Tuesday, April 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ በዘረመል የተለወጡ ህያው የጥጥ ዝርያዎች እንዲመረቱ ፈቀደች

ተዛማጅ ፅሁፎች

በበቆሎ ላይ የዘረመል ምርምሮች እንዲካሄዱ ‹‹ልዩ ፈቃድ›› ተሰጥቷል

ከሁለት ዓመታት ጥብቅ የመስክ ላይ ሙከራ በኋላ መንግሥት በዘረመል የተለወጡ ህያው የጥጥ ዝርያዎች እንዲመረቱ የሚያስችል ፈቃድ፣ ለኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት መሰጠቱ ታወቀ፡፡

ኢንስቲትዩቱ ፈቃድ ለሚሰጠው ለአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ሚኒስቴር ያቀረበውን የምርምር ውጤት መነሻ በማድረግ ለቀረበለት የጽሑፍ ማመልከቻ፣ ሚኒስቴሩ ፈቃድ መስጠቱን በሚኒስቴሩ የደኅንነተ ሕይወት ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ጉዲና ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ አቶ አሰፋ እንደሚሉት ፈቃድ የተሰጠው ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን በጥብቅ የተከለለ የመስክ ምርምር ውጤት በመፈተሽ ነው፡፡

በመሆኑም በዘረመል የተለወጡት ህያው የጥጥ ዝርያዎች በአካባቢ፣ በሰው ጤና እንዲሁም በሥነ ምኅዳር ላይ የሚያደርሱት ተፅዕኖ እንደማይኖር በመረጋገጡ በብሔራዊ የደኅንነተ ሕይወት አዋጅ መሠረት፣ የምርምር ውጤቶቹ የሚጠበቅባቸውን መሥፈርቶች አሟልተው በመገኘታቸው ወደ ምርት ሥራ በመግባት ለኢንዱስትሪ ፍጆታ መዋል እንዲችሉ ፈቃድ ተሰጥቷል፡፡ በዘረመል የተለወጡት ዝርያዎች ለመራባት ወደ ሌሎች እፅዋት በመብነን (ርክበ ብናኝ) የማይፈጽሙ በመሆናቸው ጭምር፣ የሚያስከትሉት ተፅዕኖ ዝቅተኛ ስለመሆኑ ተብራርቷል፡፡ በመሆኑም አሜሪካን ቦልዎርም የተባለውንና በከፍተኛ ደረጃ የጥጥ ዝርያዎችን የሚያጠቃውን ተባይ ጨምሮ ሌሎችም የጥጥ በሽታ አምጪ ተህዋስያንና ነፍሳትን በመከላከል፣ አዲሱ የዘረመል ጥጥ እስካሁን ሲገኝ የነበረውን ምርት እንደሚያሻሽለው ተስፋ ተደርጓል፡፡

በዘረመል የተለወጡ ህያው ዝርያዎችን በሚመለከት በርካታ ክርክሮችና ሙግቶች ሲደረጉ ቢቆዩም፣ ሚኒስቴሩ ግን ሳይንሳዊ እውነታዎችን መሠረት ያደረጉ ማስረጃዎችን በማቅረብ በርካታ ምክክሮችን እንዳካሄደና ግንዛቤ እንዳስጨበጠ አስታውቀዋል፡፡

የዘረመል ልውጥ ሕያው የጥጥ ዝርያዎቹ የአገሪቱን የጥጥ ምርት እጥረት በመቅረፍ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪውን የግብዓት ፍላጎት እንደሚያሟሉ ተስፋ ተደርጎባቸዋል፡፡ በመሆኑም መነሻቸው ከህንድ የሆኑ ሁለት ዓይነት የጥጥ ዝርያዎች ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ባሉት አምራቾች ዘንድ መመረት እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡

ከዘረመል ጥጥ ዝርያዎች ባሻገር በዘረመል ልውጠ ህያው በቆሎ ላይ የላቦራቶሪ ምርምር እንዲካሄድ ‹‹ልዩ ፈቃድ›› በሚኒስቴሩ ለግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት መሰጠቱም ታውቋል፡፡ በተሻሻለው ደኅንነት ሕይወት አዋጅ ቁጥር 896/2007 መሠረት፣ ልዩ ፈቃድ የሚሰጠው ልውጠ ህያው ዝርያዎችን በዝግ አጠቃቀም ለምርምር ወይም ለትምህርት ለመዋል፣ እንዲሁም ልውጥ ህያው ዝርያዎችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ከሚኒስቴሩ በጽሑፍ የሚሰጥ ፈቃድ ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን ፈቃድ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በማግኘቱ የምርምር ሥራዎቹን በበቆሎ ላይ እንደሚጀምር ይጠበቃል፡፡ መረጃዎች እንዳመለከቱት፣ በበቆሎ ላይ ለሚደረገው የላቦራቶሪ ምርምር ሥራ የአምስት ዓመታት ልዩ ፈቃድ መሰጠቱ ታውቋል፡፡

በአዋጁ መሠረት በአገር ውስጥ ወደ አካባቢ ለመልቀቅ፣ እንዲሁም በአንድ ልውጥ ህያው ላይ እንቅስቃሴ እንዲደረግ ከሚኒስቴሩ በሚሰጥ የጽሑፍ አዎንታ አማካይነት ‹‹ከግንባዜ የመነጨ ስምምነት›› የሚባለው ፈቃድ ይሰጣል፡፡ ይህም ከላቦራቶሪና ከተከለለ የመስክ ምርምር፣ እንዲሁም ከትምህርት ወይም ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ከሚሰጠው የጽሑፍ ፈቃድ ይልቅ የዘረመል ልውጥ ህያው ዝርያዎች እንዲመረቱ የሚሰጥ ፈቃድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ታደሰ ዳባ (ዶ/ር)፣ ከሚኒስቴሩ ስለተገኘው ፈቃድ አረጋግጠው ወደፊት ዝርዝር መረጃ እንደሚሰጡበት ገልጸዋል፡፡ ሪፖርተር ባረጋገጠው መሠረት፣ የአገሪቱ የግብርና ሳይንቲስቶች የእንሰት ሰብል ላይ የሚታዩ በሽታዎችን ለመቋቋም የሚያስችሉ ተመሳሳይ የዘረመልና የዘመናዊ ጥበበ ሕይወት (ባዮቴክኖሎጂ) ምርምር ሥራዎችን ለማካሄድ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች