Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትከሪዮ ኦሊምፒክ በፊት የጦፈው የዝግጅት ግምገማ

ከሪዮ ኦሊምፒክ በፊት የጦፈው የዝግጅት ግምገማ

ቀን:

  • የአበረታች መድኃኒት ጉዳይ ለድርድር እንደማይቀርብ ተነግሯል

ከመንፈቅ በኋላ በብራዚል ሪዮ ደጀኔሮ እንደሚካሄድ የሚጠበቀው 31ኛው ኦሊምፒያድ እጅግ ትኩረትን እየሳበ ነው፡፡ አገሮች በየጓዳቸው የድል ስንቃቸውን እያዘገጃጁ በሚገኙበት በዚህ ወቅት ዓለም አቀፍ የፀረ አበረታች መድኃኒት ኤጀንሲ (ዋዳ) በበኩሉ የተጠረጠሩ አገሮችን ምስጢር በአደባባይ እየዘረገፈ ዛቻን ሲዘነዝር እኛስ ምን እየሠራን ነው? የሚለው የብዙ አገር ወዳድና የስፖርቱ ቤተሰቦች ሥጋት ከሆነም ስነባብቷል፡፡

ዓርብ የካቲት 11 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጽሕፈት ቤት የተጀመረውና ተከታታይነት እንደሚኖረው የተነገረለት የዝግጅት ግምገማ እስከ ዛሬ ከተለመደው ወጣ ብሎ ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው መልኩ መከናወኑ ደግሞ የበለጠ ተስፋን የሚያስጨብጥ መሆኑ እየተነገረለት ነው፡፡ ከሐምሌ 29 እስከ ነሐሴ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ በሚካሄደው የሪዮ ዲጄኔሮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በሦስት ስፖርቶች መሳተፍ የሚያስችላትን ቅድመ ሁኔታ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ማስታወቁ በዚሁ የዝግጅት እቅድ ግምገማ ላይ ተነግሯል፡፡ ተሳትፎውን ወደ አራት የስፖርት ዓይነት ያደርሳል ተብሎ እምነት የተጣለበት ቦክስ ከአንድ ወር በኋላ ለሚደረገው ማጣሪያ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑና ኦሊምፒክ ኮሚቴ በቅንጅት እየሠሩ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በግምገማው የዝግጅት እቅዶቻቸውን ካቀረቡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ውስጥ፣ አገሪቱ በሪዮ ኦሊምፒክ በዋናነት ሜዳሊያ ስንጠረዥ ውስጥ እንደምትገባበት የሚጠበቀው አትሌቲክሱ ይጠቀሳል፡፡ በቅርቡ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አምበሳው እንየው በመሩት የግምገማ መድረክ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እቅዱን ከአጭር ርቀት እስከ ማራቶን ድረስ በምስል በመታገዝ በዝርዝር አቅርቧል፡፡ እቅዱ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከብሔራዊ አሠልጣኞችና ከሌሎችም ከሚመለከታቸው አካላት በተውጣጡ ሙያተኞች መዘጋጀቱን የፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ በመግቢያው ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዱን የውድድር ዓይነትና ክንውን ከጥቅል ወደ ዝርዝሩ በመግባት ያመላከተውን ይኼንኑ የእቅድ ዝግጀት ያቀረቡት ደግሞ የአሥርና የአምስት ሺሕ ሜትር ምክትል ዋና አሠልጣኝ አቶ መላኩ ደረሰ ናቸው፡፡

በእቅዱ መሠረትም ለሪዮ ደጄኔሮ ኦሊምፒክ ዝግጅት በተለይም በአሁኑ ወቅት 38 አትሌቶች በቋሚነት፣ 18 አትሌቶች ደግሞ በተጠባባቂነት ተይዘው በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ፣ ከዚህ ጎን ለጎንም ሌሎች ተፎካካሪ አትሌቶችን ለማግኘት ሚኒማ የሚመጣባቸውን ውድድሮች በጊዜውና በሰዓቱ የመለየትና የማግኘት ሥራ መሥራት፣ እስከ ሪዮ ኦሊምፒክ አትሌቶች አቅማቸውን ያላገናዘበ ውድድር እንዳያደርጉ ወይንም ወደ ውድድር እንዳይገቡ ቴክኒካዊ ሥራዎችን መሥራትና ኦሊምፒክ ሲቃረብ ‹‹እኔ አልተመረጥኩም›› ከሚለው አለመግባባትና መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ በወቅታዊ አቋምና ብቃት የተመረጡ አትሌቶችን በወቅቱ ለኅብረተሰቡና ለሚመለከተው አካል ማሳወቅና ይህንን የኃላፊነት ድርሻ የሚወሰዱ በተለያዩ የውድድር ዲሲፕሊኖች የተመረጡ 15 ብሔራዊ አሠልጣኞች መመደባቸው በእቅዱ ተካቶ አስተያየትና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡

ከሪዮ ደጄኔሮ ከተማ አየር ፀባይ ጋር ተያያዞ በአገሪቱ ተዛማጅ የሆነ የአየር ፀባይና ስፍራ በመለየት ከወዲሁ ዝግጅት እንደሚጀመር በተለይም የውድድሩ ስፍራ  በደን የተሸፈነ ከመሆኑ ባሻገር ቀዝቃዛማ አየር ስለሚገኝበት ይህንኑ ግምት ውስጥ ያስገባ ሥልጠናና ዝግጅት እንደሚኖር ተጠቁሟል፡፡ የስፖርት ሥነ ልቦናንና የሥነ ምግብ ሥርዓትን በመከተል ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ፣ ከዚህ ጎን ለጎን በአሁኑ ወቅት ለስፖርቱም ሆነ ለዓለም አገሮች ትልቅ አደጋ እየሆነ የመጣው የአበረታች መድኃኒት ጉዳይ እያስከተለ ያለውን የጎንዮሽ ጉዳት አስመልክቶ ተገቢው ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግበትን ሁኔታ ማመቻቸት በዋናነት ተቀምጠዋል፡፡ ውይይትና ማብራሪያም ተሰጥቶበታል፡፡

በእቅዱ ሥጋቶች ተብለው የቀረቡት ደግሞ የሚኒማ ማሟያ ውድድሮች በበቂ ሁኔታ ያለመኖር፣ በድንገት የሚከሰቱ ጉዳቶች፣ የውድድሩ ሥፍራና የአዲስ አበባ የአየር ፀባይ ያለመጣጣምና በተለይ ታዋቂ አትሌቶች የውድድር ቦታዎችን ለመምረጥ ፍላጎት ማጣት የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡

በቀረበው እቅድ ላይ የተነሱ አስተያየቶችና በግብአትነት ሊያካትቱ ይገባቸዋል ተብሎ የተወሰዱ ሐሳቦች ደግሞ እቅዱ እንደ እቅድ እስከዛሬ ከተለመደው ወጣ ብሎ የቀረበ መሆኑ በጠንካራ ጎኑ ተጠቅሶ፣ ነገር ግን በጥቅሉ ሲታይ ከንድፈ ሐሳብ ባሻገር የተግባራዊነቱ ጉዳይ ሊታሰብበት እንደሚገባው የመድረኩ ስብሳቢ ሚኒስትር ዴኤታውን ጨምሮ ለሁሉም ሥጋት መሆኑ በትኩረት ታይቷል፡፡ በተጨማሪም ይህ እቅድ እንደ ከዚህ ቀደሙ ከፌዴሬሽኑና አሠልጣኞች በተጨማሪ ይመለከታቸዋል የሚባሉ ባለድርሻ አካላት አትሌቶችና የአትሌቶች ተወካዮች፣ የሥነ ልቦናና የሥነ ምግብ ባለሙያዎች፣ ሐኪሞችና ሌሎችም አስተያየታቸው ሊሰጡበት እንደሚገባ ታምኖበት ተቀባይነትም አግኝቷል፡፡

ሌላው ቀደም ሲል በእቅዱ እንደተመለከተው የአበረታች መድኃኒት ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን አስመልክቶ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አምበሳው እንዳብራሩት ከሆነ፣ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉን ፀረ አበረታች መድኃኒት (ዋዳ) ስምምነቶችን ፈርመው ከተቀበሉ አገሮች አንዷ ነች፡፡ ስለሆነም በዚህ ጉዳይ ከሚመለከተው አካል በማስረጃ የተረጋገጠ ተጨባጭ ማስረጃ ሲመጣ እርምጃ የማይወስድበትና ውሳኔውንም ለኅብረተሰቡ በይፋ የማይገለጽበት ምክንያት እንደማይኖር ጭምር አስረግጠው ተናግረዋል፡፡

ከአትሌቲክሱ ባልተናገሰ ሌላው የዝግጅት እቅድ ግምገማ የተደረገበት ኢትዮጵያ በሪዩ ደጄኔሮ ኦሊምፒክ በአንድ ወንድና በአንዲት እንስት ተሳትፎ  እንደሚኖራት የተነገረለት የውኃ ዋና ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ ባለሙያ እንደ አትሌቲክሱ ሁሉ ዝርዝር የዝግጅት እቅድ ባያቀርቡም፣ ነገር ግን ለወደፊቱ አገሪቱ በውኃ ዋና ለሚኖራት ተሳትፎ ከዓለም አቀፋዊነት እድል ወጥታ በሚኒማ የምትካፈልበት እቅድ መንደፉን ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እያደረገላቸው ያለው ድጋፍና ትብብር መልካም እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ በዕለቱ በተከናወነው የእቅድ ግምገማ ከአትሌቲክስና ውኃ ዋና በተጨማሪ የብስክሌትና ቦክስ ፌደሬሽኖች ቀደም ሲል በተያዘው ፕሮግራም መሠረት እቅዶቻቸውን አቅርበው ግምገማዊ ውይይቱ እንደሚካሄድ ቢታሰብም በጊዜ እጥረት ምክንያት ለሌላ ቀን እንዲሸጋገር ተደርጓል፡፡ የሪዮ ደጄኔሮ ኦሊምፒክን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር አቶ ታምራት በቀለ ያለውን አጠቃላይ ዝግጅትና በተለይም በብራዚል ከተከሰተው የዚካ ቫይረስ ጋር ተያይዞ በተለይ ለሪፖርተር የሰጡትን ተጨማሪ ማብራርያ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በሪዮ ኦሊምፒክ በእቅድ ከያዛችኋቸው ስፖርቶች እስካሁን በሦስት ዓይነቶች ኢትዮጵያ እንደምትሳተፍ ይፋ ሆኗል፡፡ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቀደም ሲል በእቅድ ይዞት የነበረው በአራት ስፖርቶች ነበር፡፡ አንዱ የት ገባ?

አቶ ታምራት፡- የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቀደም ሲል በአራት የስፖርት ዓይነቶች ተሳትፎ ለማድረግ እቅድ ይዞ ቢቆይም በአሁኑ ወቅት በአዘጋጅ ኮሚቴው ማረጋገጫ የተሰጠን በሦስት ስፖርቶች አትሌቲክስ፣ ውኃ ዋናና በወንዶች ብስክሌት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ወደፊት የተለያዩ ማጣሪያዎች ለምሳሌ በቦክስ ከአንድ ወር በኋላ የማጣሪያ ውድድር ስለሚኖር ሚኒማ ለማምጣት ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ በብስክሌት እስከአሁን ማረጋገጫ የደረሰን በአንድ ወንድ ስለሆነ በሴቶች ለመሳተፍ የሚያስችለን የሚኒማ ውድድሮች በቀጣይ ይኖራሉ፡፡ በዚህም እንደ ቦክስ ፌዴሬሽን ሁሉ ከፍተኛ ጥረትና ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኦሊምፒክ ኮሚቴው ቀደም ሲል በሰጠው መግለጫ በወርልድ ቴኳንዶ ኢትዮጵያ የተሳትፎ እድል እንደሚኖራት ተናግሮ ነበር፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን በሴቶች ብስክሌት የኦሊምፒክ ሚኒማ እንደተሟላ ተነግሮ ነበር፡፡

አቶ ታምራት፡- የሴቶችን ብስክሌት በተመለከተ እንደተባለው ሁለት ተወዳዳሪዎች ሚኒማ እንዳሟሉ ተደርጎ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መነገሩ እውነት ነው፡፡ ሆኖም የሪዮ ኦሊምፒክ አዘጋጅ ኮሚቴ ሚኒማን በሚመለከት በላከው ዝርዝር ውስጥ የሴቶች አልተካተተም፡፡ በቅርቡ ሞሮኮ ላይ ተጨማሪ ውድድር ስለሚኖር በሴቶች ለመሳተፍ የሚያበቃንን ሰዓት እናመጣለን የሚል እምነት አለ፡፡ ለዚህም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስፈላጊውን ሁሉ የቁሳቁስና የፋይናንስ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ የወርልድ ቴኳንዶን ተሳትፎ በተመለከተ በሁለቱም ጾታ የማጣሪያ ውድድሮች ቢደረጉም አልተሳካም፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አገሪቱ በሪዮ 2016 የተሳካ ተሳትፎ ይኖራት ዘንድ ከሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ጋር ተያይዞ የተለያየ ንዑሳን ኮሚቴዎች ተዋቅረው እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ መድረኮች ተዘጋጅተው እቅዶች ፀድቀው አስፈላጊው ሁሉ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ንዑስ ኮሚቴዎች በዋናነት የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ይጠቀሳል፡፡ ኮሚቴው በቅርቡ ከስፖንሰሮች ጋር ተገናኝቶ የሚያከናውናቸው ይኖራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከአትሌቶች  ሥልጠና ጋር ተያይዞ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ክትትልና ድጋፍ ምን ይመስላል?

አቶ ታምራት፡- በአትሌቲክሱ በኩል እስካሁን የሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት  ኮሚቴ በላከልን መረጃ መሠረት 34 አትሌቶች ባላቸው ሰዓት ሚኒማ ያሟሉ መሆኑን አረጋግጦልናል፡፡ ተጨማሪ አትሌቶችን ለማግኝት ደግሞ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ባለበት ኃለፊነት ከአትሌቲክስ ፌደሬሽን ጋር ተከታታይነት ያላቸው መድረኮችን በመፍጠር ለዝግጅቱ ጥንካሬ የበኩሉን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡ ሥልጠናው በተገቢው ሁኔታ መጀመሩን አረጋግጠናል፡፡ በጣም ውስን ከሆኑ አትሌቶች በስተቀር በአብዛኛው ተሰባስበው እየተዘጋጁ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ውስጥ በተለይ ከመሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ ጋር በተያያዙ ምክንያቶች አለመግባባት መፈጠራቸው ይነገራል፡፡ ይኼ ከኦሊምፒክ ዝግጅት ጋር ተያያዞ ችግር ይፈጥራል የሚሉ ወገኖች ስላሉ ምን ይላሉ?

አቶ ታምራት፡- እንደ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ብሔራዊ አሠልጣኞች ተመድበው ብሔራዊ ዝግጅት ተጀምሯል፡፡ እርግጥ ነው ፌዴሬሽኑ በለውጥ ሥራ ላይ እንዳለ እናውቃለን፡፡ ሆኖም ጉዳዮን አስመልክቶ የተነጋገርንባቸው ነጥቦች ስለሌሉ እምለው ነገር አይኖረኝም፡፡ ሆኖም የሥልጠናውን ሒደት በተመለከተ ግን በቀጣይ የውይይት መድረኮች ይኖሩናል ብለን እናምናለን፡፡ ዓርብ (የካቲት 11 ቀን 2008 ዓ.ም.) በጋራ የተመለከትነው የዝግጅት እቅድ ግምገማም የዚሁ አንድ አካል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅት ጋር ተያያዞ በአስተናጋጇ አገር ብራዚል የተከሰተው የዚካ ቫይረስ ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡

አቶ ታምራት፡- በሽታውን በተመለከተ ክትትል እያደረግን ነው፡፡ በጉዳዩ ከአይኦሲ ጋርም ግንኙነት እናደርጋለን፡፡ እነሱም በየጊዜው ሪፖርት ያደርጉልናል፡፡ ዚካ ቫይረስ አሁን በአገሪቱ በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል፣ ምን ያህል ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፣ በዋናነት መተላለፊያ መንገዱ ምንድነው? የሚለው ጭምር ቅድመ ዝግጅት እንድናደርግ መረጃዎችን ይልኩልናል፡፡ እኛም ዝግጅት የምናደርገው ይህንኑ መነሻ አድርገን ነው፡፡ ምክንያቱም የአይኦሲ መርሕ ‹‹ቅድሚያ ለአትሌት›› ስለሚል ማለት ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...