Friday, September 30, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  አነስተኛና መካከለኛ አልባሳት አምራቾች ያልተገባ የጉምሩክ ቀረጥ መጠየቃቸውን ተቃወሙ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ከ80 በላይ አምራቾች የባንክ ሒሳባቸው መታገዱን አስታውቀዋል

  በርካቶቹ በተጠየቁት ቀሪ የኋላ ሒሳብ ሳቢያ ሥራ ለማቆም ጫፍ መድረሳቸውን ይናገራሉ

  በአነስተኛና በመካከለኛ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራችነት ሥራ ላይ እንደተሰማሩ የገለጹ አምራቾች፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከሕግ አግባብ ውጪ ለአምራቾች የተፈቀደውን የቀረጥ ማስከፈያ ሒሳብ ተላልፎ በመጠየቃቸው ያልተገባ ቀረጥን በመቃወም አቤቱታ አቀረቡ፡፡

  ከ150 በላይ አምራቾች ያልተገባ የጉምሩክ ቀረጥ መጠየቃቸውን በማስመልከት፣ በወኪሎቻቸው እንዲሁም በሕግ አማካሪና ጠበቃቸው በኩል ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ መንግሥት በሰጣቸው የጉምሩክ ቀረጥ ማበረታቻ ተጠቃሚ ቢሆኑም፣ ለምርት የሚጠቀሙበትን ጥሬ ዕቃ ዋጋ ከፍ በማድረጉ ህልውናቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ተደቅኖባቸዋል፡፡

  የአምራቾቹ ጠበቃና የሕግ አማካሪው አቶ ተካ መሐሪ ለሪፖርተር እንዳብራሩት ከሆነ፣ ከ150 በላይ በሆኑ አነስተኛና መካከለኛ አምራቾች ላይ የተፈጠረው ሥጋት በውዝፍ ግብር ጥያቄ ሳይወሰን ወደ ህልውና ሥጋት መሸጋገር ጀምሯል፡፡ አብዛኞቹ የተጋነነና ከእውነታው ያፈነገጠ ግብር እንዲከፍሉ የተጠየቁት በድኅረ የታክስ ኦዲት አሠራር መነሻነት እንደሆነ ያስታወቁት አቶ ተካ፣ ከሦስት ዓመት በፊት ላስገቡት ጥሬ ዕቃ አሁን ክፈሉ የተባሉት ሒሳብ ከእውነታው የወጣና በትልልቅ አምራቾች ደረጃ የተሠራ ነው ብለዋል፡፡

  አብዛኞቹ አምራቾች በገጠሩ አካባቢ ለሚኖረው ሕዝብ የሚውሉና በዝቅተኛ ዋጋ ለሽያጭ የሚቀርቡ የፖሊስተር አልባሳትን ከቻይና አምራቾች ራሳቸው ሄደው በመግዛት በየፋብሪካዎቻቸው ይሰፋሉ፡፡ የሚያስመጧቸው የፖሊስተር ጥሬ ዕቃዎች ‹‹Polyester knitted fabric, polyester semi-finished knitted fabric, polyester trimming material›› የተሰኙት ሲሆኑ፣ እንደ አቶ ተካ በእነዚህ ጥሬ ዕቃዎች ላይ የተተመነው የመግዣ ዋጋ ነው የቅሬታው ዋነኛ ምንጭ፡፡

  በ2006 ዓ.ም. እና ከዚያም ወዲህ ለአንድ ኪሎ ግራም ፖሊስተር የሚጠየቀው የጉምሩክ ቀረጥ ከ0.50 ዶላር እስከ 0.70 ዶላር ድረስ ባለው የዋጋ ክልል ውስጥ እንደነበር፣ ሆኖም ባለሥልጣኑ ይህንን በማስቀረትና የራሱን ዋጋ በመተመን በኪሎ ግራም 2.80 ዶላር መክፈል አለባችሁ ማለቱ አብዛኞቹን አምራቾች አሳዝኗል ያሉት አቶ ተካ፣ ባለሥልጣኑ ጥሬ ዕቃው በተሸጠበት እንጂ በተገዛበት ዋጋ ሒሳቡን ለመቀበል እንደማይፈልግ በማስታወቁ ላለፉት ሰባት ወራት በየቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ ሲያቀርቡት የነበረው አቤቱታ ሰሚ ማጣቱን አስረድተዋል፡፡

  አምራቾቹ የወከሏቸው ግለሰቦች ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ጥሬ ዕቃ የገዙበትን የደረሰኝ ዋጋ ከዕቃው ዋጋ በታች ነው በማለት ውድቅ ያደረገው ለውጭ ገበያ ከሚያቀርቡ ትልልቅ አምራቾች ጋር በማወዳደር ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአንዳንዶቹ አምራቾች የደረሰኝ ዋጋ ተቀባይነት እያገኘ፣ የአብዛኞቹ ውድቅ ሲደረግ መታየቱም በባለሥልጣኑ የቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች በኩል ሆን ተብሎ የሚፈጸም የሕግ ጥሰት ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የተወሰደብን ዕርምጃ ገቢ ለመሰብሰብ ብቻ ያለመና ሕግ የተላለፈ በመሆኑ መንግሥት ቆም ብሎ እንዲያጤው እንጠይቃለን፤›› ያሉት አምራቾቹ፣ ጥያቄዎቻቸውን በጽሑፍ ለባለሥልጣኑ ዋና መሥሪያ ቤት እንዲሁም ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር አስገብተዋል፡፡

  ‹‹ድርጅት የሚያዘጋ ዕርምጃ እየተወሰደብን ነው፡፡ ችግራችን ሊደመጥልን ይገባል፡፡ የመንግሥት አካላትም ፋብሪካዎቻችንን በአካል እንዲጎበኙና እውነታውን እንዲገነዘቡልን እንፈልጋለን፤›› የሚሉት አምራቾቹ፣ ከአቅማቸው በላይ የተጠየቁትን ቀረጥ መክፈል እንደማይችሉ፣ አንዳንዶቹም እስከ 34 ሚሊዮን ብር ውዝፍ የቀረጥ ሒሳብ በመጠየቃቸው ሳቢያ የጤና መታወክ እንደደረሰባቸው አስታውቀዋል፡፡

  እስከ 30 ሺሕ ለሚገመቱ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ወደ ከፍተኛ ደረጃ አምራችነት ለመሸጋገር በሚያልሙበት ወቅት፣ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እንኳ ሳይደርሳቸው የባንክ ሒሳባቸውና የግብር ከፋይነት መለያቸው ቁጥራቸው (ቲን) እንዲታገድ መደረጉ፣ ይበልጥ አደጋ ውስጥ እየጣላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን በተደረገባቸው ዘመቻም 80 ያህል አምራቾች ይህ ዕርምጃ እንደተወሰደባቸው ገልጸዋል፡፡

  እየተወሰደባቸው ያለው ዕርምጃ ተጨባጭ ማስረጃ ሳይኖር ያውም ከዓመታት በፊት ወደ አገር በገባ ጥሬ ዕቃ ዋጋ ላይ ተመሥርቶ በሚጠየቅ ሒሳብ መሆኑ፣ ከዘርፉ እንዲወጡ የሚደረግ ጫና ያለ ስለሚያስመስል፣ መንግሥት ጉዳዩን በጥሞና ይመልከተው ያሉት አምራቾቹ፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ርካሽ አልባሳትን እዚሁ በማምረት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ከግምት ያላስገባ አሠራር ከመሆኑ ባሻገር፣ ፋብሪካ እንዲዘጉና ሠራተኛ እንዲበትኑ የሚያስገድድ ዕርምጃ ተወስዶብናል በማለት አቤታተቸውን አሰምተዋል፡፡

  ይሁንኑ ቅሬታ በመንተራስ ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ምላሽ ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ በስልክ የተደረጉ ሙከራዎችም ምላሽ አላገኙም፡፡ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ ስለ ጉዳዩ ሲጠየቁ፣ አጣርተው በመጪው ሳምንት ምላሽ እንደሚሰጡ ከመግለጻቸው በቀር ሌላ ምላሽ ማግኘት አልተቻለም፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች