ግዮን ሆቴል የሚገኘው የሙላቱ አስታጥቄ አፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ ማስተናገድ ከሚችለው በላይ በታዳሚዎች ተሞልቷል፡፡ መጠነኛ መብራት በበራበት መድረክ ከበሮና የሥዕል ሸራ ይታያሉ፡፡ ረዘም ያለ ዱላ በቀኝ እጁ ይዞ በኩራት የሚንጎማለል ወጣት እየፎከረ ወደ መድረኩ ወጣ፡፡ በኢትዮጵያ ጥንታዊ ታሪክ በተለይም ከጦርነት ጋር በተያያዘ ጀግንነትና አሸናፊነት የሚንፀባረቅበትን ፉከራ፣ ሽለላና ቀረርቶ አሰማ፡፡ ከነጩ ሸራ በስተጀርባ ያለው ሠዓሊ ሸራውን በልብ ቅርፅ ቀደደ፡፡ እጁን ቀይ ቀለም ነክሮም በቀዳዳው እጁን እያወጣ ይሥል ጀመረ፡፡
ሁለቱ አርቲስቶች ከመድረክ ሳይወርዱ ቀጠን ያለ ድምፅ ያላት እንስት ዘፋኝ፣ የዊልያም ሼክስፒርንና የፀጋዬ ገብረመድኅንን ግጥሞች እያጣመሩ የራሳቸውንም ስንኝ እያከሉ የሚያነበንቡ ወጣቶች ተቀላቀሉ፡፡ መድረኩ ተመሳሳይ መልዕክት ባዘሉ ነገር ግን በተለያዩ የጥበብ ዓይነቶች ደመቀ፡፡
“To be or not To be ሼክስፒር እንዳለው፤ መሆን አለመሆን ፀጋዬ እንደቃኘው፤ እንግዲያ ልቀኛ፤ የማይሆነው ሁሉ ሆኖ ይታየኛል፤ ጥያቄውን ዘሎ መልሱ ይታየኛል፤ መልሱ ይቀናኛል፤ እንዲህ ያደርገኛል…›› ሠዓሊት ምሕረት ከበደ ካቀረበችው ግጥም የተቀነጨበ ሲሆን፣ ድምፃዊቷ ሳራ ቲ ታጅባታለች፡፡ ሠዓሊው ታምራት ገዛኸኝ ደግሞ ሸራው ላይ ፍቅርን የሚያመላክቱ ሥራዎች ያሳያል፡፡ የካቲት 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ትርኢት ካሳዩ ሰባት ኢትዮጵያውያን ወጣቶች መካከል ናቸው፡፡ ወጣቶቹ በብሪትሽ ካውንስል ሆርን ኦፍ አፍሪካ ሊደርሺፕ ኤንድ ለርኒንግ ፎር አክሽን (ሆላ) ፕሮጀክት ሱዳን፣ ካርቱም ላይ ከእንግሊዛዊው ራፐር አካላ ጋር ሥልጠና የወሰዱ ናቸው፡፡
ራፐር፣ ገጣሚና በይበልጥም አፍሪካ ነክ በሆኑ አስተምሮቶቹ የሚታወቀው አካላ የመሠረተው ሂፕ ሃፕ ሼክስፒር ካምፓኒ አፍሪካ ውስጥ ከሚያካሂዳቸው የወጣቶች ሥልጠና አንዱ በሆነው ፕሮጀክት የተሳተፉት ኢትዮጵያውያኑ የትርዒታቸውን ትኩረት ፍቅር ላይ አድርገው ነበር፡፡
የእንግሊዛዊው ፀሐፊ ተውኔትና ገጣሚ ሼክስፒር ሥራዎች ከሚያጠነጥኑባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ፍቅር፣ ኃያልነትና ስግብግብነት ይጠቀሳሉ፡፡ ወጣቶቹ ከእነዚህ ፍቅርን መርጠው፣ ርዕሰ ጉዳዩን ይገልጻሉ ያሏቸውን ጥበባዊ ሥራዎች አሳይተዋል፡፡ ሂፕ ሃፕ ሼክስፒር ካምፓኒ በዋነኛነት የሼክስፒርን ሥራዎች ከሂፕ ሃፕ ጋር አጣምሮ በማስኬድ የሚታወቅ ሲሆን፣ ለወጣቶቹ የተሰጠው ሥልጠናም ይኸው ነበር፡፡
በትርኢቱ ከወጣቶቹ በተጨማሪ ኢትዮጵያውያኑ የሂፕ ሃፕ አርቲስቶች ሰናይ መኰንን (ዋህ) እና ጁክ ቦክስ ዘ ኢሉስትረስ እንዲሁም ታዋቂው ራፐር አካላም ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡ ‹‹ፋይንድ ኖ ኢነሚ››፣ ‹‹ሰን ዙ››፣ ‹‹ሚስተር ፋየር ኢን ዘ ቡዝ››ና ‹‹ማልኮም ሰይድ ኢት››ን የመሰሉ ዝነኛ ዘፈኖቹን አስደምጧል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1983 እንግሊዝ የተወለደው አካላ በአጭር ጊዜ ተፅዕኖ ማሳደር ከቻሉ የሂፕ ሃፕ አርቲስቶች አንዱ ነው፡፡ ኪንግስሊ ጄምስ ዳሊ ወይም በመድረክ ስሙ አካላ፣ በተለያዩ ተቋሞች እየተዘዋወረ ስለ አፍሪካና ሕዝቦቿ ታሪክ እንዲሁም ስለሌሎች ጉዳዮች ትምህርት ይሰጣል፡፡ በቅርቡ በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የጥቁሮች ታሪክ ወርን ምክንያት በማድረግ ያቀረበው ንግግርም ተጠቃሽ ነው፡፡
ቅኝ ግዛትና ዘረኝነት የአፍሪካውያን ታሪክን ጥላሸት ቢቀቡም፣ አፍሪካዊያን የጥንታዊ ሥልጣኔ ባለቤት መሆናቸውን የሚያትት ገለጻ አድርጓል፡፡ የገለጻው መሠረት ደግሞ የሰው ልጅ መገኛና የሥልጣኔ መነሻ የሆነችው ኢትዮጵያ ነች፡፡ ከ3.2 ሚሊዮን ዓመታት አስቀድሞ የኖረችውና ከአውስትራሎፒቲከስ አፋረንሲስ ዝርያ ረዥም ዕድሜ ካስቆጠረችው የሉሲ (ድንቅነሽ) አፅም ጀምሮ ስለ አፍሪካ ሥልጣኔ በጥልቀት ያትታል፡፡
አካላ ከሪፖርተር ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ እንደገለጸው፣ ዘመናትን ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ታሪክ በጥበባዊ ሥራዎች መንፀባረቅ አለበት፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ሂፕ ሃፕ ሙዚቃ የኢትዮጵያ ባህል፣ ቋንቋና የማኅበረሰቡ ችግሮች ሊዳሰሱ ይገባል፤›› ይላል፡፡ አገርኛና ጥበባዊ ፈጠራ የሞላው ሂፕ ሃፕ የአገሪቱ ነፀብራቅ ሆኖ ማየት እንደሚሻም ያክላል፡፡
ይህንን ከግምት በማስገባትም ትርኢቱን ያቀረቡት ወጣቶች በአማርኛ ራፕ ያደርጉ ነበር፡፡ በእንግሊዝኛ ራፕ የሚያደርጉት ደግሞ የተለየ ኢትዮጵያዊ ቅላጼ ይጨምሩበታል፡፡ ባለሙያዎች ሂፕ ሃፕ ከኢትዮጵያው ፉከራ፣ ሽለላና ቀረርቶ ጋር ተመሳሳይነት አለው ይላሉ፡፡ አካላም የሂፕ ሃፕ መነሻ ጥንታዊ የፍሪካ ባህል እንደሆነና ዘዬው ወደ አውሮፓና የካረቢያን ደሴቶች የተስፋፋው በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ወቅት እንደሆነ ይናገራል፡፡
ቲምቡክቱ፣ ዮሩባላንድ፣ ጋናና ሌሎችም ጥንታውያን የአፍሪካ አገሮች ለሂፕ ሃፕ ያበረከቱት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ችላ እንደሚባል ይገልጻል፡፡ ‹‹ዓለም አቀፍ መድረክ የሚያገኙት የሂፕ ሃፕ አርቲስቶች የማኅበረሰቡን ችግር አጉልተው የሚያወጡት ሳይሆኑ ስለ ወሲብ፣ አደገኛ እፅና ግድያ የሚያነሱት ናቸው፤›› ይላል፡፡ እሱ በተቃራኒው ጥቁር አሜሪካውያን፣ ጥቁር እንግሊዛውያንና በየአገሩ ያሉ ጥቁሮች እለት ከእለት በሚገጥሟቸው ፈታኝ ሁኔታዎች ላይ ያተኩራል፡፡
ዘረኝነት፣ ቅኝ ግዛት፣ ድህነት፣ የፆታ እኩልነት አለመኖርን የመሰሉ አንገብጋቢ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በሙዚቃዎቹ ያነሳል፡፡ ከእንግሊዛዊት ስኮትላንዳዊት እናትና ከትውልደ ካረቢያን አባት የተወለደው አካላ፣ ወደ ሙዚቃ ከመግባቱ አስቀድሞ መሰል ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ዘፈኖችን ያዳምጥ ነበር፡፡ ዴኒስ ብራውን፣ ግሪጎሪ አይዛክስ፣ ቦብ ማርሌና ፒተር ቶሽን፣ የመሰሉ የሬጌ ሙዚቀኞችን ይሰማል፡፡ ፐፕሊክ ኢነሚ፣ ኬአርኤስ ዋን፣ ውታንግ ክላን፣ ኢሞርታል ቴክኒክና ናስ ደግሞ የሂፕ ሃፕ ምርጫዎቹ ናቸው፡፡
ሙዚቀኛዋ እህቱ ሚስ ዳይናማይትና ዲጄ የእንጀራ አባቱን ጨምሮ በአርቲስቶች ተከቦ ማደጉ ለሙዚቃ ሕይወቱ አስተዋፅኦ እንዳለው የሚገልጸው አካላ፣ ‹‹ከኢትዮጵያውያን ድምፃዋያን የሙላቱ አስታጥቄን ‹‹ስኬችስ ኦፍ ኢትዮጵያ›› አልበም አዘውትሬ አዳምጣለሁ፤›› ይላል፡፡ ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ስለ ባህላዊው ጥሩ እውቀት እንዳለው ይናገራል፡፡
አካላ ስለ ቀደምት የአፍሪካውያን ሥልጣኔ ሲያወሳ እንደ ጎንደርና አክሱም ያሉ ከተማዎችን አያይዞ ያነሳል፡፡ ካምፓኒው አፍሪካ ውስጥ ከሚንቀሳቀስባቸው አገሮች ዚምባብዌ፣ ናይጄሪያ፣ ሞሮኮና ቱኒዚያ ይጠቀሳሉ፡፡ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና ደቡብ ሱዳን ሙዚቀኞችን ለማጣመር ያለመ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ከአዲስ አበባ ያሰባሰባቸው ወጣቶች በአማርኛ ግጥሞች ሂፕ ሃፕ መሥራታቸውን አወድሶ፣ ጠንካራ ስንኝ እንደሚያሰናኙና ጥሩ መልዕክት እንደሚያስተላልፉ ያለውን እምነት ገልጿል፡፡
በአካላ አስተያየት፣ ሙዚቃ የማዝናናት ሚና እንዳለው ሁሉ የማኅበረሰቡ ችግሮችንም አፅንኦት ሊሰጥ ይገባል፡፡ በደቡብ አፍሪካ የፀረ አፓርታይድ ትግል እንደ ማርያ ማኬባ ያሉ ድምፃውያን እንዲሁም በዚምባብዌ የነፃነት ትግል ፌላ ኩቲ የነበራቸውን ሚና ያነሳል፡፡
በጥቁር አሜሪካውያን የነፃነት ትግል እንደ ሳም ኩክና ቢሊ ሆሊዴይ ያሉ ድምጻውያን እንዲሁም በእንግሊዝ ፀረ መደብ ትግል የተሳተፉትንም ይጠቅሳል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያን ጨምሮ በየአገሩ ፈታኝ ሁኔታዎች አሉ፤ ኢፍትሐዊነት ይስተዋላል፤›› የሚለው አካላ፣ ሙዚቃ ይህን መዋጊያ መሣሪያ መሆን እንደሚችል ያስረዳል፡፡ ‹‹በሙዚቃዎቼ ስለማኅበረሰቡ መሻሻል መልዕክት አስተላልፋለሁ፤›› ይላል፡፡
ሙዚቃ ለለውጥ ማነሳሻነት እንዳይውል ፈርጣማ ክንዳቸውን የሚያሳርፉ መንግሥታት እንዲሁም የግል ተቋሞች በአየገሩ መኖራቸው ፈታኝ እንደሆነም አያይዞ ይናገራል፡፡ በድህነት ባደገበት ለንደን ዘረኝነት፣ የወጣቶች አልባሌ ሱስ ተገዢነትና ሌሎችም ውጣ ውረዶች እንደሚከሰቱ በማጣቀስ፣ የሙዚቃዎቹ መነሻ ተሞክሮዎቹ እንደሆኑ ይገልጻል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2006 የመጀመሪያ አልበሙን ‹‹ኢትስ ኖት ኤ ሩመር›› ከለቀቀ በኋላ ስድስት አልበሞችን አሳትሟል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1996 የተጀመረው የእንግሊዙ ሚውዚክ ኦፍ ብላክ ኦሪጅን ሽልማት (ኤምኦቢኦ አዋርድ) ምርጥ ራፕር ተብሎም ተሸልሟል፡፡
ከልጅነቱ ጀምሮ ለትምህርት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል፡፡ ‹‹ኖሌጅ ኢዝ ፓወር›› (እውቀት ኃይል ነው) በሚል ስያሜ የለቀቃቸው ሥራዎቹ ዝነኛ ናቸው፡፡ ሙዚቀኞች ስለ ማኅበረሰባቸው ነባራዊ ሁኔታ ማወቅ፣ ማንበብና ሁለገብ መሆን እንዳለባቸው ያምናል፡፡ ‹‹ትምህርት ብዙ ነገሮችን እንድጋፈጥ አስችሎኛል፤ በተለይም ታሪክ አጥብቄ እወዳለሁ፤›› ይላል፡፡
አካላ ከሚጽፋቸው ግጥሞች በተጨማሪም ‹‹ዘ ሩውንስ ኦፍ ኢምፓየር›› የተሰኘ መጽሐፍ አሳትሟል፡፡ ቦክሰኛው መሐመድ አሊ፣ የቻይናው ፈላስፋ ሰን ዙ፣ የነፃነት አቀንቃኙ ማልኮም ኤክስ ለጥበባዊ ሥራዎቹ ከሚያነሳሱት ታላላቅ ሰዎች ውስጥ ናቸው፡፡ እሱም በተለያዩ ጥበባዊ ሥራዎቹ ስለ ነፃነትና እኩልነት ይሰብካል፡፡
በሙዚቃ ስላሳለፈው ሕይወት ሲገልጽ፣ ‹‹ዓለምን በመዞሬ፣ ስድስት አልበሞች በማውጣቴና ከታታላቅ ሙዚቀኞች ጋር አብሬ በመሥራቴ ደስተኛ ነኝ፤ ለወደፊትም እንደምቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ፤›› በማለት ይናገራል፡፡