የሰማዕቱ አርበኛ ጳጳስ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ዳግም ተከላ በጥር መጨረሻ ሲከናወን የኢትዮጵያ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ለመንግሥትና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ያስተላለፉት ጥብቅ መልዕክት ሌላኛውን በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ሰማዕት የሆኑትን ብፁዕ አቡነ ሚካኤልን መታሰቢያ የተመለከተ ነበር፡፡
እንዲህም ጻፉ፡- ‹‹እንደ ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በተመሳሳይ ሁኔታ በጎሬ ከተማ በ1929 ዓ.ም. በፋሺስት ኢጣሊያ በግፍ የተገደሉት ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤልም ለሀገር ክብርና ነፃነት የከፈሉትን የሕይወት ዋጋ ትውልዱ ሁሉ እንዲዘክረውና እንዲማርበት በቅዱስ ሲኖዶስ አማካይነት የተዘጋጀው ሐውልታቸው ሰማዕትነትን በተቀበሉበት ቦታ በጎሬ ከተማ በክብር እንዲመለስና እንዲቆም ለሚመለከተውና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡››
ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ማን ናቸው?
‹‹ቃና ዘገሊላ ተሰጠው ሥልጣን፣
እኛን ለነፃነት ውኃውን ለወይን፣
አርበኞች መሞትን ማን አስተማራቸው
አቡነ ጴጥሮስ ነው ባርኮ የሰጣቸው
ሚካኤል ቀድሞ መንገድ ቢመራቸው
በኦሜድላ በኩል ብርሃን ወጣላቸው፡፡››
ይህ የመዝሙር ግጥም አንድ አርኬ (አንጓ) ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወርሮ (1928-1933) ከነበረበት በእርመኛ አርበኞችና ሕዝቡ ተጋድሎ ድል ተመትቶ ከወጣ በኋላ የተዘመረ ነበር፡፡
ለነፃነት ተጋድሎ ከተሰማሩት መካከል የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይገኙበት እንደነበር ከተመለከቱባቸው ቅኔዎች ውስጥም፣
‹‹ደህና ሁኚ ድጓ ደህና ሁኚ ቅኔ
ጀግኖች ከዋሉበት መዋሌ ነው እኔ›› ይገኝበታል፡፡ ከላይ የተገለጸው ባለስድስት ስንኙ ሰም ለበስ ቅኔም ይህንኑ በጉልህ ያመለክታል፡፡
‹‹ቃና ዘገሊላ›› በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩት በዓላት አንዱ ሲሆን በየዓመቱ ጥር 12 ቀን ይከበራል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ውኃውን ወደ ወይን የለወጠበት ዕለት ነውና፡፡ በዚሁ ጥር 12 ቀን በ1933 ዓ.ም. ላይ በኢትዮጵያ ታሪክም አዲስ ምዕራፍ ተከፍቶባታል፡፡ ፋሺስት ኢጣሊያ የአምስት ዓመት የወረራ ዘመኑ ጀንበሩ እየጠለቀችበት መሆኑ የተረጋገጠበት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ከስደት መልስ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በምዕራብ ኢትዮጵያ ኦሜድላ (ቤንሻንጉል ጉሙዝ) ላይ ያውለበለቡበት ዕለት ናት፡፡
ለዚህም ነው ባለቅኔው፡-
‹‹ቃና ዘገሊላ ተሰጠው ሥልጣን
እኛን ለነፃነት ውኃውን ለወይን›› ብሎ ያመሰጠረው፡፡
በአምስቱ ዘመን እነዚያን እርመኞች አርበኞችን ያነቁ ከመጀመሪያዎቹ አራት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት መካከል ሁለቱ ብፁዓን ጳጳሳት እዚህ ላይ ይነሳሉ፡፡ ፋሺስቶች አዲስ አበባ በገቡ በሦስተኛው ወር (ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም.) ሰማዕት የሆኑት አቡነ ጴጥሮስና አዲስ አበባ በጠላት በመያዟ ምክንያት ዋናው ከተማ ወደ ኢሉባቦር ጎሬ ሲዛወር ጳጳስ የነበሩትና ፋሺስቶች ጎሬ ከተማን በኅዳር 1929 ዓ.ም. በያዙ በሳምንቱ (ኅዳር 24 ቀን 1929 ዓ.ም.) ሰማዕት የሆኑት አቡነ ሚካኤል ናቸው፡፡
ለዚህም ነው ባለቅኔው እንዲህ ያገናዘበው፡-
‹‹አርበኞች መሞትን ማን አስተማራቸው
አቡነ ጴጥሮስ ነው ባርኮ የሰጣቸው፤
ሚካኤል ቀድሞ መንገድ ቢመራቸው
በኦሜድላ በኩል ብርሃን ወጣላቸው፡፡››
ለኦሜድላው ብርሃን ፋና ወጊ ከሆኑት አንዱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በቀደም መጠርያው በበጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ከደብረ ታቦር ከተማ በስተ ደቡብ አቅጣጫ በሚገኘው አፈረዋናት ምክትል ወረዳ ልጫ መስቀለ ክርስቶስ በተባለ ሰበካ በ1874 ዓ.ም. መወለዳቸውን ገጸ ታሪካቸው ያመለክታል፡፡
በ‹‹መዝገበ ሰብ›› የታሪክ መድበል እንደተገለጸው በስመ ጥምቀታቸው ኃይለ ሚካኤል ይባሉ የነበሩት አቡነ ሚካኤል፣ ዜማና ቅኔ ከነምሥጢሩና አገባቡ የብሉያትና ሐዲሳት ትርጓሜንም በተለያዩ አካባቢዎች ተምረዋል፣ ሊቅነታቸውንም አስመስክረዋል፡፡ በመምህርነት ከማገልገላቸው ባሻገር ሙያቸውና ግብረገብነታቸው የጠነከረና የተመሰከረላቸው በመሆኑ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቤተ መንግሥት በመግባት የምክር ድጋፍ እንዲያደርጉ መደረጉን የዶ/ር መርሻ አለኸኝ ‹‹ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን›› መጽሐፍ ያወሳል፡፡
አራት ኢትዮጵያውያን መምህራን ቆሞሳት በግንቦት 1921 ዓ.ም. በእስክንድርያ ጵጵስና ሲቀበሉ አንዱ አባ ኃይለ ሚካኤል ይባሉ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ናቸው፡፡
አቡነ ሚካኤልም ‹‹ጳጳስ ዘአዜበ ኢትዮጵያ›› ተብለው ሲሾሙ አዜበ ኢትዮጵያ (ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ) አካባቢ ኢሉባቦርን፣ ወለጋንና ከፊል ከፋን ያጠቃለለ ነበር፡፡ ‹‹የጐሬ ትምህርት ቤት የወርቅ ኢዮቤልዩ›› መጽሔት ሥር ‹‹ኢትዮጵያዊው ሰማዕት አቡነ ሚካኤል ጳጳስ ዘአዜበ ኢትዮጵያ›› በሚል ርእስ ባቀረበው ሐተታ፣ አቡነ ሚካኤል በዚህ ሰፊ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሰበካ ክልል ሲሠሩ አንዱን መንፈቅ በኢሉባቦር ጐሬ ላይ፣ ሌላውን መንፈቅ ዓመት ወለጋ እየተቀመጡ እንዲሠሩና እርሳቸው በሌሉበት ጊዜ በኢሉባቦር በኩል የጐሬ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ደብር አለቃ፣ በወለጋ በኩል የአርጆ ደብር አለቃ ተክተዋቸው እንዲሠሩ መንግሥት በ1923 ዓ.ም. ባወጣው አዋጅ ወስኖ እንደነበር ተመልክቷል፡፡
አቡነ ሚካኤል የተማረኩት ኅዳር 17 ቀን 1929 ዓ.ም. እንደነበር ሊቀጠበብት እንዳለ ቢረሳው ለጐሬ ቅድስት ማርያም ወጣቶች ክርስቲያናዊ ማኅበር በሰጡት የታሪክ ማስታወሻ ላይ ተጠቅሷል፡፡ አቡኑ ቄስና ሽማግሌ ስለሆኑ ይፈቱልን ብሎ ሕዝቡ ልመና ቢያቀርብም የኢጣሊያ ጦር አዛዥ ልመናውን ሳይቀበል ቀረ፡፡ በተጻራሪው ኮሎኔል ማልታ ለኃያሉ የኢጣሊያ መንግሥት ለመገዛት ቃል እንዲገቡና ሕዝቡም እንዲገዛልን ይስበኩልን በማለት በልዩ ልዩ የመሸንገያ ዘዴ ቢያባብላቸውም ብፁዕነታቸው ከአገራቸው ከኢትዮጵያ ጠላት ጋር እንደማይተባበሩ አስረግጠው ነግረውታል፡፡ ‹‹እኔ የማምነው በአንድ እግዚአብሔር ነው፤ ጣልያን የሚባል ገዥ አላውቅም፤ ለፋሺስት ጣልያን የተገዛ እንደ አርዮስ የተወገዘ ይሁን፤ እንኳንስ ሕዝቡ ምድሪቱም እንዳትገዛላቸው አውግዤአለሁ፤›› በማለት በዚያ ለተሰበሰበው ሕዝብና ሠራዊት ውግዘታቸውን አሰምተዋል፡፡ ጠላት የዓላማ ጽናታቸውንና ቆራጥነታቸውን ተመልክቶ እርሳቸውን መሸንገል እንደማይቻል ስለተረዳ ከሁለት እውቅ አርበኞች ማለትም ከግራዝማች ተክለሃይማኖትና ከቀኛዝማች ይነሱ ጋር በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ወስኗል፡፡
አቡነ ሚካኤል እጃቸው ከተያዘ በኋላ ለሰባት ቀናት በእስር ላይ ቆይተው ጠላት ኅዳር 24 ቀን 1929 ዓ.ም. ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ወረድ ብሎ አሮጌ ቄራ መሄጃ ላይ በመትረየስ ገድሏቸዋል፡፡ አቡኑ ለሰማዕትነት ሲቆሙ ለጥቂት ደቂቃዎች ጸሎት ማድረስ እንዲችሉ ፋታ ጠይቀው ተፈቀደላቸውና ጸሎታቸውን አድርሰው ሲያበቁ ግንባራቸውን መስቀል ላይ እንደደፉ ‹‹በል እንግዲህ የፈለግከውን ፈጽም›› ብለው በመናገር ርሸናው ተፈጽሞባቸዋል፡፡
የኢጣሊያ ፋሽስት አቡኑንና ሁለቱን አርበኞች በግፍ ከገደለ በኋላ በጐሬ ከተማና በአካባቢው በሚገኙት ቤተክርስቲያኖች ውስጥ የሚያገለግሉትን ቀሳውስትና ካህናት ሰብስቦ ባደረገው ገለጻ፣ አቡነ ሚካኤል የተገደሉት ለኃያሉ የኢጣሊያ መንግሥት አልገዛም በማለትና ሕዝቡም እንዳይገዛ በመቀስቀስና በማውገዝ በፈጸሙት ጥፋት መሆኑን አውስቶ፣ እኚህ ጳጳስ ሐሳባቸውን እንዲለውጡ ተጠይቀው እምቢተኛነታቸውን ስላሳዩ መገደላቸውን አስታወቀ፡፡ በዚሁ ላይ ካህናቱ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ በመጋበዝ አቡኑ መገደላቸው ተገቢ ነው ወይስ አይደለም? ሲል አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጡት አፋጠጣቸው፡፡
አቶ ዘውዴ ዱባለ ‹‹ኢሉባቦር›› በሚል ርእስ ከጻፉት ያልታተመ ጥራዝ ላይ እንደገለጹት፣ ካህናቱ በቀረበላቸው ጥያቄ ላይ በአፋጣኝ ተወያዩና ከመካከላቸው የንግግር ዘይቤ ያውቃሉ ብለው የሚያምኑባቸው አለቃ ቢረሳውን ወክለው እርሳቸው መልስ እንዲሰጡ አደረጉ፡፡ አለቃ ቢረሳውም ለኮሎኔል ማልታ አስቸጋሪ ጥያቄ በሰጡት መልስ ‹‹እናንተም ደግ ገደላችሁ፤ እርሳቸውም ደግ ሞቱ›› በማለት ተናገሩ፡፡ አቡነ ሚካኤል በጣም ደግ ሰው ስለነበሩ፤ ምንም እንኳ አለቃ ቢረሳው ሰም ለበስ በሆነ አነጋገር የአቡኑን ደግነት በማስታወስ መገደላቸው ተገቢ ያለመሆኑን ቢያወሱ ምስጢሩ ያልገባው ኮሎኔል ማልታ ግን ለእርሱ ድጋፍ የሰጡት መስሎት በመደሰት ‹‹አንተን ጳጳስ አድርጌ ሾሜሃለሁ በሉ የሟቹን ጳጳስ መስቀልና መቋሚያ ለአለቃ ቢረሳው ስጡ›› ብሎ በማሰናበት ካህናቱ ሁሉ በሰላም ወደየቤታቸው ተመለሱ፡፡
ሊቀጠበብት እንዳለ ቢረሳው ባቆዩት የታሪክ ማስታወሻ ደግሞ አቡኑ ከሞቱ በኋላም በሥርዓት እንዲቀበሩ ኢጣሊያ አልፈቀደም ነበር፡፡ እኒህኑ ጳጳስ ለመቅበር ብዙ ጥረትና ልመና ከተደረገ በኋላ ሬሳቸውን ለመቅበር አምስት ምዕመናን ብቻ ተፈቅዶላቸው እነኚሁ ሊቀብሯቸው ችለዋል፡፡
ከድል በኋላም በ1936 ዓ.ም. አጽማቸው ተለቅሞ በመውጣት በሳጥን ተደርጐ በክብር በመታጀብ በጐሬ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ እንዲያርፍ ተደርጓል፡፡ ደጃዝማች ጣሰው ዋለሉ የኢሉባቦር ጠቅላይ ገዥ በነበሩበት ዘመን እዚያው ሰማዕት በሆኑበት ቦታ ላይ ሐውልት አቁመውላቸዋል፡፡ ይኸው ሐውልት በ1980 ዓ.ም. መጠነኛ እድሳት እንደተደረገለት ታውቋል፡፡
ጎሬ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት የሚገኘው አደባባይ የሰማዕቱ የአቡነ ሚካኤል ፎቶ በትልቅ ፍሬም ተሠርቶ ተሰቅሎበት ቢኖርም ወታደራዊው የደርግ መንግሥት ሲመጣ የሰማዕቱን ፎቶ አንስቶ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም ባለሟሎቹን የካርል ማርክስ፣ የፍሬድሪክ ኤንግልስና የቭላድሚር ኢሊዩች ሌኒንን ፎቶግራፎች በአንድነት ሰቅሎበታል፡፡ የአካባቢው ካህናት፣ ምእመናንም የብፁዕነታቸውን ፎቶግራፍ እግዚአብሔር ሲፈቅድ ሁሉ ይሆናል በማለት ወደ ሙዚየሙ አስገብተው በክብር መቀመጡን ዜና ታሪካቸው ያመለክታል፡፡
‹‹አቡነ ሚካኤል ከማልዘነጋቸው ቆራጥ ኢትዮጵያውያን አንዱ ናቸው››
የስዊድናዊው ኮሎኔል ምስክርነት
ስለ እኚሁ ታላቅ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን አባት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት እስከ ሕይወታቸው ፍጻሜ የኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ጽኑ ወዳጅ የነበሩት ስዊድናዊ ኮሎኔል ካውንት ካርል ጉስታፍ በንሮዝን የሚከተለውን የምስክርነት ቃል መስጠታቸውን የዶ/ር መርሻ መጽሐፍ ያስታውሳል፡፡
‹‹ፎከር የምትባለውን አውሮፕላን እያበረርኩ በጎሬ አቅራቢያ አረፍኩ፡፡ በምዕራብ ኢትዮጵያ የነበሩትን ስደተኞች አግኝቼ በራስ እምሩ ይመራ ለነበረውም ጦር መገናኛ ከፈትኩ፡፡ ጎሬ እንዳረፍኩ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል አስጠሩኝ፡፡ ‹በእርግጥ አንተ ዘመዶችህን ከድተህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለማገልገል ወስነሃልን? ክርስቲያን ነኝ ብለኸኛል፡፡ ለዘመዶችህ ሳታደላ ለዚች ለተጨነቀች ሀገር ከልብህ ለመሥራት መወሰንህን መስቀሌን በመምታት ማልልኝ› ሲሉኝ የሀገር ፍቅር እንዳቃጠላቸው ተሰማኝ፡፡ ‹ጓደኞቼ በዕለት ጥቅም እየተደለሉ ለጠላት ማደራቸውን ስሰማ በጣም አዘንኩ፡፡ ሌላው የልብ ጓደኛዬ አቡነ ጴጥሮስ ግን ለጠላት አልገዛም ብለው ለመስዋዕትነት መቃረባቸውን ስሰማ በጣም ደስ አለኝ፡፡ ይህ ነው መሀላን ማክበር፡፡ እኔም የምከተለው የጴጥሮስን ፈለግ ነው› ብለው አጫወቱኝ፡፡ ቆራጥነታቸውን ሳደንቅ ፋሺስት ንፁሐንን ለምን እንደሚገድል በማሰብ በጣም ተገረምኩ፡፡ መስቀላቸውን መትቼ ከጎሬ ተመለስኩ፡፡ ወደ ሎንዶን ከሄድኩ በኋላ ጳጳሱ ተገድለው ጎሬም በጠላት መያዟን ስሰማ በጣም አዘንኩ፡፡ አቡነ ሚካኤል ከማልዘነጋቸው ቆራጥ ኢትዮጵያውያን አንዱ ናቸው፡፡ በነፃነት ጉዳይ ኢትዮጵያውያን የተለየ አቋም አላቸው፡፡ ቋንቋ ፈጽሞ አያግዳቸውም፡፡ አይበግራቸውም፡፡ ሁሉም በሀገራቸው ጉዳይ ቀልድ እንደማያውቁ የጎሬው ጳጳስ የአቡነ ሚካኤል ጥንካሬ በሚገባ አስረድቶኛል፡፡ የጳጳሱ ድፍረትና የሀገር ፍቅር ምን ጊዜም አይረሳኝም፡፡››
የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ዳግም ተከላ ጥር 29 ቀን 2008 ዓ.ም. ሲከናወን ያገኘናቸው አቶ ሳሙኤል ኃይለማርያም የሰማዕቱ አቡነ ሚካኤል ታሪክና ገድል እንደ አቡነ ጴጥሮስ ስፍራ አለማግኘቱ ምነው አሰኝቷቸዋል፡፡ ‹‹ምዕራባዊቷ አክሱም›› እየተባለች የምትጠራው ጐሬ ቅድስት ማርያም ደጀ ሰላም ውስጥ ያለው ሐውልታቸው ወደ አደባባይ እንዲወጣና እንዲተከልም ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ሚካኤል የሰማዕትነት አክሊል በተቀዳጁባት ጎሬ ከተማ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በስማቸው ተሰይሞላቸዋል፡፡ አፅማቸው ካረፈበት ጎሬ ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በሚገኘውና ቀድሞ ፎቶግራፋቸው ተሰቅሎበት ይኖር በነበረው አደባባይ ሐውልታቸው የሚተከለው መቼ ነው? የሰማዕትነታቸው 80ኛ ዓመት ኅዳር 24 ቀን 2009 ዓ.ም. ሐውልታቸው በሚቆምበት አደባባያቸው ላይ ይከበር ይሆን?