Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​አጀማመሩ እንጂ አጨራረሱ አያስጨንቀን!

ሰላም! ሰላም! የአንዳንዱ ሰው የዴሞክራሲ ጽንሰ ሐሳብ ፍቺ ደግሞ አጀብ ያሰኛል እባካችሁ። መቼም አሁን አሁን አጀብ ራሱ ሌላ የማዳነቂያ ቃል ካልተካልን በቀር የጉዳችን ብዛት ቃል አጥሮታል። ለዚህ እኮ ነው ዘር መተካትን የመሰለ ነገር የለም የሚባለው። ‹‹ታዲያ ቃል አያስምጥም፣ ተብሎ ግርምት ፈዟል ተብሎ ሰው ያለመሆን መብቴ እስካልተጠበቀ ድረስ በዴሞክራሲ አላምንም ይባላል?›› አንዱ ያልኳችሁ እኮ ነው ይኼን የሚለው። ‹‹ቀድሞ ነገር እኛ ሰው የመሆን እንጂ ያለመሆን ችግር ነበረብን እንዴ? ኧረ ቆዩኝማ አሁንስ አለን ወይ? የምደነቅበት ቃል አጣሁ እኮ ዘንድ፤›› በማለት ባሻዬን መቼስ የሰዋሰውና የቃል ሚስጥርን ከእኔ በላይ ያውቃሉ ብዬ ባዋያቸው፣ ‹‹ቃል ሞልቶ ቃል በጎደለበት በዚህ ዘመን እንዴት ቃል ይጠፋሃል?›› ብለው ተቀኙብኝ። የእሳቸውን ቅኔ እፈታ ብዬ ብጀምር የጎጆዬ ቋጠሮ ስላለብኝ ኅብረ ቃሉም ይኼ ነው ሳልል ወደ ድለላዬ ተቀየስኩ።

እና ያ አንዱ ያልኳችሁ መፈናፈኛ ቢያጣ ውድቀት፣ መወድስ ይኑረው ብሎ ይኼው በአደባባይ ጅምሩን የዴሞክራሲ ባህል ያጣጥላል። ግን ቆይ ነገር ዓለሙን በረባ ባረባው የማጣጣል ዝናችን የሚከስመው መቼ ነው? ‹‹ሳስበው… ሳስበው…›› አለች ማንጠግቦሽ በአርምሞ አቦል እየቀዳች። ‹‹ሳስበው… ሳስበው… የተቃርኖ የተፈጥሮ ሕግ እኛ ላይ ሲሆን ይብሳል መሰል። ‹‹እንጃ ምንም ነገር አይጣመን ካልን እኮ አፍራሽ መንገድ የመቀየስ ችግር የለብንም፤›› ብላ አዕምሮዬን በአገላለጿ ሰቅዛ ያዘችው። እኔም ቆያይቼ ሳስበው ሳስበው ድንጋይ ዳቦ ሲሆን የታየው እዚህች ምድር ላይ ብቻ ይመስለኛል። ከቤተሰብ እስከ ኅብረተሰብ ታሪካችን ቆሎ በማይደፋ ተቃርኖ የተገነባው ታዲያ ለምንድነው? ደግሞ አትቃወሙ አላልኩም አደራ። ‘እንኳን ዘንቦብሽ እንዲያውም ጤዛ ነሽ’ ሲሉ የሰማሁ መሰለኛ ተቃሚዎች!

ታዲያላችሁ እያደር የሰው ‘ግራ አውለኝ’ ማለት በዘመናት የተግባር ልምድ የተገነባው የመግባባት ልምዴ ላይ ተፅዕኖ መፍጠር አመጣ። የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ለምን በቀላሉ አትግባባም?›› እያለ ይጨቀጭቀኛል። በማያግባባ ነገር በቀላሉም ሆነ በከባዱ መግባባት ብሎ ነገር ምንድነው? ኧረ ተውኝ እስኪ። ኢትዮጵያዊ ሲባል የማውቀው አንድም ፀረ አስመሳይነት አቀንቃኝ መሆኑን ነበር። ለይምሰል ‘አቤት አቤት፣ ልክ ነው፣ ኤግዛክትሊ፣ ዴፍነትሊ፣’ ወዘተ ከመቼ ወዲህ እንደመጡ እንጃ። ይህን እንጃዬን አንድ የሥራ ባልደረባዬ ሰምቶ፣ ‹‹ምናልባት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታችን ወረቀት ላይ ብቻ ሰፍሮ ቀርቶ በመቅረቱ ይሆናል፤›› አይለኝ መሰላችሁ? እንዲያው አደራችሁን ይህቺ የሺሕ ዘመናት ውድ አገር ጥርሷን የነቀለችበት የመንግሥት አወቃቀር ይመስል፣ ይልቅ ከቀን ቀን ከደንበኛ፣ ከወዳጅ፣ ከዘመድ፣ ከጓደኛ የሚያቃቅረኝ ውሸታምነት፣ ግብዝነት፣ አጭበርባሪነትና መሰል ቤተሰቦች መጎልበት ነው። ሥር የሰደደ የመቻቻል ባህላችን ውጤት ከሆነም አላውቅም።

ኋላ የባሻዬ ልጅ ዘዴ አለኝ ብሎ ለጥቂት ወራት የሥነ ልቦና ሳይንስ ሥልጠና ውሰድ አለና ተመዘገበልኝ። በስተርጅና ተማሪ ቤት ብዬ ሳጉረመርም ባሻዬ ሰምተው፣ ‹‹ወየው በሆነልኝና እኔም በተማርኩ። ከሊቅ እስከ ደቂቅ ተምታቶበት ሲያምታታኝ፣ ወየው ከራሴ መታረቂያ ዕውቀት በገበየሁ…›› እያሉ አደፋፈሩኝ። ለጊዜው እጄ ላይ የነበረ አንድ ቪላ ነበረና እሱን ጆሮውን እስክል ብቻ ታገስኩ። የቤቱ ባለቤቶች የጠሩትን 3.5 ሚሊዮን ብር በማግሥቱ አፍርሰው የለም ሰባት ሚሊዮን ነው ያልንህ ሲሉኝ ከአንድም ሦስት ውድ ደንበኞቼ ‘ደላላ አይወለድብሽ’ እያሉ አገሬን ረገሟት። ቱግ ብዬ ሄጄ ባለቤቶቹን ማማከርና ዋጋ ማጣራት ያለ ነው። ‹‹ያልጠራችሁትን ጠራን ብላችሁ ያሰፈሰፉ ደንበኞቼ እኔ ላይ ፈረዱ…›› ብላቸው፣ ‹‹ጆሮህን ተመርመር፣ መታከሚያ ከሌለህ እናሳክምሃለን…›› ብለው አላገጡብኝ፡፡ አሁን እሺ እንዴት ብዬ ነው ከእነዚህ ሰዎች ጋር በቀላሉ የምግባባው?

ወሰንኩላችኋ እኔ አንበርብር የምንተስኖት ልጅ። ኑሮና ፖለቲካው (ማለቴ ኑሮና ብልኃቱ) አልሰምር ብሎኝ እንጂ ድሮም እኮ ኮከብ ተማሪ ነበርኩ። ምን ዋጋ አለው? ይህቺ ዓለም እንኳን ለተራዎቹ ኮከቦች ለአጥቢያዎቹም አትመችም። የቀለም ቀንድ ከመሆናችን በፊት ቀንዳችንን እያለ የሚያስጎነብሰን መከራ ዋዛ አይደለም ጎበዝ። ቢሆንም ሞኝነት አልፎበታል ብዬ ቢረፍድም ሳይሆን ቢመሽም ይነጋል ብዬ፣ የባሻዬ ልጅ ያስመዘገበኝ የአጭር ጊዜ የሳይኮሎጂ ሥልጠና ጀመርኩ። ‘አጀማመሩን ቻሉበት እንጂ አጨራረሱ ለራሱ ይጨነቃል’ ብሏል አሉ ማን ነው  . . . ቶማስ ኤድሰን። ልብ አድርጉ የጠቀስኩት ስም ሳይኮሎጂኛ ዘዴ በመጠቀም ሥልጠናዬን ስተገብር ነው። ደግሞ በኋላ ነፍሱ ካረፈች ሰው ጋር እንዳታጣሉኝ። እሺ?!

ምን ነበር የምናወራው? አዎ ባሌ ትምህርት ቤት ገባ ብላ ደግሞ ማንጠግቦሽ በምሳ ዕቃ ምሳ ቋጥራ፣ አዲስ ኮሮጆ ገዝታ፣ ሦስት ባለስኩዌር ሁለት ባለመስመር ደብተር ገዝታ አንግተው አለችኝ። ‹‹ምነው ማንጠግቦሽ የዘመኑ ትምህርት እኮ ሳይካበድ ነው ወደ አዕምሮ መሰስ ብሎ ነው የሚገባው። አታይውም ተማሪውን ዩኒፎርሙን አንዘላዝሎ ክላሰር እስክታክል ደርዘን ደብተሩን አመንምኖ፣ በየካፌውና በየሬስቶራንቱ ቁርስ፣ ምሳ፣ እራቱን ጥስቅ አርጎ እየበላ በእጁ ይዞ፣ ኢርፎን ጀሮው ላይ ሰክቶ ፌስቡክ እየጎረጎረ ክላስ ነበርኩ ሲል? ምነው መሳቂያ ባታደርጊኝ?›› ብዬ ተቆጥቼ ባዶ እጄን ‘ጀንተል’ ብዬ ከአስተማሪዋ ሃያ ደቂቃ አርፍጄ ክላስ ገባሁ። በቀላሉ ለመግባባት ማምሻዬን ትምህርት ከጀመርኩ አይቀር እንዲህ አይመስላችሁም? መሰለኝ ለእኔ!

አጀማመሩን እንጂ አጨራረሱን አትጨነቁበት ያልኩትን እያስታወሳችሁ ታዲያ። ማለቴ የቶማስ ኤድሰንን ጥቅስ ማለቴ ነው። እናም የመሀሉን ላጫውታችሁ። መቼም ምቀኛ ከሩቅ አይመጣም አይደል? በሥነ ልቦና ሳይንስ እያሸነፈ ገቢውን ሊያሳድግ እኛን ሊበልጠን ነው ብለው ነው መሰል ደላላ ባልንጀሮቼ አሳልፈው የማይሰጡኝን ሥራ ሁሉ እየደወሉ ይነግሩኝ ጀመር። አርፌ መማር አልቻልኩም። ሳሳድደው የማላገኘው ሽያጭና ኪራይ ሁሉ ተግተልትሎ መጣ። ‹‹ሶሪ ከሥራ ቦታ ነው…›› እያልኩ አስተማሪዋን ጠቅሼ ‹‹መጣሁ፣ በዚያ አድርገው፣ ለነዚያ አትንገራቸው…›› እያልኩ ክንፍ አውጥቼ እበራለሁ። መቼም የዕውቀት መጥፎ የለውም። ሥልጠናው ከሰጠኝ እገዛ አንዱ ዘዴ ፈጣሪነት ነው። ታዲያላችሁ አንዱን ለፋብሪካ የሚሆን ቦታ አጋዝቼው ሳበቃ መልሶ ደውሎ የግንባታና የቅድመ ምርት ማስታወቂያ ፈቃድ ነገር ነው ተብሎ ይሁንታ ማግኘት እንዳልቻለ ነገረኝ።

እኔም እንዳልኳችሁ ልብ ገዝቻለሁ አሉ በዘመኑ አኗኗር ዘይቤ እ? አንድ ሠፈራችን ትምባሆ ሲያቦን የሚውል ነገር ሁሉ እንዳሰበው ያልሆነለት ህንዳዊ አለ። እሱን የተወሰነ ኮሚሽን እንደማስብለት ነገርኩትና ያዘዝኩትን ብቻ እንዲፈጽም ጠየቅኩት። እንዴት ተግባባችሁ ስትሉ ሰማሁ ልበል? በአማርኛ ነዋ! ዘንድሮ እኮ ዕድሜ ለልማት አጋሮቻችን ፍልሰት ቻይናና ህንድ ቤተኛ ሆነው መስሎኝ። እንዴት ያለ ነገር ነው እናንተ! ኋላ እሺ ሲለኝ የክት የምለው አንድ ወዳጄ ለሠርጉ ከጣሊያን ድረስ ገዝቶ ያመጣልኝን ሱፍ አልብሼ፣ ጥርሱን በከሰል ወላ በኮልጌት ልቡ እስኪጠፋ አስፈግፍጌ ከባለፋብሪካው ደንበኛዬ ጋር አድርጌ ፈቃድ ወደሚጠየቅበት ቢሮ ላኩዋቸው። በቃ! ‹‹የአገሬ ልጅ የምሠራው ከህንዶች ጋር ነው። የሚሠራበት ካምፓኒ ዓለም አቀፋዊና ግዙፍ የሆነ ነው…›› ምናምን ብሎ ቀባጠረ፡፡ ህንዳዊው መንደርተኛዬም ‹‹የስ የስ…›› አለ ተፈቀደላቸው። ሙሉ ልብሴን ለማስወለቅ ያየሁትን አበሳ ግን እኔ ነኝ የማውቀው።

እንሰነባበት መሰል። ከዚህም ከዚያም ሥራ ተንዛዛ ብያችሁ የለ? ኪሴ ዘጭ ሲል ደግሞ ትምህርቱ ሰለቸኝ። ምን ሆኜ ነው ከፈጣሪ በቀር አውቆ የሚጨርሰው የሌለን የልቦና ሐሳብ የማጠናው እያልኩ ለማቋረጥ ሰበብ መፈለግ ጀመርኩ። ‘አንድ ቀን’ የሚሏት የለችም? የአንዱ መጀመሪያ የሌላው መቋጫ ሆና የምትከሰት? አዎ! አንድ ቀን ወጣቷ አስተማሪያችን አያውቁም ይሁን፣ ምን ያመጣሉ ይሁን አላውቅም የሌለ ነገር መቀባጠር ጀመረች። ‹‹ለምሳሌ…›› አለች ከየት እንደተንደረደች ሳናውቅ። ‹‹ለምሳሌ ወላጆቹ በልጅነቱ ሲፋቱ ያየ ልጅ ያለጥርጥር እሱም አግብቶ መፍታቱ አይቀርም፤›› ብላ አረፈችው። ‹‹እንዴ! እንዴ! እኛ እኮ በጥናትና ምርምር የታገዘ ሳይንሳዊ ገለጻ እንጂ፣ የፕሮፓጋንዳ የፕሮፓጋንዳማ የመንግሥት ልሳን ምን አጎደለብን?›› ብሎ ነገር ጀመረ አንዱ። ሲከስትባት ነው እንጂ ሰውዬው ከሦስት እንስቶች ጋር አጠገቤ ተቀምጦ ቻት ሲያደርግ አይቼዋለሁ።

ሌላ ምሳሌ ቀጠለች መምህርት። ‹‹የሚያጨሱ ሰዎች በራስ መተማመን የጎደላቸውና ለማንም ለምንም የማይጠቅሙ ዜጎች ናቸው፤›› ብላ መነሻ መድረሻ የሌለው ነገር ተናግራ አረፈችው። ይኼኔ፣ ‹‹የለም መምህርት አንድ ጥያቄ አለኝ። ዓለማችንን የሚመሩ አሉ የተባሉ ሰዎች እኮ በአብዛኛው አጫሾች ናቸው። ቶማስ ጀፈርሰንና ጆርጅ ዋሽንግተን በአሜሪካ የትምባሆ እርሻ ያስፋፉ ናቸው። ደግሞም የአሜሪካ አብዮት ሙሉ ለሙሉ ማለት ይቻላል የተደጎመው ከሲጋራ ሽያጭ በተገኘ ገቢ ነበር…›› ሲላት ከወዲያ ማዶ የሻትኩት ሰበብ ተገኘና ቀረሁ ቀረሁ። ኋላ የተለመደችዋ ግሮሰሪያችን እኔና የባሻዬ ልጅ አንድ አንድ ስንል፣ ‹‹የዘንድሮ አስተማሪ እንዲህ ከአመክንዮ ውጭ የባጥ የቆጡን ማስረጃ እያደረገ የሚያስተምር ከሆነ፣ እውነትም ተማሪው ትምህርቱን እየቀጨው ነው፤›› ብለው በምፀት ፈገግ ብሎ፣ ‹‹አስተማሪው የተማሪውን ቦታ ስለያዘው አይመስልህም? ተናጋሪው አድማጭ አድማጩ ለፍላፊ ሆኖ አገር እያቃጠለ ያለው ለዚህ አይመስልህም? አገልጋዩ ተገልጋይ፣ ተገልጋዩ አገልጋይ ስለሆነ አይመስልህም መልካም ሥነ ምግባርና መልካም አስተዳደርስ የህልም እንጀራ የሆኑብን?›› ብሎ መልሱን ራሱ መለሰው። እውነት ነው ተማሪው መምህር፣ መምህሩ ተማሪ! ይኼኔ ነው እንግዲህ የአጀማመርና የአጨራረስ ወጉ በሰፊው የሚደራው፡፡ መልካም ሰንበት!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት