Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትእስኪ እንነጋገር ስለለውጡና ስለዓብይ አስተዳደር

እስኪ እንነጋገር ስለለውጡና ስለዓብይ አስተዳደር

ቀን:

በታደሰ ሻንቆ

ዶ/ር ዓብይ ላይ የተንፀባረቀው (ከቋንቋ ጀምሮ፣ ያታከቱ ጠምዛዛ አባባሎችን ጥሎ በሥዕላዊና አይረሴ አገላለጽ ከሕዝብ ጋር መነጋገርን ያወቀ) አመለካከት በዕርቅ ለመተቃቀፍ፣ ኢወገንተኛ ባልሆኑ አውታራት ላይ ዴሞክራሲን ለመገንባት፣ ብሔረሰባዊ ማንነትን ከኢትዮጵዊነት ጋር ለማግባባትና እንደ አገር ህልውናን በሚወስኑ የቀጣናችንና የአኅጉራችን አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ ለማተኮር የሚያስችል መልካም ዕድል የፈነጠቀ ነው፡፡ ይህ ዕድል ተጨባጭ እንዲሆን ገልጀጅ ሲል በብልኃት ነቅነቅ እያደረጉ ወደፊት ማስኬድ የዴሞክራቶች ኃላፊነት ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነት የመወጣትም ተግባር አርቆ አስተዋይነትን፣ ንቁነትንና ሕዝብ የማትመም ጥንካሬን መጠየቁ አይቀርም፡፡ ይህንን ጥንካሬ የማሟላት ነገርም ከቁጥር አስገቡኝ የሚሉ የሚከተሉት ጉዳዮች አሉት፡፡

ሁላችንም ባለገመና መሆናችን፣ በወገንተኛ አድልኦና ጥላቻ፣ በማላኮስና በማፈናቀል በመሳሰሉት ገመናዎቻችን ውስጥ ሁላችንም የጥፋት ድርሻ እንዳለን መገንዘባችን፣ ዕርቅና ተሃድሶ ውስጥ ለመግባት ወሳኝ ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ከዚህ ቀደም የተባበረ ውጤታማ ትግል ከማድረግ የገታን፣ የጥያቄና የዕይታ አለመገናኘት በጥርጣሬ ከመከፋፈል ጋር ተጋግዞ እንደነበረ፣ ያንን መከፋፈል ስናልፍ ደግሞ ምን ያህል አቅም እንዳገኘን አለመርሳትም አስፈላጊያችን ነው፡፡

በኢትዮጵያ የቅርብ ዘመን የዴሞክራሲ ትግል ታሪክ ውስጥ የኦሮሞ አታጋይነት መፈልቀቁም እሰየው የሚያሰኝና ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ኅብረተሰባዊ አቀነባበር ታሪክ የኦሮሞ ሥርጭትና አዛናቂነት ታሪክ ነውና፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የትግል መሪነት መንገድ እንዳይስት መሥራት ይጠይቃል፡፡ የኦሮሞ ዴሞክራቶች መሪነት የሴሞችን/የሰሜነኞችን ገዥነት ዘመን ዘግቶ የኦሮሞ ገዥነትን ዘመን ከመክፈት ፍላጎት ጋር እንዳይሳከር፣ የሚፈለገው ድል የትኛውንም ዓይነት የበላይ ገዥነት ዘመንን የሚዘጋ ሁሉን አቀፍ የዴሞክራሲ፣ የፍትሕና የልማት ዘመንን ማምጣት መሆኑን መጨበጥና ማስጨብጥ አስፈላጊ ነው፡፡ በዚህም አቅጣጫ ለውጡን አፍጥኖ ጥያቄዎች የአመፅ መንገድ ውስጥ ሳይገቡ የሚስተናገዱበትንና (ወንጀሎች የትግል ሽፋን የማያገኙበትን) የሕዝብ አስተዳደር ሥርዓት መገንባት የማናወላውልበት ተግባር ነው፡፡

ይህንን ተግባር መወጣት ቀላል ፈተና አይደለም፡፡ ምክንያቱም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ላይ የተሰባሰበው ድጋፍ ባለብዙ አቅጣጫ ስለሆነ፡፡ ያሁን ሕገ መንግሥትና የፌዴራል አከፋፈል እንዳለ ሆኖ ዴሞክራሲ ብቻ እንዲታከል የሚሻ አለ፡፡ ዴሞክራሲ ቢቋቋምም የብሔር ብሔረሰብነት መነጽር ያለው ሕገ መንግሥትና የፌዴራል አካላት አከፋፈል ካልተቀየረ፣ የማኅበረሰቦች መንገዋለልና መፈናቀል አይወገድም የሚል አለ፡፡ ያለው የፌዴራል አካላት አከፋፈል የአገረ ብሔር ድርሻ ሆኖ እንዲታወቅለትና የአገረ ብሔሩን ሀብትና ምድር የብሔሩ ልጆች መጠቀሚያ እንዲሆን የሚሻ አለ፡፡ ሁሉም ወገን ወደ የራሱ አቅጣጫ ጠቅላይ ሚኒስተሩን ለማስጠጋት የገመድ ጉተታ እያካሄደ ነው፡፡ ዓብይ በጠቅላይ ሚኒስትርነት መመረጣቸው የታወቀ ዕለት በደስታ ሲጨፍሩ ካደሩ መሀል ከእንግዲህ የኦሮሞ ዘመን መምጣቱ የታያቸው እንደነበሩ ሁሉ፣ ዓብይ ትግራይ ሄዶ ትግርኛ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ሰውዬው ኦሮሚኛ የሚናገር ሕወሓት ይሆን ብለው የደነገጡና የተነጫነጩም ነበሩ፡፡ በየጓዳችን ውስጥ ሆነን ሳሎንና ግቢ ውስጥ ያሉ ግንኙነቶችን ስለመዘንጋታችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመናገራቸው አንጀታቸው የራሰ እንደነበሩ ሁሉ፣ የአካባቢ ጉዳይ በጓዳ በመመሰሉ ቅር የተሰኙም ተከስተዋል፡፡

ያም ሆነ ይህ፣ አገሪቱ ውስጥ የሚታዩት ዝንባሌዎች ዞሮ ዞሮ ወደ ሁለት ጫፍ  ወደ ኢትዮጵያ አንድነትና ወደ ብሔርተኛ መስመሮች የሚሰባሰቡ እንደ መሆናቸው፣ ከዚህም በላይ ሁለቱም መስመሮች በግራና በቀኛቸው ያሉ የውድቅት አዘቅቶችን አምልጠው ሰላምና ግስጋሴን ከነፃነት ጋር መቀዳጀት የሚችሉት የጋራ መገናኛቸው ላይ ብቻ መሆኑ፣ ለለውጡ መሳካት ትልቅ የተስፋ ዕድል ይሰጠዋል፡፡ የዓለም፣ የአፍሪካና የምሥራቅ አፍሪካ አዝማሚያ በኢትዮጰያ ደረጃ መጥኖ አገርንነት ማሰብን እንኳ ጠባብ አድርጎታል፡፡ እንኳን በየብሔር ደረጃ አገር ሊሆን ይቅርና፡፡ እየመጣ ያለው የአፍሪካ አገሮች የነፃ ንግድ ትስስርና ያለ ይለፍ ካንዱ የአፍሪካ አገር ወደ ሌላው የመግባት ፍላጎት ሁሉ ይህንን አባባል የሚያጠናክር ነው፡፡ በየብሔር ወደ አገርነት ማደግ ቅዠት የሚሆነው ፈላጊ የለሽ  ስለሆነ ሳይሆን፣ ቅንጥብጣቢ አገርነት በቀላሉ ሊደፈር የሚችል አቅመ ቢሰነት ስለሆነና ተናቁሮ ለመፈጀት ስለሚያጋልጥ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ትንቢት ሳይሆን በዙሪያችን በተግባር እየሆነ ያለና እኛም እንዳንጠለፍ የምንሠጋበት አደጋ ነው፡፡

በሌላ ጎን ትልቅ አገርነት ጥንካሬ የሚሆነውም ሕዝብን በመብቶች፣ በግስጋሴና በሚሻሻል ሕይወት ውስጥ ማትመም እስከተቻለ ብቻ ነው፡፡ ይህ ራሱ ራስን ደሴት ለማድረግ ከተሞከረ ይጨነግፋል፡፡ በውጫዊ ትርምስ፣ በሽብርና በፍልሰት ላለመወረር ድህነትንና ቀውስን ከዙሪያ ክፍለ አኅጉር በማራገፍና ልማትን በማዛመት መስተጋብር ውስጥ መግባትን ይጠይቃል፡፡ የአውሮፓና የአሜሪካ ልምድ ሳይቀር የሚያስገነዝበው ይህኑን ኃላፊነት ነው፡፡ እናም ይህን መሳዩ ዓለማዊና ቀጣናዊ እውነታ የሚደግፈን እስከሆነና ይህንን በትክክል እስከተጠቀምንበት ድረስ ምን ሊያስፈራን? የመላው ሕዝብ ትኩረት በሌሎች የጎን ጉዳዮች ሳይበታተን፣ ጽንፈኛ ገደሎችን ከሁሉም አቅጣጫ ዓይቶ የማሳየትን ኃላፊነት የለውጥ ኃይሎች ተባብረው በብልኃት መወጣት ከቻሉ፣ አንድነትንም ብሔረሰባዊ መብቶችንም አንድ ላይ ማሳላት ከባድ አይደለም፡፡

የንግግር ነፃነት በተግባር ከተረጋገጠና ዕለታዊ የኑሮ ሁኔታ ከሆነ በየቀኑ ስለንግግር ነፃነት መስበክ፣ በየጊዜው የንግግር ነፃነት ደህና አድሮ ይሆን ወይ እያሉ መባነን ትረጉመ ቢስ ይሆናል፡፡ ትርጉም የሚኖረው ነፃነቱን ራሱን መኖር ነው፡፡ ነፃነቱን ከኖሩት ደግሞ ነፃነቱ ከሌባ እየተጠበቀ ነው ማለት ነው፡፡ እስካሁን ባሳለፍነው የ27 ዓመታት ልምድ ውስጥ የብሔር ብሔረሰብ መብት 27 ዓመታት ሙሉ የተለፈለፈለት በአምባገነንነት መዳፍ ውስጥ ሽንክፍክፉ የወጣ ስለነበርና ከብሔር የበላይነት በደል ገና አልወጣሁም ባይ ብሶት ይፈልቅ ስለነበር ነው፡፡ የአገሪቱም አንድነትና ኢትዮጵያዊነት በሥጋት ሲጎሳቆል የቆየው ‹‹ብሔሬ ለብሔሬ›› ባይነት ጭቆናን ለመገላገል አንዱ መወራጫ መንገድ ተደርጎ ተወስዶ ስለነበረ ነው፡፡ ዴሞክራሲን የሚተነፍስ ፌዴራላዊ አስተዳደር ኖሮ ሕዝቦች ከበላዬ አፋኝና ቦጥቧጭ ጌታ አለብኝ የማይሉበት እውነታ ውስጥ ከገቡ አንድነትና የብሔረሰብ መብት ይተጋገዛሉ እንጂ፣ አንዱ በሌላው ላይ አይጮህም አንዱ ሌላውን አያስፈራራም፡፡ እዚህ ውጤት ላይ ለመድረስ የዛሬ እውነታችን የሚጠይቀን ጠንቃቃና ብልህ ጉዞ ምንድነው ታዲያ?

አንደኛ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳቱን እሰየው እንደምንል ሁሉ፣ በአዋጁ ጊዜ ጭምር ሄድ መለስ እያለ ያስቸገረን የታጠቀ ጥቃት፣ ግጭትና የማፈናቀል ተግባር ወደ ግርሻ ሳይቀየር እንዲያቆም የሚከተሉትን ተያያዥ ተግባራት ማካሄድ የሚበጅ ይመስለኛል፡፡ ርቅና ይቅርታ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ የበጎ ሥራ ጉዳይ ሳይሆን በመዋቅር አንካሳ የሆነው  የዴሞክራሲ ለውጣችን ወደ ስኬት ለመድረስ ግድ የሚለው ተግባር መሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜ የትኛውም ዓይነት ግርግር ለቅልባሰ ቀዳዳ የሚከፍትና የለውጥ ዕድልን የሚያስቀጭ መሆኑ፣ ለኢትዮጵያ አንድነትም ሆነ ለአካባቢያ (ብሔረሰባዊ) መብቶች መጨነቅ ፍሬያማ የሚሆኑት በተቃረነ ጉዞ ሳይሆን በተያያዘ ጉዞ መሆኑ ነው፡፡

ማፈናቀል ባንድ ጊዜ ሁለት ጥፋት የሚሠራ (በዘመናት ውስጥ  የተገነባ ማኅበራዊ መስተጋብርን የሚበጣጥስ፣ የማኅበረሰቦችንና የሰውነት መብቶችን የሚዳምጥ፣ በዚህም ወደ መፋጀት የሚወስድ) መሆኑ በመንግሥትም ሆነ በፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ፣ በሕዝብም ዘንድ በአግባቡ መጤኑ ለለውጡ ወሳኝ ጉልበት ነው፡፡ በጋራ መድረክ ተሰባሰቦም ሆነ በየተናጠል ሁሉም ለውጥ ፈላጊ የተጠቃቀሱትን ፍሬ ነጥቦች ይፋ አቋም ሊያደርጋቸው ይገባል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ‹‹ጅምሩ ጥሩ ነው. . . ገና ይቀራል. . . ይህ ይሟላ. . .›› ከማለት ባሻገር ለውጡን ለማሳካት ንቁ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባት የዘገዩበት ተግባር ነው፡፡ ተሰባሰቦ መምከር፣ ለውጡ እንዳይቀለበስና እንዲቀጥል የሚያስችል ሚና ለአባሎቻቸውና ለብዙኃን ደጋፊዎቻቸው ማሸጋገር፣ አለመረጋጋትና መፈናቀል በሚደጋገምባቸው አካባቢዎች የፓርቲ መዋቅራቸውን መዘርጋትና ከሌሎች የዴሞክራሲ ወገኖች ጋር የተጋገዘ አዎንታዊ እንቅስቃሴ ማካሄድ ፍጥነት የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ በየአካባቢው ሕዝብ የቅልበሳ ልዩ ልዩ ቀዳዳዎችን መድፈንና ለፀጥታው ዘብ የመቆም ንቁ ተሳትፎ የሚያደርገው፣ ሁሉም የለውጥ ኃይሎች ሕዝብ ገብ የጋራ ኃላፊነታቸው ላይ መደጋገፍ ሲያውቁበት ነው፡፡ ተመልካች ሆኖ ኢሕኢዴግ ድጋፍ በዘዴ እያሰባሰበ ነው እያሉ ከመቅናት ፋንታ ድጋፍን ማበራከት ውስጥ የሚገባውም በዚህ መንገድ ነው፡፡

በአንዳንድ አካባቢ የሚታየው ከልካይና ወደ ነበረበት መላሽ ያጣው ግጭት አነሳሽነትና አፈናቃይነትም፣ አካባቢያዊ የአስተዳደር ነፃነትን የጥቂቶች የአድራጊ ፈጣሪነት ነፃነት አድርጎ ከማጉደፍ ጋር የተገናኘ ነውና በዴሞክራሲ ለውጥ ውይይቶች ውስጥ ከብዙ አካባቢ የተውጣጡ ተሰሚነት ያላቸው ሰዎችን ማሳተፍና ክንዋኔው የመገናኛ ብዙኃን ሥርጭት እንዲያገኝ ማድረግ፣ ለውጡን የማስፋፋትና ችግሮችን የማቅለል ሒደትም መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

ነፃ የመብት ተከራካሪ ነን ባዮችም ሆኑ የሰብዓዊ መብት ጉባዔ፣ ችግር ተከሰተ ሲባል ከአዲስ አበባ ሰው ከመላክ ባለፈ በየአካባባቢው መዋቅር ዘርግተው የመብት ጥሰትን የመከላከልና ሲከሰትም የቅርብ ምስክርነትን የመስጠትና እንዲበርድ የማገዝ ሚና ለመጀመር መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል፡፡

እስረኛ አፈታት ረገድ በደረቅ ወንጀል የታሰረ ሁሉ እየተፈታ ነው ወይ የሚል ውዥንብር መጥራቱና የሚፈቱት ምን ዓይነት ተከሳሾችና ፍርደኞች እንደሆኑ፣ በፊቺው ውስጥ የተጓደለ የዋስ መብትን የማሟላት ዕርማት ስለመቀላቀል አለመቀላቀሉ፣ እንዲሁም ይቅርታም ሆነ ምሕረቱ እስከምን ጉዳይና ጊዜ ድረስ መሆኑ ለሁሉም ወገን ግልጽ መደረጉ ሰላምና ሕግን በማስከበር ረገድ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡

እስካሁን የተጠቃቀሱት ተደጋጋፊ ሥራዎች ከተሟሉና ፖለቲከኛና ሕዝብ አቀፍ መግባባት ከተፈጠረ፣ በወሰንም ሆነ በብሔር መብት ስም ግርግርና ግጭት ማነሳሳትንም ሆነ የማፈናቀልና ንብረት የማውደም ተግባራትን መከላከል፣ ሲያፈተልኩም በቶሎ ማስቆምና ጥፋተኞችን ያለማወላወል በሕግ መጠየቅ ሁሉም የተቀበለው (አፃፋ ፕሮፓንዳ የማይሠራበት) ጉዳይ ይሆናል፡፡ ይህን መሳይ መግባባት ከተገኘ፣ ቀሪው የፌዴራልና የአካባቢ አስተዳደሮች መደበኛ ሥራ ነው፡፡

በዚህ ረገድም በተለይ የአለመረጋጋት ችግሮች በተደጋገሙባቸው አካባቢዎች የፌዴራል የፀጥታ፣ የምርመራና የፍርድ አካላት በቅርብ የመገኘታቸው ነገር፤ ከዚያም አልፎ፣ በሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ወሰን ውስጥ ሥራን ለማከናውን የሚያስችሉ ውላጅ ሕጎችን ለማጠናከርም ሆነ የሕግ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚስፈልጉ አዋጆችን አሰናድቶና አፀድቆ ወደ ሥራ የማስገባቱ ነገር የሚያሳስብ ነው፡፡

ጋዊና መዋቅራዊ አቅምን የማጠናከሩ ጉዳይ የራሱን ጊዜ ይፈልጋልና ለውጡ የሚሻውን ሰላም የማሟላቱ ዋና ሸክም በመላው ሕዝብ፣ ወጣትና በለውጥ ፈላጊ ኃይሎች ላይ ማረፉ አይቀርም፡፡ እውነቱን እንናገር ካልንም፣ የዓብይ አህመድ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ወደ ማስነሳት የሄደው አስቸኳይ አዋጁ በታወጀበት ጊዜ ከነበረው ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር የተዋጣ ሰላም ተገኝቶ ሳይሆን፣ እያደገ የመጣውን የሕዝብ ድጋፍና ለውጥ ፈላጊዎችን አለኝታ በማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም መላ የለውጡ ወገኖች ላይ ያለው ኃላፊነት ድርብ እንደሆነ ልብ ይሏል፡፡ አሁንም በሌላ መንገድ ደግሜ ልግለጸው፡፡ ግጭት አመጣሽ ትርምስንና መፈናቀልን መግታት የለውጡን መክሸፍና መሳካት የሚወስን ተግባር ነው፡፡

ሁለተኛና እጅግ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ መንግሥት ሕዝብ እንዲታመነው እንደፈለገ ሁሉ፣ መንግሥትም ለሕዝብ መታመን ይጠበቅበታል፡፡ ዓብይ የተቀመጡበት መንበር የሕዝብ ልዕልና ጉድለት ያለበት እንደመሆኑ (ለዴሞክራሲ ግንባታ ደፋ ቀና የሚባለውም ያንን የሕዝብ ልዕልና ጉድለት ለመሙላት ነውና)፣ ያለው መንግሥት ያለበትን የሥልጣን አንካሳነት አውቆ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝቦች ጥቅም ላይ የተፈጸመው ዓይነት ጥፋት ውስጥ እንዳይገባ፣ ከፖለቲካ ቡድኖች ጋር የሚያደርገው ድርድር በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ድንበር ውስጥ የተመጠነ እንዲሆን፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ሉዓላዊ ይሁንታ የሚሹ ጉዳዮችንና ጥያቄዎችን ለበኋላ እያቆየ የተጀመረውን ልማት በጥራት ከማራመድ ጋር በዋናነት ከዴሞክራሲ ኃይሎች ጋር ተጋግዞ በኢትዮጵያ ምድር የማይቀለበስ (የሕዝብ ልዕልና የተፈለቀቀበት) ዴሞክራሲ በመገንባት ላይ እንዲያተኩር ይመከራል፡፡

የሕዝብ ልዕልናን የመፈልቀቅ ተግባር ደግሞ የመንግሥት የፀጥታ አውታራትን ከፓርቲ ወገናዊነት ነፃ ከማውጣት፣ የብዙ ፓርቲ ውድድርን ከማንተርከክና ባልተጭበረበረ ምርጫ የሕዝብ ምክር ቤቶችን ከማደራጀት ያልፋል፡፡ ሕዝቦች በአካባቢዎች ደረጃም ሆነ በፌዴራል ደረጃ በሾሟቸው አካላት የመረገጥ ፍዳ ውስጥ ሳያውቁት ከመግባት ሊያመልጡ የሚችሉት (ከሚዲያዎች አጋላጭነት ባለፈ)፣ የምክር ቤቶች እንደራሴያዊነት መላሸቅ አለመላሸቁን ራሳቸው በራሳቸው መከታተልና የላሸቁ እንደራሴዎችን ብዙ ብልሽት ሳያደርሱ ለመቀየር ንቁነቱን የሚያገኙት እንደ ዕድር በየቀዬና በቀዬዎች አቀፍ ቀበሌያት ደረጃ  ለማንም ተቀጥላ ያልሆኑ መደበኛ ሸንጎዎች ሲኖራቸው ነው፡፡ ማለትም ዴሞክራሲ የሠፈር ኑሯቸው እስከመሆን ድረስ ሲዋሀዳቸው ነው፡፡

ሦስተኛ የብዙ ችግሮች መቃለያ የሆነው ይህ የዴሞክራሲ ግንባታ ብዙ ሥራ ያለበት እንደመሆኑ፣ የዴሞክራሲን ያህል አጣዳፊ ያልሆኑ ጉዳዮችን ማዘግየት ዴሞክራሲን ማገዝ ነው፡፡ ያለ ፍርኃት ነገሮችን አብላልቶ የተማመነ ስምምነት ላይ ለመድረስ ራሱን ዴሞክራሲን የሚሹ ጉዳዮችን (ለምሳሌ የወልቃይትንንና ወሰን ነክ ጉዳዮችን) አሁን አለመወትወት ተመልሶ ጥሬ የማይሆን ውጤት ወደ ማግኘት ያደርሳል፡፡ የዴሞክራሲ ግንባታ ጉዟችንን ሊያዘገዩም ሆነ ሊያስቱ የሚችሉ ችግሮች፣ ጊዜያቸውን ባልጠበቁ ጥያቄዎች ከመዋከብ የሚመጡ ብቻ ግን አይደሉም፡፡

በሶማሌ ክልል በኩል በተደጋጋሚ በልዩ ኃይል አማካይነት የሚደረግ ሰላም አደፍራሽነት፣ በሌላ አካካቢ ባለ የወሰን ችግር ዓይን ከመታየትም የሚያልፍ ነው፡፡ በግዙፍ ውስጣዊ ቀውስ መነሻነት የዴሞክራሲ ጉዞን ከማወላከፍም ባሻገር ከሶማሊያና ከሰሜን ሶማሌላንድ ጋር ያለንን ግንኙነት ለሚያደፈርስ መዘዝ እንዳይሆን ያስፈራልና የፖለቲካ ጥበብ ያልተለየው ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡

ከጋዜጠኝነት የሙያ ሥነ ምግባርም ከአስተዋይ ፖለቲከኝነትም አንዳቸውንም ያልጨበጠ እንቅስቃሴ፣ ለሕዝብ ሰላምና በአገር ደኅንነት ሳያውቀው ጠንቅ መሆን ይችላል፡፡ በኢሳት ጋዜጠኞች ላይ አንዱ የሚታየው ችግር ይህ ለወቀሳም ያልተበገረ ዝንባሌ ነው፡፡ አሁን የተገኘውን ደግ ውጤት ሁሉ የሕዝብና የወጣቱ የትግል ውጤት አድርገው ሲያቀርቡ፣ አገዛዙ በትግሉ ግፊት ምክንያት ከሄደበት መልካም መንገድ ውጪ ሊሄድባቸው ይችል የነበሩ ክፉ መንገዶችም እንደነበሩ ለማየት አይሹም፡፡ ከዚህ የሚብሰው ደግሞ የሕወሓቶች ስህተቶችና ጥፋቶች ለትግራይ ሕዝብ ለተረፈ አሉታዊ ስሜት መነሻ እንደሆኑ ሁሉ፣ ስህተቶችና ጥፋቶች ላይ ሲካሄድ የቆየ ትክተካም አሉታዊ ስሜትን ወደ ሕዝብ ሲያጋባ እንደኖረ፣ ዛሬም እነሱ ሙጭጭ ያሉበት ትክተካ ይህንኑ እያመረተ ስለመሆኑ መረዳት ተስኗቸዋል፡፡ ኢሳቶችም ሆኑ ሌሎች ትክተካቸውን በመቀጠላቸው እየሰሩ ያሉት፣ በሕወሓትና በትግራይ ሕዝብ ዓውድ ውስጥ ለውጠኞችና የለውጥ ተቀናቃኞች አንድ ላይ የተድበሰበሱበትና የተከላካይነት ውድማ ላይ የተፋፈጉበት ሁኔታ እንዲፈጠር የሚጫን፣ ሌላውም ኢትዮጵያዊ ከጥፋት የላቀ መልካም ሥራቸውን እንዳያመሠግን ጭጋግ የመሆን ሥራ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ፣ ዴሞክራሲን የሚጎዳ አወቅሁ ባይ ድንቁርና ከዚህ የበለጠ ያለ አይመስለኝም፡፡

ሕወሓትም በኩል የግንቦት 20ን ፍሬ በማሰብ አጋጣሚ ከአንዳንድ ትልልቅ ነባር አመራሮች የሰማነው፣ የጥፋት ባለድርሻነት ኃፍረት ባልዘለቀው ስሜት ‹‹የሥነ ልቦና ጦርነት እየተካሄደብን ነው›› በማለት መልክ የችግሩን መሠረት ውጪያዊ የማድረግ ዝንባሌም ለተግባባ ለውጥ የሚበጅ አይመስለኝም፡፡ በትግል ጊዜም ሆነ ወደ ሥልጣን የተወጣበት ምዕራፍ ከተከፈተ ወዲህ ሊካዱና ሊደበቁ የማይችሉ ስህተቶችና ጥፋቶች ተፈጽመዋል፡፡ ለዘመናት ተላልሶ በኖረው በትግራይ ሕዝብና በአማራ ሕዝብ መሀል የተሰነቀረው የወልቃይት ጉዳይ ሳይቀር የሁለት ወገን ሕዝብ የጋራ መግባባትን ካልተቆናጠጠ አካሄድ የመጣ ችግር ነበር፡፡ ሕወሓት ኢሕአዴግ ‹‹ፀረ ሕዝቦች››ን በመታገል ስም ለዓመታት የሠለጠነበትን ውስጠ ወይራ የአገዛዝ ዘይቤ መላው የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ እስከ ትግራይ ድረስ ለሁላችንም ቅርብ የሆነና ሁላችንንም ሲደባብሰንና ሲያመናትለን የቆየ መሆኑን ማስታወስ ይገባል፡፡ እናም ገመናን ተቀብሎ ለማራገፍ ዝግጁ መሆንን ሳያረጋግጡ፣ ‹‹ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከኢሕአዴግ የተሻለ አማራጭ የለም›› ብሎ በኩራት መናገር ጥቅም የለውም፡፡  በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ የትግራዊ ቁጥር 14 በመቶ ስለመሆኑ መወራቱስ ምን ይጠቅመኝ ተብሎ? ሠራዊቱ በትግራዊ የተጥለቀለቀ ነው ብሎ የሚያምን ዛሬ አለ ተብሎ ይሆን? ወይስ እንዲያ የተባለ ለማስመሰል? ጥላቻ ካጨራመታቸው ጋር ስንደዶ እየተማዘዙ ከመተካተክ ይልቅ፣ የሚያዋጣው ዴሞክራሲን በኢወገንተኛ አውታራት ላይ የመገንባት ይፋ የለውጥ ተዋናይ ሆኖ ጥላቻን አፍ ማሳጣትና መሞለጭ ነው፡፡ ከዚህ ዝቅ ቢባል፣ ለኢትዮጵያና ለትግራይ ሕዝቦች እስከታሰበ ድረስ ከውስጣዊ ልዩነቶች ጋር በኢሕአዴግ ግንባር ውስጥ መቆየት ኃላፊነት የሚሰማው ድርጅት ተግባር ነው፡፡ የስብስብ ሽግሽግ አድርጎ ግንባር ወደ ማፍረስ ቢሄድ እንኳ፣ በዴሞክራሲ ሜዳ ውስጥ ከተቀናቃኞች ጋር ተወዳድሮና በፕሮግራም የኢትዮጵያንም ሆነ የትግራይን ሕዝብ ረትቶ ወደ ሥልጣን ከመውጣት ውጪ ሌላ አማራጭ እንደማይኖር መታወቅ አለበት፡፡ ከዴሞክራሲ ውጪ ያለው ሁላችንንም ወደ ሲኦል የሚወስድ የሴራ መንገድ አማራጭ አይደለምና እዚያ ዘግናኝ ምናልባት ውስጥ ገብቼ ወሬ አላደራም፡፡

አራተኛ ‹‹የብሔሬ ምድር ለብሔሬ›› ባይነት አለመረጋጋት እየፈጠረ የዴሞክራሲ ግንባታን ከማደናቀፍም በላይ፣ በእኩልነትና በአገር ልጅነት ተሳስቦ መኖርን ይቀናቀናል፡፡ በቅርብ ጊዜ ልምዳችን ውስጥ እንደታየው በመዝባሪነት የታዩ ኩባንያዎች ላይ ጥቃት ማድረስ መደጋገሙ ከቀጠለም፣ በመዋዕለ ንዋይ ፍሰትና በሥራ ፈጠራ ላይ የሚደርሰው ጉዳት ዕድገትን አሰናክሎ ለፖለቲካ ቀውስ ማጋለጡ አይቀሬ ነው፡፡

የውጭ መንግሥትና የውጭ መዋዕለ ንዋይ ጥገኝነት ውስጥ ሳይወድቁ በልማት መገስገስ፣ የውጭ ቀጥተኛ መዋዕለ ንዋይን ከማስገባት ጋር አይጣላም፡፡ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት የገንዘብ፣ የሥራና የቴክኖሎጂ ችግርን የማቃለያ አንድ ሁነኛ ምንጭ እንደመሆኑ፣ መተናኮልና በተለያየ ሥልት ማንገላታት በገዛ ጥቅም ላይ ጥፋት መሥራት ይሆናል፡፡ አፈሳ እያተረፉ ትርፍን ወደ ውጭ የማሽለክ ጉዳትን ለመከላከል መደረግ ያለበት፣ እጅግ ብልህ መሆንና በመጀመርያም ሆነ በስተኋላ የውጭ ሥራ ከፋቹን በልዩ ልዩ መንገድ ማርኮ በሽርክና መጎዳኘት፣ ወይም በሥራው ውስጥ ኖሮ ቴክኖሎጂን በመቅሰም የገዛ ራስን ሥራ መክፈት፣ ወይም ሥራ ፈጣሪውን የአገር ልጅነት በሚሰማው ደረጃ ከባይተዋርነት አውጥቶ/ተዛምዶ ትርፉን እዚያው የሥራ ማስፋፊያ እንዲያደርገው መጠበብ ነው፡፡ በኦሮሚያ ክልል የዳንጎቴ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ የነበረውና ዛሬ በሕይወት የሌለው ህንዳዊ፣ ኦሮሞዎች በማደጎ ልጅነት ተቀብለው የኦሮምኛ ስም እንዲያወጡለት ማድረጉ፣ ብልህነት ምን እንደሆነ ላልገባው ትምህርት ይሰጣል፡፡

በመጨረሻ ማርክሲዝምን አሽትተን መሳፍንትንና ከበርቴን በፀረ ዕድገትነት እንዳልተፀየፍን፣ በሥራ ልክ ተከፋይ ስለመሆን ሰባኪ እንዳልነበርንና ዓለም አቀፋዊ አመለካከት አለን እንዳላልን፣ ዛሬ በየብሔረሰብ ጎጆ ውስጥ መወሻሸቅና ጥላቻ ላነካከተን፣ እንዲሁም እንብርታችን እስኪገለበጥና ትንፋሽ እስኪያጥረን የቢሮ መሳፍንት ለሆንን፣ ምንተፍረት ቢዘልቀን በማለት የልዑል ራስ መንገሻ ሥዩምን የትውልድ አደራ እንድታነቡ እጋብዛለሁ፡፡

እኝህ ሰው በአባታቸው ላይ በደል በፈጸመ ንጉሥ ላይ ቂምና ጥላቻን ሳይቋጥሩና በዚህ ዓይነት ደካማነት በራሳቸውና በዓላማቸው ላይ መሰናክል ያልሆኑ፣ በብልኃት ንጉሡን እየቀረቡ ከመቃብር በላይ የሚውል ሥራ የሠሩ፣ በመስፍንነት ሳይኮፈሱና ‹‹ክብር አዋራጅ›› ለሚል ትችት ሳይበገሩ መስፍንነትን ከዶማ ጋርና ከቡልዶዘር ማገላበጥ ጋር ያገናኙ፣ በጎጥ ሳይሸበቡ በየተመደቡበት ‹‹ጠቅላይ ግዛት›› ውስጥ ሁሉ አገሬን ብለው ለልማት የተጉ፣ ለትግራይ ልማት ከሐረማያ ኮሌጅ የሙያ ዕውቀት ለማምጣት የአመለካከት ጥበት ያላሳቀቃቸው፣ ከሕዝብ ተማክሮና በሕዝብ ፍቅር ተከቦ እየሠሩ የማሠራት ምሳሌነትን ለዛሬ ዘመንም ያትረፈረፉ የስኬት ልዑል ናቸው፡፡ ከ1966 ዓ.ም. የለውጥ ፍንዳታ በፊት የአጠጋገብ ለከት ኖሯቸው፣ የገጠርም የከተማም ሰፊ ርስት ለጭሰኛና ለአገልጋዮች ያከፋፈሉ ተራማጅም ናቸው፡፡ ዕድሜ ይጨምራላቸው፡፡ ለአገሬ ሠራሁ እንጂ አልዘረፍኳትም የሚል ኩራቴን አራግፈው የላባ ያህል ስላቀለሉልኝ በልቤ ውስጥ ሐውልት ተክዬላቸዋለሁ፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በፍቅር አስተቃቅፎ ወደፊት ማራመድ ተራራ የሆነባችሁ መንግሥታዊ ሹሞቻችንም ሆናችሁ ወንጋራ ፖለቲካኞቻችን፣ ከእሳቸው ጋር ራሳችሁን ስታመዛዝኑ የክብደታችሁን ልክ እንደምታገኙት አልጠራጠርም፡፡ 

ከአዘጋጁ፡– ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...