Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅ​ለአፍሪካውያን የባህል ሙዚቀኞች የተበረከተው ግራሚ

​ለአፍሪካውያን የባህል ሙዚቀኞች የተበረከተው ግራሚ

ቀን:

የዘንድሮው ግራሚ የዓለም አቀፍ አልበም ሽልማትን ያገኘችው የቤኒኗ አንጀሊክ ኪጆ፣ ሽልማቷ በአፍሪካ ላሉ የባህል ሙዚቀኞች መታሰቢያ እንዲሆንላት እንደምትሻ የተናገረችው ሽልማቱን ሎስ አንጀለስ ውስጥ የካቲት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. በተረከበችበት ወቅት ነው፡፡

ነዋሪነቷን አሜሪካ፣ ኒዮርክ ያደረገችው ድምፃዊቷ ሽልማቱን ስትረከብ ‹‹ሽልማቱ በአገሬና በአፍሪካ ላሉ ባህላዊ ሙዚቀኖችና ወጣቱ ትውልድ መታሰቢያ ይሁንልኝ፤›› ብላለች፡፡ ይህን ሽልማት ስታገኝ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡

የተሸለመችበት አልበም የአፍሪካን ሙዚቃ ከአውሮፓውያን ክላሲካል ሙዚቃ ጋር  ያጣመረ ነው፡፡ ከዝነኛው የአሜሪካዊ አቀናባሪ ፊሊፕ ግላስ ጋር በጥምረት የምትሠራው አንጀሊክ አፍሪካ በማንሰራራት ላይ ናት ብላለች፡፡ ሽልማቱን ስትቀበል ‹‹አፍሪካ ቀና ናት፤ አፍሪካ የደስታ ቦታ ናት›› ስትል ተናግራለች፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የ55 ዓመቷ ድምፃዊት አፍሪካን በቀና መንገድ እንድትታይ ለማድረግ እንደጣረችና ሙዚቃ ዓለምን በማስተሳሰር የሰላም መሣሪያ መሆን እንደሚችል ያላትን እምነት ገልጻለች፡፡ ‹‹በርካታ አርቲስቶች ከአፍሪካ እንዲወጡ ሥራዬን መቀጠል አለብኝ፤›› ስትልም ለቢቢሲ አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

****

ላደለው

እንኳንስ የሰው ልጅ ትግል የበዛበት

   ክፉ ደግ ያወቀው፤

እህል እንኳን ባቅሙ ከሚዛን አይገባ

   ሲገኝ ያለ ቦታው፡፡

ሰርጎ ተቀላቅሎ ከበቆሎ ክምር

    ጤፍ ኾኖ ከመኖር፤

ከፍ ዝቅ የሌለው ከዘንጋዳ መሃል

   ዘንጋድነት ያምር፡፡

ያለስፍራው ገብቶ ማኛ ቢሆን ጤፉ

   ምን ዋጋ ያወጣል፤

ተመርጦ ተለቅሞ በንፋስ ተገፍቶ

     በብጥር ይወጣል፡፡

መስሎ ተመሳስሎ አንድ ኹኖ ባንድነት

    ተቀላቅሎ መኖር፤

    ሳያንሱ ሳይበልጡ ከወገን ቢኖሩ

         እንዴት ደግ ነበር?

  • መላኩ ደምለው “ብልጭታ”

******

 

*********

‹‹አብሮ የመብላት ባህል አላዳበርንም››

“አበሻ አብሮ መብላት እንጂ አብሮ መሥራት አይችልም ሲባል እንሰማለን፡፡ ለመኾኑ አብረን መብላትስ እንችላለን፡፡ ቤተሰብ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ቀደም ባሉት ዓመታት በተለይ በበርካታ የገጠር አካባቢዎች ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር በጋራ እንዲመገቡ አይፈቀድም ነበር፡፡ ስለሆነም ወላጆቻቸው ተመግበው እስኪጨርሱ መጠበቅ ግዴታቸው ነበር፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ ግን ምንም እንኳ ከቦታ ቦታ የተለያየ ቢኾንም በተለይ በከተሞች አካባቢ መጠነኛ ለውጥ እየመጣ ነው፡፡ ሕፃናት ከወላጆቻቸው ጋር በአንድ ገበታ እንዲመገቡ የማድረግ ጅምር የምናየው ወላጆች የልጆቻቸውን ፍላጎት በመገንዘብና ትኩረት በመስጠት በኩል የተወሰነ የመሻሻል አዝማሚያ ስላለ ነው፡፡ እንዲህም ኾኖ ግን አብሮ የመብላት ባህል ገና አላዳበርንም ማለት ይቻላል፡፡ ለብዙ ቤተሰቦች በጋራ የሚመገቡበት ጊዜ እምብዛም ጠቃሚ መስሎ አይታያቸውም፡፡ እስቲ እናስታውስ፣ ከሚወዷቸው የቤተሰብ አባላት ጋር በቋሚነት መመገብ ስለሚችሉበት ኹኔታ አስበው ያውቃሉ? አብሮዎት ከሚመገቡ የቤተሰብ አባላት ጋር ምን ያህል ይጨዋወታሉ ወይም ይወያያሉ? በጋራ የሚመገቡበት የመመገቢያ ክፍል፣ የምግብ ጠረጴዛዎችና ወንበሮች፣ የተመጋቢዎቹ አቀማመጥ ምን ቢመስል ይሻላል ብለው አስበው ያውቃሉ?

በጊዜ እጥረት በተጨናነቀው፤ በኑሮ ሩጫ በተወከበው የዘመናችን የጥድፊያ ሕይወት ምክንያት፤ ብዙ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መመገብ አስቸጋሪ መስሎ ሊታያቸው ይችላል፡፡ ነገር ግን ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ማእድ እየቆረሱ የሚያሳልፉት ጊዜ እጅግ ውድ ለኾነ ነገር እንዳዋሉት ሊረዱት ይገባል፡፡ እጅግ በጣም የሚዋደዱ የቤተሰብ አባላት አንዱ የሌላውን ሃሳብ የሚረዳበት፤ ልብ ለልብ የሚተዋወቁበት፤ አብረው የሚስቁበት፣ የሚወያዩበትና የሚደሰቱበት ስለኾነ በልጆችም ኾነ በወላጆች ሕይወት ውስጥ ልዩ ስሜትን ይፈጥራል፡፡ ቤት ያፈራውን ምግብ ከቤተሰብ አባላት ጋር እየተጨዋወቱና እየተጎራረሱ መመገብ የሕይወት እርካታን ያጎናፅፋል፡፡ ለሕፃናት አስደናቂ፣ አዝናኝ፣ አስደሳችና አስተማሪ የኾኑ ታሪኮች ይነገሩበታል፡፡ አብሮ ከመመገብ ጋር የሚያያዙ በርካታ ትዝታዎች ከአእምሮ የማይጠፉና ተቀርጸው የሚቀሩ ናቸው፡፡ ከቤተሰብ አባላት ጋር መመገብ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት በተለያዩ አገሮች የተደረጉ ሳይንሳዊ ጥናቶች ያረጋግጣሉ፡፡

ሙላት አስናቀ፣ “አትላስ” ላይ የጻፉት(2001)

የዕንጨቶች ምክር

ከዕለታት አንድ ቀን ዕንጨቶች ኹሉ ጠላታቸውን ለማጥፋት ምክር ሊመክሩ ተሰበሰቡ፡፡ ከመኻከላቸውም አንዱ ተነሥቶ ጠላታችንን ማጥፋት አንችልም ብሎ ተናገረ፡፡ ኹሉም ባንድ ቃል ስለ ምን አሉት፡፡ ጠላታችን (መጥረቢያ) ብቻውን መጥቶ ባልጐዳንም ነበር፤ ነገር ግን ከውስጣችን አንዳንድ ጠማማ ውስጣወቅ ይወጣና እየሄደ ከሱ ጋራ ይስማማል (ይዋደዳል)፤ ምስጢራችንንም ይነግረዋል፡፡ እኛንም ለማጥፋት እጅ ለጅ ተያይዘው ይመጣሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ልብስ ቅርፊታችንን ይገፋሉ፤ ዐንገት ቅርንጫፋችንን ይቈርጣሉ፣ ብልት ቅጥያችንንም ይሰልባሉ ብሎ መለሰላቸው፡፡ ይኸ ተረት ባንጥያኮስ ጊዜ በእስራኤል ላይ ተፈጽሟል፡፡ ባገራችንም ባጤ ቴዎድሮስ ጊዜ ተደርጓል፡፡

አለቃ ደስታ ተክለወልድ ከ‹‹ገበታዋርያ›› ድርሳናቸው እንደጻፉት (1928)

*************

አንድ አያሳጣን

ታሪኩ ወደ ፓሪስ ይወስደናል፡፡ ካመታት በፊት በአንድ ቤተ ኦፔራ ውስጥ የተከሰተ ነው፡፡ አንድ ዝነኛ ዘፋኝ የሙዚቃ ኮንሰርት ሊያቀርብ ተጋብዞ አድናቂዎቹ ትኬታቸውን ገዝተው የኮንሰርቱን ቀን ይጠባበቃሉ፡፡

በኮንሰርቱ ምሽት አዳራሹ እስከገደፉ በሰው ተጨናነቀ፡፡ የኮንሰርት አቅራቢው ሰው ተጠበቀ፡፡ ፕሮግራሙን ያዘጋጀው ሰው በድንገት ወደ መድረኩ ብቅ አለና፣

‹‹ክቡራትና ክቡራን ታዳሚዎቻችን ስለ ጋለው ትብብራችሁ እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፡፡ አንድ አሳዛኝ ዜና ደርሶኛል፡፡ ጊዜአችሁን ሰውነታችሁ በዚህ ምሽት በናፍቆት የጠበቃችሁት ዝነኛው እገሌ በድንገት ታሞ ስለቀረ ኮንሰርቱን ልናቀርብ አልቻልንም፤ ይሁን እንጂ በእርሱ ምትክ ከጋበዝነው ሌላ ሰው ጋር ባልተናነሰ መልኩ ጥሩ የመዝናናት ጊዜ እንደምታሳልፉ ተስፋ እናደርጋለን›› አለ፡፡

ታዳሚው አጉረመረመ፡፡ የተተኪውን ሰው ማንነት እንኳ ለመስማት ትዕግስት አልነበረውም፡፡ የአዳራሹ ድባብ ከጋለ ድምቀት ወዲያው ጨፈገገ፡፡ የተተካው ሰው ዝግጅቱን አቀረበ፡፡ እንደ ጨረሰ፣ አዳራሹ በፀጥታ ተዋጠ፤ ከአንድም ታዳሚ ጭብጨባ አልተቸረውም፡፡

ይህን ጊዜ በድንገት ካዳራሹ ሠገነት ላይ አንድ ትንሽ ልጅ ብድግ ብሎ ‹‹ባቢ፣ አደንቅሃለሁ! ለእኔ ድንቅ ነህ! የሚል የአድናቆት ጩኸት አሰማ፡፡ አዳራሹ እንደገና ነቃ፤ ከዳር እስከ ዳር ታላቅ ጭብጨባ አስተጋባ፡፡

ሁላችንም በሕይወታችን አንዳንድ ጊዜ ብድግ ብሎልን፤ ‹‹አደንቅሃለሁ! ለእኔ ድንቅ ነህ! የሚለን ሰው አያስፈልገን ይሆን?

  • ኃይል ከበደ ‹‹ጉርሻ እና ፌሽታ›› (2006)

 

                               

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...