Sunday, March 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የነጋዴውና የግብር ሰብሳቢው ውሎ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሚያዝያ 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ፣ በርካታ ጥያቄዎች እንደቀረቡ ይታወሳል፡፡ ከቀረቡት ጥያቄዎችም በርካቶቹ የመሬትና የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮችን የተመለከቱ ነበሩ፡፡ የጉምሩክ አሠራርን በተመለከተም በርካታ ችግሮች ተነስተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተነሱት ችግሮች በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በኩል ቀርበው ጉዳዩ ከሚመለከታቸው መሥርያ ቤቶች ጋር ውይይት እንዲደረግና እያንዳንዱ ጉዳይ ላይ የሚደረገው ውይይትም በሚዲያ ይፋ እንዲደረግ አሳስበው ነበር፡፡

ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር ውይይት እንዲያደርጉ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማሳሰቢያ ከተሰጣቸው መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይኙበታል፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ውይይት በማዘጋጀቱና በማካሄዱ በኩል ቀዳሚ ሆኗል፡፡ ሐሙስ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑመር ሁሴን በተገኙበት ውይይት ተደርጓል፡፡

በመድረኩም የታክስና ጉምሩክ ጉዳዮች ላይ ቅሬታ ያላቸው ባለሀብቶች አቤቱታቸው በኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት በኩል ቀርቧል፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ ከቀረበው አቤቱታና በውይይት መድረኩ ወቅት የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት ያነሷቸው ሌሎችም ችግሮች ለባለሥልጣኑ ኃላፊዎች ቀርበዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) እንዳመለከቱት፣ ከግብር ነፃ አጠቃቀም ጋር በተለይም ኤክሳይዝ ታክስ፣ ተጨማሪ እሴት ታክስና ሱር ጋር በተያያዘ በሕግ የተሰጡንን መብቶች ተነፍገናል በማለት አምስት ኩባንያዎች አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ በሕግ የተፈቀደላቸውን የኤክዛይዝ ታክስ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስና፣ የሱር ታክስ ነፃ መብት በተለያዩ ምክንያቶች በባለሥልጣኑ ያለአግባብ መነፈጋቸውን የጠቅሱ አቤቱታዎች ተደምጠዋል፡፡ ይህንንም በመቃወም መፍትሔ ለማግኘት በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ የመንግሥት አካላት አቤቱታቸውን ቢያቀርቡም ጥያቄያቸው ውድቅ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በሽያጭ፣ በግብዓት፣ በተሽከርካሪዎችና ሌሎች መሣርያዎችን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ሒደት ከፍተኛና የተጋነነ ግብር እንዲከፍሉ መወሰኑም ለከፋ የፋይናንስ እጥረትና ለኪሳራ እንደዳረጋቸው የአቤቱታ አቅራቢዎቹን መረጃዎች በመንተራስ አቶ መላኩ ለባለሥልጣኑ ጥያቄዎቹን አቅርበዋል፡፡

በግንባር ቀርበው ለባለሥልጣኑ አቤቱታውን ለማሰማት ዕድሉን ካገኙ ባለሀብቶች መካከል አንዱ ንግግራቸውን ‹‹የታክስ ሥርዓቱ ታሟል›› በማለት ነበር የጀመሩት፡፡ ያለው ‹‹በትክክል ሕግና ሥርዓት ጠብቆ የሚሠራው አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገባ ሲደረግ፣ ከሕግ ውጭ የሚሠራው ግን እንደ ልቡ እየፈነጨ ነው፤›› በማለት የታክስ ሥርዓቱን አተገባበር ይኮንናሉ፡፡

በአንድ ዓይነት የሥራ ዘርፍ ውስጥ የሚሠሩ ነጋዴዎች ሆነው ሳለ፣ አንደኛው ቫት ከፋይ ሌላኛ ከቫት ነፃ ሆኖ መገኘቱ ፍትሕ መጓደል ምሳሌ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይጠየቅ የሚሠራው ተዘናንቶ ሠርቶ ፎቅ ሲገነባ እናያለን፤›› ያሉት ባለሀብቱ፣ የታክስ ሥርዓቱ በሚገባ እንዲፈተሽና እንዲስተካከል ጠይቀዋል፡፡  የውድድር ሜዳው እኩል ባለመሆኑ ሳቢያ ገጠመኝ ያሉትን ለማስረዳት ያቀረቡት 700 ሰዎችን የሚያስተዳድሩ ፋብሪካዎች እንዳላቸው በመግለጽ ነበር፡፡ አሁን ግን አጣብቂኝ ውስጥ መግባታቸውንም ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በውጭ ምንዛሪ ዕጦት ምክንያት ፋብሪካዎቹ ሦስት ወር እየሠሩ ሦስት ወር እንደሚያርፉም ተናግረዋል፡፡ ሠራተኛን መበተኑ የሞራል ጥያቄ ስለሆነባቸው እንጂ ሠራተኞቻቸውን ይዘው ለመቆየት የሚያስችል አቅም እንደሌላቸውም አክለዋል፡፡

እንዲህ ባለው አጣብቂኝ ውስጥ እየሠሩም በባለሥልጣን ተፈጸመብኝ ያሉት ተግባር  ምሬት ውስጥ ከቷቸዋል፡፡ እንደ ባለሀብቱ ገለጻ፣ ለፋብሪካዎቻቸው የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን በዓለም ከሚታወቁ አቅራቢዎች ጋር በመደራደር ሌሎች ከሚያመጡበት ዋጋ ባነሰ ማስገባት ቢችሉም ይህ ተግባራቸው ግን ዋጋ አስከፍሏቸዋል፡፡ ኩባንያቸው የሚፈልገውን ጥሬ በአሥር ብር ሳያስመጣ ሌላው ተመሳሳዩን ጥሬ ዕቃ በልዩ ልዩ ምክንያት በ15 ብር ገዝቶ ሊስያመጣ እንደሚችል አስረድተው፣ ከሌላው ባነሰ ዋጋ ባስገቡት ጥሬ ዕቃ የተመረተው ምርት ለደንበኞች ቀርቦና ተሸጦ ካበቃ ከዓመት በኋላ ጥሬ ዕቃው የመጣበት ዋጋ ሌላው ካስመጣበት የ15 ወይም የ20 ብር አኳያ ያነሰው ነው ተብለው የልዩነቱን ቀረጥ እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡ ቀረጡ ብቻ ሳይበቃም፣ መቀጫ ታክሎበትና ወለድ ተጨምሮበት መጠየቃቸውን አስታውቀው፣ እንዲህ ባለው አሠራር ግን አንደኛው ፋብሪካቸው ሦስት ሚሊዮን ብር ሌላኛው ደግሞ አንድ ሚሊዮን ብር እንዲክፍሉ መጠየቃቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ከስህተት ወይም ከአሠራር ግድፈት የተነሳ ተፈጽሞ ሊሆን ይችላል ያሉት ባለሀብቱ፣ ዱብ ዕዳ የሆነባቸውን ውዝፍ ክፍያ ባለሥልጣኑ በ15 ቀን እንዲከፍሉ ደብዳቤ እንደጻፈላቸው በመግለጽ የደረሰባቸውን በደል አመልክተዋል፡፡ በዚህ አላበቁም፡፡ በተሰጣቸው 15 ቀናት ውስጥ መልስ ለመስጠት እየተዘጋጁ ባሉበትና ደብዳቤው በደረሳቸው በሦስተኛው ቀን ለሁሉም ባንኮች ያልከፈሉት ግብር ስላለ የባንክ ሒሳባቸው እንዲዘጋ መባላቸውን በምሬት ተናግረዋል፡፡ ‹‹ስድስት ወር ሙሉ ደጅ ጠንቼ የተፈቀደልኝን ብድር ከጉምሩክ ደብዳቤ ስለተጻፈብህ ብድሩን ማግኘት አትችልም ተባልኩ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ለዓመታት ታክስ ስንከፍል የቆየን ሰዎች ባልተገባ ሁኔታ ስማችን እየጠፋ፣ በመከራ ያገኘነውን ብድር እንዳናገኝ እየተደረግን ነው፤›› በማለት ባለሥልጣኑ የፈጠረባቸውን ችግር አስረድተዋል፡፡ የባለሥልጣኑ አሠራር ታሟል ለማለት ያስደፈራቸውም፣ የሆነ ሰው ያመጣሁት ዕቃ በዚህ ዋጋ ነው በማለቱና ያም ዋጋ እንደ ማመሳከሪያ ተይዞ ያልተገባ ክፍያ እንድንከፍል መደረጉ ትክልል አይደለም ብለዋል፡፡ በ15 ቀን ውስጥ ቅሬታ ማቅረብ ስንችል ቀኑ ሳይደርስ የባንክ ሒሳብ መዝጋቱም ቢሆን አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

 ‹‹እኛ ጥሩ ተደራድረን ሌላው በ15 ብር ያመጣውን ዕቃ በአሥር ብር ማምጣታችን የውጭ ምንዛሪ ወጪ በመቀነሳችን በርቱ ልንባል ሲገባን፣ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ያስወጣውን ሰው ትክክለኛ ነህ ብሎ ተፅዕኖ ማድረስ ተገቢ አይደለም፤›› ያሉት ባለሀብቱ የተወሰነባቸው አግባብ ባለመሆኑ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል፡፡

የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት አሠራር የማይተነበይ፣ የማይታወቅ፣ የማይገመትና ለመጉላላት የሚዳርግ ስለመሆኑ የገለጹ ሌላ አስተያየት ሰጪም ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ የአስፈጻሚዎች ወይም የባለሙያዎች ውሳኔ የማይገመት ስለመሆኑ፣ ቅሬታ ሰሚ የሚባለው አካል የሚሰጣቸው ውሳኔዎች የማይጨበጡ በመሆናቸው ግብር ከፋዩን እንዳማረረው ተናግረዋል፡፡

ከተሳታፊዎችና ከንግድ ምክር ቤቱ በኦዲት አሠራር ላይ የተለያዩ ችግሮች መኖራቸውን የሚያመላክቱ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል፡፡ አንድ ባለሀብት በሰጡት አስተያየት፣ ኦዲት ለመደረግ የሚሰጧቸው መረጃዎች ጠፍተዋል በሚል ምክንያት ችግር ውስጥ መግባታቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ኦዲተሮች በየመሥሪያ ቤቱ በመሄድ ማየት ያለባቸውን ሰነድ አመሳክረው ኦዲት ቢያደርጉ እንደሚሻል ሐሳብ አቅርበው፣ 20 እና 30 ሚሊዮን ብር ታክስ ለሚከፍሉ ድርጅቶች አንድና ሁለት ኦዲተር በመመደብ ችግሩን መቀነስ ይቻል እንደነበርም አስረድተዋል፡፡ የኦዲተሮች የብቃትና የሥነ ምግባር ችግሮች እያገጠመን ነው ያሉ ባለሀብችም ስለደረሱባቸው ችግሮች አስረድተዋል፡፡ ችግር አድርሰዋል ባሏቸው ባለሙያዎች ላይ ይግባኝ ሲጠይቁም፣ ይግባኙን እነዚያው ኦዲተሮች እንዲያዩት መደረጉ ተገቢነት የጎደለው አሠራር ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡ ይግባኝ ማለት ዳኝነት መሆኑ እየታወቀ ይህንን የሚያከብር አሠራር አለመተገብሩን በመግለጽ፣ የሥነ ምግባር ችግር እንዳለባቸው የተጠቀሱ የባልሥጣኑ ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ ሳይወስድ መቆየቱን፣ ኋላ ላይ ግን በሥነ ምግባር ጉድለት እንዳባረራቸው ነጋዴው አስታውሰዋል፡፡ ኦዲተሮቹ የፈጠሩት ችግር ግን ይግባኝ ሰሚ ችሎት አስቀርቦ ሁለት ዓመት እንዳጉላላቸው ጠቅሰዋል፡፡

በጉምሩክ አሠራር ላይ የወረዱ ሮሮዎች

ከጉምሩክ አሠራር ጋር በተያዘዘ ችግር እንደገጠማቸው አቤት ያሉ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት ነበሩ፡፡ አቤቱታቸውን ያሰሙ አስመጪዎች የቀረጥ ነፃ መብት አጠቃቀምና የአስመጪዎች የታሪፍ መብት አመዳደብን በተመለከተ የደረሰባቸውን የተመለከተ ቅሬታ አሰምተው ነበር፡፡ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ከጉምሩክ አሠራር ጋር በተያያዘ የአስመጪዎች የቀረጥ ነፃ መብት አጠቃቀምና የአስመጪዎች የታሪፍ አመዳደብ በተለይ በጨርቃ ጨርቅና በአምራች ኢንዱትሪ፣ በቱሪዝምና በኮንስትራክሽን ዘርፎች የተሰማሩ ድርጅቶች ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የወጡ ሕጎች በሚፈቅዱላቸው መሠረት ቀደም ሲል ባስገቧቸው የማምረቻ ጥሬ ዕቃዎች፣ ግብዓቶችና ተሽከርካሪዎች ላይ ባለሥልጣኑ ወደ ኋላ ተመልሶ ከፍተኛ ግብር እንዲከፈሉ ማስገደድ መጀመሩ በብዙዎቹ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሯል፡፡

ኦዲትና የወጪ ደረሰኝ

የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት፣ ከንግዱ ኅብረተሰብ ከተሰበሰቡ ጥያቄዎች ውስጥ ከኦዲት አሠራርና ከወጪ ደረሰኝ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ያቀረቡ የአሥር ኩባንያዎችን አቤቱታ አሰምተዋል፡፡ ነጋዴዎች ሒሳባቸው ኦዲት በሚደረግበት ወቅት የባለሥልጣኑ የኦዲት ሠራተኞች የወጪ ደረሰኞችን እንደማይያዙላቸውና የወጪ ደረሰኝ አጠቃቀም ላይ ችግር እንዳለባቸው ጠቅሰዋል፡፡

ከቀረበው ማብራሪያ መረዳት እንደተቻለው፣ የሽያጭ ደረሰኝ ለመስጠት ከማይችሉ አርሶ አደሮች ወይም አቅራቢዎች የተገዙ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የመሳሰሉት ላይ ነጋዴዎች በወጪነት ሊያዙ የሚገባቸው የተለያዩ ሒሳቦች፣ ከውጭ አገር ለተገኘ ብድር፣ ለሥራ ማስኬጃ የወጡ ወጪዎች በባለሥልጣኑ የኦዲት ሥራ ወቅት ያቀረቧቸው ሰነዶች ውድቅ እየተደረጉ ተቸግረዋል፡፡ በመሆኑመ ወጪያቸው እየቀነሰ ገቢያቸው ግን የጨመረ ስለሚመስል የሚከፈሉት የገቢ ግብፈር ሲጨምር እንደሚታይ ጠቅሰዋል፡፡

ከወጪ ጋር በተያያዘ የንግዱ ኅብረተሰቡ ያቀረበው ሌላው ጉዳይ የውሎ አበል ተመንን የሚመለከት ነው፡፡ ለሠራተኞችና ለሥራ አስኪያጆች የሚከፈለው የቤትና የትራንስፖርት አበል ተመን አነስተኛነት መሆኑ ካለው የገበያ ሁኔታ ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ፣ ድርጅቶች ከገበያው አኳያ ለመክፈል ቢገደዱም መመርያው ይህንን በተገቢው መንገድ ማስተናገድ አልቻለም፡፡ ተቀባይነት ያላቸውና ተቀባይነት የሌላቸው ወጪዎች በነጋዴውና በባለሥልጣኑ በኩል በግልጽ ባለመቀመጣቸው፣ ነጋዴዎች ሒሳባቸውን ሠርተው ሲሄዱ ወጪያቸው ተቀባይነት እያጣ ውድቅ እየተደረገባቸው ስመሆኑ በመድረኩ አቅርበዋል፡፡ አንዳንዶቹ ከሞባይል ስልካቸው ወጪ በቀር 75 በመቶ ወጪያቸው ውድቅ እንደሚደረግና ለግል ጉዳያቸውን ተጠቅመውበት ሊሆን እንደሚችል እየተገለጸላቸው  መቸገራቸውን ያመለክታሉ፡፡

ከወጪ አንፃር የጉምሩክ ባለሥልጣንን አሠራር ትችት ውስጥ የከተተና አስገራሚ የተባለ ገጠመኝም በመድረኩ ቀርቧል፡፡ ግንባታው ከመጠናቀቁ በፊት አስገንቢው አካል ምድር ቤቶችን ሲያከራይ ከሚገጠሙት ችግሮች ጋር የተያያዙ ችግሮች በአስረጅነት ቀርበዋል፡፡

በአዲሱ የታክስ አስተዳደር አዋጅ ‹‹‹የሕንፃ አዋጁ ተሠርቶ ያላለቀ ሕንጻ ጥቅም ላይ ሊውል አይችልም› ስለሚል ምንም እንኳ ገቢ ቢያስገኝም ገቢውንና ታክሱን እንቀበላለን እንጂ ወጪውን ወይም እርጅና ተቀናሹን አናሰላም›› በማለት ግንባታቸው ሳያልቅ የሚከራዩ ቤቶችን የሚያከራዩ ሰዎች መቸረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

ሕገወጥ ደረሰኝ

የንግድ ኅብረተሰቡ በምሬት ያነሳው ሌላው ጉዳይ፣ ሕገወጥ ደረሰኝ በሚል ሰበብ የሚደርስባቸው ውጣውረድ ነው፡፡ ነጋዴው ሕጋዊና ሕገወጥ ደረሰኞች የትኞቹ እንደሆኑ ለመለየት የሚችልበት አሠራርና ዘዴ ባለመኖሩ፣ ግዥ ሲፈጽም ሕጋዊ የተባለውን ደረሰኝ በእምነት እንደሚቀበሉ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ግዥ የፈጸሙበት ደረሰኝ ለግብር አስከፋዩ ሲቀርብ ሕገወጥ ይባላል፡፡ በዚህ ሳያበቃም ሐሰተኛ በተባለው ደረሰኝ ሳቢያ በወንጀለኛነት መጠየቀን እያስከተለባቸው በመሆኑ፣ ስለሆነ ባለሥልጣኑ ሕገወጥና ሕገወጥ ያልሆኑ ደረሰኞች የሚለዩበትን አሠራር እንዲዘረጋ ጠይቀዋል፡፡

የዳይሬክተሯ ምላሽና ማብራሪያ

ለነጋዴው ጥያቄዎች ባለሥልጣኑን ወክለው ምላሽ የሰጡት፣ የአገር ውስጥ ታክስ አሠራርና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ዓባይነሽ አባተ፣ የኤክሳይዝ ታክስ በተወሰኑ ምርቶች ላይ ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ ወይም በተመሳሳይ አገር ውስጥ ሲመረቱ ለእያንዳንዱ ምርት በተቀመጠ መቶኛ መሠረት ግብር የሚከፈልበት አሠራር አንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የኤክሳይዝ ታክስ የአገር ውስጥ ምርት ላይ የምርት ወጪን መሠረት በማድረግ እንደሚሠራበትም ጠቅሰዋል፡፡ ከተነሱት የንግዱ ኅብረተሰብ ጥያቄዎች አንፃር ሲታይ በሥራ ላይ ካሉት 19 ዓይነት የኤክሳይዝ ታክስ ምድብ ውስጥ ነፃ የሚለው ነገር ከየካቲት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለሦስት ዓመት ለጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ በገደብ ነፃ ከተደረገው በቀር ነፃ የተደረገ ነገር እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡ ከጨርቃ ጨርቅ ጋር ተያይዞ የአልባሳት ድርጅቶች ከአገር ውስጥ ከሚገዙትም ሆነ ከውጭ ወደ አገር ከሚያስገቡት ጥሬ ዕቃ ላይ የሚከፈለውን የኤክሳይዝ ታክስ ከምርታቸው ላይ እንዲቀንሱ በአዋጁ ስለመቀመጡ አብራርተው፣ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በኩል ከወጣው መመርያ አኳያ ነፃ ተደርጓል የሚለው ግንዛቤ ትክክል እንዳልሆነ ተከራክረዋል፡፡

የተጨማሪ እሴት ታክስን በተመለከተ በሰጡት ምላሽም፣ የሚከፈልበትና ነፃ የሚሆንበት አሠራር መኖሩን በማስታወስ፣ ነፃ የማድረግ ሥርዓት በአዋጅ ወይም በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ምላሽ የሚሰጥበት አሠራር ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

ከወጪ አያያዝ ጋር በተመለከተ በሕጉ የሚፈቀዱ ተቀናሽ ወጪዎች መኖራቸውን የገለጹት ወ/ሮ አባይነሽ፣ በገደብ የሚቀነሱ ወጪዎች እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡ የማይፈቀዱ ወጪዎችም በሕግ መደንገጋቸውን አመላክተዋል፡፡ ተቀናሽ የሚደረጉ ወጪዎች ቀጥታ ከንግድ ሥራው ጋር ግንኙነት ያላቸው፣ ገቢ ለማስገኘት ጥቅም ላይ የዋሉ እንዲሁም በሕጋዊ ማስረጃና ደጋፊ ሰነድ መረጋገጥ እንደሚኖርባቸው አስረድተዋል፡፡

‹‹እነዚህ ሁሉ ማስረጃዎች ታይተው፣ ተመዝነው እውነትም ገቢውን ለማገኘት የወጡ ወጪ ናቸው ወይ?  ወጪዎቹ የግብር ከፋዩን  ስም፣ መለያ ቁጥር ወዘተ ያሳያሉ ወይ ተብሎ ይታያል፤›› ብለዋል፡፡

እንደ ምሳሌ ያነሱትም የነዳጅ ወጪን ነው፡፡ መረጃው ነዳጅ የተቀዳለትን ተሽከርካሪ የታርጋ ቁጥር ጭምር ሊያካት እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡ በሕጉ በገደብ ስለሚያዙ ወጪዎች ዳይሬክተሯ ሲያብራሩም፣ ከጠቅላላ ገቢው ውስጥ ይህንን ያህል መቶኛ፣ ያውም በአንድ ጊዜ የሚቀናነስ ሳይሆን፣ በአገልግሎት ዘመናቸው ለዚህን ያህል መጠን የሚቀነሱ የዕርዳታና መሰል ወጪዎች ምን ያህል መሆን እንዳለባቸው ስለመቀመጡ ጠቅሰዋል፡፡

አበልን በተመለከተ አዋጁ ለባለሥልጣን ገደብ እንዲሰጥ ማስመቀጡን፣ ወቅቱን እየጠበቀ ማሻሻያዎችን ሲያደርግ እንደቆየ ምክትል ዳይሬክተሯ ተናግረው፣ በአዋጅ የመዘዋወርያ አበል የደመወዝን አንድ አራተኛ ሆኖ፣ ከአንድ ሺሕ ብር መብለጥ እንደማይችል ስለመደንገጉ ጠቅሰዋል፡፡ ከኅዳር 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ግን የደወመዝን አንድ አራተኛ ድረስ ሆኖ፣ ከ2,200 ብር እንዳይበልጥ ተደርጎ መሻሻሉን አስታውሰዋል፡፡ የቀን ወጪ አበል እስከ ኅዳር 2007 ዓ.ም. ድረስ 150 ብርና አራት በመቶን በማነጻጸር ከፍተኛውን እንደሚይዝ፣ ከኅዳር 2007 ዓ.ም. እስካሁን ድረስ ግን ከ225 ብር እንዲሁም ከደመወዙ አራት በመቶ ጋር አነፃፅሮ ከፍተኛውን እንደሚወስድ አብራርተዋል፡፡ እስከዚህ ድረስ ያለው አበል ከገቢ ግብር ነፃ ቢሆንም፣ ወጪው ተቀባይነት ሊያጣና ሊመለስ የሚችለው ሕጉ በገደብ ካስቀመጠው በላይ ተከፍሎበታል ሲባል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሯ ምላሽ የሰጡበት ሌላው ጉዳይ የመጠቀሚያ ጊዜው አልፎበት የተቃጠለ መድኃኒት ግብር ተጠይቆበታል ተብሎ ለቀረበ ጥያቄ ነው፡፡ የመጠቀሚያው ጊዜ ያለፈ፣ ሊሸጥ ወይም ሥራ ላይ ሊውል የማይችል ምርት ወይም የተገዛ ዕቃ እንዴት ሊወገድ ይችላል? ከተወገደስ በኋላ እንዴት በወጪ ሊያዝ ይችላል? ለሚለው ጉዳይ  መመርያ መውጣቱን አስታውሰው፣ የተወገዱ ዕቃዎችን በተመለከተ የወጣው ሕግ ዓላማም፣  የተወገደውን ዕቃ በወጪነት ለመያዝ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ላለው የማስወገድ ተግባር ግብር ከፋዩ ለማስወገድ እንድችል ይፈቀድልኝ የሚል ጥያቄ ማቅረብ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ጥያቄው ከቀረበው ማስረጃ ጋር ተመሳክሮ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች በተገኙበት፣ ግብር ከፋዩም ባለበት ዕቃው እንዲወገድ ይደረጋል ያሉት ኃላፊዋ፣ ለሚወገዱ ዕቃዎች ቆጠራ የሚደረግ ከመሆኑ አኳያ የገዙበትን መረጃ በዝርዝር አያይዞ መቅረብ እንደሚገባ አብራርተዋል፡፡

በመድረክ ጉዳዩን ለመፍታት ያስቸግራል ያሉት ሌላኛው የባለሥልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዘመዴ ተፈራ ናቸው፡፡ ‹‹ዋና ዳይሬክተሩ በሚያስቀምጡት አቅጣጫ መሠረት የዘርፉ የተናጥል ጉዳዮች ቀርበው መተማመን ላይ የሚደርስባቸውና መፈታት ያለባቸው እንዲፈቱ ይደረጋል፤›› በማለት ከሌላው ጊዜ በተለየ የንግድ ኅብረተሰቡን ጥያቄ ለማስተናገድ ቃል ገብተዋል፡፡

የታክስ አስተዳደሩ አሠራሮቹ ላይ የተሰጠው አስተያየት ትክክል ነው ያሉት አቶ ዘመዴ፣ አስተዳደሩ ችግር እንዳለበት፣ በየጊዜው በሚደረግ ምርመራና ክትትል እንደሚረጋገጥ በመጥቀስ ችግር ስለመኖሩ አምነዋል፡፡

ፍትሐዊ ውድድር የለም በሚል ለቀረበው ጥያቄም፣ ‹‹እኩል የመወዳደሪያ ዕድል ከመስጠት አኳያ ጉድለቶች አሉ፡፡ ይኼ ጥያቄ የለውም፤›› ብለዋል፡፡ ወደፊት በሚደረጉ ውይይቶችም እየተፈቱ የሚሄዱ በርካታ ጉዳዮች እንደሚኖሩ አስረድተዋል፡፡

የባለሥልጣኑ አሠራሮች ችግሮች ያሉባቸው ቢሆኑም ከግብር ከፋዩም የሚመጣ ችግር ስለመኖሩ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በሁለቱም ወገን ያሉ ክፍተቶችን አስታርቆ መሄድ ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ከኦዲት ሥነ ምግባር ጋር ተያይዞ የቀረቡ ቅሬታዎችን ሁሉንም ኦዲተሮች የሚገልጽ አይደለም ብለዋል፡፡

ከመድረኩ ምን ተገኘ?

ከባለሥልጣኑ ጋር በተደረገው የውይይት መድረክ፣ የእያንዳንዱ ነጋዴ ችግር በተናጠል ምን ይምስላል የሚለውን ያላሳየ ነበር፡፡ ከባለሥልጣኑ የተሰጡት ምላሾች በጥቅል አሠራሩን የሚመለከቱ ሲሆኑ፣ የባለሥልጣኑ ክፍተቶች በደፈናው እኛም እናውቃቸዋል የሚሉ ዓይነት ምላሾች ሲሰጡም የተደመጠበት መድረክ ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚህ ውይይት በኋላ የሁሉም ነጋዴዎች ጉዳዮች በተናጠል እንደሚታዩ ኃላፊዎቹ ቃል ገብተዋል፡፡

አቶ ዑመር እንዳሉት በዕለቱ እንደተካሄደው ዓይነት ውይይት በቋሚነት የሚካሄድ ውይይት ይኖራል፡፡ በተናጠል መታየት ያለባቸውን ጉዳዮች ተመልክቶ ውሳኔ እንደሚሰጥባቸውም አስረድተዋል፡፡ ችግሮችን ለመቅረፍ በጋራ መሥራት አስፈላጊ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንትም ከባለሥልጣኑ ጋር የተደረገው  ውይይት በተናጠል ለቀረቡ ጥያቄዎች ባለሥልጣኑ ምላሽ ለመስጠት ፈቃኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ወደፊትም የአቤቱታ አቅራቢዎችን ጉዳይ ተከታትሎ የማስፈጸም ሥራ ይሠራል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች