Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢኮኖሚውንም ይዘውሩ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሁለት ወራት የሥልጣን ቆይታቸው በአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ እንግዳ ሊባሉ የሚችሉ በርካታ ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡ ጠቅላይ ከወሰዷቸው ዕርምጃዎች ውስጥም አገር ለማረጋጋት ይጠቅማሉ የተባሉትን በማስቀደም፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታታቸው ይጠቀሳል፡፡

ወደ ውጭ በመጓዝ በእስር ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን እስከማስፈታት መድረሳቸውም በትልቁ ሲወሳ ሰንብቷል፡፡ በአገር ውስጥ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ያደረጉት ውይይትም ቢሆን ጥሩ ውጤት እንዳመጣ መናገር ይቻላል፡፡ ጊዜ ውስጥ በየሄዱበት ያደርጉት የነበረው ንግግር፣ የብዙዎችን ልብ ሲሞላ፣ ቀልባቸውን ሲገዛ ታይቷል፡፡ በየንግግሮቻቸው ኢትዮጵያን እያጎላ አንድነትን የሚሰብከው አንደበታቸው ዜጎች በአገራቸው ተስፋ እንዲሰንቁ ማድረግ ችሏል፡፡

      ከንግግራቸው ጎን ለጎን ሊተኮርበት የሚገባው ግን ለመፈጸም ቃል የገቡባቸው ጉዳዮችን መሳካታቸው ላይ ነው፡፡ ሊደረጉ ቀርቶ ሊታሰቡ የማይችሉ ዕርምጃዎችን ሲወስዱ የታዩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ወደ ሥልጣን በመጡ አፍታ የፈጸሟቸው ተግባራት አገር ቢያረጋጉም፣ ከዚህ በኋላ የሚጠብቃቸው የቤት ሥራ ግን ከእስካሁኑም የበለጠ እንደሚሆን ግልጽ ነው፡፡

       እየታየ ያለው ለውጥ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስካሁን በቅጡ ያልዳሰሱት ነገር ግን ጊዜ የማይሰጠው የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ችግር ነው፡፡ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ጀምሮ የታየው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ፣ ሥልጣን ከተረከቡ በኋላም ብሶበታል ማለት ይቻላል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ ይህም ገበያውን እያጋጋለ ከሄደ ውሎ አድሯል፡፡ በእንቁላል ላይ የተደረገው ጭማሪ ጉድ አሰኝቷል፡፡ የዳቦ መጠን ማነሱ ሳይበቃ፣ አቅርቦቱ ከቀደመውም ጊዜ ያነሰ ሆኖ መገኘቱ አሳሳቢን ወቅታዊ ችግር ያሳያል፡፡ ጭብጥ የማይሞሉ ዳቦዎችን በሁለት ብር ሲገዛ የነበረ ሸማች ‹‹ይቺን ዳቦ ከቁርስ በፊት ወይስ ከቁርስ በኋላ ልዋጣት ይሆን›› በማለት ዳቦን በክኒን መልክ ቀይሮ ስለመቀልዱ ሰምነተናል፡፡

ከዕለት ፍጆታ እስከ ካፒታል ዕቃዎች ላይ የታየውን የዋጋ ጭማሪ፣ በአጭሩና በጅምሩ የሥልጣን ቆይታቸው አገር በማረጋጋት የተቃናላቸው ሰው፣ ኢኮኖሚውንም ይታደጉታል በሚል ተስፋ ሰው ሁሉ ችግሩን እየቻለው እንጂ፣ የገበያ ጉዳይ ብዙ ጉድ ባፈላ ነበር፡፡

በ60ዎቹ ቀናት ውስጥ ከችግር ወደ ችግር እያማተረ ያለውን ኢኮኖሚ ለመታደግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት ምን ዕርምጃ እንደሚወስድ የጠቆሙበት ንግግራቸው በሚፈለገውና በሚጠበቀው ልክ አልነበረም፡፡ እርግጥ ነው ወደ ጎረቤት አገሮች ተጉዘለው የወደብ አገልግሎትን የተመለከቱ ትላልቅ አጀንዳዎችን በማንሳት መግባባቶችን መፍጠራቸው መልካም ዕርምጃ ነው፡፡

የአገሪቱን ግዙፍ የመንግሥት ተቋማት በከፊል የባለቤትነት ይዞታ፣ አብላጫውን ድርሻ መንግሥት እንደያዘ በመቀጠል ወደ ግል ይዛወራሉ የተባለት ውሳኔ፣ ሌሎች ተቋማትም ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል የግል ባለሀብቱና የውጭ ኩባንያዎች ይደረጋል መባሉ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የ60 ቀናት የሥልጣን ቆይታ በኋላ የተሰሙ የኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ሊባሉ ይችላል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን አሁንም ኢኮኖሚውን ሊጠግኑ የሚችሉ ፈጣን ዕርምጃዎች ያሻሉ፡፡

የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ እሳቸውም እንዳሉት፣ በውጭ ምንዛሪ ጉዳይ ‹‹አገር ታማለች››፣ ተቸግራለች፡፡ ይህ ከታወቀ መፍትሔውም በቶሎ ሊገለጽ ይገባ ነበር፡፡ እርግጥ ነው እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለው ድርሻው ተሸጦ የውጭ ምንዛሪ የሚያመጣ ኩባንያ በመፍትሔነት ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም ኢኮኖሚው ብርድ ብርድ እያለው እንዲቀጥል ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ ከአገሪቱ የፋይናንስ አቅርቦት፣ ከውጭ ምንዛሪ ግኝትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ከተቆራኙ ችግሮች አኳያ የተነሰኑ ችግሮች ናቸው ካልን፣ የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት ከላይ እስከ ታች መፈተሽ አንዱና ዋነኛው ተግባር መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡

እስከ ዛሬ ድረስ በታው የፋይናንስ ተቋማቱ ጉዞ በርካታ ችግሮች የታዩ ሲሆን፣ የፋይናንስ ተቋማቱ አገር በሚጠቅም ብቃት ላይ እንዳይገኙም አድርገዋቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ ለቁጥር አታካች መመርያዎች እየወረዱላቸው የሚንቀሳቀሱት የፋይናንስ ተቋማቱ፣ የቱንም ያህል የራሳቸው ችግር ቢኖርባቸው፣ ወቅት እየጠበቁ የሚጫኑባቸው የብሔራዊ ባንክ መመርያዎች ብዙውን ሲያበረታቷቸው አይታዩም፡፡ የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት የሚመሩና በዘርፉም ብዙ ዕውቀት ያላቸው ባለሙያዎች፣ ዕውቀታቸውን እንዲጠቀሙና የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችሉ አሠራሮችን በብቃት ይዘው እንዳይቀረቡ የሚያስፈራሩ መመርያዎች እየወጡባቸው ተቸግረዋል፡፡

በፋይናንስ ተቋማቱና በተቆጣጣሪው ብሔራዊ ባንክ መካከል ያለው ግንኙነት ላይ ትልቅ የባቢሎን ግንብ በመገንባቱ፣ ዘርፉ በመነጋገርና በመካከር የተሻለ አሠራር ከመፍጠር ይልቅ በምሬትና በእሮሮ በተሞላ፣ በገዥና ተገዥ ግንኙነት ሲዳክሩ ኖረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀጣይ ጉዞ ለማመላከት ዘገዩ ቢባልም፣ ወደዚህ ወሳኝ ጉዳይ ሲገቡ ሪፎርም ሊደረግባቸው ከሚገቡ ኢኮኖሚ ዘርፎች ውስጥ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው አንዱ እንደሚሆን ይገመታል፡፡ ሪፎርሙ ከተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቱ ጀምሮ በኢንዱስትሪ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ተቋማትን ሁሉ የሚቃኝ መሆን እንደሚኖርበትም ይጠበቃል፡፡

ጤናማ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ካስፈለገን፣ በእስከዛሬው ጉዞ የታዩ ተብታቢ አሠራሮችን ሰብሮ ሊያሠሩ፣ ለዝማኔ የሚያነሳሱ ሕግጋት ሊመጡ ይገባል፡፡ የኢንዱስትሪው ባለሙያዎች አገርን ታሳቢ ያደረገ፣ ከሙሰና የፀዳ አሠራር እንዲከተሉ ማድረግ ካስፈለገም፣ የዘርፉን ባለሙያዎች ማዳመጥ፣ ባለው ሕግም ቢሆን ትርፍ አግኝተው ለባለአክሲዮናቸው ከማከፋፈል ባለፈ ትልቅ አገራዊ ራዕይ ኖሯቸው እንዲሠሩ የሚያነሳሳ ምቹ አሠራር ሊፈጠርላቸው ይገባል፡፡ በነፃነት እንዲሠሩ ተፈቅዶ የሚውሸለሸሉትንም ሊገታ የሚችል አሠራር ይጠበቃል፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ ተቋማቱና እንቅስቃሴዎቸው ይፈተሹ እንላለን፡፡

አንዱን የእንጀራ ልጅ ሌላውን ግን እሹሩሩ እያሉ የሚያቆላምጡ አሠራሮችን በንፁህ ውድድር የሚተኩ ሕግጋትን በማስፈን፣ ውስጥ ለውስጥ የሚሠሩ ሸፍጦችን መስበር በአዲሱ መንግሥት ይጠበቃል፡፡ ሁሉንም የሚያግባባ፣ ኢኮኖሚውን በሚጠቅም መልኩ ሊቃኝ የሚገባው የፋይናንስ ዘርፍ ተፍታቶ ሊገሰግስ ይገባዋል፡፡ የሚያፈነግጠውንም በሕግ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

በመቆጣጠር ሰበብ የሚፈጠርና አግባብ ያልሆነው ጫና ግን ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ መረሳት የሌለበት ሌላው ጉዳይ የባለአክሲዮኖች ሚና ከፍተኛ ነው ሲሆን፣ ወፍራም ትርፍ ከማካበት ባሻገር፣ የፋይናንስ ተቋሞቻቸው የአገርን ኢኮኖሚ ማሳደግ በሚያስችል ማማ ላይ እንዲቀመጡ የማድረግ ከፍተኛ ድርሻና ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የባንክ ኃላፊዎችንና የማኔጅመንት አባላትን ለትርፍ ብቻ ከመወጠር አገር አቋራጭ ሩጫ እንዲጀምሩ በወትወቱም ላይ ይበርቱ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት