Friday, December 2, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  በሕግ አምላክሥራንና ሠራተኛን የማያገናኝ ዝውውር ዕጣ ፈንታ

  ሥራንና ሠራተኛን የማያገናኝ ዝውውር ዕጣ ፈንታ

  ቀን:

  የሠራተኛን ዝውውር በተመለከተ በድርጅቶች ውስጥ ተንሳርፍቶ የሚታየው ልማድ ዝውውርን ያለ ዓላማ ማለትም ለድርጅቱ መሠረታዊ ጥቅም ታስቦ ሁሉንም በሚያስማማ መስፈርት የማይፈጸም መሆኑ ነው፡፡ ይህ ሁሉንም ዝውውር ባይመለከትም በተግባር ሕጉ ከሚያስበው ለተቃራኒ ዓላማ በአሠሪው እንደሚውል በዕለት ተዕለት ኑሮአችን እናስተውላለን፡፡ በሥራ ላይ እያሉ ሙስናን ለበላይ አካል ለማስተላለፍ እንቅፋት የሚሆኑ፣ ከቅርብ ኃላፊዎች ጋር የግል አለመስማማት ያላቸው፣ በዘር ወይም በሃይማኖት ከበላይ ኃላፊ አካል ጋር አንድ ያልሆኑ፣ በዕውቀታቸውና ሐሳባቸውን በገሀድ በመግለጽ ከአሠሪው ጋር የማይስማሙ ሠራተኞች በግዴታ እንዲዛወሩ ሲደረግ እናስተውላለን፡፡ የዝውውሩ ዋና ዓላማ ድርጅቱን ለመጥቀም ወይም ከባለሙያ ልምድ ለመጠቀም ሳይሆን ሠራተኛው በዕርምጃው ምክንያት ተበሳጭቶ ድርጅቱን እንዲለቅ ለማድረግ ነው፡፡ በእንዲህ ዓይነት ጊዜ ሠራተኞቹ የሚወስዱት ዕርምጃም ለጉዳዩ እልባት የማይሰጥ እንዲያውም ራሳቸውን ተመልሶ የሚጎዳ ነው፡፡ ሠራተኞቹ ዝውውሩን ተቀብለው ቅሬታቸውን ከማሰማት ይልቅ ቅሬታ በማቅረብ ሰበብ ወደ ሥራ ሳይመለሱ እየቀሩ ሲሰናበቱ ይታያል፡፡ የኢትዮጵያ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ የሠራተኛ ዝውውርን በተመለከተ ዘርዘር ያሉ ድንጋጌዎችን አልያዘም፡፡ ያም ሆኖ በተግባር ፍርድ ቤቶች ለሚቀርቡላቸው በዝውውር ምክንያት ለሚነሱ ክርክሮች እልባት ሲሰጡ እናስተውላለን፡፡  የፍርድ ቤቶቻችንን ተሞክሮ ካስተዋልነው ግን ይህ አሠሪው በዝውውር ምክንያት የሚፈጽመው ስውር ደባ በፍርድ ቤቶች በጥብቅ ሳይመረመር የሚያልፍበትን ልማድ ነው፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጣቸው ውሳኔዎች ውስጥ በአብዛኛው የሚንፀባረቀው ሠራተኛን ማዘዋወር የአሠሪው ገደብ የለሽ ሥልጣን ስለመሆኑ ነው፡፡ ይህ ፍርድ ቤቶች ለጉዳዩ ከሰጡት አነስተኛ ቦታና ዋናውን የዝውውር ምክንያት ካለመመርመር የሚመነጭ ነው፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በቅርቡ ባወጣው አሥራ ስምንተኛው ቮልዩም ግን የሰበር አቋም ዝውውር የአሠሪው ሥልጣን ከመሆን ባለፈ አሠሪው ሥልጣኑን ከሕግ ወይም ከኅብረት ስምምነት ውጪ ወይም አሳማኝ የዝውውር ምክንያት በሌለበት ሁኔታ ዝውውሩን ማከናወን አለማከናወኑ በጥብቅ ሊመረመር የሚገባበትን አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ በፍርዱ ይዞ መጥቷል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የሰበር ሰሚ ችሎቱ በተለያዩ ጊዜያት የሰጣቸውን ፍርዶች መሠረት አድርገን  ዝውውር ከአሠሪ ምሉዕ ፈቃደ ሥልጣን መስፈርት ወደ ሥራንና ሠራተኛን የማገናኘት ዓላማ መለወጡን ለመዳሰስ እንሞክራለን፡፡

  እንደመነሻ

  ዝውውር በአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት የተለያዩ ትርጉሞች አሉት፡፡ የአንድ ሠራተኛ ከአንድ አሠሪ ወደ ሌላ አሠሪ የሚዘዋወርበት አንዱ ነው፡፡ ይህ የዝውውር ዓይነት የድርጅቱ ወይም የአሠሪው ዝውውር (transfer of the undertaking) በመሆኑ የሠራተኛው ዝውውር አንድ ውጤት እንጂ ሙሉ ውጤት አይደለም፡፡ አንድ ደርጅት ሲሸጥ፣ ከሌላው ጋር ሲቀላቀል ወይም ወደ ብዙ ድርጅቶች ሲከፈል እንዲህ ዓይነት ዝውውር ያጋጥማል፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጁ አንቀጽ 28 አሠሪው በማስጠንቀቂያ የሠራተኛውን የሥራ ውል ሊያቋርጥባቸው ከሚችላቸው መንገዶች እንደ አንዱ ተቀምጧል፡፡ በአንቀጽ 28(1) (ሐ) መሠረት ድርጅት ወደ ሌላ ቦታ ሲዛወር ሠራተኛው ወደ አዲሱ ቦታ ተዘዋውሮ ለመሥራት ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀር በአሠሪው በማስጠንቀቂያ ሊሰናበት ይችላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ድርጅቱ ወደ ሌላ ቦታ ሲዛወር ስለሚኖረው የሠራተኞች ዝውውር አንመለከትም፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው አሠሪው ሠራተኛውን በዚያው ድርጅት ውስጥ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ፣ ከአንድ የሥራ መደብ ወደ ሌላ የሥራ መደብ አዘዋውሮ ስለሚያሠራበት ሁኔታ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ዝውውር በሠራተኛው ፈቃድ ወይም በአሠሪው አስገዳጅነት ሊፈጸም ይችላል፡፡ በሠራተኛው ጠያቂነት አንዳንዴም በአሠሪው አነሳሽነት በሠራተኛው ፈቃድ ሊፈጸም የሚችል ሲሆን፣ በአብዛኛው ለአሠሪውና ለሠራተኛው አለመስማማት መነሻ ሲሆን አይስተዋልም፡፡ ሁለተኛው ዓይነት በአሠሪው አስገዳጅነት የሚፈጸመው የዝውውር ሒደት ግን በአብዛኛው ላለመግባባት መነሻ መሆኑ የተለመደ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም እንዲህ ዓይነት ዝውውርን ከሕገ አንፃር መመልከት ነው፡፡

  አሠሪው ሠራተኛውን በግዴታ የማዛወር ሥርዓት ሁለት ተቃራኒ አስተሳሰቦች ይንፀባረቁበታል፡፡  አንዳንዶች አሠሪው ሠራተኛውን በግዴታ የማዛወር ሥልጣን እንዳለው በመቀበል የዝውውሩን ዝርዝር አፈጻጸም ከመመርመር ወደ ኋላ ሲሉ ይስተዋላል፡፡ ሌሎች ደግሞ አንድ ሠራተኛ በቋሚነት ከተቀጠረበት ቦታ ወይም ምድብ ወደ ሌላ አሠሪው የማዛወር ሥልጣኑ ፍጹማዊ ያልሆነና በጥብቅ የፍርድ ቤት ወይም ለመዳኘት ሥልጣን ባለው አካል ሊከለስ የሚገባ ነው የሚል ሐሳብ ያንፀባርቃሉ፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር ለመገንዘብ እንድንችል የፍርድ ቤቶችን ተሞክሮ በመጥቀስ አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ፡፡

  የአሠሪው ሥልጣን

  የኢትዮጵያ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ አሠሪው ሠራተኛውን አዘዋውሮ በማሠራት ረገድ ግልጽ ድንጋጌ የለውም፡፡ የአሠሪና የሠራተኛ ሕግ ድንጋጌ ላይ በግልጽ ያልሰፈረ በመሆኑ ዝውውር በአብዛኛው በኅብረት ስምምነት ወይም በሥራ መመርያ ወይም ደንብ ውስጥ እንዲካተት ይደረጋል፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጁም በዚህ ረገድ አመላካች ድንጋጌ አለው፡፡ በአንቀጽ 129(3) በኅብረት ስምምነት ይዘት ሊካተቱ ከሚችሉ ጉዳዮች ውስጥ ስለ ሠራተኞች ተሳትፎ በተለይም በዕድገት፣ በደመወዝ፣ በዝውውር፣ በቅነሳ፣ በዲሲፕሊን አፈጻጸም ስለሚኖራቸው ተሳትፎ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የዚህን ድንጋጌ ይዘት በጥሞና ለተረዳው ዕድገት፣ ደመወዝ፣ ዝውውር፣ ቅነሳና ዲስፕሊን የሠራተኛውን ተሳትፎ በሚያረጋግጥ መልኩ መቀረፅ እንደሚገባቸው ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ኅብረት ስምምነቱ የሠራተኛ ዝውውርን በሚመለከተው ኮሚቴ ውስጥ የሠራተኛ ተወካይ እንዲኖር ሠራተኛውም አስተያየቱን እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡ በተግባር ግን የኅብረት ስምምነት ወይም የሰው ኃይል መመሪያ በአሠሪው ሙሉ ሥልጣን ብቻ ዝውውር እንዲፈጸም የሚያስችል ስለሚሆን፣ ፍርድ ቤቶች ከሕጉ መስፈርት ያነሱ የሥራ ሁኔታዎችን ሊያስፈጽሙ እንደማይገባ መከራከር ይቻላል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 134 መሠረት በሕጉ የተቀመጠው በዝውውር የሠራተኛው ተሳትፎ መኖር በኅብረት ስምምነት ከሌለ የኅብረት ስምመነቱ ለሠራተኛው የበለጠ ጥቅም ስለማይሰጥ ተፈጻሚነት ሊኖረው አይገባም፡፡ በእርግጥ በአንዳንድ ድርጅቶች በተለይ በመንግሥት ተቋማት ዝውውር በኃላፊዎች የግል ስሜት የሚፈጸም ሳይሆን ሠራተኛው አባል በሆነበት ኮሚቴ በጥንቃቄ ተመርምሮ በመሆኑ ለዚህ መሠረት የሚሰጠው የኅብረት ስምምነት ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡

  እንዲህ ዓይነት አተረጓጎም በፍርድ ቤቶች አካባቢ አናስተውልም፡፡ በተከራካሪሪ ወገኖች የሕግ ክርክሩ ባይቀርብ እንኳን ፍትሕን የመስጠት ግዴታ ያለባቸው ዳኞች የአስተዳደር መመርያን የሕግ ቅቡልነት ሲመረምሩ የሕግ አውጪውን መንፈስ ሊከተሉ ይገባል፡፡ ፍርድ ቤቶች በዝውውር ላይ ያላቸው አመለካከት ግን የአሠሪው ሥልጣን አድርጎ የመውሰድ ነው፡፡ ለዚህ አስረጂ እንዲሆነን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠውን አንድ ገዥ ፍርድ እንመልከት፡፡

  ሰበር ችሎት በሰበር መዝገብ ቁጥር 44033 በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትና በአቶ ይበልጣል አጥናፉ መካከል በሰጠው ፍርድ የሠራተኛው ዝውውር የአሠሪው ሥልጣን እንደሆነ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ሠራተኛው ባቀረቡት ክስ አሠሪው ያላግባብ ያዛወራቸው በመሆኑ፣ ቀደም ብሎ ወደነበሩበት የሥራ መደብ እንዳይመለሱ ጠይቀዋል፡፡ አሠሪው ዝውውሩ የተፈጸመው ሠራተኛው በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ በደረሰበት ድብደባ እንዲታረቅ ተጠይቆ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሕጋዊ ዝውውር ነው ሲል ተከራክሯል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትና ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሠራተኛው ዝውውር ሕጋዊ ባለመሆኑ ወደነበሩበት ቦታ ይመለሱ ሲሉ ፍርድ ሰጥተዋል፡፡ የሁለቱንም ፍርድ ቤቶች ውሳኔ የሻረው ሰበር ችሎቱ አሠሪው ሠራተኛውን ቀጥሮ በእርሱ መሪነት የሚያሠራ በመሆኑ የሠራተኛውን ጥቅም በመጠበቅ የማዛወር መብት አለው ብሏል፡፡ ችሎቱ በሰጠው ትንታኔ፣

  ‹‹አሠሪው ሥራውን የሚመራ እንደመሆኑ መጠን አንድ ሠራተኛ የት ቦታ ተመድቦ ቢሠራ ለሥራው ይጠቅማል የሚለውን የመወሰን አስተዳደራዊ መብት ሊኖረው ይገባል፡፡ የአሠሪው ሥራውን ቅልጥፍና፣ ውጤታማነት፣ የኢንዱስትሪ ሰላም ወይም ሌሎች በተለያዩ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት አንድን ሠራተኛ ከአንድ የሥራ መደብ ወደ ሌላ ወይም ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ የማዛወር መብቱ ሥራ መሪነቱ ወይም ከአሠሪነቱ የሚመነጭ ነው፡፡ በእርግጥ አሠሪው ይህንን የዝውውር ዕርምጃ ሲወስድ የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ሊጠብቅ ይገባል፤›› ብሏል፡፡

  ይህ ፍርድ ሠራተኛን የማዘዋወር ሥልጣን የአሠሪው መሆኑን ከመግለጽ በተጨማሪ አንድ ዝውውር ሕጋዊ ሊባል የሚችልባቸውን መስፈርቶች ያብራራል፡፡ ከፍርዱ ሀተታ ለመገንዘብ እንደሚቻለው ዝውውሩ ሕጋዊ እንዲሆን ለሥራው ቅልጥፍና፣ ውጤታማነት ወይም የኢንዱስትሪ ሰላም የሚጠቅም መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም ሠራተኛው ያገኘው የነበረውን መብትና ጥቅም የሚጠብቅ ሊሆን ይገባል፡፡

  በሌላ የሰበር ችሎት ፍርድ አሠሪ ሠራተኛን የማዘዋወር ሥልጣኑን ከአሠሪና ሠራተኛ ሕጉ አንቀጽ 13(2) እንደሚያገኝ ተተንትኗል፡፡ በሰበር መዝገብ ቁጥር 50182 ግንቦት 13 ቀን 2002 ዓ.ም. በተሰጠ ፍርድ አሠሪ ሠራተኛን ከነበረበት የሥራ መደብ ተመሳሳይ ደረጃ ደመወዝና ጥቅም ወዳለው የሥራ መደብ አዛውሮ ለማሠራት የወሰደው አስተዳደራዊ ማስተካከያ ከአዋጁ አንቀጽ 13(2) መሠረት ያከናወነው ተግባር እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በዚህ መዝገብ አሠሪው ሠራተኞቹን በዘፈቀደ ሳይሆን ያዛወረው የድርጅቱን ምርታማነት ለመጨመር በተደረገው ጥናት በተደረሰበት መደምደሚያ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡

  ሰበር ችሎቱ በሌላ መዝገብ በሰጠው ገዥ ፍርድ የአሠሪው ሠራተኛን የማዛወር መብት ከአስተዳደር ማኑዋል እንደሚመነጭ አቋም ተወስዶበታል፡፡ በሰበር መዝገብ ቁጥር 29415 ጥር 27 ቀን 2000 ዓ.ም. ችሎቱ በሰጠው ፍርድ አንድ ድርጅት ሠራተኛን አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ አዛውሮ ማሠራት እንደሚችል በአስተዳደር ማንዋሉ ላይ በግልጽ ከተመለከተ የማዛወር መብት ይኖረዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የሠራተኛ ዝውውሩ ከአንድ የሥራ መደብ ወደ ሌላ የሥራ መደብ ሊደረግ የሚችል ሲሆን፣ ሠራተኛውን መጥቀሙ እስከተረጋገጠ ድረስ ዝውውሩ ሕጋዊ ይሆናል፡፡ ለሰበር መዝገብ ቁጥር 41786 ግንቦት 26 ቀን 2001 ዓ.ም. የተሰጠ የሰበር ፍርድ ለዚህ አስረጅ ነው፡፡ በዚህ ፍርድ አሠሪው ሠራተኛው ሲሠራው የነበረው የሥራ መደብ ሲሰረዝ ወይም ሲዘጋ ወደ ሌላ የሥራ መደብ ሠራተኛውን ያዘዋወረው በመሆኑ ማሠራቱ በፍርድ ቤቱ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡

  አታባርረው ግን እንዲለቀቅ አድርገው

  ከላይ የተመለከትናቸው የሰበር ፍርዶች ዝውውር የአሠሪው ሥልጣን መሆኑን ዕውቅና ቢሰጡም፣ አሠሪው በዘፈቀደ ሊያከናውነው የሚችለው ወይም የሚገባው እንዳልሆነ አመላካች ነው፡፡ አሠሪው ዝውውሩን ለመወሰን ሲዘጋጅ ዓላማው ምን እንደሆነ በጥሞና ሊመረምር ይገባል፡፡ ከሕጉ መንፈስ እንዲሁም ከሰበር አስገዳጅ ፍርዶች በመነሳት ሠራተኛ ከአንድ የሥራ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ወይም ከአንድ የሥራ መደብ ወደ ሌላ የሥራ መደብ ሲያዛውር ሊከተለው የሚገባውን ሥርዓት መተንተን ይቻላል፡፡

  የመጀመሪያው ዝውውሩ በኅብረት ስምምነት ወይም የአስተዳደር መመርያ ሥልጣን በሚሰጠው አካልና በተቀመጠው ሥርዓት መፈጸም አለበት፡፡ አንዳንድ አሠሪዎች ሥልጣኑ ከተለያዩ ክፍሎች ለተውጣጣ ኮሚቴ የተሰጠ ቢሆንም፣ አንድ ኃላፊ ብቻ ዝውውሩን ሲፈጽሙ ይስተዋላል፡፡ ኃላፊው ከሠራተኛው ጋር ባለው የግል ወይም የሥራ አለመግባባት በመነሳት ዝውውሩን የሚፈጽመው ከሆነ ዝውውሩ ሕገወጥ መሆኑ አይቀርም፡፡ በሌላ በኩል የዝውውሩ ሥርዓትም በጽሑፍ ሆኖ የሚፈጸምበትን ጊዜ የሚገልጽ መሆን አለበት፡፡ ዛሬ ተነስቶ ከነገ ጀምረህ ወደዚያኛው አገር ሄደህ ካልሠራህ ብሎ ሠራተኛን ማስፈራራት ፍትሐዊ አይሆንም፡፡ ዝውውሩም ለሠራተኛው በቃል ሳይሆን በጽሑፍ ሊሰጠው ይገባል፡፡ በሰበር ችሎቱ በተሰጠ አንድ ፍርድ (ሰበር መዝገብ ቁጥር 77113) አሠሪው ለሠራተኛው ዝውውሩን በጽሑፍ ባለማድረጉ ሕገወጥ እንደሆነ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በዚህ ጉዳይ ሠራተኛው ባቀረበው ክስ በአሠሪው ድርጅት ሥራዬን በአግባቡ እየተወጣሁ እያለ አሠሪው ወደ ሌላ የሥራ መደብ ተዛውረሃል በአዲሱ የሥራ መደብ ሄደህ ሥራ በማለት በቃል ሲገለጽልኝ በተዛወርኩት ቦታ ሥራዬን በኃላፊነት በአግባቡ እንድወጣ በዝውውር ደብዳቤ ይድረሰኝ በማለት በመጠየቄ በጥበቃ ኃላፊው እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ በዚህም የተነሳ የሥራ ውሉ የተቋረጠ ስለሆነ ስንብቱ ሕገወጥ በመሆኑ የሚገባኝ ልዩ ልዩ ክፍያ ይከፈለኝ ሲል ጠይቋል፡፡ አሠሪው በሰጠው መልስ ከአሠሪነት በመነጨ ሥልጣን ሠራተኛው በሌላ የሥራ መደብ ተዛውሮ እንዲሠራ፣ የዝውውር ደብዳቤ በቀጣይነት እንደሚደርሰው በሥራ ኃላፊው ቢነገረው ሥራ ሳይጀምር በፈቃዱ ለቆ ሄዷል ሲል ተከራክሯል፡፡ ሰበር ችሎቱ የሥር ፍርድ ቤቶችን አቋም በፍርዱ ባይገልጽም በፍርዱ ለጉዳዩ እልባት ሰጥቷል፡፡ በፍርዱም ‹‹አሠሪው የዝውውር ዕርምጃውን በቃል ለመስጠት የማያስገድድ አጣዳፊ ሁኔታ መኖሩን ካላስረዳ በቀር የዝውውር ዕርምጃውን በቃል አስተላልፌአለሁ፤ በቀጣይም በደብዳቤ እገልጻለሁ ማለቱ የአስተዳዳሪነት ሥልጣኑን በዘፈቀደ ለማከናወን ከመሻት የመነጨ ምክንያት ነው ከሚባል በቀር የዕርምጃውን ሕጋዊነት አያሳይም፤›› በማለት ችሎቱ ሠራተኛው የጠየቀው ክፍያ በሙሉ እንዲከፈለው ፍርድ ሰጥቷል፡፡

  ሁለተኛው አሠሪው የሠራተኛ ዝውውር ማድረግ ያለበት ለድርጅቱ ሥራ ለቅልጥፍና፣ ለውጤታማነት ወይም ለኢንዱስትሪ ሰላም መሆን አለበት፡፡ ሰበር ችሎቱ የሰበር መዝገብ ቁጥር 44033 በሰጠው ፍርድ እነዚህ የድርጅቱን ዓላማ የማያሳኩ ዝውውሮች ሕገወጥ መሆናቸውን በፍርዱ አስምሮበታል፡፡ ‹‹የኢንዱስትሪ ሰላም›› የሚለውን ዓላማ እንክን ነጥለን ብንመለከት አንድ ዝውውር በሠራተኞች መካከል፣ሠራተኛ ከአዲሱ ቦታ አንፃር አለመግባባትን የሚያስከትል መሆኑ ከተረጋገጠ የኢንዱስትሪ ሰላምን ማምጣት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ለዘመናት ቤትና ቤተሰቡን መሥርቶ ሥራውን በከተማ በትጋት የሚሠራን ሠራተኛ ወደ ገጠር ማባረር ምን ዓይነት የኢንዱስትሪ ሰላም ሊያሰፍን ነው? ያለፈቃዱ ገጠር ሄዶ ለድርጅቱ ዓላማ ሊወጣ ሊወርድ ነው? ይህን ውሳኔ የሚወስን ኃላፊ በሠራተኛው ቦታ ቢሆን ውሳኔውን ተቀብሎ ይፈጽመዋልን?

  ሦስተኛው ሠራተኛው ሲዛወር መብቱና ጥቅሙ ሊጠበቅለት ይገባል፡፡ የሠራተኛ ዝውውር በምንም መልኩ ሠራተኛው ቀደም ሲል ያገኝ የነበረውን ጥቅም የሚቀንስ ወይም የሚያሳጣ ከሆነ ሕገወጥ መሆኑ አይቀርም፡፡ ከላይ በሰበር መዝገብ ቁጥር 44033 የተመለከትነውም ፍርድ ይህን በግልጽ አስምሮበታል፡፡ ለምሳሌ ሠራተኛው ይከፈለው የነበረውን ደመወዝ፣ ያገኘው የነበረው ጥቅማጥቅም (የውክልና አበል፣ መኪና፣ ነዳጅ፣ የቤት አበል ወዘተ.) የሚያስቀር ወይም የሚቀንስ ከሆነ ዝውውሩ ሕገወጥ ነው፡፡

  በመጨረሻ ዝውውሩ ወይም አፈጻጸሙ በሠራተኞች መካከል ያልተገባ ልዩነት (discrimination) የሚያደርግ ከሆነ ዝውውሩ ሕገወጥ ነው፡፡ ለምሳሌ ዝውውሩ ወይም የዝውውሩ ውጤት የተወሰነን ጎሳ ወይም ዘር የሚጠቅም ወይም የሚጎዳ መሆኑ ከተረጋገጠ ሕገወጥ ይሆናል፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 14(1) በግልጽ እንደተመለከተው፡፡ በብሔረሰብ፣ በጾታ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከትና በሌላም ሁኔታ በሠራተኞች መካከል ልዩነት ማድረግ ሕገወጥ ነው፡፡

  ከላይ ሕጉን ወይም የሰበር አስገዳጅ ትርጉሞችን መሠረት አድርገን ከገለጽናቸው ሁኔታዎች ውጭ የተፈጸመ ዝውውር ሕገወጥ ይሆናል፡፡ ከዕለት ተዕለት ኑሮአችን እንደምናስተውለው አሠሪ የማይፈልገውን ሠራተኛ ለማባረር ሲፈልግ በግዴታ ወደማይፈልገው ቦታ ማዛወር ነው፡፡ ‹‹አታባረው ግን እንዲለቅ አድርገው›› የሚለው ፈሊጥ ለሙያው ታማኝ የሆነ፣ ሙስናና ብልሹ አሠራርን የሚቃወምን ሠራተኛ በማዛወር በራሱ ፈቃድ እንዲለቅ መግፋት የአንዳንድ አሠሪዎች ድብቅ አጀንዳ ነው፡፡ ስለዚህ በዝውውር ምክንያት አለመግባባት ተከስቶ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሲመጣ ዳኞች ይህንን የአሠሪውን ድብቅ አጀንዳ ሁሉም በሚስማማበት የፍትሕ መስፈርቶች በመፈተሽ ማጋለጥ ያስፈልጋል፡፡

  የዝውውርን ምክንያት የመመርመር ግዴታ

  ከላይ የተመለከትናቸው ፍርዶች ፍርድ ቤቶች ዝውውርን የአሠሪው ሥልጣን አድርገው ከመውሰድ የመነጨ ለዝውውሩ ምክንያት የሆነው ድርጊት በተጨባጭ ለድርጅቱ ሥራ ቅልጥፍና፣ ለውጤታማነት ወይም ለኢንዱስትሪ ሰላም ዓላማ የተፈጸመ ስለመሆኑ በጥንቃቄ ሲመረምሩ አይስተዋልም፡፡ በኅብረት ስምምነት ወይም የሥራ መመርያ አሠሪው ሠራተኛውን በፈለገበት የሥራ ቦታ አዛውሮ የማሠራት ሥልጣን አለው የሚል ድንጋጌ ካገኙ ይህንኑ ተከትለው አሠሪው ማዛወሩ አግባብነት ስለመኖሩ አቋም ይወስዳሉ፡፡ ሰበር ችሎቱ ከሕግ መሠረት በዘለለ ሥልጣኑ አሳማኝ ምክንያት ስለመኖሩ ግልጽ ቢያደርግም፣ በተግባር ፍርድ ቤቶቹ የዝውውሩን ምክንያት በጥልቀት ሲመረምሩ አይስተዋልም፡፡ በ18ኛው ቮልዩም በሰበር መዝገብ ቁጥር 105997 ሚያዝያ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. የሰጠው ገዥ (አስገዳጅ) ትርጉም ግን በዚህ ረገድ ምክንያትን በጥልቀት ለሚመረምሩ ፍርድ ቤቶች ጠቃሚ ፍርድ ነው፡፡ በዚህ መዝገብ ሠራተኛዋ በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ክስ አመልካች የኢንዱስትሪ ሰላም ያለአግባብ ንትርክ እየፈጠሩ መረበሻቸውን ሳያረጋግጥ ድርጅቱ የሠራተኛዋን የግል ታሪክ በሚያጎድፍ ደብዳቤ ከኦዲት ወደ ማርኬቲንግ ክፍል ያለአግባብ ስላዘዋወራቸው እንዲሰረዝላቸው ዳኝነት ጠየቁ፡፡ ተከሳሽ ድርጅትም አመልካች ከኦዲት ሠራተኞች ጋር ባላቸው አለመግባባት የተነሳ የኢንዱስትሪ ሰላም ለመጠበቅ የሥራ ደረጃቸውና ደመወዛቸው ተጠብቆ ተዛውረዋል በሚል ዝውውሩ አግባብ መሆኑን ተከላከለ፡፡ የሥር ፍርድ ቤቱ ማስረጃውን መርምሮ ዝውውሩ ተገቢ ነው የሚል ፍርድ የሰጠ ሲሆን፣ ይግባኝ የቀረበለት ከፍተኛው ፍርድ ቤትም ይህንኑ አፅድቆታል፡፡ ሰበር ችሎቱ በበኩሉ በአመልካች የቀረበለትን ቅሬታ መርምሮ፣ ግራ ቀኙን አነጋግሮ የዝውውሩ የተሰጠው ምክንያት አግባብነትን መምርሯል፡፡ ሰበር ችሎቱ በትንታኔው ድርጅቱ በሥር ፍርድ ቤት ካቀረበው ክርክር በአንድ በኩል ዝውውሩ የተፈጸመው በአመልካች ጥያቄ መነሻ መሆኑን ጠቅሶ የተሻለ ደመወዝ አመልካች እንዲያገኙ ማድረጉን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የአመልካችን ተገቢ ያልሆነ ባህርይ መነሻ በማድረግ ለኢንዱስትሪ ሰላም የተደረገ ዝውውር ነው በማለት መከራከሩ እርስ በእርሱ የሚጋጭና አሳማኝ ለዝውውር መነሻ የሚሆን ምክንያት አለመኖሩን የሚያሳይ ነው፡፡ በፍርዱም ለዝውውር አስገዳጅ የሚሆነውን ትርጓሜ እንደሚከተለው በመስጠት የሥር ፍርድ ቤቶችን ፍርድ ሽሯል፡፡ የችሎቱ መርህ ‹‹አንድ አሠሪ አንድን ሠራተኛ ከአንድ የሥራ መደብ ወደ ሌላ የሥራ መደብ የማዛወር አስተዳደራዊ ሥልጣኑ ነው ተብሎ የሚታመነው አሠሪው ሥራንና ሠራተኛን ለማገናኘት የሚችልበት አግባብ ነው በሚል ምክንያት ሆኖ ዝውውሩም ተቀባይነት የሚያገኘው የሠራተኛውን መብትና ጥቅም በማይነካ መልኩና ተመሳሳይ ወደሆነው የሥራ መደብ ተከናውኖ …›› ሲገኝ ነው፡፡

  ማጠቃለያ

  ዝውውር የአሠሪው ከኅብረት ስምምነት ወይም ከሰው ኃይል አስተዳደር መመርያ በሚያገኘው ሥልጣን የሚተገብረው ቢሆንም በዘፈቀደ ሊፈጸም አይችልም፡፡ ዝውውሩ ለድርጅቱ (ቅልጥፍና፣ ትርፋማነትና ኢንዱስትሪ ሰላም) አስተዋጽኦ ማድረጉ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ ዝውውሩ አድሎዓዊ ከሆነ፣ ሠራተኛው የሚያገኘውን መብትና ጥቅም የሚቀንስ ከሆነ፣ ወይም ሠራተኛውን በእጅ አዙር ለማባረር ያለመ ከሆነ ሕገወጥ ነው፡፡ የሕገወጥ ዝውውር ሰለባ የሆኑ ሠራተኞችም ሰከን ባለ አዕምሮ አሠሪውን ሥልጣን ባለው አካል መፋረድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕጋችን ዝውውርን የመሰሉ የሠራተኛ መብት የሚጣስባቸውን ጉዳዮች በዝርዝር አለመደንገጉ የመብቱን ጥሰት ቢያባብሰውም፣ ፍርድ ቤቶች ፍትሕ በመስጠት ሥራቸው እንደሚያስተካክሉት ይታመናል፡፡ ፍርድ ቤቶች አሠሪው የማዛወር መብት አለኝ ቢልም፣ ከዝውውሩ በስተጀርባ ያለውን የአሠሪውን ድብቅ አጀንዳ በመመርመር ለሁሉም የሚያረካ ፍትሕ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሠራተኛውን ከሞቀ፣ ለድርጅቱ በተሻለ ከሚጠቅምበት ቦታ፣ ያለፈቃዱ በግዴታ በማዛወር የሚሳካ የኢንዱስትሪ ሰላም አለመኖሩን በመረዳት አንዳንድ አሠሪዎች ወደ ትክክለኛ አሠራር ሊመለሱ ይገባል፡፡  በአሥራ ስምንተኛው ቮልዩም የተመለከትነው የሰበር ፍርድ በዚህ ረገድ ጥሩ አብነት ሊሆን ይችላል፡፡              

  ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን የሕግ ጠበቃና አማካሪ ሲሆኑ፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...