Friday, March 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

​መሬትን የአገሬው ሀብት የማድረግ ትግልና ፖለቲካዊ ሽኩቻው

ዓለም አቀፍ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የከተማ መሬትን ሳይጨምር ዓለም አራት ቢሊዮን ሔክታር ገደማ የሚደርስ የእርሻ መሬት አላት፡፡ እንደ የአገሮቹ የአየር ንብረት፣ የመሬት ለምነትና አቀማመጥ የምርታማነት ሁኔታው ቢለያይም፣ የተለያዩ ዕፅዋት፣ ሰብሎች፣ አትክልቶችና የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ደኖችን ለመያዝ የሚችለው ዕምቅና ያልተነካ ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተለያዩ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ ህንድና ቻይናን ጨምሮ አንዳንድ በፍጥነት ያደጉ አገሮች ኩባንያዎች የዓለምን የእርሻ መሬት እየተቀራመቱ ነው ይባላል፡፡ ዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት የተባለ ተቋም በቅርቡ ባወጣው ጥናት መሠረት እ.ኤ.አ. ከ2008 እስከ 2013 ባለው ጊዜ ብቻ 28 ሚሊዮን ሔክታር ያህል መሬት በሽያጭም ሆነ በሊዝ በታዳጊ አገሮች ለባለሀብቶች ተሰጥቷል፡፡

ሌላው ተቋም (Land Portals Land Matrix) እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2013 በወጣው መግለጫ በዓለም ዙሪያ በአሥር ዓመታት ውስጥ 49 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ተሸጧል ሲል፣ 26 በመቶ የሚሆነው ይዞታ ከአገሮቹ ውጪ በመጡ ባለሀብቶች የተወሰደ ነው ብሏል፡፡

ከቅርቦቹ ናይል ትሬዲንግ አንድ ዴቭሎፕመንት የተባለ ኩባንያ ደቡብ ሱዳን ውስጥ አንድ ሚሊዮን ሔክታር መውሰዱ ይጠበቃል፡፡ ቻይና ከኮሎምቢያ ያገኘችው 400 ሺሕ ሔክታር መሬት፣ አግሪሶል የተባለ የእንግሊዝ ኩባንያ ታንዛኒያ ውስጥ 325 ሺሕ ሔክታር መሬት በሊዝ መውሰዳቸው ይጠቀሳል፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ፓኪስታን ውስጥ 324 ሺሕ ሔክታር መሬት፣ ቻይና አርጀንቲና ውስጥ 320 ሺሕ ሔክታር በግዢ ማግኘታቸውም ይታወቃል፡፡ ያም ሆኖ እስካሁን በዓለም ካለው ሰፋፊ እርሻ አንፃር ጥቅም ላይ የዋለው ከአሥር በመቶ በታች እንደሆነ ይታመናል፡፡

ወደ አገራችን እውነታ ስንመለስ ኢትዮጵያ በአነስተኛ የአርሶ አደር ማሳና በተበጣጠሰ ሁኔታ ካላት የእርሻ መሬት ውጪ ሦስት ሚሊዮን ሔክታር የሚደርስ የእርሻ መሬት እንዳላት ይነገራል፡፡ እነዚህ በጋምቤላ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ ሰፋፊ መሬቶች፣ በሶማሌና በአፋር (ለእርሻ አመቺ በሆኑት አካባቢዎች) የሚገኙትን ሲጨምር አኃዙ ከዚህም በላይ ሊልቅ እንደሚችል ይወሳል፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊና ለም መሬት ያህል በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ባለሀብት ማልማት አልቻለችም፡፡ በመንግሥት ደረጃም ቢሆን በ‹‹ሶሻሊዝም›› ስም ሲንፈራገጥ የነበረው ደርግ ከሞካከራቸው የመንግሥት እርሻዎች (በአዋሽ፣ አርሲ፣ ባሌ፣ ምሥራቅ ጎጃም፣ ኦሞና ጋምቤላ) ውጪ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ አልነበረም፡፡ እርሱም ቢሆን በጅምር የቀረና ተጀምሮ ያልዘለቀ ሆኗል፡፡ በመሆኑም እስከ 1990ዎቹ መጨረሻ ደርሶ የሰፋፊ መሬቶች የእርሻ አጠቃቀም አገራዊ መረጃ ከሁለት በመቶ ያነሰ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ እርሻ (ሜካናይዝድ) መሬት ለባለሀብቶች ያቀረበችው፣ ይዞታውን አጥንታና ለክታ፣ ግልጽ መመርያና አሠራር ዘርግታ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በክልሎች የመልካም አስተዳደር መሰናክል እንዳይደናቀፍ የፌዴራል መንግሥታዊ አካል ተዋቅሮም ነው፡፡ በአንፃራዊነት ሲታይም ዝቅተኛ የሊዝ ዋጋ በመተመን አስፈላጊው መሠረተ ልማትና የፀጥታና የደኅንነት (ጋምቤላ አሁንም ታጥቦ ጭቃ ቢሆንም) ለማስፈን በመሞከር እንደሆነ የመንግሥት መረጃ ያስገነዝባል፡፡

ያም ሆኖ እንደ ካሩቱሪ ያሉ (ከ300 ሺሕ ሔክታር በላይ የወሰደ)፣ ሳዑዲ ስታር ያለ 100 ሺሕ ሔክታር የወሰደና የተለያዩ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች በአሥር ሺዎች ሙከራ የተፈለገውን ያህል ባለሀብት ሊመጣ አልቻለም፡፡ በተለይ በሜካናይዝድ ግብርና ትልቅ ስምና ልምድ ያላቸው የአውሮፓ (እንግሊዝ) እና አሜሪካ ኩባንያዎች ጨረታውን እንዳልሰሙ አልፈውታል፡፡

እንደዚያም ሆኖ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን መሬት ቸብችቦ ሸጠው፣ በታዳጊ ክልሎች ያለው ነዋሪና ባለይዞታ እየተፈናቀለ ‹‹ባዕዳን›› ኢትዮጵያን ወርሯት፣ የሚመረተው ምርትም ለአገሪቱ አይጠቅምም፣ የሊዝ ዋጋውም ቢሆን በነፃ ማለት ነው … የሚሉ በርካታ ቅስቀሳዎች ተካሂደውበታል፡፡ በአንድ በኩል በመዘንጋት፣ በሌላ በኩል ለጊዜያዊ የፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ‹‹እኔ ካልበላሁት ልድፋው›› መርህን የተከተሉ ዘምተውበታል፡፡

እውነትም ዘመቻው በርትቶ ወይም የዕድልና የአጋጣሚ ጉዳይ የኢትዮጽያ የሰፊ እርሻ ልማት ሥራ አልተሳካም፡፡ ውጤቱም ከታሰበው በታች ብቻ ሳይሆን ተሰነካክሎ የቀረ ነው፡፡ ከሳምንታት በፊት በዚሁ በሪፖርተር ጋዜጣ በጥልቀት እንዳነበብነው የህንዱ የካሩቱሪ እርሻ ኩባንያ 300 ሺሕ ሔክታር መሬቱን እንዲመልስ ተደርጓል፡፡ እንዲያውም ከውልና ከስምምነት ውጪ ከአምስት ዓመታት ላላነሰ ጊዜ መሬቱን ካለጥቅም በመያዙ ሊከሰስና ሊጠየቅ ይገባል የሚሉ ዜጎች እየተደመጡ ነው፡፡

በተቃራኒው  ካሩቱሪ ከብድርና ሀብት ማሰባሰብ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኝ ነበር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አንዳንድ ባለሥልጣናት ናቸው ከሥራ ያስወጡኝ ሲል ተደምጧል፡፡ ይህ በመሆኑም ጉዳዩን ወደ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤትና የህንድ-ኢትዮጵያ ግንኙነት ድረስ ለመውሰድ ሲዝት ተደምጧል፡፡ የሳዑዲ ስታር የእርሻ ልማት ሥራም ቢሆን ገና ፍሬው አልተቀመሰም፡፡ እርግጥ በመንግሥት ደረጃ የተጀመሩ የመስኖና የስኳር ፕሮጀክት የሸንኮራ ልማት ሥራዎች በሁሉም የተጀመሩባቸው ክልሎች ከሞላ ጎደል የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው፡፡ ምንም ተባለ ግን በአሁኒቷ ኢትዮጵያ የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት የሀብት ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱ ግንኙነትና ፖለቲካዊ ሥልጣን መሠረት መሆኑ አልተቋረጠም፡፡ እርግጥስ ሊቋረጥ ይቻለዋልን?!

መሬት የመንግሥታት ፖሊሲ ምሰሶ!

የዓለም ፊውዳላዊ ሥርዓቶች ሁሉ የሚመሰሉባቸው አንዱ ገጽታ የሙሉ ሥልጣን ፈላጭ ቆራጭነት በአንድ ግለሰብ ላይ ማረፉ ብቻ አይደለም፡፡ ወይም ካለምርጫና የሕዝብ ይሁንታ ሥልጣንን በዘር ሐረግ የማስተላለፍ ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ መሬትን የመሰለ የአገርና የሕዝብ ሀብት ጨምድዶ በመያዝ፣ ሕዝብን ገባርና ጭሰኛ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ነው በሀብት ጠቅላይነት ሥሌት የሥልጣን ዋስትናና የበላይነት ማረጋገጥ የሚቻለው፡፡ በኢትዮጵያም የአፄ ኃይለ ሥላሴ ንጉሣዊና ፊውዳላዊ አገዛዝ ገጽታ ይኼው ነበር፡፡

ደርግ በአቋራጭ ወደ ሥልጣን ሲመጣም በኮሙዩኒዝም መርሆ ስም ‹‹መሬት ላራሹን›› ባያውጅ ኖሮ ሕዝባዊ ማዕበሉ በቀናት ዕድሜ ገፍትሮ ይጥለው እንደበር የሚገልጹ ብዙዎች ናቸው፡፡ በኋላ በእጅ አዙር መሬት ለሕዝብ ቢልም ምርት የሚሰበሰብበት፣ ትርፍ አምራችን የማይበረታታበት ሥርዓት ተንሰራፍቶ መሬትና የግብርናው መስክ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ሊያበረክተው የሚገባውን ጥቅም አቅቦት ቆይቷል፡፡ በገጠር በኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ድርጅታዊ ጥርነፋም መሬት በእጅ አዙር የሥርዓቱ አገልጋዮች ብቻ እንዲጠቀልሉት ሆኗል፡፡ በእርግጥ በሳይንስና በበቂ የምርታማነት አመራር ባይጠናከሩም፣ የመንግሥት እርሻ ልማት መልካም ጅምሮች ብቅ ብቅ ብለው እንደነበር ይታወቃል፡፡

አሁን ያለው ኢሕአዴግ መራሹ መንግሥትም ከመሬት ጋር የጠበቀ የፖሊሲ ቁርኝት አለው፡፡ ለዚህም ሲል በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 (የንብረት መብት) ንዑስ አንቀጽ ላይ ‹‹የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት ነው፤›› ሲል በብረት መዝጊያ ቆልፎበታል፡፡

ይህም ማለት ዛሬ ዜጎች በከተማም ሆነ በገጠር በምትክ፣ በውርስና ቦታው ላይ ባለው ሀብት (ቤት) ስም መሬትን ውስጥ ለውስጥ ቢሸጡም፣ መሬት የመሸጥ መብት ያለው መንግሥት ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ሀብቱ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነው ከተባለ፣ እነዚህ አካላት የመረጡትና በሥልጣን ላይ ያለው ሕጋዊ አካል ነው ሊሸጥ የሚችለው እንጂ ሕዝብ ተሰባስቦ በአንድ ድምፅ ወስኖ ሊሸጥ አይችልም፡፡ ይህን ፖሊሲ በመቃወም ‹‹መሬት ወደ ግል ይዞታ መዞር አለበት›› የሚሉ ፖለቲከኞችን ኢሕአዴግ ኒዮሊበራል ኃይሎች ከማለት አልፎ፣ ፖሊሲው የሚቀየረው በኢሕአዴግ መቃብር ላይ መሆኑን አስምሮበታል፡፡

በአሁኒቷ ኢትዮጵያ የዚህ ፖሊሲ መተግበር ጥቅምም ጉዳትም አስከትሏል፡፡ ጥቅሙ በአብዛኛው መንግሥት እንደሚለው አርሶ አደሩ መሬቱን በባለሀብቶች በሞኖፖል ተነጥቆ ከመሰደድ ድኗል፡፡ በማሳው ላይ የባለቤትነት ማረጋገጫ በማግኘቱም በዚያው ላይ ምርታማነትን ለማሳደግ እንዲፍጨረጨር አስችሎታል፡፡ ከዚሁ ሁሉ በላይ መንግሥት አቅምና ሁኔታውን እየመረመረ የፈለገውን ልማት (መንገድ፣ የባቡር መስመር፣ የጋራ ኮንደሚኒየም፣ ትልልቅ መስኖ ወይም ሌላ) መሥራት ቢፈልግ መጠነኛ ካሳና ምትክ ቦታ ለዜጎች በመስጠት ብቻ ለመተግበር አስችሎታል፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከተማ መሬትን መረጃ በባንክ ይዞ በተሻለ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሊዝ ሥርዓትን በመከተሉ፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለመሰብሰብና መልሶ ለልማት ለማዋል እንደሚያግዘውም ግልጽ ነው፡፡

በጉዳት ረገድ የሚገለጸው በሥልጣን ላይ ያሉ ጥገኛ ኃይሎችና ወደ ሥርዓቱ በመጠጋት በአቋም የሚነግዱና የሚደልሉ የሚመስሉ ኃይሎች ዋነኛ ምሽግ መሬት መሆኑ ነው፡፡ አንዳንድ ውስጥ አዋቂ መረጃዎች እንደሚያስረዱት፣ ዛሬ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ዙሪያ ብሎም ሐዋሳ፣ ባህር ዳርና መቐለን በመሳሰሉ ከተሞች ‹‹በጄት ፍጥነት›› የበለፀጉ ሰዎች የሀብት ምንጭ በሕዝብ መሬት ላይ የተፈጸመ ሕገወጥነት ነው፡፡ ይህ አደጋ አሁን አሁን መጠነኛ የአሠራርና የተጠያቂነት መሻሻል ቢደረግለትም አሁንም አለ፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት ያለበቂ ካሳና ምትክ ቦታ የፈለገውን መሬት ለመጠቀም በመቻሉ የሚጎዱ ዜጎች መኖራቸው ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ለተከታታይ ሳምንታት የተቀሰቀሰው ሁከትና ተቃውሞ የጋራ ማስተር ፕላኑን መሠረት አድርጎ ይሁን እንጂ፣ ‹‹መሬቴን ተነጠቅኩ›› በሚል ሥጋት ነው፡፡ መንግሥት ማኅበራዊ መሠረቴና ደጋፊዬ ነው ለሚለው አካል መሬትን ለመስጠትና ተቃዋሚ ወይም ባላንጣዬ ለሚለው የመከልከል ዕድል የሚፈጥርለት መሆኑ፣ የሥልጣን መሠረቱ ከመሬት ጋር የተቆራኘ ነው እንዲባል አድርጎታል፡፡

የአገራችን የመሬት ፖሊሲ ይህ በመሆኑ ብቻ ወደ ሰፋፊ እርሻ ሥራ የልመጡ የአውሮፓና የአሜሪካ ኩባንያዎች (ኒዮሊበራል የሚባሉት) እንዳሉ ተገምቷል፡፡ የገቡቱ የህንድ፣ የመካከለኛው ምሥራቅና አንዳንድ የአውሮፓ (አበባ እርሻ) አምራቾችም ‹‹በአንቀልባ መታዘል›› የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ሀብትም እያላቸው በአገሪቱ ገንዘብ መሠረት የሚፈልጉ፣ ከያዙት መሬት ያልተፈቀደ ምርት ማምረትና የተፈጥሮ ደን በማቃጠል ከሰል እስከ መሸጥ የወረዱም ታይተዋል፡፡ ስለዚህ የመሬት ፖሊሲ መሬት ለአገር የሚውል ሀብትና ለሕዝብ በፍትሐዊነት የሚጠቅም እንዲሆን ከማድረግ ባሻገር፣ ዓለም አቀፉን ባለሀብት የሚስብና የሚገፋ የፖለቲካ ሽኩቻ መሠረት መሆኑን ማጤን ይገባል፡፡

መሬት ዜጋውን ካልታደገ ጥፋት ይጋብዛል

በዚህ ጽሑፍ የፖሊሲ ክርክር በማድረግ ያ ይጠቅማል ይህ ይጎዳል ለማለት አልሻም፡፡ ነገር ግን ምንም ተባለ ምንም የገጠርም ሆነ የከተማ መሬት በፍትሐዊነት ሕዝብን ሊጠቅም የግድ ነው፡፡ አርሶ አደሩ በዕለት ችግሩ ምክንያት ለዘመናት ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበትን ሀብት በእፍኝ ገንዘብ ሸጦ ለችግር እንዳይጋለጥ ጥበቃ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በአገሪቱ ገንዘብና ዕድል አጥተው ሰፋፊ የእርሻ ልማትን ማከናወን ያልቻሉ፣ የተማሩና ጥረቱ ያላቸው ዜጎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግም ያሻል፡፡ (ዚምባቡዌ ከነጮች የተቀማውን መሬት በዚህ መልክ ጥቅም ላይ ለማዋል ሞክራለች፡፡)

በቅርቡ በፀደቀው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ እንደተገለጸው፣ ዜጎች ተደራጅተውና የዘርፉ ባለሀብቶችም ተደጋግፈው ሰፋፊ የእርሻ ልማት እንዲያከናውኑ ይደረጋል፡፡ በከተሞችም ለልማት የዋለ ወይም ለከፍተኛ ግንባታ በመንግሥት በሊዝ የተላለፈ ቦታ ካሳ ሲከፈል፣ በአንድ በኩል ሌላ ቤት ለመገንባትም ሆነ ተጨማሪ ሥራ ለመሥራት የሚበቃ መሆን አለበት፡፡ በሌላ በኩል ተነሺዎች ያገኙትን ሀብት በጋራም ሆነ በተናጠል ለተሻለ ጥቅም እንዲያውሉት፣ መንግሥትና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች የመደገፍና የመምራት ሥራ ማከናወን አለባቸው፡፡

በሰሞኑ የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ከተሞች የጋራ ማስተር ፕላን ጉዳይ ላይ የሚደመጡ የተለያዩ መከራከሪያዎች፣ ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ዙሪያ ከተሞች ከአርሶ አደሩ የተወሰዱ የእርሻ መሬቶች መጠነኛም ቢሆን ካሳ ተከፍሎባቸው፣ ወይም አርሶ አደሩ በግል ሸጦ ገንዘብ አግኝቶባቸዋል፡፡ ይሁንና ዛሬ ብዙ የማባለው ባለነባር ይዞታ ከቀዬው ተፈናቅሎ በቂ መተዳደሪያ ገንዘብ ሳይኖረው (አንዳንዱ ያገኘውን በፍጥነት አደፋፍቶ በመጨረስ) አሁን እያለማ ላለው ዜጋ ጥበቃና የቀን ሠራተኛ ሆኗል፡፡

ይህ ሁኔታ ደግሞ ‹‹ሺሕ ቢታለብ ያው በገሌ ነው›› እንዳለችው እንስሳ፣ ኢንዱስትሪም ተስፋፋ ወይም መንግሥት በመሬት ሊዝ ከፍተኛ ሀብት ሰብስቦ መልሶ ለልማት አዋለው ‹‹ምን ሊደርሰኝ?›› ከማለት አይወጡም፡፡ ስለዚህም ልማትን ከመደገፍና ከመሳተፍ ይልቅ መቃወም ብሎ የግልም ሆነ የመንግሥት የልማት ሥራዎችን በስሜት ተነሳስቶ ወደ ማጥፋት መሄድ ይመጣል፡፡ በቅርቡ እንደታየው የኦሮሚያ ሁኔታ ማለት ነው፡፡

በቅርቡ በውጭ የሚኖረው ጽንፈኛ ተቃዋሚ ኃይል በስፋት እንደቀሰቀሰው የአዲስ አበባ መስፋፋት ተዓምራዊ ለውጥ እንደሚያመጣ ሊክድ አልቻለም፡፡ ነገር ግን በመሬትህ ላይ እነ እገሌ ኢንዱስትሪ ሊገነቡና ሊያለሙበት ነው በሚል አፍራሽና ዘረኛ አካሄድ፣ ነባሩን ባለይዞታ ሊታደግ የሚችል የመሬትም ሆነ የልማት ፖሊሲ እንደሌለ አድርጎ ቀስቅሶታል፡፡ ይህ በእውነታ ላይ ያልተመሠረተ አካሄድ የትም የማያደርስና የሚጋለጥ ቢሆንም፣ ለጊዜው የፖለቲካ ትርፍ አላስገኘላቸውም ማለትም አይቻልም፡፡

ከዚህ አንፃር በቀጣይ መንግሥት የሚጠብቁትን ተግባራት መጠቆም ተገቢ ነው፡፡ አንደኛው መሬትን የህልውናው መሠረት፣ ድንበርን የሉዓላዊነት መገለጫ ባደረገ አጥባቂ ማኅበረሰብ ውስጥ መንግሥት በመሬትና በድንበር ጉዳይ ላይ ግልጽ፣ ሕዝብ ያሳተፈና ኮስታራ አቋም መያዝ አለበት፡፡ የአገራችን ሕዝብ ዕድሜ ልክ የኢትዮጵያን ለም አፈርና ማዕድን ጠራርገው ከሚሄዱ ወንዞቻችን በላይ አሥር ሜትር መሬት ለሌላ አገር ተላለፈ ቢሉት (ተወሰደ ቢባል) እንዴት እንደሚደፈርስ እይታየ ነው፡፡ ይኼ ክልል ከክልል ቢሆንም በትኩረት መታየት አለበት፡፡

መንግሥት የሰፋፊ እርሻ ልማት ሀብትን በመጠቀም ረገድም በጀመረው መንገድ ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል፡፡ የተለያዩ የውጭ ኩባንያዎች በርካሽ የሊዝ ዋጋ ማግኘታቸው መልካም ቢሆንም፣ በታለመላቸው መሠረት ‹‹በጊዜ የለኝም›› መንፈስ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ ያሻል፡፡ የሚያመርቱት ምርት ሽያጭና የምንዛሪ ግኝት ላይም እንዲሁ ዓለም አቀፍ መርህን ፈትኖ መተግበር ግድ ይላል፡፡ ከሥራ ዕድል ፈጠራና ቴክኖሎጂ ሽግግር አኳያ ሊሰጡት የሚገባውን ጥቅም በተቆርቋሪነት መንፈስ ማስፈጸም ብቻ ሳይሆን፣ ለአካባቢ ማኅበረሰብ ልማት ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርጉና የባለቤትነት ስሜት እንዲፈጠር ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡

በመጨረሻ ቀዳሚና ወሳኙ ተግባር ግን የመሬት አስተዳደር ሥርዓቱ የግልጽነትና የተጠያቂነት መንፈስ እንዲላበስ፣ የፍትሐዊነትና የተቆርቋሪነት ባህል እንዲገነባለት ማድረጉ ላይ ነው፡፡ መሬት አላቂ ሀብት ነው፡፡ ዛሬ ከ90 ሚሊዮን በላይ ነው የሚባለው የአገራችን ሕዝብ 120 ሚሊዮን ለማድረስ ከ15 ዓመታት ያነሰ ጊዜ በቂ ነው፡፡ የአገሪቱ የከተማም ይባል የገጠር መሬት ግን ያው ነው፡፡ አይጨምርም፣ አይሰፋም፡፡ ነገር ግን እንዳይቀንስና እንዳይጠብ መመከት የሕዝብና መንግሥት ብሔራዊ ግዴት ነው፡፡

ከዚህ አንፃር አገራዊ መሬትን ብቻ ሳይሆን የግለሰብና የዜጎችን ፍትሐዊ ድርሻ ከሞኖፖል ቀማኛ፣ በተለይ ከኪራይ ሰብሳቢውና ሕገወጡ ደላላ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ወደ መንግሥትና ሥርዓቱ ተጠግቶ፣ የቀድሞዎቹ ፊውዳሎች ነጭ ለባሽ ይመስል የመሬት ካርታን በየዘመዱና ወዳጁ ስም እየያዘ የሚቸበችብና በውለታ የሚሰጥ የሥራ መሪና ሙያተኛ ሁሉ እጁ ሊቆረጥና አርፎ እንዲቀመጥ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት በውስጥ ሌቦች እምነቱ እንዳይጓደልና ጉዞው እንዳይደናቀፍ ሊጠነቀቅ ግድ ይለዋል፡፡

እንደ ርስትና ጉልት ከመንገሥት ለልማት የወሰዱትን መሬት አጥረው ያለሥራ ዓመታት እያስቆጠሩ ያሉ ‹‹ባለሀብቶች›› ጉዳይም ዕርምጃ ይሻል፡፡ እነዚህ የአገር ውስጥም ይሁኑ የውጭ ባለሀብቶች እንደ ካሩቱሪ ፈጣንና ቆራጥ የመንግሥት ዕርምጃ ካልጎበኛቸው፣ የመልካም አስተዳደር ብልሽትና የኢፍትሐዊነት መገለጫ መሆናቸው አይቀርም፡፡ ስለዚህ አስፈላጊውን ዕርምጃ እየወሰዱ የሕዝቡን ጥርጣሬና ሥጋት መግፈፍ ያስፈልጋል፡፡ መሬትን የሕዝብና የአገር ሀብት የሚያደርጉበትን ፖለቲካዊ ሽኩቻ በድል ማለፍ የሚቻለው ይህና ይህ ሲደረግ ብቻ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles