Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየጤናው መድኅን ዕርምጃ?

የጤናው መድኅን ዕርምጃ?

ቀን:

ከሠራተኛና ከአሠሪ ከእያንዳንዳቸው ሦስት በመቶ በሚደረግ መዋጮ ጥር ወር ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን የተነገረለት የማኅበራዊ ጤና መድኅን እንደታሰበው በታቀደው ጊዜ ሳይጀመር ቀርቷል፡፡ ከጥር ወር ደመወዝ ላይ መዋጮው ተጀምሮ አገልግሎቱ በየካቲት መሰጠት እንደሚጀምር ተነግሮ ነበር፡፡ መዋጮው ከጡረተኞች የጡረታ አበል ላይ መቆረጥ ጀምሮ የነበረ ቢሆንም የኢትዮጵያ የጤና መድኅን ኤጀንሲ የፕሮግራሙ ትግበራ፤ የመዋጮው መቆረጥም ለጊዜው መቋረጡን አስታውቋል፡፡ ለዚህ ኤጀንሲው የሚያስቀምጠው ምክንያት ሲኖር የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎችን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ፕሮግራሙ ውጤታማ ሆኖ እንዲተገበር መደረግ አለባቸው የሚሏቸውን የተለያዩ ሐሳቦች ይሰነዝራሉ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ በተደረጉ እንቅስቃሴዎች ክፍተት የሚሉትንም ይነቅሳሉ፡፡

የጤና መድኅን ፕሮግራም መሠረት ሰዎች በሚያደርጉት ቅድመ ክፍያ መዋጮ ለሁሉም ዜጋ የሕክምና አገልግሎትን ተደራሽ ማድረግ፤ ገንዘብ ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ የሌላቸውም የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበት የጤና አገልግሎት ሥርዓት ማስፈን ነው፡፡

በተለያዩ አገራት የዜጎች የጤና አገልግሎት ወጪ በተለያየ መንገድ ይሸፈናል፡፡ ጠንካራ ኢኮኖሚ ባላቸውና የጤና አገልግሎት ሥርዓታቸው በሚፈቅድ አገሮች የጤና አገልግሎት ወጪ ሙሉ በሙሉ በመንግሥት ይሸፈናል፡፡ እንደ እኛ አገር ባለ ይህ የማይታሰብ ቢሆንም የዜጎች መሠረታዊ የጤና አገልግሎት ወጪን መንግሥት ይሸፍናል፡፡ ከዚህም ባሻገር በመንግሥት የጤና ተቋማት የሚጠየቀው ክፍያ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ምክንያቱ አገልግሎቱ በመንግሥት የሚደጎም መሆኑ ነው፡፡ ነገር ግን የሕክምና አገልግሎት ፍላጎት በጣም በጨመረበት፣ የተገልጋዩ ቁጥርም እንደዚያው ከፍተኛ በሆነበት በአሁኑ ወቅት የአገልግሎት ዋጋ ከባድና ብዙዎች የማይሸከሙት ሆኗል፡፡ የአኗኗር ዘዬን ተከትለው የተለያዩ በሽታዎች መምጣት ቴክኖሎጂም የሕክምና አገልግሎት ዋጋ ከፍተኛ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የጤና ኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ዳመን ኃይለ ማርያምም “በዚህ ሁኔታ ውስጥ አንድ የታመመ ሰው የሕክምና ወጪውን መሸፈን ይከብደዋል” ይላሉ፡፡ የጤና መድኅንን ኅበረተሰቡ ለረዥም ዓመታት ከኖረበት ከዕድር ጋር ይመሳሰላሉም፡፡

እሳቸው እንደሚሉት የጤና መድኅን ሽፋኑ ምንን ምንን ይሸፍናል የሚሉና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው የሥርዓቱ መኖር ችግር የደረሰባቸውን ይደግፋል መንግሥት ለጤና አገልግሎት የሚያደርገውን ወጪም ይደጉማል፡፡ ይህ ደግሞ አሁን በመንግሥት የሕክምና ተቋማት የማይገኙ አገልግሎቶች መድኃኒቶችም እንዲገኙና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲኖር ያስችላል፡፡

ቢሆንም ግን ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡ ምን ዓይነት የሕክምና አገልግሎቶች በጤና መድን ይሸፈናሉ? የሚለው የፕሮግራሙ ዝግጅት ይፋ ከሆነ ጀምሮ የብዙዎች ትኩረት ነው፡፡ ‹‹መጀመሪያ ላይ ለምሳሌ የኩላሊት እጥበት አልተካተተም ነበር፡፡ መሻሻሎች ተደርገው አሁን እንዲካተት ሆኗል›› ይላሉ ፕሮፌሰር ዳመን፡፡ ልክ እንደዚህ አገልግሎቶች በደንብ ታይተው ሊካተቱ ወይም ከመድኅን ሽፋኑ ውጭ ሊሆኑ ይገባል የሚል አስተያየት አላቸው፡፡

በሌላ በኩል አገልግሎቱን የሚሰጡት ተቋማት እነማን ናቸው? የሚለው ይነሳል፡፡ የግሉ ዘርፍ ምንም እንኳን በስትራቴጂ ደረጃ አገልግሎት ሰጭ ባለድርሻ ሆኖ የተቀመጠ ቢሆንም በፕሮግራሙ ተግባራዊነት ዋዜማ ዝግጁ እንዲሆኑ የተደረጉት የመንግሥት ተቋማት ብቻ ናቸው፡፡ ‹‹ጥቁር አንበሳ ወይም ሌላ የመንግሥት ሆስፒታል ለመታከም ለምን ኢንሹራንስ እገባለሁኝ?›› የሚል የአገልግሎት ጥራት ጥያቄ የሚያነሱ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህም ሊታሰብበት የሚገባ ነገር ነው ይላሉ ፕሮፌሰር ዳመን፡፡

በአገሪቱ ያለውን የጤና ፋይናንስ ክፍተት ለመሙላት ከጥቂት ዓመታት በፊት በመንግሥት ይፋ የተደረጉት የጤና መድኅን አይነቶች ሁለት ናቸው፡፡ ማኅበራዊና ማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅን፡፡ ማኅበራዊ የጤና መድኅን በመደበኛው ክፍለ ኢኮኖሚ የተሰማራውን፤ ማኅበረሰብ አቀፍ ደግሞ ደመወዝተኛ ያልሆነውንና መደበኛ ባልሆነው ክፍለ ኢኮኖሚው የሚገኘውን ያቅፋል፡፡ ለማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን የተሰጠው ትኩረት በቂ እንዳልሆነም ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሶሲዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶ/ር የራስ ወርቅ አድማሴ የጤና መድኅን አስፈላጊነትን ሲገልጹ ‹‹ጤናማ የሆነ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ከተፈለገ የሰፋ ሀብትና ጥቅም ባለውና በሌለው መካከል ያለው ልዩነት ሊጠብ ይገባል፤›› ይላሉ፡፡ ይህ ማለት ገንዘብ ያላቸው ወደ ተለያዩ አገሮች እየሄዱ የተሻለ ሕክምና እያገኙ ባሉበት በዚህ ወቅት የሌላቸው ጥሩ ሕክምና በአገራቸው የሚያገኙበት የጤና አገልግሎት ሥርዓት እንዲዘረጋ መሥራት የሁሉም ሰው ኃላፊነት እንደሆነም ያምናሉ፡፡

የፕሮግራሙ ይፋ መሆንን ተከትሎ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ከሠራተኞች ጋር በተደረገ ውይይት በሠራተኞች ይነሳ የነበረው ነገር የኑሮ ውድነት ባየለበት፣ ከሚከፈላቸው ዝቅተኛ ክፍያ ላይ ሦስት በመቶ መዋጮ ማድረግ ከባድ መሆኑ ነበር፡፡ ዶ/ር የራስ ወርቅም አዲስ አበባን በምሳሌነት በማንሳት የቤት ኪራይ እንዲሁም የምግብ ዋጋ ሰማይ በነካበት የትራንስፖርት ወጪም ከባድ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ ከወር ደመወዝ ላይ ሦስት በመቶ ማዋጣት ቀላል አለመሆኑ ይሰማቸዋል፡፡ ‹‹ማንንም ይቆነጥጣል ነገር ግን ይህ በጋራ የምናደርገውና የደሀውን ሸክም የሚያቀል በመሆኑ ልንችለው ይገባል›› ይላሉ፡፡ የጤና መድኅን አስፈላጊነት ጥያቄ የማይነሳበት ቢሆንም መዋጮው ሠራተኛው ላይ ጫና እንደሚያሳድር የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ዘገየ ኃይለ ሥላሴም ይናገራሉ፡፡

ጫናውን ለማስረዳትም የዛሬን የ5000 ብር ዋጋ ከባለፉት ዓመታት የ500 ብር ዋጋ ያነፃፅራሉ፡፡ ‹‹አምስት ሺሕ ብሩ የአምስት መቶ ብር ዋጋ ሳይኖረው 35 በመቶ የገቢ ግብር፣ ሰባት በመቶ የማኅበራዊ ዋስትና፣ ሦስት በመቶ የጤና መድኅን፡፡ በተጨማሪም በምናገኘው አገልግሎት ሁሉ 15 በመቶ የተጨማሪ እሴት ግብር እንከፍላለን›› በማለት የሠራተኛው ሸክም የከበደ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ዶ/ር የራስ ወርቅም ሠራተኛው ግብር አይክፈል ሳይሆን ሁሉም በገቢው መጠን እንዲከፍልና በግብር ሥርዓቱ ፍትሃዊነት እንዲሰፍን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልጸሉ፡፡ አቶ ዘገየም የሠራተኛ የገቢ ግብር ላይ መንግሥት አደርጋለሁ ያለውን የግብር ማሻሻያ ተግባራዊ ሊያደርግ የሚገባበት ጊዜ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

የጤና ተቋማትን በሕክምና መሣሪያዎች፣ በሰው ኃይልና በሌላም በሌላም በማዘጋጀት ረገድም በቂ ሥራ አለመሠራቱን፤ ይልቁንም የተያዘው መሬት ላይ ተገቢው ሥራ ሳይሠራ ከላይ የወረዳውን መመሪያ የማስፈጸም ዕርምጃ እንደሆነ አስተያየታቸውን የሰጡም አሉ፡፡

ለምሳሌ ቀደም ሲልም በተቋማቸው የጤና ሽፋን ያላቸው ሠራተኞች በጤና መድኅን እንዲካተቱ ሲደረጉ የሚያገኙት የአገልግሎት ጥራት ላይ ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ለዚህ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን በበቂ ሁኔታ ዝግጁ ማድረግ እንዲሁም ጥራት ላይ ማተኮር የግድ ይላል፡፡

ከሁለት ዓመታት በፊት ሪፖርተር የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፍሎን ባነጋገረበት ወቅት ኮንፌዴሬሽኑ ለሠራተኞች ጤና መድኅንን ባስተዋወቀበት ወቅት በሥርዓቱ ላለመታቀፍ ወደኋላ የማለት ነገር በተለያየ መልኩ ታይቶ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም ከጤና መድኅን ፅንሰ ሐሳብ ጀርባ ያለው ነገር ገንዘብ ያለው ብቻ ይታከም ሳይሆን ያለው የሌለውን ባቅሙ ይደግፍ የሚል መሆኑን በመግለጽ ማሳመን መቻሉን ገልጸው ነበር፡፡

በተመሳሳይ መልኩ ዛሬም የሠራተኛው ማመንና ፍላጎት ወሳኝ ነው ይላሉ አቶ ዘገየም፡፡ ከዚህም ባለፈ በአንድ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግ ከመነሳት ይልቅ ደረጃ በደረጃ ለመተግበር ቢሞከር ሰዎች እያዩ ሊሳቡ እንደሚችሉ ያስረዳሉ፡፡ የአገልግሎት ጥራት ላይ ትኩረት የሚያደርጉት አቶ ዘገየ የግሉ ዘርፍ የጤና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ተሳትፎም በደንብ ሊታሰብበት እንደሚገባ ያሳስባሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት ለግሉ ዘርፍ አለመካተት የሚቀመጠው ምክንያት በግሉ ዘርፍ የሚጠየቀው ክፍያ ከፍተኛ መሆን ሲሆን የኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ ሐኪሞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ዶ/ር ወንደሰን አሰፋ ክፍያው ውድ ነው ከመባሉ በፊት መታየት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ መካከል የቤት ኪራይ፣ የሕክምና መሳሪያ ዋጋ፣ የባለሙያ ክፍያና ሌሎችም የአገልግሎት ሰጪው ወጪዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ከምን አንፃር? ምን ያህል ውድ ነው? የሚለውን ማየት ግድ ይላል የሚል አቋም አላቸው፡፡

በጤና መድኅን አገልግሎት አሰጣጥ ተሳታፊ የመሆን ፍላጎት በግሉ ዘርፍ ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ወንደሰን ከመንግሥት ጋር በመወያየት ምክንያታዊ የአገልግሎት ዋጋ አስቀምጠው በፕሮግራሙ ሊካተቱ እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹80 በመቶ የሚሆነው ሕዝብ በጤና መድኅን እንደሚታቀፍ ተገልጿል፡፡ እናም የግሉ ዘርፍ እንዴት ከዚህ ውጪ ሊደረግ ይችላል?›› የሚል ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ በሌላ በኩል መደበኛ ባልሆነው ክፍለ ኢኮኖሚ ያሉትን የሚያካትተው ማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድኅንን በሚመለከት ዶ/ር ወንደሰን የፕሮፌሰር ዳመንን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ ተጠቃሚዎቹ የሚያገኙት የአገልግሎት ጥራት ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ እሳቸውም፡፡

የጤና መድኅን ቅድሚያ በሚደረግ መዋጮ ግለሰቦችና ቤተሰቦች ከድንገተኛ የሕክምና ወጪ የሚጠበቁበት ሥርዓት ሲሆን ሰዎች በገንዘብ ማጣት በቀላሉ ሊታከሙና ሊፈወሱ ሲችሉ ጤናቸው ላይ ሊፈጠር የሚችል ከፍተኛ አደጋን እንደሚያስቀር ይታመናል፡፡ በጤናው ዘርፍ ይህን ሥርዓት በመዘርጋት የሕክምና አገልግሎትን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ እንዲሠራ የኢትዮጵያ ጤና መድኅን ኤጀንሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 191/2003 ተቋቁሟል፡፡

በአሁኑ ወቅት የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድኅን የሙከራ ማስፋፊያ በደቡብ፣ ኦሮሚያ፣ አማራና ትግራይ ክልሎች በ161 ወረዳዎች ላይተግባራዊ እየሆነ እንዳለ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በሌላ በኩል ባለፈው ወር መዋጮው መቆረጥ ጀምሮ የነበረው የማኅበራዊ (በመደበኛ ክፍለ ኢኮኖሚ ያሉትን የሚያቅፈው) ጤና መድኅን ትግበራ ወዲያው መቋረጡ ይታወቃል፡፡ የግንዛቤ መፍጠር ሥራውና ዝግጅቱ በበቂ ሁኔታ ሲጠናቀቅ ደግሞ እንደሚጀመር ኤጀንሲው ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...