Tuesday, February 20, 2024

የመንግሥትን የፖሊሲ ለውጥ የሚያመላክቱ ሁለቱ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውሳኔዎች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያ ለለፉት ሦስት ዓመታት የፖለቲካ ውጥረት፣ ከፍተኛ የሆነ የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመትን ያስከተሉ ተቃውሞዎችና አመፆች ውስጥ ቆይታለች፡፡ ይሁንና በአገሪቱ ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ እንዲጠራና የተሻለ የፖለቲካ መረጋጋት እንዲኖር በማሰብ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሥልጣናቸውን ለቀው፣ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሰይመዋል፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመጀመሪያው ቀን አንስተው በርካታ ነገሮችን በፍጥነት እየተገበሩ ነው፡፡ በሦስት ሳምንታት ውስጥ ካቢኔ መሥርተው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበው ሲያሾሙ፣ የተለያዩ የመንግሥት፣ የደኅንነትና የልማት ተቋማት፣ በተለይም በመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲና በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ነባር አመራሮችን በአዳዲስ በመተካት፣ በውጭ አገሮች ጉዞዎችን በማድረግና በውጭ አገር ያሉ እስረኞችን ሲያስፈቱና የተለያዩ የወደብ ልማት ስምምነቶችን ከውጭ አገር መንግሥታት ጋር ሲያደርጉ፣ በአገር ውስጥም በተለያዩ ምክንያቶች የታሰሩና በክስ ሒደት ላይ የነበሩና የተፈረደባቸውን ሲያስፈቱና ይቅርታ ሲያሰጡ፣ በርካቶች ዕርምጃዎቻቸው በእጅጉ ፈጣን እንደሆኑ እየተናገሩ ነው፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተመረጡ ገና ሁለት ወራት ከጥቂት ቀናት ብቻ ያስቆጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በርካታ ውሳኔዎችን በፍጥነት ሲያስተላልፉና ሲያስፈጽሙ የቆዩ ቢሆንም፣ የኢሕአዴግ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ግንቦት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሁለት ቀናት ታቅዶ የነበረውን ስብሰባ በአንድ ቀን ቋጭቶ በሰጠው መግለጫ እንደተጠቀሱት ውሳኔዎች፣ ብዙኃኑን ያጋገረና እያወያየ ያለ ጉዳይ ከፍተኛ ሚዛን እየተሰጠው ነው፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው  ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ካሁን ቀደም ኢሕአዴግ ይታወቅባቸው ከነበሩና ከተለመዱት ወጣ ያሉና ምናለልባትም የተጻፈ የፖሊሲ ለውጥ ባይኖርም፣ የድርጊት የፖሊሲ ለውጥን የሚያመላክቱና የቀደሙትን ፖሊሲዎች ውጤት አልባነት የሚያመላክቱ እንደሆኑ ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከስብሰባው በኋላ ባወጣው መግለጫ ሁለት ውሳኔዎችን ይፋ አድርጓል፡፡ የመጀመርያው ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ዜጎች በመንግሥት የልማት ድርጅቶችና በመሠረተ ልማቶች ውስጥ የአክስዮን ድርሻ እንዲኖራቸው፣ የተወሰኑ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፊል ለግል አልሚዎች እንዲተላለፉ የተላለፈ ውሳኔ ነው፡፡

ለዚህ ውሳኔ እንደ መነሻ ምክንያት የተቀመጠው የአገሪቱን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል፣ የኤክስፖርት አፈጻጸም ለማሳደግ ሲባል አገሪቱ ከደረሰችበት የዕድገት ደረጃ ጋር የሚመጣጠን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ዕርምጃዎች በማስፈለጋቸው እንደሆነ መግለጫው ያትታል፡፡

መግለጫው መሻሻል አለባቸው ብሎ ከሚያስቀምጣቸው የኢኮኖሚው አፈጻጸም ጉዳዮች አንዱ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ማስፋት፣ የገቢ መሰብሰብ አቅምን ማሳደግ፣ የኑሮ ውድነትን ማቃለልና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት ሲሆኑ፣ የግብርናና ኢ,ንዱስትሪ አምራች ዘርፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በተለይ የውጭ ምርቶች ላይ መረባረብ እንደሚጠይቅ ነው፡፡

ይኼንን የሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴ ውሳኔ በተለያዩ ገጽታዎች የሚመለከቱ አስተያየቶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተንፀባረቁ ይገኛሉ፡፡

የድርጅቶቹን ለሽያጭ መቅረብ አስመልክተው ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት የግብርና ቢዝነስ ማበልፀጊያ የሆነው ድርጅት ብሉ ሙን መሥራችና የቀድሞ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ መሥራችና የመጀመሪያዋ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት እሌኒ ገብረ መድኅን (ዶ/ር)፣ ድርጅቶቹን ሙሉ በሙሉም ሆነ በከፊል ለግል ባለይዞታዎች ማስተላለፍ መልካም ጅምር እንደሆነና አስፈላጊ ዕርምጃ እንደሆነ ያምናሉ፡፡

‹‹ይህ በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ማዘዋወር ነው፡፡ ይህ የንግድ ዘርፉን ነፃና ተወዳዳሪ ማድረግ አይደለም፡፡ ነገር ግን ይህ ድርጊት ከፍተኛ ጥቅሞችን ሊያስገኝ የሚችል ነው፡፡ የመጀመርያው የታለመለት ሽያጭ ከሆነ በርካታ ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች በማስገባት ለዘርፉ ዕድገት አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለመንግሥት ገንዘብ ያስገኛል፤›› ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ‹‹ነገር ግን፣ እነዚህ ውጤቶች በሽያጮቹ ዓላማ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፤›› ይላሉ፡፡

እንደ እሳቸው ምልከታ፣ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ወደ ገበያው ማስገባት ላይ በማተኮር የሚደረግ ሽያጭ ከሆነ፣ በኬንያ የኬንያ ብሔራዊ የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ ድርጅትን ለቮዳፎን ባደረገው የድርሻ ሽያጭ የታየውን ዓይነት ውጤት ሊያስገኝ ይችላል፡፡ ቮዳፎን የኬንያ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ እ.ኤ.አ. በ1997 ከገዛ በኋላ በአገሪቱ የቴሌኮም አገልግሎትን በማስፋፋት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የአስተዳደር ክህሎቶችን በማምጣት ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡

‹‹ነገር ግን ይህ የግል ተፎካካሪ ድርጅቶች ወደ ገበያው ገብተው የሚሠሩበትን አግባብ መፍጠር ባለበት ሁኔታ መቃኘት አለበት፡፡ ልክ በኬንያ እንደታየው፤›› ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ቀጥታ ተፎካካሪ ድርጅቶች ወደ ገበያው እንዲገቡ ከማድረጉ በፊት የድርሻ ሽያጭ አስቀድሞ መምጣቱ ትክክለኛ አካሄድ ነው የሚሉት እሌኒ (ዶ/ር)፣ ቀጥታ ተፎካካሪዎችን በማስገባት ወደ ገበያ ሊበራላይዜሽን ቢኬድ ከባድ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ፡፡

በተመሳሳይ ጉዳዩን በማስመልከት ለሪፖርተር መግለጫ የሰጡት የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ቺፍ ኤግዜክዩቲቭ ኦፊሰርና ፕሬዚዳንት አረጋ ይርዳው (ዶ/ር)፣ ‹‹መንግሥት የወሰደው ከባድ ዕርምጃ የሚደገፍ ነው›› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ይህ ዕርምጃ ወደ ካፒታሊዝም ወይም ገበያ መር ኢኮኖሚ የሚደረገውን ጉዞ ያጠናክረዋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹የወጪ ንግድ በቀዘቀዘበትና የውጭ ምንዛሪ ኩባንያዎችን ሽባ እያደረገ ባለበት፣ ወጣቱ በሥራ ማጣት ፈተና ላይ ባለበት፣ ቴክኖሎጂና ካፒታል ለተወዳዳሪነት አስፈላጊ በሆኑበት ወቅት የተወሰደ ትክክለኛ የመንግሥት ዕርምጃ ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የሕብረት ባንክ የቦርድ ሰብሳቢና ለረዥም ጊዜ የፋይናንስ ዘርፍ ልምድ ያካበቱት አቶ ኢየሱስ ወርቅ ዛፉ፣ ይህ ውሳኔ እንዲመጣ ሲመኙት የነበረ፣ ሲሰሙትም በእጅጉ እንደተደሰቱ ይገልጻሉ፡፡ አቶ ኢየሱስ አክለውም፣ ይህ ውሳኔ እንዲወሰን ዋነኛ ምክንያት የሆኑት የአገሪቱ የውጭ ዕዳ ጫና፣ የአገር ውስጥ ገቢ የሚጠበቀውን ያህል አለመሆንና የውጭ ምንዛሪ እጥረት የሥራ እንቅስቃሴን እየገታ መሆኑ ነው ይላሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት እያለማቸው የሚገኙና በሥራ ላይ የሚገኙ የልማት ድርጅቶች ብድርም ከፍተኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አጠቃላይ ብድር 115 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ግንባታቸው ለተጀመሩ የስኳር ፋብሪካዎች የተወሰደው ብድር ሁለት ቢሊዮን ዶላር ቢሆንም፣ የስኳር ፋብሪካዎቹ አፈጻጸም እስከ ዛሬ የሚተችና ያልተሳካ ነው፡፡

የያዩ የማዳበሪያ ፋብሪካን ለመገንባት 11 ቢሊዮን ብር በጀት ቢያዝም በአሁኑ ወቅት በጀቱ 23 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከአሥር ዓመታት በኋላም መጠናቀቅ ባለመቻሉ፣ ባለቤቱ የኬሚካል ኮርፖሬሽን አዋጭ አይደለም በማለት መንግሥት ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠይቋል፡፡

ነገር ግን ይህ ሒደት ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግለት የሚገባ እንደሆነ ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች የሚስማሙበት ነው፡፡

‹‹ትግበራው እጅግ በጣም ጥንቃቄ ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም በዓለም ላይ እንደዚህ ዓይነት ነገር መምጣቱን አጥብቀው የሚከታተሉ ኩባንያዎች ገብተው ሊያዛቡብን ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርምና በተቻለ መጠን ጥንቃቄ ጨምረን እንሂድበት እንጂ ውሳኔው የሚያስደስትና ለአፈጻጸሙ ሁላችንም ታጥቀን መነሳት ነው ያለብን፤›› ሲሉ አቶ ኢየሱስ ወርቅ ያሳስባሉ፡፡

የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋም (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ይህን ሽግግር ሥራ ላይ የማዋሉ ጉዳይ ራሱን የቻለ ጥንቃቄ ካልተደረገበት፣ የታሰበውን ግብ መምታት አዳጋች ሊሆን ስለሚችል ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፤›› ይላሉ፡፡

ይሁንና ሐሙስ ግንቦት 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፓርላማ ቀርቦ ለዝርዝር ዕይታ ለቋሚ ኮሚቴ የተመራው በጀት ውስጥ በገቢ ምንጭነት ከተዘረዘሩት ውስጥ፣ ከእነዚህ ድርጅቶች ከሚገኙ ሽያጮች የሚል ባለመኖሩ፣ ሽያጮቹ በቀጣዩ በጀት ዓመት ላይከናወኑ እንደሚችሉ የሚያመላክት ነው፡፡

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያስተላለፈው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ሽያጭ ኢሕአዴግ ከሚከተለው ከልማታዊ መንግሥት ርዕዮተ ዓለም ጋር የሚጋጭ ነው ሲሉ የሚከራከሩም አሉ፡፡ በተለይ በማኅበራዊ ሚዲያው አስተያየታቸውን የሚሰጡ ሰዎች ይኼንን አስተሳሰብ በእጅጉ ሲያንፀባርቁ ተስተውለዋል፡፡

ነገር ግን የልማታዊ መንግሥት ግብ ኢኮኖሚውን እዚህ ደረጃ አድርሶ ለካፒታሊዝም ማስረከብ ነው ሲሉ፣ የአክሰስ ካፒታል መሥራች አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሚያዝያ ውስጥ በጻፉት ጽሑፍ አስፍረዋል፡፡

‹‹ኢኮኖሚውን የማስመንጠቅ ስኬት በዋናነት የመንግሥት ተግባር ነው፡፡ ይህም ሲሆን፣ የዕድገትና ልማት አካሄድ ይቀየራል፡፡ እዚህ ላይ ነው ያለነው እንግዲህ አሁን፤›› ይላሉ አቶ ኤርሚያስ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች ውስጥ ሁለተኛው የአልጀርሱን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመቀበል፣ የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ የሚለው ነው፡፡

ይህ ውሳኔ ብዙ ሰዎችን ያነጋገረና የኤርትራ መንግሥትን በሚመለከት የኢትዮጵያ መንግሥት ይዞት የቆየውን ፖሊሲ መቀየሩን የሚያመላክት እንደሆነ እንደ ማሳያ የሚቀርብ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቴ የሕግ ክፍል መምህርና የዓለም ዓቀፍ ሕግ ተመራማሪው ደረጀ ዘለቀ (ዶ/ር) እስከዛሬም የአፈጻጸሙ መቆየት አግባብ እንዳልነበረ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በእብሪተኝነት በመረጠው ዳኛና ፍርድ ቤት የተወሰነውን ውሳኔ ላለመቀበል ማንገራገሩ ልክ አይደለም ይላሉ፡፡

‹‹ይህ ተግባር መጀመርያ ነበር መቀልበስ የነበረበት፡፡ የትኛውም አገር ተወሮና በጦርነት አሸንፎ ከተሸናፊ ጋር ለድርድር አይቀመጥም፡፡ ግን ኢትዮጵያ ለድርድር ተቀመጠች፡፡ ለዚያውም የኤርትራን በቅኝ ግዛት ላይ የተመረኮዘ የድርድር ጥያቄ መሥፈርቶች ተቀብላና ይሁን ብላ፤›› ሲሉ ይተቻሉ፡፡

እንደ ተመራማሪው ገለጻ፣ ኢትዮጵያ ቅድመ ሁኔታዎችን ራሷ አስቀምጣ ድርድሩን እንኳን በድል መወጣት ትችል ነበር፡፡ ነገር ግን ኢሕአዴግ የኤርትራን ጥያቄ ከትግል ወቅት ጀምሮ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው የሚል እምነት ስለነበረው ነው ያንን በተግባር ያረጋገጠው፡፡

ነገር ግን ኤርትራን እንደ መስፈንጠሪያ ተጠቅሞ ኢትዮጵያን ለመግዛት የተቀመጠው የጣሊያን ቅኝ ገዥ ክስተት እንደ መደራደሪያ መቅረቡ ያሳፍራል ባይ ናቸው፡፡

‹‹ለዛሬው ቁጭት መደላድል የተፈጠረው ያኔ ነው፤›› ይላሉ፡፡

ስምምነቱ ላይ ቁጭ ብለው በማይጠቅማቸው መንገድ ድርድር አድርገው በግልግል ከተለያዩ በኋላ፣ አፈጻጸሙን ለማዘግየት ሲሰጡ የነበሩ ምክንያቶች ምስቅልቅል አበዙ እንጂ ምንም አልፈየዱም ባይ ናቸው፡፡ የግልግል ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ማስፈጸም ስለነበረበትም፣ በመሬት ላይ ለመፈጸም የሁለቱ አገሮች ስምምነት ላይ አለመድረስ እንቅፋት ስለሆነ፣ በኤሌክትሮኒክስ መንገድ ተጠቅሞ ችካሎቹ የሚቀመጡበትን ሥፍራ ልየታ እንደሠራም ያስረዳሉ፡፡

‹‹ይባስ ብለው ውሳኔው የመጨረሻና ተፈጻሚ እንዲሆንና ይግባኝና ተጨማሪ ድርድሮች እንዳይኖረው ብለው ተስማሙ፤›› ሲሉም ቁጭታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ይህ ሁሉ ሆኖ ሲያበቃ ኢትዮጵያ ራሷ በመረጠችው ሕግና ፍርድ ቤት ተዳኝታ ውሳኔውን አልፈጽምም ማለቷ፣ የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰትና አገሪቱ ካለችበት ደረጃና ተቀባይነት ጋር የማይመጣጠን ነው፤›› ይላሉ፡፡

በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በመከላከያ ሠራዊት ውስጥ ያገለገሉት የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖትም፣ ቀድሞ የተደረገው ስምምነት ሕዝቡንና ምሁራንን ያላሳተፈና በአንድ ፓርቲ ብቻ የተወሰነ እንደሆነ ያስታውሳሉ፡፡

‹‹ኤርትራ ኢትዮጵያን ከወረረች በኋላ ጥያቄው አገርሽቶ እንደገና በብዕራቸው የመንግሥት ሥልጣን የተቆጣጠረውን ባለጠመንጃ መወትወት ጀመሩ፡፡ በትዕቢት የተወጠረው መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ጥናት ሳያካሂድ አልጀርስ ሄዶ ተዘፈቀበት፤›› የሚሉት ሜጀር ጄኔራል አበበ፣ ‹‹ይህ ስምምነት ወራሪና ተወራሪን፣ አሸናፊና ተሸናፊን እኩል የሚያደርግ በመሆኑ አሳፋሪ ቢሆንም፣ የአገራችንን መብት አሳልፎ የሰጠ በመሆኑ ዘላቂ ሰላም ሊያረጋግጥ አይችልም፡፡ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ደኅንነት፣ በተለይም የኢኮኖሚ ደኅንነትን አደጋ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክና ክብር የማይመጥን ስምምነት ነው፤›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡

ነገር ግን ሜጀር ጄኔራል አበበ፣ ከዶ/ር ደረጀ በተለየ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ ተፈጻሚ እንዳይሆን መሥራት እንደሚያስፈልግ ይከራከራሉ፡፡

‹‹የኮሚሽኑን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲቆም በአክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ ይህ ደግሞ የተሟላ ተፅዕኖ የሚያሳድር (Full Package) ማለትም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ አዕምሯዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና የደኅንነት ማዕቀፍ በማዘጋጀት  የኤርትራን መንግሥት አስገድዶ አዲስ ስምምነት ላይ መድረስ ይጠይቃል፤›› ይላሉ፡፡

በተመሳሳይ በዋናነት በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሰውና የመድረክ አባል ፓርቲ የሆነው ዓረና ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ዓረና መድረክ ይኼንን ትልቅ አገራዊና ሕዝባዊ አጀንዳ ሕዝብ ሳይመክርበትና ሳይወያይበት በእንዲህ መልኩ ይፋ መደረጉ፣ የኢሕአዴግ አምባገነናዊ ባህርይ አሁንም መቀጠሉንና በወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች እንኳ ፖለቲከኞችንና ምሁራንን እንዲሁም ሕዝብን ለማሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው በግልጽ ያሳየ ነው፤›› ብሏል፡፡

‹‹ዓረና መድረክ ይኼንን የአገር ሉዓላዊነትን በቀጥታ የሚፃረር ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ እንዲቃወመው ጥሪ ያደርጋል። ዓረና መድረክ የአልጀርስ ስምምነት በሻዕቢያ የፈረሰና የተጣሰ በመሆኑ ሕጋዊነቱ ያበቃለትና ፈጽሞ ወደ ኋላ የማይመለስ ነው። ዓረና መድረክ የኢሕአዴግ ውሳኔ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚነካ ከመሆኑ ባሻገር የለየለት የአገር ክህደት መሆኑ በፅኑ እንደሚያወግዝ ይገልጻል። የኢትዮ ኤርትራ የድንበር ጉዳይ ትልቅ አገራዊ አጀንዳ እንደመሆኑ መጠን በአንድ ፈላጭ ቆራጭ ፓርቲ የሚያልቅ ሳይሆን፣ ሁሉም ሕዝብ ተሳታፊ ሆኖ ውሳኔ እንዲሰጥበት ይጠይቃል። ዓረና ይኼንን የአገር ክህደት ለማክሸፍ ከመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች አገር ወዳድ ወገኖቻችን በጋራ እንደሚሠራ እያስታወቀ፣ በቅርቡ በመላ ትግራይ ታላላቅ ሕዝባዊ ስብሰባዎችና የተቃውሞ ሠልፎች እንደሚጠራ ያስታውቃል፤›› በማለት ውሳኔውን በሚመለከት ተቃውሞ ጠርቷል፡፡

ከዚህ ጥሪ አስቀድሞ ግን በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች በተለይም በኢሮብ ወረዳ በተደረገ ጥሪ የተቃውሞ ሠልፎች ዓርብ ሰኔ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ተደርገው ነበር፡፡

የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) በክልሉ ከተሞች እየታዩ ያሉ የተቃውሞ ጥሪዎችን ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተላለፈው ውሳኔ ዓላማም የሁለቱን አገሮች ሰላምና ብሔራዊ ጥቅምን ለማረጋገጥ በመሆኑ፣ ውሳኔው የትግራይን ሕዝብ የሚጎዳ ባለመሆኑ ሕዝቡ በሚናፈሱ ወሬዎች መደናገር የለበትም፡፡ የኤርትራ መንግሥትም በኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበለትን የሰላም ጥሪ ተቀብሎ ለመተግበር ዝግጁ ከሆነ፣ በአልጀርስ ስምምነት የተላለፉ ውሳኔዎችን እንደ ማዕቀፍ ለመተግበር በቀጣይ ምክክር ይጠይቃል፤›› ብሏል፡፡

መንግሥት ይህን ውሳኔ ሊወስን የቻለበት ምክንያት እስካሁን ሲያሸንፍበት የመጣው መንገድ እንደማያዋጣ ስላየ፣ የኢሳያስ መንግሥትን እንደ ጠላት የሚመለከት ፖሊሲ ውጤታማ ስላልነበረ፣ ብሎም በዓለም አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ጥቅም ላይ የተመረኮዘ እየሆነ ስለመጣ አገሮች ከኤርትራ ጋር ቀረቤታን መመሥረት መጀመራቸው፣ ከዚህ በላይ ግን የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ውጤታማ ሳይሆን ስለቀረና አገሪቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተፈጠሩት ክስተቶች ምን ያክል ደካማ አገር መሆኗን ያየችበት በመሆኑ፣ ቢያንስ በጽሑፍ ባይሆንም በተግባር የፖሊሲ ለውጥ ለማድረግ በመገደዱ እንደሆነ ዶ/ር ደረጀ ይናገራሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከውሳኔው በኋላ በሰጡት ማብራሪያ፣ አሁን ያለውን ጦርነትም ሆነ ሰላም አልባ ሁኔታ እንደማይቀበሉትና ‹ሞት አልባ ጦርነት› እንደሚሉት ገልጸው፣ ከዚህ ውጥረት ኢትዮጵያም ኤርትራም እንደማይጠቀሙ፣ ሙሉ ኃይልን ከጥቃቅን ግጭቶች ይልቅ ሰላም ላይ ለማዋል እንዲሠራና የኢትዮጵያን ህዳሴ ማረጋገጥ እንዲቻል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በብሩክ አብዱና በዮሐንስ አንበርብር

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -