Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናሜቴክ ከፍተኛ የሀብት ብክነት እንዳለበት አመነ

ሜቴክ ከፍተኛ የሀብት ብክነት እንዳለበት አመነ

ቀን:

ያለ ጥናት የተመረቱ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ማሽነሪዎች ለብክነት ተጋልጠዋል

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ከፍተኛ የሀብት ብክነትና የውጤታማነት ችግር እንዳለበት አመነ። ኮርፖሬሽኑ ይህንን ያስታወቀው ረቡዕ ግንቦት 29 ቀን 2010 ዓም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለፓርላማ የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበበት ወቅት፣ ለተሰነዘረበት ከፍተኛ የሀብት ብክነት ወቀሳ ምላሽ ሲሰጥ ነው።

የቀድሞው የንግድ ሚኒስትር በቅርቡ የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ሆነው የተሾሙት በቀለ ቡላዶ (/) በሰጡት አስተያየት፣ በተቋሙ ውስጥ የመንግሥትን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመደገፍ የሚያስችል ትልቅ አቅም መኖሩን እንደተገነዘቡ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ኮርፖሬሽኑ የያዛቸው ግዙፍ የመንግሥት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እየተከናወኑ አለመሆኑን፣ የውጤታማነትና የሀብት ብክነት ችግሮች መኖራቸውን እንዳረጋገጡ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በቀጣይ ችግሮቹን ለማስተካከል እንደሚጥሩ አስረድተዋል።

- Advertisement -

ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው ግምገማ ኮርፖሬሽኑ የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ተረክቦ ለመፈጸም አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ በራሱ የጀመራቸውን ሥራዎችም በተመለከተ ከፍተኛ ብክነት የታየበት መሆኑን አረጋግጧል። በአጠቃላይ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማባከኑን ቋሚ ኮሚቴው አስታውቋል። ኮርፖሬሽኑ ምንም ዓይነት የገበያ ጥናት ሳያደርግ የተለያዩ ማሽኖች፣ መለዋወጫ ዕቃዎችና መሣሪያዎችን በማምረት አከማችቶ እንዲቀመጡ ማድረጉን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል። በጥቅሉ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ንብረቶች ያለ ጥናት ተመርተው ገበያ በማጣታቸው፣ ለበርካታ ዓመታት በመጋዘን ተከማችተው እንደሚገኙ ጠቁሟል። የአገሪቱን ኢኮኖሚ ሊደግፍ በሚችል መንገድና በጥናት ላይ ተመሥርቶ ባለመሥራቱ 4.4 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያላቸው የእርሻ ትራክተሮች፣ መሣሪያዎችና የመለዋወጫ ዕቃዎች በአዳማ የእርሻ መሣሪያዎች ኢንዱስትሪ ክምችት ውስጥ እንዲቀመጡ ማድረጉን ጠቁሟል። አሥር ሺሕ በላይ የእርሻ ትራክተሮችና መለዋወጫዎች ተመርተው በገበያ ዕጦት በመጋዘን እንዲከማቹ ያደረገው ኮርፖሬሽኑ፣ ለአርሶ አደሮች በረዥም ጊዜ የዱቤ ሽያጭ ለማከፋፈል ዕቅድ ቢኖረውም ዕቅዱን በተመለከተ ከክልል መንግሥታት ጋር ስምምነት አለማግኘቱ ተገልጿል። በቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ ክምችት ክፍል ደግሞ 4.6 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የተለያዩ መለዋወጫዎች ያለ ሥራ በመቀመጣቸው ለብክነት እየተዳረጉ መሆኑም ተጠቅሷል።

ሜቴክ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ በጥናት ላይ ተመሥርቶ እየሠራ አለመሆኑን የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ በግምገማው ላይ አውስተዋል። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ገብረ እግዚአብሔር አርዓያ ኮርፖሬሽኑ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በውሉ መሠረት ማጠናቀቅ አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ በውል ከተፈቀደው የጊዜ ገደብ በእጅጉ ርቆ በረዥም ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ አለመቻሉን ተናግረዋል። ተቋሙ በየጊዜው ለምክር ቤቱ የሚያቀርባቸው ሪፖርቶች ወጥነት የጎደላቸውና የሚዋዥቁ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ገብረ እግዚአብሔር፣ ለአብነትም የያዩ ማዳበሪያ ፕሮጀክት አፈጻጸም ሪፖርት ተዓማኒነቱን ጥያቄ ውስጥ የከተተው ነው ብለዋል። ያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካ 11 ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም፣ በሁለት ዓመት እንደሚጠናቀቅ የታቀደው ይህ ፋብሪካ ከስምንት ዓመት በኋላም አፈጻጸሙ 50 በመቶ በታች ነው፡፡ ለማጠናቀቅ የሚያስፈልገው ወጪም 22 ቢሊዮን ብር መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

በተጨማሪም የኦሞ ኩራዝ ቁጥር አንድ የበለስ ቁጥር አንድ ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታቸው 90 በመቶ በላይ እንደተጠናቀቁ ከአንድ ዓመት በፊት የተገለጸ ቢሆንም፣ አዲሱ ዋና ዳይሬክተር በቀለ ቡላዶ (ዶ/ር) ያቀረቡት ሪፖርት ግን ከአምናው ያነሰ መሆኑን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ጠቁመዋል። በዚህም ምክንያት ለስኳር ፕሮጀክቶቹ ተብለው የተተከሉ የሸንኮራ አገዳ ምርቶች በመድረሳቸው ከፍተኛ ብክነት መድረሱን አስረድተዋል። ኮርፖሬሽኑ ባሉበት የመልካም አስተዳደር ችግሮችና አነስተኛ ክፍያ ምክንያት ከፍተኛ የሠራተኛ ፍልሰት እየገጠመው መሆኑ ታውቋል። አዲሱ የተቋሙ አመራር ኮርፖሬሽኑ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመደገፍ እንዲችል በጥናት ላይ ተመሥርቶ እንዲሠራ የማስተካከያ ዕርምጃ እንዲወስድ ቋሚ ኮሚቴው ጠይቋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...