Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​​​​​​​የግብፅ ኩባንያዎች በ120 ሚሊዮን ዶላር የኢንዱስትሪ ፓርክ ለመገንባት ቦታ እያማረጡ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግብፅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የራሳቸውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ገንብተው ማምረት የሚችሉባቸውን ፋብሪካዎች ለመትከል፣ 120 ሚሊዮን ዶላር መመደባቸውን የግብፅ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡

በግብፅ ኤምባሲ የንግድ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዋሊድ አልዛውመር ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ትልልቅ የግብፅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዞን ለማቋቋም የ200 ሔክታር መሬት ጥያቄ ለመንግሥት አቅርበዋል፡፡

ከዚህ ቀደም የኢንዱስትሪ ፓርኩን ለመገንባት ግብፆቹ የመረጡት ቦታ ዱከም ከተማ ላይ እንደነበር ያስታወሱት አልዛውመር፣ መንግሥት በበኩሉ ከዱከም ይልቅ በሌሎች አካባቢዎች ፓርኩን እንዲገነቡ በመጠየቁ እንቅስቃሴው ሲጓተት ቆይቷል ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት በኢንዱስትሪ ቀጣናነት በተመረጡ አካባቢዎች ግንባታ እንዲካሄዱም ዕድሉን ሰጥቷቸዋል፡፡

ግብፆች በሐዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በመቐለና በሌሎች ለኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ በተመረጡና መንግሥት እየገነባባቸው በሚገኙ አካባቢዎች የራሳቸውን ፓርክ እንዲያቋቁሙ አማራጭ ሐሳብ መንግሥት ማቅረቡን አልዛውመር ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የኩባንያዎቹ ልዑካን ቡድን በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጉብኝት ካካሄደ በኋላ ውሳኔውን እንደሚያሳውቅ ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡

የቀድሞው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ባልደረባ አቶ መላኩ ጁሐር የኢትዮጵያና የግብፅ ንግድ ምክር ቤት ዳይሬክተር ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ አቶ መላኩ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ትልልቅ የግብፅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ጥያቄ እያቀረቡ እንደሚገኙና በተለይ በመድኃኒትና በሕክምና መስክ ሦስት ትልልቅ የግብፅ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ተዘጋጅተዋል፡፡

መንግሥት የግብፆችን ጥያቄ ተቀብሎ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ከተገነባ፣ በዱከም የሚገኘውን የቻይናውያንን ኢስተርን ኢንዱስትሪ ዞን በመከተል ሁለተኛው የውጭ ኢንዱስትሪ ፓርክ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ በተመሳሳይ ከህንድና ከቱርክም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለመገንባት የመሬት ጥያቄዎች ለመንግሥት ሲቀርቡ መቆየታቸው አይዘነጋም፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች