግርን ያስታወሱ አምባሳደሩ፣ ፀረ እስራኤል ከሆኑ አገሮች ወደ ጀርመን በሚገቡ ስደተኞች ምክንያት አሁንም በጀርመን ፀረ ፅዮናዊነት አመለካከት ላይ ሥጋት ስለተሰማቸው የአይሁድ ማኅበረሰቦች ተናግረዋል፡፡ አንገላ መርኬል፣ ‹‹እጅግ በጦርነት ከታመሱ አገሮች የመጡ ዜጎች እንቀበላለን፡፡ ነገር ግን እንዲህ ዓይነት ፀረ ፅዮናዊነት አመለካከት ሲከሰት የማጥፋትና የማክሰም የጀርመንና የሕዝቦቿ ግዴታ ነው፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ አምባሳደር ስካሚድት፣ ‹‹የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች የልጅ ልጆች ድርጊቱን እኩል በማውገዝና ሰማዕታትን በማሰብ በእኩል እናከብራለን፤›› ብለዋል፡፡

የእስራኤል የዘር ማጥፋት ማስታወሻ ማዕከል የጥናትና ምርምር ፕሮጀክቶች ዳይሬክተር ዶ/ር ሊ ፕራይስ በዕለቱ ተገኝተው ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡ ዶ/ር ፕራይስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማዕከሉ የተቋቋመው የተፈጸመውን ጥፋት ለማጥናት፣ ለመሰነድና ለመመርመር ነው፡፡ ‹‹ድርጊቱ በሰው ልጅ ዘለዓለማዊ ትምህርት ሆኖ እንዲኖርና እንዳይረሳ ለማድረግ ነው፡፡ የሆነው ሆኗል፣ ምንም ቢደረግ አይመለስም፡፡ የእኛ ዓላማ እንዲህ ዓይነት ፍፃሜ እንዳይደገም ለማስተባበር ነው፡፡ ምልክቶች ሲኖሩም አፋጣኝ መፍትሔና መከላከያ መንገዶች ለመጠቆም እንዲረዳ ነው፤›› ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -