Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

​የአክሰስ ሪል ስቴት ኩባንያን ህልውና የሚያራዝም ውሳኔ ተላለፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የመጀመሪያ ደረጃ የፋይናንስ ሪፖርት ቀረበ

የአክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ባለአክሲዮኖች የኩባንያቸው ህልውና ተጠብቆ እንዲቆይ 25 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ አክሲዮኖች ለገበያ እንዲቀርቡ ውሳኔ አሳለፉ፡፡

ባለአክሲዮኖች የካቲት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ባካሄዱት አስቸኳይ ጉባዔ 25 ሺሕ አክሲዮኖች ለገበያ እንዲቀርቡና አክሰስ ሪል ስቴት ህልውናው እንዲጠበቅ በአብላጫ ድምፅ ወስነዋል፡፡ ነገር ግን በተካሄደው ውይይት በአሁኑ ወቅት አክሰስ ሪል ስቴት ያለው ስም የጎደፈ እንደመሆኑ አክሲዮኖቹ ፈላጊ ይኖራቸዋል ወይ? የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር፡፡

የአክሰስ ሪል ስቴት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት አክሲዮኖቹ ፈላጊ እንደሚያገኙ በመተማመን፣ አክሲዮኖቹ በቅድሚያ ለቤት ገዥዎች እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል፡፡

ከአክሰስ ሪል ስቴት ባለአክሲዮኖችና ቤት ገዥዎች የተወጣጣ የፋይናንስ ኮሚቴ በጉባዔው ወቅት ግርድፍ ያለውን የመጀመሪያ ደረጃ የፋይናንስ ሪፖርት አቅርቧል፡፡ ሪፖርቱ እ.ኤ.አ. ከ2012 እስከ መስከረም 2015 ድረስ የአክሰስ ሪል ስቴት ገቢ፣ ወጪና ዕዳ ያጠቃለለ ነው ተብሏል፡፡

በዚህ መሠረት አክሰስ ሪል ስቴት ከአገር ውስጥ ቤት ገዢዎች 1.4 ቢሊዮን ብር፣ ውጭ አገር ከሚኖሩ ቤት ገዥዎች ደግሞ 74.7 ሚሊዮን ብር ሰብስቧል፡፡ በድምሩ አክሰስ ሪል ስቴት 1.5 ቢሊዮን ብር የሰበሰበ ሲሆን፣ 67.5 ሚሊዮን ብር እንዲመለስላቸው ለፈለጉ ቤት ገዥዎች ተመልሷል፡፡ ለካፒታልና ለብድር 71.1 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ በ426.7 ሚሊዮን ብር የቤትና የመሬት ግዥ እንደተፈጸመ፣ 540.6 ሚሊዮን ብር ደግሞ በግንባታ ላይ መዋሉ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

አክሰስ ሪል ስቴት በሌሎች ድርጅቶች አክሲዮን በመግዛትና አብሮ በመሥራት 131.9 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት ማድረጉ፣ ከውጭ አገር ለገዛቸው የግንባታ መሣሪያዎች 33.9 ሚሊዮን ብር ማውጣቱ በፋይናንስ ሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ ለተለያዩ ጉዳዮች ከዋለው 6.3 ሚሊዮን ብር ጋር 1.3 ቢሊዮን ብር አውጥቷል፡፡ ለሥራ ማስኬጃ ካወጣው 111.3 ሚሊዮን ብር ጋር ሲደመር በጠቅላላ 1.4 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉ ተመልክቷል፡፡ በዕዳ ደግሞ 215.8 ሚሊዮን ብር ተመዝግቧል፡፡ በባለአክሲዮኖቹ ጠቅላላ ጉባዔ በአቶ ሰለሞን መንግሥቱ በቀረበው የፋይናንስ ሪፖርት ላይ ምንም ዓይነት አስተያየት አልተሰጠም፡፡

የፋይናንስ ኮሚቴው አክሰስ ሪል ስቴት አክሲዮን ማኅበር ሊያተኩርባቸው ይገባል ያላቸውን ነጥቦች ጠቁሟል፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በአክሰስ ሪል ስቴት ኩባንያ የተፈጠረውን መመሰቃቀል ለማስተካከል ከፋይናንስ በተጨማሪ ጠንካራ የመንግሥት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ፣ በሁለተኛ ደረጃ አክሲዮን ማኅበሩን ለማጠናከር የቤት ገዥዎች ጠንካራ ተሳትፎ ነው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው ደግሞ ከሦስተኛ ወገኖች ጋር በሚደረግ ድርድርና በአጠቃላይ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ጠንካራ ማኔጅመንት ያስፈልጋል የሚለው ነው፡፡

እነዚህ ጉዳዮች በጥሩ መንገድ የሚጓዙ ከሆነ የፋይናንስ ኮሚቴው የሚኖረውን ቀጣይ ተስፋ አትቷል፡፡ ኮሚቴው እንዳለው የቀድሞ የአክሰስ ሪል ስቴት ቤቶች ዲዛይን የማይቀየር በመሆኑና ተጨማሪ የሕንፃ ከፍታ ስለሚኖር በቤቶች ቁጥር ላይ ጭማሪ ይኖራል ተብሏል፡፡

በዚህ ሥሌት 266,218 ካሬ ሜትር ቦታ ተጨማሪ ይገኛል፡፡ ቀደም ሲል ከነበረው ጋር ሲደመር በአጠቃላይ 471,17 ካሬ ሜትር ቦታ ለግንባታ ዝግጁ ይሆናል፡፡ በዚህ ቦታ ላይ ግንባታ ለማካሄድ 4.2 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ኮሚቴው በሪፖርቱ ገልጿል፡፡

በፋይናንስ ሪፖርቱ ትንታኔ አዲሶቹ ቤቶች ተገንብተው በካሬ ሜትር 30 ሺሕ ብር ቢሸጡ 7.9 ቢሊዮን ብር እንደሚገኝ፣ በዝቅተኛ ግምት በካሬ ሜትር 20 ሺሕ ብር ቢሸጡ እንኳ 5.3 ቢሊዮን ብር እንደሚያገኝ ኮሚቴው በግርድፍ የፋይናንስ ሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡

በከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ኃይሌ የሚመራው የአክሰስ ሪል ስቴት ችግር ፈቺ ዓብይ ኮሚቴ ጥር 2 ቀን 2008 ዓ.ም. ከአክሰስ ሪል ስቴት ባለአክሲዮኖችና ቤት ገዥዎች ጋር ባካሄደው ጉባዔ፣ ሁለቱም አካላት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በየራሳቸው ውይይት አድርገው ሐሳብ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

በዚህ መሠረት ቤት ገዥዎች ራሱን የቻለ ድርጅት እንዲመሠርቱ፣ ባለአክሲዮኖች ደግሞ ካፒታል እንዲጨምሩ ውሳኔ ተላልፎ ነበር፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች